ለመጪው መንግሥት አንኳር ምልከታ


በምሕረት ሞገስ
ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ መጪው የኢትዮጵያ መንግሥት ማድረግ ከሚገባቸው ጉዳዮች ጥቂቶቹን የሚገልጹት በዓድዋ ሃሃይለ በሚባል አካባቢ የተወለዱትና ረዥሙን ዘመን በአሜሪካ አሳልፈው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ኃይለሚካኤል ገብረአናንያ ናቸው፡፡
አቶ ኃይለሚካኤል እንደሚሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያረፉት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው፡፡ ወሳኝ ወቅት ያሉበት ምክንያትም ከዚህ በፊት ያልታየ የልማት ብርሃን በኢሕአዴግ ዘመን በመታየቱ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አፄ ቴዎድሮስ ሕይወታቸው ያለፈበት ምክንያት ኢትዮጵያን ለማሻሻል ያደረጉ በነበረው ተጋድሎ ነው፡፡ አፄ ምኒልክም ኢትዮጵያን ለማሻሻል ጀምረው፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ቀጥሎ ነበር፡፡

ተጨባጭ የሆኑና የሕዝብን ሕይወት የሚቀይሩ ልማቶች በተግባር የታዩት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን ነው፡፡ አዲስ የጀመሯቸው ሥራዎች ደግሞ ከዚህ በፊት ከሠሯቸው በበለጠ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚቀይሩ ናቸው፡፡

የተጀመሩት አጀንዳዎች ተግባራዊ ሆነው ሳይጨርሷቸው መሞታቸው በወሳኝ ጊዜ ሞቱ ያስብላል፡፡ የሕዳሴው ግድብ ዋናው ነው፡፡ በእርግጥ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመሥራት በማቀድ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ አይደሉም፡፡  በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን ስሜታዊ በሚያደርገው የዓባይ ግድብ ሥራን በመተግበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የባቡር መስመር ዝርጋታው፣ የስኳር ፕሮጀክቱ፤ በመሠረተ ልማቱም በሕክምናው፣ በግብርናው፣ በንግዱም፣ የመሳሰሉትም ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ጥራቱ አልተሻሻለም እንጂ ትምህርትም እየተስፋፋ ነው፡፡ ጥራቱን ማሻሻል ግን ግድ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች በየቦታው ስለተገነቡና መሠረተ ልማቱ ስለተስፋፋ ጥራቱን ለመቀየር ጊዜ አይወስድም፡፡ ቀጣዩ መንግሥትም የተጀመሩትን ሥራዎች ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አገዛዝ፣ መንግሥት ብዙ ልማቶች ያደረገ ሲሆን እሳቸው ከሞቱ በኋላ እየተንፀባረቀ ያለው በአንድ ሰው ላይ የመመርኮዝ አዝማሚያ ግን ትክክል እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ በአንድ ሰው ላይ መመርኮዝ የኋላቀርነት ምልክት መሆኑንና ከኢትዮጵያ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተካ የለም ብሎ መደምደም የሥልጣኔ ምልክትም አይደለም ይላሉ፡፡ “በአንድ ሰው ላይ የምንመረኮዝ ከሆነማ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅም አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ብዙ የተማሩና ልምድ ያላቸው ሰዎች አሉን፡፡ ለአገራቸው በቆራጥነት የሚሠሩ አሉ፡፡ የሚያስፈልገው ዕድል መስጠት ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግርን አላየም፡፡ መሪዎችም ሲሞቱበት ችግር ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ሲሞቱ ብዙ ነገር ተበላሽቷል፡፡ አፄ ዮሐንስ ሲሞቱ ብዙ ነገር ተደበላልቋል፡፡ አፄ ምኒልክ ሲሞቱ ግርግር እንዳይፈጠር ተብሎ ዕረፍታቸው ተደብቆ ቆይቷል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ላይ ደርግ መጥቶ ብዙ ችግር እንዳሳለፍን እናውቃለን፡፡ ከሁሉም ጋር ስናነፃፅረው በሰላም የኖርንበት ጊዜ በኢሕአዴግ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወደፊት እንዴት መሔድ እንዳለብን ማሰብ አለብን፡፡”

እንደ ታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ኢትዮጵያን የገዙት የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን ይህ የኋላቀርነት ምልክት ነው የሚሉት አቶ ኃይለሚካኤል፣ ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪውን መምረጥ ያለበት ከየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል መጣ ብሎ ሳይሆን መምረጥ ያለበት በትምህርቱ፣ በሥራ ልምዱ በዓላማው፣ በራዕዩ መሆን እንዳለበት ‹‹ከየት መጣ የሚለው ላይ ቀይ መብራት ማስቀመጥ ያስፈልጋል፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በማይኖሩበት ጊዜ ምክትሉ ተክቶ ይሠራል በሚለው አንቀጽ ‹‹የማይኖሩበት ጊዜ›› አሻሚ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባውና ከዚህ በፊት የተሠሩ ጥሩ ነገሮችን እያመሰገንን የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ግንመሥራት እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትርን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ላይ ክፍተት እንዳለው ታይቷል፡፡ ስለዚህ በሕገ መንግሥታችን ላይ መሪያችንን በሞት ስናጣ፣ በሕመም ጊዜም ማን ተክቶ እንደሚሠራ  በማያሻማ መልኩ፣ ብጥብጥ በማይፈጥር ሁኔታ የሥልጣን ሽኩቻ የማያስከትል ሆኖ ቁልጭ ብሎ መቀመጥ አለበት፡፡ ጊዜው ስህተትን እያረምን የምንሔድበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኃይለሚካኤል፣ ከድንበር ጋር በተያያዘ ያልተቋጩ ችግሮችም መታየት ያስፈልጋቸዋል ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች ጊዜያቸውን በአብዛኛው ያጠፉት የኢትዮጵያን ድንበር በመጠበቅ ነው፡፡ በተለይ አፄ ዮሐንስና ራስ አሉላ የኢትዮጵያን ድንበር ለማስከበር ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ሆኖም የድንበር ጉዳይ ከበፊት ጀምሮ ችግሮች አሉበት የሚሉት አቶ ኃይለሚካኤል የኤርትራን ጉዳይ እንደ ምሳሌ ያነሣሉ፡፡

በአፄ ምኒልክ ጊዜ በኤርትራ ጉዳይ ስህተቶች ተፈጽመዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከባድ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ተደርጓል፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ደግሞ ስህተቶች ተሠርተዋል፡፡ ዋናው ነገር ስህተት ተደረገ ብሎ ጊዜ ማጥፋት ሳይሆን ስህተቶችን ለወደፊት ማረም ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ኤርትራውያን ነፃ መውጣታቸው ላይ ችግር ባይኖርም ፍቺው ፍትሐዊ አልነበረም ይላሉ፡፡ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተያየት ስላልወሰደ ስትራቴጂክ ስህተት እንደፈጸመም ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ከዚህ በመቀጠል የሚመራው መንግሥት የድንበር ጉዳይን በተመለከተ በኤርትራ ላይ እንደተሠራው ዓይነት ስህተት መድገም እንደሌለበት ይጠቁማሉ፡፡ እንደ አቶ ኃይለሚካኤል አነጋገር፣ “የተበላሸው ነገር እንዲስተካከል እንፈልጋለን፡፡ የሚመጣው መንግሥት በኢትዮጵያና በኤርትራ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ባሉ የድንበር ጉዳዮች ላይ መሥራት አለበት፡፡ የድንበር ጉዳይ ሲኖርም መንግሥት ብቻውን መወሰን የለበትም፡፡ ሕዝብ የማወቅና የመወሰን መብት አለው፡፡ መንግሥት በሕዝብ ላይ ጫና መፍጠር የለበትም፡፡ ካለፈው ስህተት መማር አለብን፡፡”

ከአጐራባች አገሮች ጋር ያለውን የጸጥታና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስጠብቆ መሔድም የመጪው መንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ ነው፡፡ በተለይ ሱዳን ለግብፅ ወታደራዊ ሰፈር (የሚሊተሪ ቤዝ) ለመስጠት ተስማምታለች የሚባለውን መንግሥት ነቅቶ ሊጠብቀው የሚገባ ጉዳይና ለምን? ብሎ በጥያቄ የሚያስቀምጠው መሆን አለበት፡፡ በተለይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በኋላ መስማቱ ለምን አሁን? ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብም በንቃት ሊጠብቀው የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተም በሁለት መንገድ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለአገራቸው ጥሩ የሚያስቡ፣ አገራቸው በኢንቨስትመንት መስክ ገብተው ብዙ የሥራ እድል የፈጠሩ አሉ፡፡ እንደ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ አቶ ታዴዎስ ጌታቸው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የመሳሰሉ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች አሉን፡፡ የነሱ ሥራ ይማርካል፡፡ አምራቾች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በፖለቲካ ተደራጅቶ በስሜት የሚመራ ዳያስፖራም አለ፡፡ ይህ በአገራችንም አሉታዊ ተጽዕኖ እያመጣ ነው፡፡ ራሳቸውን አገር ውስጥ ካለው ኢትዮጵያዊ በላይ ከፍ አድርገው የሚያስቡ ናቸው፡፡

ሥልጣን ቢያገኙ ኢትዮጵያን ገነት እንደሚያደርጓትም የሚያስቡ ናቸው፡፡ እነዚህኛዎቹ ወገኖች መጀመርያ ኃላፊነት ማለት ምን እንደሆነ እንዲያውቁት አቶ ኃይለ ሚካኤል ይመክራሉ፡፡ ‹‹ፖለቲካ ማለት ውይይት ሆኖ ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሞቱ ሻምፓኝ የከፈቱ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ባህል በኢትዮጵያም የተለመደ አይደለም፡፡ እንዲህ ያደረጉ ሰዎች አገር ይመራሉ ብሎ ማሰቡ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሆኖም መንግሥት ከዳያስፖራው ጋር የጀመረውን ትስስር በማጠናከር ልማቱን በየዘርፉ ማጠናከር እንዳለበት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በሌላ በኩል ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ያለው ችግርም በግልጽ መነጋገርን ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ችግሮች እየታዩ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ከመከሠቱ በፊት ስላለው ነገር በግልጽ መነጋገርና መፍትሔ መፈለግ የቀጣዩ መንግሥት ሥራ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ኃይለሚካኤል ገብረአናንያ የተባበሩት መንግሥታት በሰላም አስከባሪነት በኩዌት፣ ሴራሊዮን፣ ቲሞር ሌስቴ (የቀድሞዋ ምሥራቅ ቲሞር) አገልግለዋል፡፡ በኒውዮርክ በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሕፈት ቤትም ሠርተዋል፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በልዑል መኰንን ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ ከአሜሪካ ኩዊንስ ኮሌጅ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በከተማ ፕላኒንግ እንዲሁም ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር ማግኘታቸውን ነግረውናል፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር