የሕግ ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምን ሠራ?



ባለፈው ዕትማችን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2004 ዓ.ም ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ከኮሚቴው አባል የተከበሩ አቶ ዳዊት ተፈራ ጋር ባደረግነው ቃለ ምልልስ ማስነበባችን ይታወሳል፤ በዚህ እትማችን ደግሞ ቀሪውን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡ 
ሕግ ከማውጣት አንፃር ቋሚ ኮሚቴው ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ አምስት ረቂቅ አዋጆችን ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በመተባበር ሰርቷል፡፡ረቂቅ ሕጎቹ የሕግ አወጣጥ ሥርዓትን በተከተለ ሁኔታ ተረቅቀው የውሳኔ ሃሳብ ሪፖርት ቀርቦባቸው በምክር ቤቱ እንዲፀድቁ ተደርጓል፡፡ ሌላው ቋሚ ኮሚቴው ብቻውን የሚመለከተው እና ኃላፊነቱን ወስዶ በማርቀቅ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ በማቅረብ የፀደቀው 'የወሳኝ ኩነት እና ብሔራዊ መታወቂያዎች' የሚለው አዋጅ ነው፡፡
በዚህ አዋጅ መሰረት የእያንዳንዱ ሰው ከልደት እስከ ሞት ያለው መረጃ ይመዘገባል፡፡ ለዚሁ ሥራ ከታች እስከ ላይ መዋቅር ያለው ጽ/ቤት ይቋቋማል፡፡ በአዋጁ መሰረትም እንደ ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም ብሔራዊ መታወቂያ ይዘጋጃል፡፡መታወቂያው ሙሉ የማንነት መረጃን የያዘ ሲሆን ፤ለብሔራዊ ደህንነት እንዲሁም መንግሥት ሊዘረጋቸው ለሚፈልጋቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ጭምር አጋዥ ነው የሚሆነው፡፡ 
ምንም እንኳን በበቂ ሁኔታ ተሳትፎበታል ለማለት ባያስደፍርም በረቂቅ አዋጁ ላይ ሕዝቡ ተሳትፎ እንዲያደርግበት ኮሚቴው ጥረት አድርጓል የሚሉት አቶ ዳዊት ረቂቁን ለማዳበር ከሚመለከታ ቸው አካላት ጋር የውይይት መድረክ ተፈጥሮ ጠቃሚ ግብአትም ከመገኘቱም በላይ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ተብሎ ለሚታሰቡ ወገኖችና ተቋማትም ረቂቁ ላይ የበኩላቸውን ሃሳቦች ሰንዝረዋል።
ሌላው ቋሚ ኮሚቴው ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡለትን ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን መርምሮ ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ ለሚመለከተው አካል የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በዓመቱ 123 ጥቆማዎችና አቤቱታዎችን ተቀብሏል፡፡48 የሚሆኑት ጥቆማዎችና አቤቱታዎች በመመሪያው መሰረት መፍትሄ ተስጥቷቸዋል፡፡44 ጉዳዮች ደግሞ መመሪያውን ያልተመለከቱና ምላሽ ያልተሰጣቸው ሲሆኑ ስድስት የሚሆኑት በመታየት ላይ ናቸው፡፡ ዘጠኝ ጉዳዮች ዘግይተው ስለደረሱ በቀጣይ የሚታዩ ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ 16 ጉዳዮች በግልባጭ ቋሚ ኮሚቴው እንዲያየው የተላኩበት ሁኔታ አለ፡፡ 
እዚህ ላይ ቋሚ ኮሚቴው የተቸገረበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ዳዊት ይናገራሉ፡፡ « በፍርድ ቤት የታዩ እና ውሳኔ የተሰጣቸውን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ሊያይ አይችልም፤ነገር ግን ሕዝቡ እስከ ሰበር ድረስ የታዩ ጉዳዮችን ወደ ቋሚ ኮሚቴው ይልካል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ይህን የሚያደርገው ከግንዛቤ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ይህ ሁኔታ ምክር ቤቱ እዚህ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሥራት እንዳለበት ያሳያል» የሚሉት አቶ ዳዊት መመሪያው የማይፈ ቅዳቸውን አቤቱታዎች፣ ቅሬታዎች፣ ለቋሚ ኮሚቴው ልኮ ያልሆነ ውሳኔና ውጤት መጠበቅ፣ ተገቢ አለመሆኑንና ለአላስፈላጊ እንግልትም የሚዳርግ በመሆኑ ሕዝቡ ምን ዓይነት ጉዳይ ነው ለኮሚቴው ማድረስ አለብኝ ብሎ ራሱን መጠየቅና የሙያ ሰዎችን ማማከር እንዳለበት ይመክራሉ።
ቋሚ ኮሚቴው ሊያይ የሚችለው በፍትሕ አስተዳደር፣በፍርድ ቤቶች፣በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ተጨባጭ የሆነ አድልዎ የተፈፀመ እንደሆነ፣ በሙስና ተግባር፣ በአጠቃላይ የፌዴራል ሥርዓትን ሊጎዱ የሚችሉ ሆነው በሌሎች አካላት ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የተያዙ ጉዳዮች ሲሆኑ ነው፡፡ 
በሀገሪቱ ለፍትህ አስተዳደር እና መልካም አስተዳደር መጐልበት የሚያግዝ አሠራር ለመቀየስ በቋሚ ኮሚቴው የተያዘው ሥራ አበረታች ነው የሚል እምነት መኖሩን ነው አቶ ዳዊት የሚገ ልጹት።
በአጠቃላይ ቋሚ ኮሚቴው በዓመቱ ይዞት ከተነሳው እቅድና ተልዕኮው አንፃር ውጤታማ ሥራ ሠርቷል ማለት እንደሚቻልም አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ኮሚቴው የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችን ከሕግ ዓይን አኳያ በመጠቆም ከሌሎች አካላት ጋር በተባባሪነት ሥራውን የሚቀጥል ሲሆን፤ በ2005 ዓ.ም ደግሞ ከዚህ በተሻለ አቅምና ብቃት በመሥራት በአሠራር የሚታዩ ጥቃቅን ግድፈቶችን በማረም ቋሚ ኮሚቴው በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ነው የገለፁት፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር