ባለስልጣኑ የገበያ ደህንነት ክትትልን ለማስፋፋት የማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አቋቋመ


አዲስ አበባ መስከረም 14/2005 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የገበያ ደህንነት ክትትልን ለማስፋፋት በሶስት ከተሞች የማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ማቋቋሙን አስታወቀ፡፡ ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በግብይት ሥርዓቱ ምርመራና ክትትል ስልቶች ዙሪያ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ስልጠና አዘጋጅቷል፡፡ ባለሥልጣኑ የሰው ሃብት ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ አበበ መስፍን ስልጠናው ዛሬ ሲጀመር እንደተናገሩት የፅህፈት ቤቶቹ መቋቋም ጤናማ ግብይትና የምርት ርክክብ መፈፀሙን ለመከታታልና ለማረጋገጥ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

 ፅህፈት ቤቶቹ የተቋቋሙት በአዋሳ፣ በጅማና በጎንደር ከተሞች ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከተሞቹ የተመረጡበት ዋና ምክንያት በብዛት የሰሊጥና የቡና ምርት የሚገኝበት አገር በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም የክትትል ሥራውን ይበልጥ ለማስፋፋትና የምርት ገበያ መረከቢያ መጋዘኖች በቅርበት በመሆን ክትትል ለማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ የህግ ጥሰት እንዳይፈፀም ለመከላከል ተፈፅሞ ሲገኝ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ አቅም ለመገንባት የሚያስችል ከፍተኛ የምርመራና የክትትል ክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና መሆኑንም አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡ ሥልጠናው የግብይት ሥርዓቱን ተአማኒነት ለማጎልበት ህብረተሰቡ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ላይ ያለው አመኔታና ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲረገጋጥ ለማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ ጥንካሬ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በግብይት ሂደት የሚያጋጥሙ ጥሰቶች ለመከላከል የተሻለ አቅም ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡ ህብረተሰቡ የዘመናዊ ምርት ግብይት ሥርዓት ጠቀሜታ ተገንዝቦ ለግብይት ስርዓቱ መዳበርና ማደግ ይበልጥ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ተሳትፎው እንዲጎለብት መልዕክታቸውን ዳይሬክተሩ አስተላልፈዋል፡፡ ባለስልጣኑ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ በገበያ ደህንነት ክትትልና እና በህግ ማስከበር የሚሰሩ ሃምሳ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር