ኮሚሽኑ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕጎችን በሦስት ቋንቋዎች በመተርጎም ያሳተመውን ሰነድ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስረከበ፤ በሲዳማ ኣፎ መቼ ነው መሰል ሰነዶች መቶርጎም የምጀምሩት?

አዲስ አበባ መስከረም 15/2005 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አገሪቱ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕጎች፣ ስምምነቶችና መርሆዎችን በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ያሳተመውን ሰነድ ዛሬ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስረከበ። ኮሚሽኑ በሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ ያሳተማቸውን 35 ሺህ "የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች" ሰነድ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች አስረክበዋል። በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዳራሽ በተካሄደው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አምባሳደር ጥሩነህ ዜና እንደገለጹት አገሪቱ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕጎች፣ ስምምነቶችና መርሆዎች በሰብአዊ መብት ማስከበር ተግባር ላይ ሳይውሉ ቆይተዋል። እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ ቋንቋዎች ለረጅም ጊዜያት ሳይተረጎሙ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። ኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ህጎቹን ወደተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው ዳኞች እና ዐቃቤ ሕጎች ከአገሪቱ ሕጎች ጋር አቀናጅተው እንዲጠቀሙባቸው ማሳተሙን አስረድተዋል። በአገሪቱ የሰብአዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ዳኞች እና ዐቃቤ ሕጎች "የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች" ሰነድ በሥራ ላይ በማዋል ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ገልጸዋል። እንዲሁም ለፌዴራልና ለክልል ሕግ አውጪ አካላት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሰብአዊ መብት ዙሪያ ለሚሰሩ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች "የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች" ሰነዱን ለማሰራጨት የሚያስችል ስትራቴጂ የተነደፈ መሆኑን አመልክተዋል። "የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች" ሰነዱ በአፋርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች በመተርጎም በክልሎቹ ለሚገኙ ዳኞች እና ዐቃቤ ሕጎች ለማዳረስ ዝግጅት መደረግ ላይ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ጥሩነህ በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎችም ተተርጉሞ እንዲዳረስ ይደረጋል ብለዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መድኀን ኪሮስ እንዳሉት "የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች" ሰነድ ውጤታማ የሆነ የዳኝነት ሥራ ለመስራት የሚያግዝ ነው። ፍርድ ቤቶች የሰብአዊ መብቶችን ለማሰከበር አገሪቱ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች፣ ስምምነቶችና መርሆዎች መሠረት በማድረግ ከሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ጋር በማጣጣም የሚሰሩበት መሆኑንም ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ደሞዜ ማሜ በበኩላቸው ፍርድ ቤቶች በሕግ ትርጓሜ በኩል ዓለም አቀፍ ሕጎችን በማካተት እንዲሰሩ የሚያደርግ ሰነድ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ተርጉመው በዳኝነት ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉ በአገሪቱ የሰብአዊ መብት ታሪክ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የዜጎችን የመብት ጥሰትን ለመከላከል ለሚያከናውናቸው ተግባራት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አቶ ደሞዜ ገልጸዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=2592

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር