የኢህአዴግ ምክር ቤት በመስከረም ወር ሊቀ መንበሩን ይመርጣል


አዲስ አበባ ነሃሴ 30/2004 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር /ኢህአዴግ/ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ትናንት ማምሻውን ተጠናቀቀ።
የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የህዝቡን መነሳሳትና ለፓርቲው የሰጠውን አደራ ገምግሞ በታላቁ መሪ በሳል አመራርና በኢህአዴግ የተነደፈውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በከፍተኛ ርብርብ ለማሳካት ውሳኔ አሳልፏል።
የህዝቡን ተነሳሽነትም የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶችን በመደገፍ ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየርና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በበለጠ ግለት ለማስቀጠልም ወስኗል።
በገጠር በተፋሰስ ልማት፣ በመስኖና በተለያዩ የውኃ አሰባሰብ ዘዴዎች እንዲሁም በዘመናዊ የግብዓት አቅርቦትና የሙሉ ፓኬጅ አጠቃቀም ዙሪያ አርሶ አደሩን በማሳተፍና በመደገፍ የገጠር ልማት ሥራዎችን፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ተጠቃሚነት በከፍተኛ ፍጥነት ለማስቀጠል አጽንኦት ሰጥቶም መክሯል።
በከተሞች የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረውን የጥቃቅንና አነስተኛ ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማስፋት በመረባረብ እንዲሁም በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸውን የባቡር፣ የኢንዱስትሪዎችና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ ሌሎች የኃይል ማመንጫ ተቋማት ግንባታዎችን ለማስቀጠል ሰፊ ምክክር አድርጓል።
በተለይ መልካም አስተዳደርን ለማሻሻልና በራሱ ተሳትፎ የህዝቡን አደራ በብቃት ለመወጣት በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ አጽንኦት ሰጥቶ መክሯል።
ኮሚቴው የመንግሥትን የገቢ አቅም የማጠናከር፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን የማበረታታት፣ የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር፣ የኤክስፖርት ገቢን የማሳደግ፣ ልማታዊ የግል ዘርፍን የማጎልበት ሥራዎችን አፈጻጸም በተመለከተ እስካሁን ያሉበትን ሁኔታዎች የቃኘ ሲሆን፣ አሁን ካለው መነሳሳት አኳያ ዕቅዶችን በፌዴራልና በክልሎች በዝርዝር ፈትሾ ለላቀ ግብ መንቀሳቀስ እንደሚገባም አመልክቷል።
የህዝቡን ቁጭትና አደራ በህዝቡ በራሱ በተደራጀና ቀጣይነት ባለው ተሳትፎ ወደ ውጤት በመቀየር የተጀመረውን ፈጣን ዕድገትና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማስቀጠል ኮሚቴው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ወደ ዝርዝር ዕቅድ ተቀይረው በመጪው የግንባሩ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዳብሮና ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር ወስኗል።
የባለ ዕራዩና ታላቁ መሪ የጓድ መለስ ዜናዊን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ የተጓደለው አመራር በሚሰየምበት አቅጣጫ ዙሪያ የመከረ ሲሆን፣ የአመራር ምደባ ጉዳይ ለጋራ ዓላማ በሚደረግ ትግል ውስጥ አንድን ጓድ ይበልጥ መስዋዕት ይከፍል ዘንድ ከመመደብ ያለፈ ትርጉም የሌለው ቀላል ጉዳይ መሆኑንና ዋናው ሥራ ሁሉም በተሰማራበት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት መሆኑን አስታውሷል።
በመሆኑም ዋናው ጉዳይ የሆነው ለህዝቡ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በቂ ምላሽ መስጠት በሚቻልበት አቅጣጫ ዝግጅት እየተደረገ የግንባሩን ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀ መንበር የመሰየም ጉዳይ የግንባሩ ምክር ቤትሥልጣን በመሆኑ በመሰከረም 2005 የመጀመሪያ ሳምንት በሚካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲፈጸም ኮሚቴው ወስኗል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቁ መሪ ህልፈት ወቅት ያሳየውን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በቀጣይም ድህነትን በፍጥነት በማስወገድ የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የአገሪቱን ህዳሴ ለማፋጠን በሚደረገው ርብርብ ከጎኑ እንዲቆም ግንባሩ ጥሪ ማድረጉን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር