የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳች ላይ እየመከረ ነው


አዲስአበባ፣መስከረም4 2005 (ኤፍቢሲ) ምክር ቤቱ  በመጀመሪያ  ቀኑ  የጉባኤው ውሎ ከጠቅላይ  ሚኒስትር  መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በአገራችንና  በአከባቢው እንዲሁም በሌሎች የዓለም ክፍሎች የተፈጠረውን ሁኔታ  ገምግሟል ።

ከዚህ በመነሳትም በአገራችን መካሄድና ይበልጥ መጠናከር ያለበትን የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት  ግንባታን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ መክሯል ።


መላውን የድርጅቱን አባላትና የትግሉን ደጋፊዎች እንዲሁም የለውጡ ባለቤቶች እና ተጠቃሚዎች የሆኑትን መላውን የኢትዮጵያ ህዝቦችን በማሳተፍ የተጀመረውን ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል በሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ስልቶች  ዙሪያም በመወያየት ከስምምነት ደርሷል ።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ምክር ቤት እስከ ነገ  በሚቆየው ስብሰባ የድርጅቱን ሊቀመንበር ይሰይማል።

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ያካሄደውን አጭር ግምገማና የ2005 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫዎች የሚመለከት ሰነድ በመመርመር ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል።

ምክር ቤቱ በአቶ መለስ ዜናዊ አመራርና በድርጅቱ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ህዳሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል የድርጅቱን የአመራር ግንባታ በተመለከተ የተዘጋጀውን ሰነድ በመመርመር መሰረታዊ አቅጣጫዎችን እንደሚያመላክትም የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት  ለፋና ብሮድካሲትንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል ።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከአራቱ አባል ድርጅቶች በእኩል የተሰየሙ 180 አባላት ያሉት ሲሆን በሁለት ጉባዔዎች መካከል የግንባሩ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ሆኖ ያገለግላል ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር