የጠቅላይ ሚኒስትሩን የዕድገትና የልማት ጅማሮዎች ኢሕአዴግ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ አልተጠቀመበትም ተባለ



በታምሩ ጽጌ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ደርግን ከጣሉ ማግስት ጀምሮ፣ በአገር ዕድገትና ልማት ሥራ ላይ የተሰማሩ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንዳልተጠቀመበት አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ1986 ዓ.ም. በአማራና በኦሮሚያ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች በመዘዋወር ያደርጉዋቸውን ጉብኝቶች የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተመለከቱት አስተያየት ሰጪዎች፣ ኢሕአዴግ በሕዝቡም ሆነ በተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደርስበትን ትችት የሚያስተባብል ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ በምርጫ ሰሞን “ልማት፣ ልማት የሚለው ሕዝቡን ለማታለልና ያልሠራውን ሥራ በመደርደር ነው፤” በማለትና በመግለጽ ሲቃወሙት የነበሩትን የውጭና የአገር ውስጥ ድርጅቶች ያስታወሱት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እላይ ካለው የመንግሥት ባለሥልጣን እስከታችኛው አርሶ አደር ድረስ ለልማት ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት ለሕዝብ ይፋ አለመደረጉ ለትችት እንዳጋለጠው ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ዘመናቸው የሠሩዋቸውን የቅርብ ጊዜና ከድል ማግስት ያደርጓቸው የነበሩትን የዕድገትና የልማት እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲያስተላልፍ የተመለከቱት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠርተዋቸው ያለፉት ሥራዎች የበለጠ የሚያስወድዳቸውና ይቃወማቸው የነበረውን ሁሉ ተቃውሞውን እንዲያነሳ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ በተለይ በምርጫ ሰሞን እታች ወርዶ ቢሠራ ከዓለም አቀፎቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ከሌሎች አገር አቀፍ ድርጅቶች ትችት ከመዳኑም በተጨማሪ፣ አብዛኛዎቹን የአገሪቱን ዜጐች የኢሕአዴግ ደጋፊ ሊያደርግ የሚያስችለው እንደነበር አውስተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት፣ ኢሕአዴግ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ቀደምት እንቅስቃሴ ተከትሎና ከታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ችግሩንና ፍላጐቱን በሚገባ በመረዳት ከሕዝቡ ጋር መሥራት ከቻለ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የልማትና የዕድገት ሥራ አጀማመር ውጤታማ ሆኖ የሚታየው “እንፈጽመዋለን” ከሚል መፈክርና ቃላት ድርደራ ባለፈ ወደ ተግባር ተገብቶ ሥራ ላይ መዋል ሲችል መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ በቴሌቪዥን መስኮት ለመታየትና “አዝኗል/ለች” ለመባል ወይም የሥራ ኃላፊዎችን ትዕዛዝ ለማክበር ብቻ የተደረገ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ላለፉት ዘጠኝ የሥራ ቀናት (ከነሐሴ 15 ቀን እስከ 25 ቀን 2004 ዓ.ም.) በተለይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በአገሪቱ ባሉ ከተሞች ያሉ ሹማምንቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕልፈተ ዜና ተገን በማድረግ አንዱን ወገን ከሌላው ጋር ቂም የሚያያይዝና ለአገርም ሆነ ለዜጐች የማይጠቅም ሕገወጥ ሥራ ሊሠሩ ስለሚችሉ፣ የመንግሥት አካላት ሊከታተሉትና ሊያተኩሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሰሞኑን በየካ ክፍለ ከተማ ውስጥ ተከስቶ የነበረውን አንድ ድርጊት በመጥቀስ አስተያየታቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀብር ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ፣ ማን ምን እንደሠራ በመመርመር የሚገኘው ውጤት ያልተገባ ሆኖ ከተገኘ፣ ለምን ይኼ ወቅት እንደተመረጠና ድርጊቱን ሊፈጸም እንደቻለ በማጣራት አስተማሪ የሆነ ዕርምጃ እንዲወሰድም መክረዋል፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ በሐዘኑ ወቅት ሕገወጥ ግንባታ በሚል ሽፋን ስለተፈጸመው ድርጊት በቅርቡ ዝርዝር ዘገባ የሚቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር