የኑሮ ውድነት ያሸበበው የበዓል ዋዜማ



በታደሰ ገብረማርያም

“የተለያዩ ዓይነት የምግብ ሸቀጦችና የእርድ እንስሳት ሥጋ ዋጋ ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሲሔድ እንጂ ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር ሲጣጣም አይታይም፡፡
በዚህም የተነሳ በክርስቲያንና በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ዘንድ የሚከበረውን የዘመን መለወጫን የሚያክል ታላቅ በዓል በጥሩ ዝግጅት ለማሳለፍ ቀርቶ የዕለት ፍጆታን ለመሸፈን በማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታም በደሀና በሀብታም መካከል ያለው ክፍተት ከመጥበብ ይልቅ እየሰፋ መምጣቱን ለማወቅ የግዴታ የኢኮኖሚ ባለሙያ መሆን አይጠይቅም፡፡”

ይህንን አስተያየት የሰነዘሩት በተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ለዘመን መለወጫ በዓል ቅቤና ዘይት፣ ዶሮ፣ በግ፣ እንቁላል፣ የጤፍና የስንዴ ዱቄት ሲሸምቱ ካገኘናቸው ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ የበዓሉን ዝግጅትና የገበያውን ሁኔታ አስመልክተው በየተራ በሰጡት ማብራርያ ነው፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አባባል ከሆነ በተለይ በምግብ ሸቀጦች ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ ነጋዴዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው መዘንጋት የለበትም፡፡

አሻጥር ከሚፈጽሙባቸውም የምግብ ሸቀጦች መካከል የምግብ ዘይትና ቅቤ፣ በአባይ ሚዛን የሚቸረችሩት ጥራጥሬዎችና የእህል ዱቄት፣ ሥጋ የመሳሰሉና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመው ይህንን የሚከታተልና የሚቆጣጠር መንግሥታዊ አካል መኖሩን በመገናኛ ብዙኅን እንደሚሰሙ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አካል በስም እንጂ በገቢር እንደማይታይና በአሻጥረኞችም ላይ ዕርምጃ ሲወስድ እንዳልተሰማ ወይም እንዳልታየ ነው ያስረዱት፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ነዋሪ የሆኑና መርካቶ ቅቤ ተራ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሐረገወይን አበበ “ኑሮዬ መካከለኛ ገቢ ካላቸው የኅብረተሰቡ ክፍሎች ይመደባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በአንድ ኪሎ ቅቤና በአንድ ዶሮ በዓሉን መጠን ባለ ሁኔታ ከቤተሰቤ ጋር በደስታ አሳልፋለሁ ብያለሁ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሕይወት ያስከተለው የሐዘን ድባብ የበዓሉን ዝግጅት አደብዝዞታል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፤” ብለዋል፡፡

ወይዘሮ አስቴር ደበበ የተባሉ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ደግሞ በወፍቻ የታሰረውን ቅቤ፣ በቀኝ እጃቸው በአየር ላይ አንጠልጥለው “ሆቼ ጉድ! እስቲ አንድ ኪሎ ትሆናለች እቺ ቅቤ? ስትነጠር ደግሞ ንጹሕ መሆኗ ቀርቶ ከሙዝ፣ ከረጋ ዘይትና ከሌላም ባዕድ አካል ጋር የተቀየጠች ሆና ትገኛለች፡፡ ይሁን እስቲ! ማን ማንን ያምናል በአሁኑ ጊዜ፤” እያሉ ሲያጉረመርሙ ሰማናቸው፡፡ ስንት ገዙት አልናቸው? “180 ብር አሉን” ቅቤ ነጋዴዎች እንደነገሩን ከሆነ አንድ ኪሎ በሳል ቅቤ 150 ብር ይሸጣል፡፡ “ተወዶም ንጹሕ ቢሆን መልካም ነው፤” አሉን ቆመው ተራቸውን ሲጠባበቁ የነበሩት ሌላዋ እናት፡፡

ፒያሳ አትክልት ተራ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 15 ብር ሒሳብ ሲቸረቸር ተመልክተናል፡፡ ሽንኩርቱ በጣም እርጥብና እሸት ከመሆኑም ሌላ ደረጃውን ያልጠበቀና አልፎ አልፎም የበቀለ ነው፡፡ “ውድ የሆነበት ምክንያት ወቅቱ ገና ስለሆነና ስላልደረሰ ነው፤” ያለን ሚዛን አንጠልጥሎ ሲቸረችር የነበረው ወጣት ነው፡፡ በገበያ ላይ ተፈላጊና አንገብጋቢ የሆነው ቀይ ሽንኩርት ጠፍቶ በምትኩ ድንች በብዛት ገብቷል፡፡ በርካታ ሸማቾችም በቀይ ሽንኩርት እጥረት ሳቢያ ግራ ተጋብተው ሲቸገሩ ተስተውለዋል፡፡

በአትክልት ተራ ዋጋ በመወደዱ በተያዘው ሳምንት መጀመርያም ታሽጐ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ቲማቲም በቄራውም ሆነ በፒያሳው አትክልት ተራ ዋጋው ንሯል፡፡ እስከ 16 ብርም እየተሸጠ ነው፡፡ በድንገት የናረውን የአትክልት ዋጋ ለማረጋጋትም ሽንኩርት ከ8 ብር በላይ እንዳይሸጡ በመንግሥት ገደብ የተጣለባቸው መሆኑን ከአትክልት ተራ ነጋዴዎች ሰምተናል፡፡ ሆኖም አዋጭ አይደለም፡፡ በሾላ ገበያም ቢሆን የእህል ጥራጥሬና የአትክልት ዋጋ ከሌላው ጊዜ ንሮ ተስተውሏል፡፡ ነጋዴዎች ስለምክንያቱ ለማስረዳት ግን ፍላጐት የላቸውም፡፡ የሚናገሩት ቢሆኑም ስናመጣውም ውድ ነው ከማለት ውጭ ዝርዝር አይሰጡም፡፡

ልጃቸውን አስከትለው በግ ሲያማርጡ ያገኘናቸው አባወራ ዋጋው እንደማይቀመስ ነው የተናገሩት፡፡ የያዙት ገንዘብና በግ ነጋዴዎቹ የሚጠሩት ዋጋ ፍጹም አይገናኝም፡፡ ሙክት በግ 3 ሺሕ ብር፣ መካከለኛ እስከ 1,500፣ አነስተኛ ጠቦት እስከ አንድ ሺሕ ብር ይጠሩባቸዋል፡፡ ጉማሬ አለንጋ በትከሻው ላይ ጣል ያደረገ አንድ በግ ነጋዴ ወደ አጠገባችን ቀረብ ብሎ “ምን እናድርግ! አሁን ይችን አነስተኛ በግ ከገበሬው የገዛሁት በአንድ ሺሕ ብር ነው የትራንስፖርት ወጪውንና ድካሜንም አስባችሁ ስንት ብር ብሸጥ ያዋጣኛል ትላላችሁ? እስቲ ፍረዱ፣ ፍርድ ከራስ ነው፤” አለን፡፡ ይኸው ነጋዴ የጠቆመንን በግ 1,300 ብር ሲጠራባት ሰማን፡፡

ካራና ሸጎሌ ከሚገኙት የቁም እንስሳት የገበያ ሥፍራዎች ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ከሆነ ነጋዴዎች ለአንድ አነስተኛ ሰንጋ የሚያቀርቡት የጥሪ ዋጋ የትየለሌ ነው፡፡ እስከ 20 ሺሕ ብር የሚጠራበት ሰንጋ እንዳለም አይተናል፡፡ 15ሺሕ፣ 12ሺሕ ብር የሚጠሩባቸው መካከለኛና ዝቅተኛ ሰንጋዎች እንዳሉ ነው፡፡ ጥጃ እስከ 9ሺሕ ብር ይጠየቅበታል፡፡ ከዘራ፣ ምርኩዝና ገመድ ይዘው ሰንጋ ለመግዛት ከሚያማርጡት አባወራዎች መካከል አብዛኛዎቹ ጥሪው ከአቅማቸው በላይ ሆኖ እንዳገኙት ነው የነገሩን፡፡

ወደ ዶሮ ተራም አቅንተን ነበር፡፡ በሥፍራው ያነጋገርናቸው ወይዘሮ አልማዝ አብርሃን ነው፡፡ በጉያቸው አንድ ቀይ ዶሮ አቅፈው፣ በግራ እጃቸው በሸቀጥ የተሞላ የፕላስቲክ ከረጢት አንጠልጥለዋል፡፡ ዶሮውን ስንት ገዙት? አልናቸው፡፡ “200 ብር” አሉን፡፡ “እንቁላል ውድ ስለሆነ ተውኩት፡፡ ዶሮ አለእንቁላል አይሠራም ያለው ማንነው? እኔ ከድንች ጋር በጥሩ ሁኔታ አዘጋጅቼ አቀርባለሁ፤” ብለውን ተለዩን፡፡ የዶሮና የእንቁላል ዋጋ አይቀመስም፡፡ ከፍተኛ እስከ 200 ብር መካከለኛው 180 ብር ሴት ዶሮ 120 ብር ሲሸጥ አንድ እንቁላል በሦስት ብር ሲቸረቸር ተመልክተናል፡፡ አንዳንድ የዶሮ ነጋዴዎች ይህንኑ አስመልክተው እንዳብራሩልን ከሆነ እነሱም ከገጠር የሚገዙት በውድ ዋጋ መሆኑንና የትራንስፖርትም ወጪ ለዋጋው መናር ምክንያት ሆኗል፡፡

ለዳቦ የሚሆን የስንዴ ዱቄት ነጋዴዎች ኪሎውን በ15 ብር ሒሳብ ሲሸጡ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች ደግሞ በ8 ብር ሒሳብ በመሸጥ ገበያውን ለማረጋጋት ሞክረዋል፡፡ በልደታ፣ በቂርቆስና በአራዳ ክፍለ ከተሞች በመዘዋወር ካነጋገርናቸው አንዳንድ እናቶች እንደነገሩን ከነጋዴውም ሆነ ከማኅበራቱ የሚገዙት የስንዴ ዱቄት ጥራቱን የጠበቀ አይደለም፡፡ ዱቄት ተቦክቶ ከተጋገረ በኋላ ቶሎ የመድረቅና የመፈርፈር ባሕሪ አለው፡፡ የሚቀልጥም ያጋጥማል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር