አቶ ኃይለማርያም፤ “ሜዳውም ፈረሱም ያው…” ታድያ በቅጡ ይጋልቡ!


አቤ ቶኪቻው 


Image

ኃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ቤተመንግስቱ በራፍ ላይ ቆመዋል። ለነገሩ እንኳ ሰውየው ደጃፍ ላይ ከቆሙ ቆይተዋል። ነገር ግን የኢህአዴግ ሰዎች “አናስገባም ሰርገኛ እደጅ ይቆይ…” ብለው ደጅ ሲያስጠኗቸው ሰነባበቱ። ይገበሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ቢያንስ ኢቲቪ እና የመንግስት “ባሉካዎች” የጠቅላይ ሚኒስሩን ሞት በሰሙ በሁለት እና ሶስት ቀናት ውስጥ ነበር። ነገር ግን ይኸው ዛሬም ገና ፓርላማው ጠቅላይነታቸውን እስኪያፀድቅላቸው እንደ ቆሎ ተማሪ ደጅ መቆም ግዴታቸው ሆኗል።

አቶ ሀይለማሪያም የኢህአዴግ ሊቀመንበርነትን ስልጣን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሲሲቲቪ” ለተበለ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል “የእኔ አመራር የጋራ አመራር መርህን የተከተለ ነው” ካሉ በኋላ፤ “እንደሚታወቀው የመለስም አመራር ለግለሰብ የበላይነት ቦታ የማይሰጥ የቡድን ስራ የጎላበት አመራር ነበር” ብለው የማናውቀውን ነገር ነግረውናል። እውነቱን ለመናገር እኛ የምናውቀው አቶ መለስ “ሁሉን ቻይ” የነበሩና ሁልገዜም ብቻቸውን እንጂ በጋራ ሲሰሩ አላየንም። እርግጥ ደንብ ነውና ሙትን ሲያነሱ ደግ ደጉን ነው። ስለዚህ ስለ መለስ የሚያወሩት በሙሉ ፅቡቅ ፅቡቁን ቢሆን ግድ የለም…

መምህር ኃይለማሪያም ሆይ መለስን ለአሁኑ እንተዋቸው እና በእርስዎ ጉዳይ እናውጋ… እናልዎ… አሁን ሜዳው ሜዳውም ፈረሱም በእጅዎ ነው። እንግዲህ በቅጡ መጋለብ የእርስዎ ፈንታ ነው።

መምህር ሆይ ይቅርታ አንድ ጊዜ ወደ መለስ መለስ እንበልና አንድ ነገር ሹክ ልበልዎትማ ባለፈው ጊዜ የመለስ ለቅሶ ላይ ጥቁር በጥቁር ለብሶ “እንባ የተራጨው” ህዝቡ ሁላ ከኢህአዴግ ጎን ነው ስለዚህ እንዳሻኝ እሆናለሁ ብለው እንዳይሸወዱ… ልብ ያድርጉልኝ “እንባ የተራጨው” የምትለዋ ቃል ራሱ ያለችው በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ነው። ለምን ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ እንደገባች በአዲስ መስመር ላይ ልንገርዎት…

በጉለሌ ክፍለከተማ በሆነው ቀበሌ ውስጥ የቀበሌው አስተዳደር ለመለስ ለቅሶ ድንኳን ደኩኖ ነበር። ታድያልዎ… አስለቃሹ የቀበሌ አስተዳደር በየቤቱ እየዞረ “በዛሬው ዕለት ጋዜጠኞች ስለሚመጡ ሁሉም ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ በድንኳን ውስጥ እንዲያለቅስ” ሲል አዘዘልዎ። የቀበሌው ሰውም ታዛዥ ነውና እሺ ብሎ ጥቁር ልብስ ያለው ልብሱን ልብስ የሌለው ደግሞ ፊቱን አጥቁሮ ወደ ለቅሶው ድንኳን አመራልዎ። ምን ዋጋ አለው አንድ ሁለት ሶስት ተብሎ ለቅሶ ሲጀመርልዎ ከአስለቃሽ ኮሚቴ አባላት አንዱ “እባካችሁ አሁን ጋዜጠኞቹ ደውለው መምጣት አንችልም ስላሉ አታልቅሱ፤ ነገ ሲመጡ እናለቅሳለን አሁን ካሜራ በሌለበት ብናለቅስ ዋጋ የለውም” ብለው አስቆሙልዎ…! ለዚህ ነው “በእንባ ሲራጩ” የምትለዋን ቃል ለማንኛውም ብዬ ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያስገባኋት። እናም አቶ ኃይለማሪያም ሆይ እንዳይሸወዱ…

የእርስዎ ነገር የሚወሰነው ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ የሚያመጣብዎም ሆነ የሚያመጣልዎ ቀጥሎ በፈረስዎ እና በሜዳዎ ላይ በሚያሳዩት ትዕንት ነው።

ለምሳሌ ከመለስ በኋላ በነበረው “የአስከሬኑ” አስተዳደር ጊዜ ከማተሚያ ቤት ደጃፍ እንዲጠፉ የተደረጉት እና ድሮውንም ትንሽ ጭል ጭል ሲሉ የነበሩ ነፃ ፕሬሶች ቢያንስ ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱ ማድረግ አለብዎ…

ሌላ ደግሞ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞችን መፍታትም ምንም ሳይጨነቁ ሊያደርጉት የሚገባ ነገር ነው። ዳሩ ትዳርን መፍታት እንጂ ምስኪን እስረኛን ለመፍታት ምን ያስጨንቅዎታል? ዝም ብለው ዛሬ ነገ ብለው ቀጠሮ ሳይሰጡ፤ ሽማግሌ ገለመሌ ሳይሉ ይፍቱዋቸው።

በነገራችን ላይ የስዊድን ጋዜጠኞች ተፈቱ አሉ እሰይ እንዲህ ነው እንጂ… ግን ያኔ አቶ መለስ “የነጭ ደምም የጥቁር ደምም አንድ ነው” ብለው ደስኩረውልን አልነበር እንዴ..!? እንዴት ነው ነገሩ ለመታሰር ጊዜ ነው አንድ የምንሆነው?

ለማንኛውም ቢያንስ እነዚህን ሁለት ነገሮች ካደረጉ ሌላውን ደግሞ ቀስ ብለው ይሰሩታል። አደራ የኑሮ ውድነቱን ነገር ለመግታት የተቻሎትን ሁሉ ያድርጉ። ካልተቻሎት ደግሞ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገለልተኞች ብቻ ግን ለዚህ መፍትሄ ያላቸውን ባለሞያዎች እገዛ ይጠይቁ…!

እንደ እርሳቸው ሁሉን ነገር እኔ ብቻ እና እኛ ብቻ አይበሉ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ ይጥሩ ይጣሩም።

አለበለዛ ሀበሻ ይተርትብዎታል “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” ይሎታል። እውነት እውነት እልዎታለሁ ተርቶ ብቻ የሚተዎት አይመስለኝም። ወጡን ለማጣፈጥ የራሳቸውን ቅመም ማበጀት የጀመሩ ብዙ ጎበዛዞች አሉ (ይሄ ሚስጥር ነው።) አራዳ ከሆኑ ግን የቀማሚዎችንም ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ።

እንግዲህ ይበርቱ! እንጂ ሌላ ምን እላለሁ…!

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር