‹‹ዳገቱ መሀል ላይ ማረፍም ሆነ መቀመጥ አይፈቀድልንም›› ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ


በጋዜጣው ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በቅርቡ እንደሚተኩ የሚጠበቁት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሰኞ ምሽት ለሕዝቡ ምሥጋና ለማቅረብ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈተ ሕይወት ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ላሳየው ጨዋነት የተሞላበት የሐዘን ሥርዓት በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ስም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ሕዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጀመሩትን ሥራ በአግባቡ መቀጠል እንዳለበት ማስገንዘቡን ያስታወሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ መሪውን በታላቅ ፍቅር፣ ክብርና ሰላም በዕንባ በታላቅ ሥነ ሥርዓትና ሞገስ መሸኘቱን ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡ ኢትዮጵያ የታላቅ ሕዝብ አገር መሆኗን ለወዳጅም ለጠላትም አስመስክሯል ብለው፣ ‹‹ዛሬ እፊታችሁ የቀረብኩት ዓለምን ስላስደነቀው ታላቅ ሥራችሁ የሚገባችሁን ምሥጋና በድርጅታችን በኢሕአዴግና በኢፌዲሪ መንግሥት ስም በታላቅ አክብሮትና ትህትና ለማቅረብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአቶ መለስን የፅናት መንፈስ ያወደሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ለራስ ሳይሆን ለሕዝብ መኖርን፣ ፅናትን፣ መስዋዕትነትንና ፈተናን መጋፈጥ ብቻ ሳይሆን በፈተና መካከል ሆነው ለሕዝብ ጥቅም መፍትሔ መፈለግንና መውጫ ማበጀትን፣ ትዕግስትን፣ ይቅርታንና ትህትናን በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ከሕይወት ተሞክሮአቸው በተግባር አስተምረው አልፈዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ራዕይ አገሪቱን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ማሰለፍ እንደነበር ጠቅሰው፣ ‹‹በእሳቸው መሪነት ዳገቱን አጋምሰናል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት ከአሥር በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበናል፤›› ብለዋል፡፡ በማከልም፣ ‹‹ጥርሳችንን ነክሰንና ትንፋሻችንን አስተባብረን ወደ ራዕዩ ሜዳ ለመውጣት መረባረብ ይገባናል፡፡ ዳገቱ መሀል ላይ መቀመጥም ሆነ ማረፍ አይፈቀድልንም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ዳገቱ ላይ ማረፍ ድካም ያመጣል ካሉ በኋላ፣ ‹‹ይልቅ የተወሰነ ፍጥነት እየጨመርን በእልህና በቁጭት ከዳገቱ ባሻገር ጫፍ ላይ ሜዳ እንዳለ እያየን መገስገስ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የአዲሱ ትውልድ የአመራር ቡድንም ከነባሩ የአመራር ቡድን ጋር በመቀናጀትና የተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ በአቶ መለስ የተጀመሩትን ሥራዎች እንደሚያስቀጥሉ ጥርጥር እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ ‹‹በልበ ሙሉነት ይህንን ስናገር እሳቸው ያስተማሩንና ያሳዩንን መስመር መከታ በማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ማክሰኞ ዕለት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ይገመገምበታል በተባለው ስብሰባ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈት በኋላ በሕዝቡ የተስተጋባውን ስሜት ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሚነሱ የተለያዩ አስተያየቶች ላይም እንደሚነጋገር የታወቀ ቢሆንም፣ ሕትመት እስከገባንበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ የስብሰባው ውጤት አልታወቀም፡፡    

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር