የመለስ ኢትዮጵያና ወራሾቿ


ፎቶ ኢንተርኔት

በሰለሞን ጎሹ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባረፉ በሁለት ሳምንታቸው ግብዓተ መሬታቸው ተፈጽሟል፡፡ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ መንገዶች ሐዘን ከመግለጽ ጋር በተያያዙ እንቀስቃሴዎች ተወጣጥሮ የነበረው መንግሥት ወደ መደበኛው ሥራው እንደሚመለስ ይጠበቃል፡፡ የሥራዎቹ ሁሉ መጀመርያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመርጥ ወይም የተመረጠውን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያፀድቅ ማድረግ ነው፡፡

በቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ዙሪያ እየተደረጉ ያሉት የሐሳብ ልውውጦች ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግል ሰብዕናና የፖለቲካ አመራር ብቃት፣ ከኢሕአዴግ የፖሊሲ ለውጥ የማምጣትና ያለማምጣት ጥያቄ፣ ከፓርቲ ፖለቲካውና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ባለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያን በፈለጉት መንገድ የቀረጿት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የአገሪቱን ፖሊሲዎች በመንደፍ፣ አመራራቸውን ማዕከላዊ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ነጥረው በመውጣታቸው የተነሳ የተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራ ከማክበዳቸውም በላይ፣ ኢትዮጵያውያን፣ የውጭ ዜጎችና መንግሥታት በቀጣይ ሥራዎች ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓል፡፡

የመለስ የአመራር ዘዬ

መለስ ከልጅነታቸው ጀምሮ ብልህና ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ ስለእሳቸው የተጻፉ ሰነዶች ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ በአድዋም ሆነ በአዲስ አበባ ዊንጌት ትምህርት ቤት ያሉ መዛግብትም ይህን ያስተጋባሉ፡፡ ያቋረጡትን የሕክምና ትምህርትም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩም ጉብዝናቸው ተከትሏቸዋል፡፡ የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውና ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነታቸው ጋር አብሮ በመሄዱ፣ የንባብ ፍላጎታቸው ከመደበኛው የትምህርት ጥናት ውጪ ወደ ፖለቲካው እንደተሸጋገረ ይነገራል፡፡ በትምህርታቸው ባስመዘገቡት ትልቅ ውጤት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚረዳቸውን የገንዘብ ሽልማት ሲሰጣቸውም፣ የተለየዩ መጻሕፍት በመግዛት የንባብ ባህላቸውን ማዳበራቸውን አብርዋቸው የተማሩ ይመሰክራሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ሳሉ በተቋቋመው የትግራይ ብሔር ተራማጆች ማኅበር (ማኅበረ ገስገስቲ ብሔር ትግራይ/ማገብት) ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው የፖለቲካ ፍላጐታቸውን ጨምሮታል፡፡

መለስ ሕወሓትን በ1967 ዓ.ም. ሲቀላቀሉ ይህን የዳበረ የንባብ ባህላቸውን ይዘው ነበር፡፡ በአንፃሩ በ1967 ዓ.ም. በዚያው ዓመት ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ (ተሓሕት) በሚል ስም የተቋቋመው ሕወሓት በጽሑፍ ደረጃ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም እንኳ አልነበረውም፡፡ በዚያው ዓመት የትጥቅ ትግል የጀመረው ሕወሓት በጽሑፍ ደረጃ የነደፈው ፕሮግራም አጠቃላይ ኢትዮጵያን ከማየት ይልቅ ጠበብ አድርጎ ትግራይን የሚያይ ነበር፡፡ በአሠራር ደረጃም ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ዋነኛው እምነት እንዲሆን ፓርቲው አስምሮበት ነበር፡፡

እስከ የካቲት 1971 ዓ.ም. ድረስ ከወታደርነት እስከ ልዩ ልዩ ክፍሎች አገልግሎት ከሰጡ በኋላ በወቅቱ የመጀመርያው ድርጅታዊ ጉባዔ ሲካሄድና ፓርቲው ስሙን ከተሓሕት ወደ ሕወሓት (ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) ሲለወጥ ከመረጣቸው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል መለስ ዜናዊ ይገኙበታል፡፡ በሁለተኛው ድርጅታዊ ጉባዔም በ1975 ዓ.ም. የፖሊት ቢሮ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) አባል ሆነው ተመረጡ፡፡

በ1977 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) ተቋቁሞ የድርጅቱ ርዕዮተ ዓለም ከመቀረፁም በላይ በሕወሓት የ10 ዓመት ጉዞ ላይ ግምገማ ተካሂዶ ነበር፡፡ ግምገማው አመራሩን ለሁለት የከፈለው ሲሆን፣ አቶ መለስ በአንፃራዊነት ወጣትና በአብዛኛው የተማሩ ከተባሉት ወገኖች ጋር ቆመው ነበር፡፡ የሐሳብ ልዩነቱ የትግራይ ሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል መለየት አለበት የለበትም? ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ዲሞክራሲያዊና ስትራቴጂካዊ ግንባር መፍጠር አለብን የለብንም? ከኤርትራ ድርጅቶች ጋር በምን መልኩ እንሥራ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይሁንና እንደ አረጋዊ በርሄና ግደይ ዘርዓፅዮን ካሉ አንጋፋ ታጋዮችና ከፍተኛ አመራሮች ጋር የተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት እነ አቶ ግደይ ማርክሳዊ ሌኒናዊ አመለካከት የላቸውም የሚል ነበር፡፡ እነ አቶ ግደይ በወቅቱ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ነን ብሎ መናገር ዕርዳታ ሊያስከለክል ይችላል የሚል መከራከሪያ ነበራቸው እንጂ የማሌ ርዕዮተ ዓለም ተከታይ ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ እነ ግደይ ለጥቅም ብለው አቋም የሚወስዱና ከእጅ ወደ አፍ ለሚውል ጥቅም የሚቆሙ ‹‹ፕራግማቲስቶች›› ነበር የተባሉት፡፡ ተቃዋሚዎቹ የሚያቀርቡት ሐሳብ ማርክሲስት ለዕርዳታ ብሎ ማንነቱን ደብቆ አይቀርም፣ አይለማመጥም፣ አያጎበድድም፣ አይንበረከክም የሚል ነበር፡፡ ለዚህም ዋናው ተከራካሪ አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡

የማሌሊት ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ መለስ በአቶ ታምራት ላይኔ ዋና ጸሐፊነት ይመራ ከነበረውና በኢሕዴን ሥር ከተመሠረተው የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ኃይል (ኢማሌኃ) ጋር ሥራ የጀመሩትም ያኔ ነበር፡፡ ሕወሓት በሚያራምዳቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማድረግ የጀመሩት አቶ መለስ ተቀባይነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በ1981 ዓ.ም. ላይ የድርጅቱ ሊቀ መንበር ሆነዋል፡፡ የሊቀ መንበርነት ቦታውን ከያዙ በኋላ የድርጅቱን አጠቃላይ አካሄድ መንደፍ ከመጀመራቸውም በላይ ከኢሕዴን ጋር በመሆን ኢሕአዴግ የተሰኘ ግንባር እንዲፈጠር ያደረጉ ሲሆን፣ የግንባሩ ሊቀመንበርም በመሆን ተመርጠዋል፡፡ በአቶ ኩማ ደመቅሳ ይመራ ከነበረው ኦሮሞ ማርክስ ሌኒናዊ ንቅናቄ ጋርም አብረው ይሠሩ ነበር፡፡

ከፍተኛ የንባብ ፍቅር እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ መለስ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተኮር ጽሑፎችን ከማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮት አንፃር እየተነተኑ ያሰራጩ ነበር፡፡ ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ የነበራቸው አቶ መለስ፣ ሕወሓት በትግሉ ዘመን የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ካላቸው አገሮችና ቡድኖች ዕርዳታ እንዲያገኝ ያደርጉ ነበር፡፡ ገና ኢሕአዴግ በደርግ ላይ ድል ሳይቀዳጅ በዓለም ዙሪያ ሶሻሊዝም እየወደቀ መሆኑን ተረድተው ከነአሜሪካ ጋር ለመሥራት ዝግጁነታቸውን የገለጹበትም መንገድ ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት እንዲሁም ከ1987 ዓ.ም. እስከ ሞቱበት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ፣ ኢትዮጵያ የሆነችውንም ሆነ ያልሆነችውን በመወሰን ረገድ ትልቁን ድርሻ ወስደዋል፡፡ ለዚህም ነው ያለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያ ‹‹የመለስ ኢትዮጵያ›› የምትባለው፡፡

አሁንም በሥራ ላይ ያለው የፓርቲው ትልቁ ምዕላድ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የመለስንና አብረዋቸው የታገሉትን ሶሻሊስቶች እምነት ዕርዳታ በመስጠት ከፍተኛ ገንቢ ሚና ከሚጫወቱት የምዕራባውያን ዲሞክራሲና ነፃ ገበያ ጋር ለማጣመር የሞከረ ነው፡፡ ዋነኛ የሐሳቡ አመንጪ ደግሞ አቶ መለስ ናቸው፡፡ አገሪቱን በዋነኛነት በበላይነት የሚገዛው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ እንደ ክፍሌ ወዳጆ ያሉ ምሁራን ቢሳተፉበትም የመጨረሻው የሕገ መንግሥቱ ቅርጽና ይዘት ለዓመታት በአቶ መለስ አዕምሮ ውስጥ የተመላለሱትን ሐሳቦች ይዟል፡፡ በሽግግር መንግሥት ወቅት ከኤርትራ መገንጠልና ከኦነግ ጋር በተፈጠረው ልዩነት አመራራቸው የተፈተነ ሲሆን፣ በ1985 ዓ.ም. ከፓርቲው አባላት ከፊሎቹ በልዩነት የለቀቁ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 42 የሚጠጉ መምህራንም እንዲባረሩ ተደርገዋል፡፡

ከሁሉም የባሰውና አመራራቸው ጋር ከፍተኛ ተግዳሮት የመጣበት በቅድሚያ በ1993 ዓ.ም. የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ለሁለት ሲሰነጠቁ ነው፡፡ የልዩነታቸው ምክንያት እስካሁንም አወዛጋቢ ቢሆንም፣ አቶ መለስ በአሸናፊነት ወጥተዋል፡፡ ልዩነቱን ለመፍታት ከሌሎች አባላት ጋር በጽሑፍ ጭምር ክርከር ሲቀርብ አቶ መለስ፣ ‹‹በትክክል አልተረዳሁትም ነበር››፣ ‹‹አሁን ተረድቼዋለሁ››፣ ‹‹ተሳስቼ ነበር›› የሚሉ ቃላትን እንዲጠቀሙ የሚያስገድዱ ክርክሮች ነበሩ፡፡ ሆኖም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት (ከ1990-92 ዓ.ም.) የተነሱት እነዚህ ልዩነቶች የሌሎች አመራሮችን መባረር ካስከተሉ በኋላ ግን አቶ መለስ አመራራቸው በጣም እየተጠናከረና ተቀናቃኝ እያጣ መጥቷል፡፡

ሁለተኛው ትልቁ የአቶ መለስ አመራር ተግዳሮት የመጣው ምርጫ 97ን ተከትሎ ነው፡፡ በምርጫው ውጤት ላይ በተነሳ አለመግባባት ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ እሱን ተከትሎ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና የሲቪል ማኅበራት አመራሮች የታሰሩ ሲሆን፣ በርካታ ዜጎችም ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡ አብዛኛው ታሳሪ በይቅርታ ቢፈታም ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የወጡት ሕጎች የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው የአቶ መለስን ፓርቲ ኢሕአዴግን ተጠቃሚ እንዳደረገና መንግሥት በሰብዓዊ መብትና ዲሞክሪሲ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው በሚል እንዲተች አድርጓል፡፡ በምርጫ 2002 ኢሕአዴግ የ99.6 በመቶ ውጤት ማስመዝገቡም በመድብለ ፓርቲ አምናለሁ ለሚሉት አቶ መለስ ዓለም አቀፍ ትዝብት ነው ያተረፈላቸው፡፡

በያዝነው ዓመት በሃይማኖት ዙሪያ በተለይ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ለአቶ መለስ አመራር ሦስተኛው ትልቁ ተግዳሮት ቢሆንም፣ መጨረሻውን ሳያዩት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ልዩነቱን ለመፍታት የእምነቱ ተከታዮች ያቋቋሙት ኮሚቴ አባላት ወደ እስር የሄዱት አቶ መለስ በሕክምና ላይ እያሉ ነው፡፡

በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተከበው አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበውን መንግሥት ሲመሩ ኢትዮጵያ ያቋቋመቻቸው ተቋማት፣ የአሠራር ዘዴዎች፣ ሕጎችና ፖሊሲዎች አፍላቂ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የመሬት አስተደደር፣ የግብርና፣ የውኃ ልማት፣ የትምህርት፣ የጤና ፖሊሲዎች በተለይ በአቶ መለስ የፈለቁ ውጤታማ የሆኑ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡

ነፃ ፕሬስና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የተጀመረው በአቶ መለስ አመራር ሲሆን፣ የሃይማኖት ነፃነትና የሴቶች መብትም በደርግ ዘመን ቢጀመርም በተሻለ ሁኔታ የተተገበረው ግን በአቶ መለስ አመራር ዘመን ወቅት ነበር፡፡ አቶ መለስ በነፃ ፕሬስና በመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ መስፋፋት ዙሪያ ግን ከሠሩት ሥራ ይልቅ ትችቱ ይበልጥ ይጎላባቸዋል፡፡

አቶ መለስ አመራራቸው እሳቸውን የሚያገዝፍና ሌሎችን የሚያገል ነው ተብለው ቢተቹም፣ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ያላቸው የዲፕሎማሲ ብቃት ግን አስደናቂ ነው፡፡ ለዓለም ሰላም ባደረጉት አስተዋጽኦ የዓለም ሰላም ሽልማት አሸናፊ ሲሆኑ፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ ባስመዘገቡት አስተዋጽኦም የዓለም አቀፍ አመራር ሽልማት አሸናፊ ነበሩ፡፡ የያራ አረንጓዴ አብዮት ሽልማትንም ያሸነፉ ሲሆን፣ ሽልማቱ በግብርናው ዘርፍ ላደረጉት አስተዋጽኦ ነው የተሰጣቸው፡፡ ከሽልማት በተጨማሪ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ኮንፈረንሶችንና ፎረሞችን በመምራት የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራት የቻሉ ሲሆን፣ እንደ ጆሴፍ ስቲግሊዝና ጄፍሪ ሳችስ ካሉ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው ኢኮኖሚስቶች ጋር የፈጠሩት ወዳጅነት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብና የልማት ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት የተሻለ እንዲሆን የራሱ ሚና ነበረው፡፡ አቶ መለስ በአፍሪካ ኅብረትና በአፍሪካ ጉዳዮችም ከፍተኛ ሚና ስለነበራቸው የምሥራቅ አፍሪካን ሰላም ለመጠበቅ ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር በመተባበር ትልቅ ሚና እንድትጫወት አድርገዋል፡፡

መለስ ስለራሳቸው
አቶ መለስ በ1982 ዓ.ም. በአሜሪካ ከፖል ሄንዝ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማርክሲስት ስለመሆን አለመሆናቸው ሲጠየቁ፣ በፓርቲያቸው ውስጥ ማርክሲስቶች መኖራቸውን፣ እሳቸውም በአንድ ወቅት ጥብቅ ማርክሲስት እንደነበሩ፣ ነገር ግን ርዕዮተ ዓለሙን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን እንደተማሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም አዲሷ ኢትዮጵያ ግራና ቀኝ ዘመሞችን እንደምታስተናግድ ተናግረው ነበር፡፡

በያዝነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ከሪቻርድ ዶውደን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በየትኛውም የዓለም ክፍል ዲሞክራሲ ፍፁም እንዳልሆነ ገልጸው፣ በለውጥ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ከቀደሙ መንግሥታት በተለየ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባሉ መንደሮች ተደራሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ለሁለት እንደሚከፍሉና ‹‹አንዱ ወገን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ትልቁ ወንጀል እንደሆነና ኢትዮጵያውያንን እንደሚከፋፍል የሚያስብ ሲሆን፣ ሌላው ወገን ግን ሰይጣናዊ የሆነ ክልሎች የራሳቸውን ግዛት እንዳይመሠርቱ የሚያቅድ ድብቅ ሴራ እንዳለን ያስባል፡፡ ሁለቱም ስህተት ናቸው፡፡ ዋነኛው ሐሳብ የአገሪቱ ትልቁ ተጠቃሚ ሕዝቡ እንዲሆን ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የጦሩን አስዋጽኦ በተመለከተም የሕወሓት የቀድሞ ታጋዮች ቁጥር ከከፍተኛ የአመራር ደረጃ ውጪ በጣም አናሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዶውደን ሌላ የነገሩት ነገር በ2007 ዓ.ም. ከሥልጣን ሲለቁ የአመራር አካዳሚ ውስጥ ሊያስተምሩ ወይም ደግሞ መጻሕፍትን ለመድረስ ማሰባቸውን ነው፡፡

በታይምስ መጽሔት ላይ ከአሌክስ ፔሪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኋላ ታሪክን በኩራት የአሁኑን ግን በድህነትና በመጥፎነት እንደምትወክል የገለጹ ሲሆን፣ ከአሜሪካ ጋር በምሥራቅ አፍሪካ ላይ እየሠሩ ያሉት ከአገራቸው ብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

በኒውስዊክ መጽሔት ላይ ከጄሰን ማክሉር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መንግሥታቸው ያለበትን ድክመት ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ እየመጣ ያለው የፕሬስ ሕግ በዓለም ላይ ካሉ የተሻሉ አሠራሮች ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

ከአፍሪካ ኮንፊደንሺያል ሃናህ ጊልክስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሥልጣን ላይ ብዙ የቆዩት በፓርቲያቸው በኢሕአዴግ ጥንካሬ ወይም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት የተነሳ ስለመሆኑ ሲጠይቃቸው፣ ሁኔታው በሁለቱም ምክንያቶች እንደተከሰተና በፓርቲያቸው ራሱ አመራሩ ለብዙ ጊዜ ስለቆየ እሱን ለመለወጥ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ ከአዲስ ወራሾች ጋር
አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማረፋቸው የተነሳ የኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ ካለፉት 21 ዓመታት የተለየ ይሆናል ወይ በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ነው የውጭ ዜጎች፣ ዜጎችና እንዲሁም ፓርቲው ራሱ ሐሳብ እየሰጡ ያሉት፡፡

የውጭ ሚዲያ

ኒውዮርክ ታይምስ ላይ ‹‹Meles Zenawi and Ethiopia’s Grand Experiment›› በተሰኘ ርዕስ አብዱል ሞሐመድና አሌክስ ዲዋል በጻፉት ጽሑፍ፣ መለስ ከትግል ዘመን ጀምሮ ሥልጣን በመርህና በዕውቀት ላይ እንዲመሠረት አድርገው መምራታቸውን ጠቁመው፣ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚፈልጉትን ለማግኘት የነበራቸውን የመደራደር ብቃት ኢትዮጵያ እንደምታጣው ገልጸዋል፡፡

በኢንተር ፕሬስ ሰርቪስ ላይ ‹‹Death of Ethiopian Leader Meles Brings ‘Opportunity for Peace’›› በተሰኘ ርዕስ ኬሪ ቢሮን በጻፉት ጽሑፍ፣ አሜሪካ የምትሰጠው ዕርዳታ በአቶ መለስ የሥልጣን ዘመን ትኩረት ባልተደረገባቸው እንደ ብሔራዊ እርቅ፣ ሰብዓዊ መብትና ፕሬስ ዙሪያ ላይ እንዲያተኩር ጠይቀዋል፡፡

ኬቨን ብሉም የተሸኑ ጸሐፊ በዴይሊ ማቭሪክስ ላይ ‹‹The Legacy of Meles Zenawi: What might have been›› በተሰኘ ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ የአቶ መለስ ብሩህ አዕምሮና የኢኮኖሚ ራዕይ በምድረ አፍሪካ ያልታየ እንደነበር መስክረው፣ ከአሜሪካና ከቻይና ጋር በጋራ መሥራት የቻለውን መሪ ኢትዮጵያ እንደምታጣ ይገልጻሉ፡፡

ሌሎች እንደ ጋርዲያን፣ ቪኦኤ፣ ዩኤን ዲስፓች፣ ዘ ዋሽንግተን ታይምስ፣ ዘ ዋሽንግተን ፖስት የመሳሰሉት የውጭ ሚዲያዎች ደግሞ በኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ የሥልጣን ሽኩቻ መጀመሩንና ይህም በቁጥጥር ሥር ካልዋለ አገሪቱ ወደ ብጥብጥ ልታመራ እንደምትችል የገለጹ ሲሆን፣ በአብዛኛው ዋቢ ያደረጉት ተቀማጭነታቸው ውጭ አገር የሆኑ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኞችንና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሁሌም የማይስማሙትን አምኒስቲ ኢንተርናሽናልና ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕን ነው፡፡

የዜጎች አስተያየት
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሕይወት እያሉ ያለያዩት ሕዝብ፣ ሲሞቱ ግን እርስ በርስ ሳይለያይ በሞታቸው እንዳያያዙት ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሁን በአመራር ደረጃ ያሉት ባለሥልጣናት ሥርዓቱን እንዳለ እንደሚያስቀጥሉት ያላቸውን ግምት ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም አዲሱ አመራር በኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በመንግሥት መካከል የተነሳው ውዝግብ እልባት አለማግኘትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የመምረጥ ሒደት እንደሚያሳስበው ግን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በማንም ላይ የበላይነት መውሰድ የሚችለውን መለስን መድገም እንደማይቻል አመልክተው፣ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለአጭር ጊዜ በተረጋጋ ሁኔታ መምራት ቢችሉም በኢሕአዴግ ሥር ባሉ ፓርቲዎች መካከልና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመቅረፍ እንደሚቸገሩ ግን ገልጸዋል፡፡

ኪሩቤል ታደሰ የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ሲሆን፣ አቶ ኃይለ ማርያም የኋላ ታሪካቸው ጠንካራ ቢሆንም ቀጣዩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ገና ያልተረጋገጠና በመስከረም ወር 2005 ዓ.ም. በሚደረገው የፓርቲው ሊቀመንበርነት ውድድር እንደሚወሰን ያለውን ግምት አስፍሯል፡ ይህ የኪሩቤል አስተያየት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን ከሰጡት አስተያየት ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው፡፡ አቶ በረከት ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በአይኤስኤስ ተመራማሪ ሆኖ የሚሠራው ሃሌሉያ ሉሌ አቶ መለስ የኢትዮጵያን መንግሥትና የዜጎችን የፖለቲካና የማኅበራዊ ሕይወት ለብዙ አሥርት ዓመታት ሲገለጽ ሊኖር የሚችል መሠረታዊ ለውጥ ማምጣታቸውን በመጠቆም፣ የኢኮኖሚ ራዕዩን አጥብቆ በመያዝ አገሪቱ መለስ ባላሳኩት የዲሞክራሲና የፍትሕ ፕሮጀክት ላይ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በስዊዘርላንድ የፒኤችዲ ተማሪ የሆኑት አቶ ተሰማ ስማቸው፣ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትር መለሰን ሞት ተከትሎ በሐዘን ያሳየነው አንድነት የማንስማማባቸውን ዝርዝሮች ችላ ያልንበትን መንገድ፣ መለስ በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብት መስመር የነበረባቸውን ድክመትና እንደ አገር ያለብንን ችግር ለሚያውቁና ለሚረዱ የኢትዮጵያ ልጆች የተሳሳተ መልዕክት ቢያስተላልፍም፣ አለመረጋጋታችን ለሚፈልጉ ጠላቶቻችን ግን አንጀት የሚያሳርር ነው፡፡ አዲሱ አመራር የተሻለ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ፣ የበለጠ አሳታፊ ለመሆን ከብልሁ ሕዝብ አመራር መማር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የኢሕአዴግ ምላሽ

ኢሕአዴግ አዲሱ አመራር የፖሊሲም ሆነ የአሠራር ለውጥ እንደማያደርግ ገልጿል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሚና በአንድ ሰው መወጣት የሚያስቸግር በመሆኑ በቡድንና በርብርብ ለመወጣት የፓርቲው አመራሮች አንድነት እንዳላቸውም ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካይነት ያገኘችውን ቦታ ለማስጠበቅ ተግተው እንደሚሠሩ የፓርቲው አመራሮች ገልጸዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ድንገተኛ ቢሆንም፣ በ2007 ዓ.ም. ሥልጣን ለመልቀቅ አስቀድመው አስበው ስለነበር ሰላማዊና ሒደቱን የጠበቀ የሥልጣን ሽግግሩ ያለምንም ችግር እንዲፈጸም ፓርቲው ሥራውን መሥራቱንም እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር