የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ጉዳይ ደጋፊም ነቃፊም አላጣም



ዩሮ ዞን በሚባለው የገንዘብና የኢኮኖሚ ጥላ ሥር ትስስር የፈጠሩት 17 የአውሮፓ አገሮች እ.አ.አ. ከ2008 ጀምሮ ከተከሰተው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ በሚፈለገው መጠን ማገገም አልቻሉም። የእነዚሁ አገሮች ከኢኮኖሚ ቀውስ አለማገገም ታዲያ ገፈቱ ለመላው ዓለም ተርፎ የኢኮኖሚ ስጋትን ከፈጠረ ውሎ አድሯል። በተለይም ዕዳዋ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷ 180 በመቶ ደርሶ የተቆለለባት ግሪክን ጨምሮ ስፔን፣ ፖርቱጋልና ጣሊያንም በከፍተኛ ዕዳና የበጀት ድጎማ ስር መውድቃቸው ለቀውሱ መባባስ ዓይነተኛ ምክንያት ሆኗል። 
የጋራ መገበያያ ገንዘባቸውን ዩሮ ያደረጉት እነዚሁ አገሮች አንዴ በየአገር ቤታቸው በየጊዜው በሚጎድል በጀት፣ በሚያሻቅብ የሥራ አጥ ቁጥርና በገበያዎች መዳከም ሲናጡ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በኢኮኖሚ ቀውሱ ክፉኛ ለሚመቱት የዞኑ ማህበርተኛ አገሮች እጃቸውን በመዘርጋት ሲቸገሩ ይገኛሉ። አሁን አሁን ቀውሱ ከምዕራባውያን አልፎ በዓለም ዙሪያ በመዛመቱ ከፍተኛ የስጋት ድባብ ፈጥሯል። የዩሮ ዞን አገራትም ቀውሱ የሚበረታባቸው ከሆነ ያስተሳሰራቸው የግንኙነት ሐረግ ቀስ በቀስ እንዳይበጠስ ተሰግቷል። 
27ቱ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የዩሮ ዞንን መስርቶ በጋራ ገንዘብ ለመጠቀምና በአንድ አህጉራዊ ማዕከላዊ ባንክ ለመመራት ለ44 ዓመታት ተደራድረዋል። የአንድ ጎልማሳ ሰው እድሜ ያክል ተደራድረው እውን ባደረጉት የገንዘብ ኅብረት ታዲያ እጅጉን ጠቅሟቸው ታይቷል። ከጠንካራው ፓውንድ ጋር የሚፎካከር አህጉራዊ ገንዘብ ባለቤት ሆነዋልና።
የኋላ ኋላ ግን በአንድ የዞኑ አባል አገር ድክመትም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚነሳ የገንዘብና የኢኮኖሚ ቀውስ ለሌላውም ማህበርተኛ ሲተርፍ ታዝበናል። በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ የከፋ ችግር ውስጥ መግባታቸው በግልፅ እየታየ ነው። እንዲያውም ለባለ ጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤቶቹ ጀርመንና ፈረንሳይ ምስጋና ይግባና ዞኑን እየደጋገፉት ባይዘልቁ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ሌሎች ምዕራባውያን አገሮችም ለዞኑ ምርኩዝ ባያቀብሉ ኖሮ እስካሁን የአካባቢውና የዓለም ኢኮኖሚ አደጋ ላይ በወደቀ ነበርም ይባላል። 
ይኸው የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (East African Community) የጋራ መገበያያ ገንዘብ ወደ መጠቀም እየተንደረደረ መሆኑ ሰሞነኛ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። ብሩንዲን፣ ኬንያን፣ ርዋንዳን፣ ታንዛንያንና ዩጋንዳን ያቀፈው ይኸው ክፍለ አህጉራዊ ጥምረት በድጋሚ ከተመሰረተበት እ.አ.አ. 2000 ዓ.ም. ጀምሮ በአባል አገራት መካከል የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥምረት ለመፍጠር ይሰራል። በተለይም የማኅበረሰቡን አባል አገራት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር በጋራ ገንዘብ እስከ መጠቀምና በፌዴሬሽን የመንግሥት አወቃቀር አንድ አገር እስከ ማድረግ ውጥን ይዞ እየሰራ ነው። 
ማኅበረሰቡ ይህንኑ የኢኮኖሚና የፖለቲካዊ ትስስር ውጥኑን ከዳር ለማድረስ በተለያዩ ጊዜያት በቅደም ተከተል የሚከናወኑ አራት ምዕራፎችን አስቀምጧል። የመጀመሪያውን ምዕራፍ እ.አ.አ. በ2005 ዓ.ም. ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በዚህም በአባል አገራቱ መካከል ድንበር ተሻጋሪ ኢንቨስትመንትን የማበረታታት፤ ምርትን ያለቀረጥና ያለኮታ ገደብ ለአገራቱ ገበያ ማቅረብ፤ ማኅበርተኛ ካልሆነ አገር የሚገባ ምርትን በተመሳሳይ ሁኔታ መቅረጥ የሚሉትንና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚመለከት (የከስተም ዩኒየን ፕሮቶኮል) አጽድቆ ተግባራዊ እያደረገ ነው። 
በሁለተኛው ምዕራፉም እ.አ.አ. ከ2010 ጀምሮ የጋራ ገበያን (Common market) መስርቷል። በዚህም ምርት፣ አገልግሎት፣ ካፒታልና የሰው ኃይል ከአንዱ አባል አገር ወደ ሌሎቹ ያለገደብ እንዲዘዋወር ሆኗል። በሦስተኛው ምዕራፍም በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ማገባደጃ የገንዘብ ኅብረትን (Monetary Union) እውን ለማድረግ የወጠነ ሲሆን፤ እ.አ.አ. በ2015 ደግሞ አምስቱን የማ ኅበረሰቡን አባል አገሮች ያቀፈ አንድ የምሥራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን ለመመስረትም ታቅዷል። 
አሁን ታዲያ አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ ማኅበረሰቡ የምሥራቅ አፍሪካ ዶላር አልያም ሽልንግን በጋራ መገበያያ ገንዘብነት ለመጠቀምና የገንዘብ ኅብረት ፈጥሮ በአንድ ክፍለ አህጉራዊ ማዕከላዊ ባንክ ለመመራት እየተንደረደረ መሆኑ ነው። ይህ የአገራቱ ውሳኔና የመንደርደር ፍጥነት ደግሞ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኗል። በአንደኛው ወገን በጋራ ገንዘብ መጠቀም የተለያዩ ገንዘቦችን ለመመንዘር የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ከማስቀረቱም በላይ የገንዘብ ምንዛሬ ስጋቶችንም ለማስቀረት ይጠቅማልና በቶሎ ወደ ገንዘብ ኅብረቱ መግባት ያዋጣል የሚል ሃሳብ ይሰነዘራል። በሌላው ጥግ ደግሞ «የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም» እንደሚሉት ብሂል በጋራ ገንዘብና በአህጉራዊ ማዕከላዊ ባንክ የተመሩቱን የዩሮ ዞን አገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ እየታየ አጣዳፊ ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ አይደለም የሚሉ ተንታኞች አሉ። 
በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ተቋማዊ ታሪክ በአንድ ገንዘብ የመገበያየት ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ መቅረብ የጀመረው ገና ከማኅበረሰቡ ምስረታ ማግስት ነበር። ማኅበረሰቡ እ.አ.አ. በ1967 ተመስርቶ እ.አ.አ. በ1977 እስከ ተበታተነበትና ኋላ ላይ እ.አ.አ. በ2000 ዳግም ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በአባል አገሮች ዘንድ አንድ ዓይነት የገንዘብ ሥርዓትን የመዘርጋቱ ፍላጎት በጣሙን ከፍ ያለ ነበር። እንዲያውም ኬንያ፣ ታንዛንያና ዩጋንዳ ከነፃነታቸው በኋላ አንስቶ ማኅበረሰቡ ፈራርሶ የየራሳቸውን ገንዘብ መጠቀም እስከጀመሩ ድረስ የምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግን ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ይህም ማኅበረሰቡ በድጋሚ መቋቋሙን ተከትሎ በአገሮቹ መካከል ተመሳሳይ ገንዘብ የመጠቀም ፍላጎት ዳግም ለመጨመሩ ምክንያት መሆኑ ነው የሚነገረው። 
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ዳግም ከተወለደ በኋላ ከጥቂት ዓመታት ድርድሮች ማግስት ለኢኮኖሚ ውህደት ወሳኝ የሆኑ ሁለት ታላላቅ ስምምነቶችን ተግባራዊ አድርጓል « ከስተም ዩኒየን» እና የጋራ ገበያ ፕሮቶኮሎችን። አሁን ደግሞ በጣም ፈጣን ሊባል በሚችል መልኩ የገንዘብ ኅብረት ለመፍጠር በመንደርደር ላይ ይገኛል። ማኅበረሰቡ ይህንኑ የጋራ የገንዘብ ሥርዓት ዝርጋታ እውን ለማድረግ እንዲቻለው ጥርጊያ የሚያመቻች የከፍተኛ ተደራዳሪዎች ግብረ ኃይል አቋቁሟል። ይህ ግብረ ኃይልም የአባል አገሮችን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ኃላፊዎችን፤ በማኅበረሰቡ የአባል አገራት ወኪሎችን፣ የማዕከላዊ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ፣ የጡረታና የብሔራዊ ስታትስቲክስ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን የያዘ ነው። 
ግብረ ኃይሉ እ.አ.አ. ከ2011 ዓ.ም መባቻ ጀምሮ ድርድር የጀመረ ሲሆን፤ 86 አንቀፆች ባሉት የገንዘብ ኅብረት ፕሮቶኮል ረቂቅ ላይ በሰባት የተለያዩ መድረኮች ምክክርና ድርድር አካሂዷል። ባለፉት የድርድር መድረኮችም በገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፎች፣ በምንዛሬና በምጣኔ ፖሊሲዎች፣ በገንዘብ ቁጥጥር ሥርዓት፣ ስትራቴጂዎችና በመሰል መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ ደርሷል። 
ከቀናት በፊትም ስምንተኛው ድርድር በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ዋና መቀመጫ በታንዛንያ አሩሻ ከተማ ላይ በማካሄድ የጋራ ገንዘብ ሥርዓቱን በሚያፋጥኑ አጀንዳዎች ላይ ምክክር አድርጓል። ከመድረክ ላይ ድርድሮችና ምክክሮች ባሻገርም 20 አባላትን የያዘ የማኅበረሰቡ ልዑክም በሦስት የዩሮ ዞን አባል አገራት ጉብኝት በማድረግ የኢኮኖሚና የገንዘብ ሥርዓት ተሞክሮን ዳስሷል። 
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ምክትል ዋና ጸሐፊ ኤኖስ ቡኩኩ እንደሚሉት፤ በከስተም ዩኒየንና በጋራ ገበያ ከተገኘው ጣፋጭ ፍሬ በጣሙን የተበረታቱት የማኅበረሰቡ አባል አገራት የጋራ ገንዘብ ሥርዓትን ለመዘርጋት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በተለይም የጋራ ገንዘብ በመጠቀም ንግድና ኢንቨስትመንትን ቀላል ማድረግን አገራቱ በቅጡ ተረድተውታል። የጋራ ገበያው የምርትና አገልግሎቶችን፣ የካፒታልና የሰው ኃይል ዝውውርን ነፃ ማድረግ የአገሮቹን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ግንኙነት ያሰፋል። በሁለቱ የማኅበረሰቡ ስምምነቶች የተገኘው ውጤት ደግሞ በገንዘብ ውህደት ስምምነቱም እንደሚደገም ይጠበቃል። 
ዶክተር ቶማስ ኪጋቦ ደግሞ የርዋንዳ ብሔራዊ ባንክ ዋና ኢኮኖሚስትና በድርድር ግብረ ኃይሉ ውስጥ የአገራቸው ተደራዳሪ ናቸው። አንዳንድ ተንታኞች የገንዘብ ኅብረት ጉዞውን ከዩሮ ዞን ጋር በማያያዝ መተቸታቸውን ይቃወማሉ። እርሳቸው እንደሚሉት አውሮፓውያን የገንዘብ ኅብረት ለመፍጠር ባደረጉት ጉዞ በርካታ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። ዩሮ ዞንም ለምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የገንዘብ ኅብረት ምሳሌ ሊሆን አይገባውም። ምክንያቱም የእነርሱና የምሥራቅ አፍሪካ ነባራዊ ሁኔታዎች ለየቅል ናቸውና። 27ቱ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች የገንዘብ ኅብረት ለመፍጠር ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ተደራድረዋል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አገሮቹ ብዙ መሆናቸውና ፖለቲካዊ ፍላጎትን አለማዳበራቸው ነው። እኛ ግን አምስት አገሮች ብቻ ነን። ይህም ድርድሩን በፍጥነት ለመቋጨት ያግዛል ይላሉ።
በሌላኛው ጥግ ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የገንዘብ ኅብረት ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጉዞ ቆም ብሎ እንዲያጤነው የሚያሳስቡ ትንታኔዎችም ይደመጣሉ። በዚህ ረገድ የሚሰነዘሩት ሃሳቦች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የዩሮ ዞን የኢኮኖሚ ቀውስን ዋቢ የሚያደርጉ ናቸው። በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት የገንዘብ ኅብረቱ ድርድር በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ተቋጭቶ የፕሮቶኮሉ ረቂቅ ለአባል አገሮች ለፊርማ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ይሁንና በእስካሁኖቹ ድርድሮች የገንዘብ ኅብረቱን የምስረታ ጥድፊያ የርዋንዳና የዩጋንዳ ተደራዳሪዎችና ባለሥልጣናት ሲተቹትና ርጋታ እንዲኖር ሲሞግቱ ተስተውለዋል።
ፕሮፌሰር ማህሙድ ማምዳኒ በዩጋንዳ ማከሬሬ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው። በቅርቡ በባንክ ኦቭ ዩጋንዳ አማካኝነት በተዘጋጀ መድረክ ላይ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የዩሮ ዞንን ፈለግ እየተከተለ ወደ ገንዘብ ኅብረት ለማምራት መጣደፉን ነቅፈዋል። ሥርዓትን ከመዘርጋቱ አስቀድሞ የፖለቲካ አንድነትን በመፍጠር ፌዴሬሽናዊ ውህደቱን ማስቀደም እንዳለበት ይመክራሉ። 
የፕሮፌሰር ማህሙድን ዓይነት ሃሳብ ከሚያራምዱ መሪዎች ውስጥ ደግሞ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ይጠቀሳሉ። « ፖለቲካዊ ፌዴሬሽን ዋና ነገር ነው። የኢኮኖሚ ጥምረት ያለ ፖለቲካ ውህደት ትርጉም የለውም። ገበያም ክፍት ቢሆን ፖለቲካዊ ውህደትን መፍጠር ካልተቻለ ፍትሐዊ የሀብትና የጥቅም ክፍፍል አይኖርም» ሲሉ መናገራቸውን ነው ኢስት አፍሪካን ቢዝነስ ዊክ የተባለ የዜና አውታር ከሰሞኑ ያስነበበው።
ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንዳተተው ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል አገሮች የዕዳ መጠን ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሳያመጣ ሊስተካከል የሚችል በመሆኑ ወደ አንድ የመገበያያ ገንዘብ የሚያሯሩጥ ምክንያት አይኖርም። ለአብነት የኬንያ የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 49 ነጥብ አምስት በመቶ ሲሆን፤ የዩጋንዳ ደግሞ 19 ነጥብ ሰባት በመቶ ነው። ይህም አገራቱ በቀላሉ መቆጣጠር የሚችሉት የዕዳ መጠን ነው። በአንፃሩ በዩሮ ዞን ውስጥ ያለችው የግሪክ ዕዳ ግን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷ 180 በመቶ ደርሶ ጦሷ ለሌሎቹም የዞኑ አገሮች ስጋት ሆኗል። 
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል አገራት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ቀውስ እየተከሰተ ባለበት በአሁኑ ወቅት በትኩረት ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ አለ። ዓመታዊ የአገር ውስጥ ምርት እድገታቸውን በትንሹ በሰባት በመቶ ማስቀጠል፤ የዋጋ ግሽበትን ከአምስት በመቶ በታች ማድረግ፤ እንዲሁም የበጀት ጉድለታቸው ከዓመታዊ የአገር ውስጥ ምርት ከአምስት በመቶ እንዳይበልጥ ማድረግ እንደ ሚገባቸው የሚመክሩ ሊቃውንትም አሉ።የ« ከስተም ዩኒየኑ» እና የጋራ ገበያ ስምምነቶች በቅጡ በሁለት እግራቸው ያለመቆማቸውና የዩጋንዳና የኬንያ የነዳጅ ማግኘትን በማንሳት የገንዘብ ውህደቱ እንዲጤን ሃሳብ የሚሰጡም አሉ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር