በሐዋሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲታከሙ አስመስለው የተነሱ ፎቶዎችን ሲሸጡ የተገኙ በፖሊስ ተያዙ፤በሐዋሳ ከተማ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነዋሪዎች እንዲሁም እሑድ የሲዳማ ብሔረሰብ አባላት በባህላዊ ሥርዓት ሐዘናቸውን በገለጹባቸው ቀናት በርካታ ፎቶ ግራፎችና ፖስተሮች የተሸጡ ሲሆን፣ ሁለቱ ግለሰቦች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የተሳሳቱ ፎቶ ሲሸጡ መያዛቸውን የፖሊስ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡


በሐዋሳ ከተማ የጠቅላይ ሚኒስትር  መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሕይወት ከተነገረበት ቀን ጀምሮ በርካታ ፎቶግራፎች ሲሸጡ የሰነበቱ ሲሆን፣ በሕክምና ላይ እያሉ አስመስለው የተነሱ ፎቶግራፎችን ሲሸጡ የተገኙ ግለሰቦች ደግሞ በፖሊስ ተይዘዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆስፒታል ውስጥ ጉሉኮስ ተደርጎላቸው የተነሱ አስመስለው በማሳተም በተለይ መስቀል አደባባይ በሚባለው አካባቢ ፎቶግራፉን በአምስት ብር ሲሸጡ፣ ትክክለኛ መስሎአቸው ነዋሪዎች እየተሻሙ ሲገዙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ይሁንና ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ሁለት ሰዎች በዚህ ድርጊት  ምክንያት ከቁጥጥር ሥር ሲውሉ፣ ሕገወጥ ፎቶዎችን በማሰራጨት ድርጊት ተጠያቂ ተደርገው በፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምርያ አስታውቋል፡፡ 

ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አንድ ፎቶግራፍ ሲሸጥ የነበረ ወጣት ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሕክምና ላይ እያሉ የሚያሳየውን ፎቶግራፍ ከየት እንዳገኙት ተጠይቆ፣ ‹‹እኔ ያንን ፎቶ አላገኘሁትም፣ ነገር ግን ሲሸጡ የነበሩት ሰዎች ከኢንተርኔት እንዳገኙት ሰምቻለሁ፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉሉኮስ ተሰጥቶአቸው ተኝተው ሲታከሙ የሚያሳየውን ፎቶግራፍ ትክክለኛ መስሎዋቸው እንደገዙ የገለጹት የሐዋሳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳንጊሶ ተሰማ፣ ‹‹ሐሰተኛ መሆኑን  ባውቅ አልገዛውም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ስለጉዳዩ የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መከላከል የሥራ ሒደት ኃላፊ ኢንስፔክተር ታደሰ በንቲ ተጠይቀው፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሕክምና ላይ እያሉ አስመስለው  የተነሱትን ፎቶግራፎች በማተም ሲሸጡ የነበሩ  ሁለት ሰዎች በመናኸሪያ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ጠቁመው፣ ሌሎች ፎቶግራፎችና ፖስተሮችን እየሸጡ በሚገኙት ላይም ክትትል እየተደረገ መሆኑን ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ 

በሐዋሳ ከተማ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ  ነዋሪዎች እንዲሁም እሑድ የሲዳማ ብሔረሰብ አባላት በባህላዊ ሥርዓት ሐዘናቸውን በገለጹባቸው ቀናት በርካታ ፎቶ ግራፎችና ፖስተሮች የተሸጡ ሲሆን፣ ሁለቱ ግለሰቦች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የተሳሳቱ ፎቶ ሲሸጡ መያዛቸውን የፖሊስ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ 

በሌላ ዜና የሐዋሳ ከተማ ባለሀብቶችና የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ሐዘናቸውን በክልሉ ሚዲያና በተለያዩ መንገዶች የገለጹ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለሁለት ቀናት በተደረገው የሐዘን ሥነ ሥርዓት  ላይ፣ እንዲሁም በቀብር ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማቸውን ሐዘን በባህላዊ ሥርዓት ድንኳን ተክለው ሲገልጹ መሰንበታቸውን ታውቋል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/7583-2012-09-01-11-53-49.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር