መረጃ:- የግልጽነትና የተጠያቂነት ቁልፍ መሳሪያ

ከኢፌዲሪ ህገ- መንግስት አምስት መሰረታዊ መርሆዎች ውስጥ የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት አንዱ ነው፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ በመንግስት ሀላፊዎች የሚወሰዱ ውሳኔዎችና የስራ እቅስቃሴዎች ለህዝቡ ግልጽ መሆናቸውንና ህዝቡም ይህንን በተመለከተ ያሉትን መረጃዎች ለማግኘት ያለውን መብት የሚያረጋግጥ መርህ ነው፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ የዲሞክራሲ ዋልታ በመሆኑም ከመርሁ ተግባራዊነት ውጪ ዲሞክራሲን ማስፈን የማይታሰብ ነው፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት ትልቁን ድርሻ የሚይዘውን የህዝቦች ተሳትፎና የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግስት አሰራርን እውን ማድረግ የግድ ይላል፡፡
ዜጎች በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና የመንግስት ሀላፊዎች ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ለመመርመር ተገቢውን መረጃ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ግልጽነትም ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ሲሆን ለተጠያቂነትም እንደ ቅድመ ሁኔታ ይቀመጣል፡፡ በመሆኑም የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ የህዝቦችን ተሳትፎ ከማሳደጉም በላይ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ዜጎች መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብታቸው መከበሩ አንድም ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ሌላም የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህን በመተግበር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተግባራዊነትን ለማረጋገጥ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው፡፡፡ ዜጎች መረጃ ለማግኘት በራሳቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪም ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን በመፈለግና ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግም የመገናኛ ብዙሀን ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የመደንገጉ ምክንያትም የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብትንና የመገናኛ ብዙሀን መረጃዎችን እንዲያገኙ የማድረግ እድልን በጥምረት ለማረጋገጥ ነው፡፡ 
አዋጁ በህገ-መንግስቱ የተረጋገጡትን ግልጽ የመንግስታዊ አሰራርና የተጠያቂነት እሴቶችን ለማዳበርና ለማጠናከር እንዲሁም የህዝብ ጥቅምን የሚመለከቱ ጉዳዮች ይፋ ወጥተው ህዝብ እንዲወያይባቸው ለማድረግ ይቻል ዘንድ በሶስቱም የመንግስት አካላት ማለትም በህግ አውጪ፣ በህግ ተርጓሚና በህግ አስፈጻሚ ደረጀ የሚገኙ የመንግስት ሀላፊዎች ለግለሰቦችና ለመገናኛ ብዙሀን መረጃዎችን የማቅረብ ግዴታ በህግ እንዲጣልባቸው አድርጓል፡፡ 
የመንግስት መረጃ የህዝብ ሀብት ነው፡፡ ስለሆነም አዋጁ ማንኛውም የመንግስት አካል ገደብ ከተደረገባቸው መረጃዎች ውጪ ያሉትን መረጃዎች ያለምንም ልዩነት መረጃውን ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው በተለያዩ ዘዴዎች ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ በሁሉም የመንግስት አካላት እንዲፈጸም መደረጉም በሁሉም የመንግስት አሰራር እርከን ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግስት አስተዳደርን በማረጋገጥ የህዝቡን ተሳትፎና የመወሰን አቅም ለማሳደግ እድል የሚፈጥር ሲሆን በሌላ በኩልም ብልሹ አሰራርንና ሙስናን በማጋለጥና በመዋጋት ሂደትም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ የመንግስት አሰራር ውጤታማነትን ለማሳደግና መልካም አስተዳደርን ለመገንባት የሚያስችል መርህ በመሆኑም ሀገራችን እየተከተለችው ያለችውን የዲሞክራሲ ስርዓት ለማጎልበት ዋነኛ መሳሪያ ነው፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ ማዕከላዊ ሀሳብ መረጃ በመሆኑም የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነጻነት አዋጁ ማንኛውም የመንግስት አካል የመንግስት መረጃን ተደራሽ በማድረግ የመንግስት አሰራር ለዜጎች ግልጽ እንዲሆንና የመንግስት ሀላፊዎችም ሀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ 

ስልክ፡- +251-111-58-06-71/76 ፋክስ፡- +251-111-58-06-38/40
ፖ.ሳ.ቁ፡- 2459

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር