የሥልጣን መተካት በሕገ መንግሥቱ

የዚህ ሰሞን የአገራችን ድባብ ተለውጧል፡፡ ሚዲያው በሐዘን ዜና፣ ሕዝቡም በትካዜ ተውጧል፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎቹን አጥቷል፡፡ ፓትርያርኩም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከነበራቸው አገራዊና አኅጉራዊ ተሰሚነት አንፃር ዜና ዕረፍታቸው አስደንጋጭ ነበር፡፡ በየሚዲያው የምንሰማው የእንጉርጉሮ የዋሽንት ድምፅ፣ በየመንገዱ የተመለከትናቸው ጥቁር አልባሳት፣ የሐዘን መግለጫዎችና ለቅሶዎች ሁሉንም የኩነቱ አካል አድርጎታል፡፡ ‹‹ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ . . . ›› እንዲል ሰዎች ከሞታቸው ጋር የሚኖሩ ቢሆንም፣ መልካም ለሠሩት ወይም ለሚሠሩት የሥራ ጊዜ ቢያገኙ መልካም ነበር፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን የሥራው መቀጠል፣ የተተኪ አመጣጥ ወዘተ. እኛው ጋ የሚቀሩ ሀቆች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‘ዓቃቤ መንበረ ፓትርያርክ’ የኢትዮጵያ መንግሥትም ‘ጊዜያዊ የጠቅላይ ሚኒስትር’ የሾሙት፡፡ የፕትርክናው አመራረጥ አካሄድ በቃለ አዋዲ የሚመራና ለሲኖዶሱ ደንብ የማውጣት፣ ኮሚቴ የማዋቀርና ምርጫውን የማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠ ቢሆንም፣ ሥራው የተወሰኑ ተግዳሮቶች እንዳሉት ይታመናል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት መጠበቅ፣ አካሄዱን በተቀደሰ መንፈስ መምራት፣ ነገሮችን በጥበብና በጥንቃቄ መፈጸም ግቡን ያሳምረዋል፡፡ የመንግሥትም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመሾም ወይም የመተካት አካሄድ የሚኖረው የሕግ ክርክር ሊኖር እንድሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕመም ላይ በነበሩበት ጊዜ በሪፖርተር ጋዜጣ የተለያዩ አምዶች ላይ ሲስተናገዱ የነበሩ የአቋም ልዩነቶች አመላካች ናቸው፡፡ ክርክሮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜና ዕረፍት በኋላም የሚነሱ በመሆናቸው ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ እልባት መስጠቱ አማራጭ የለውም፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሚስተናገደውም ሐሳብ ግራ ቀኙን ለመመርመር ያለመ በመሆኑ በሰሞኑ እየተደረጉ ካሉ ኩነቶች ጀርባ ያሉ የሕገ መንግሥት ክርክሮችን በአጭሩ ይቃኛል፡፡ መነሻውም መድረሻውም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 75 ይዘትን መቃኘት እንደመሆኑ መጠን በጉዳዩ ላይ ለሚደረጉ ሕግ ነክ ሙግቶች መነሻ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ 

የሥራ አስፈጻሚነት ሥልጣን


ማንኛውም መንግሥት የሕግ አውጪ፣ የሕግ ተርጓሚና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ይኖሩታል፡፡ የእነዚህ አካላት አወቃቀር፣ የእርስ በርስ ግንኙነትና ተግባራት የሚወሰነው በየአገሮቹ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በ1987 ዓ.ም. የወጣው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በዝርዝር ከወሰናቸው ጉዳዮች ውስጥ የእነዚህ አካላትን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የሥራ አስፈጻሚ አካልን የሚመለከተው የሕገ መንግሥቱ ክፍል ምዕራፍ ስምንት ሲሆን፣ በውስጡ ከአንቀጽ 72 እስከ 77 ያሉትን ስድስት ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ በአንቀጽ 72 መሠረት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ዓይነት ሥልጣን በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የተለመደ ሲሆን፣ በፕሬዚዳንታዊ የመንግሥት ሥርዓት ደግሞ ከፍተኛ ሥልጣን ለፕሬዚዳንቱ የሚሰጥ ነው፡፡ ለአብነት የፓርላሜንታዊ ሥርዓት የምትከተለው እንግሊዝ ለጠቅላይ ሚኒስትሯ፣ የፕሬዚዳንታዊ የመንግሥት ሥርዓት የምትከተለው አሜሪካ ደግሞ ለፕሬዚዳንቷ ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ ሥልጣን መስጠታቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አወቃቀሩ እንደየአገሮቹ ታሪክ፣ የፖለቲካ ልማድና ብሔራዊ መግባባት መሠረት በሕገ መንግሥታቸው የሚደነገግ ነው፡፡ የአገራችን ሥርዓተ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ስለመሆኑ በአንቀጽ 45 የተደነገገ ሲሆን፣ ፓርላማው (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) ከሕዝቡ የሚመረጥ (አንቀጽ 54) እና የሕዝቡ የሉዓላዊነት መገለጫ ነው፡፡ (አንቀጽ 8) በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌደራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅ/ጁ፤ እንደሚመራ/ሩ በአንቀጽ 56 ደንግጓል፡፡ በዚሁ መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት የምክር ቤቱ አባል የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚሾም ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ነው፡፡ /አንቀጽ 75/ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው እንደመሆኑ ሥልጣንና ተግባሩም እንዲሁ ሰፊ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤቱን የሚያደራጅ፣ የሚመራ፣ የሚያስተባብርና የሚወክል፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎች መመርያዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን የሚከታተል፣ የሚያረጋግጥ፣ ኮሚሽነሮችን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን፣ ምክትል ፕሬዚዳንትንና ዋና ኦዲተርን መርጦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን የሚያፀድቅ እርሱ ነው፡፡ ሌሎችም ዝርዝር ሥልጣኖች እንደተሰጡት አንቀጽ 74 ያመለክታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ያህል ቢሆንም፣ ለብዙ ጊዜያት እየተመረጠ እንዲያገለግል የሚከለክል ድንጋጌ የለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዚዳንትነት ሊመረጥ አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ገደብ በጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን ላይ አልተቀመጠም፡፡ 


ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት ይተካል?

ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን የማይሠራባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ማሰብ ሰዋዊ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕመም፣ ሥራውን በመልቀቅ፣ በአቅም ማነስ ወይም በሞት ሥራውን ለመሥራት የማይችልበት ሁኔታ ስለሚኖር ሕገ መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባ ዕሙን ነው፡፡ የአገራችን ሕገ መንግሥት እነዚህ ጉዳዮች በተከሰቱ ጊዜ ስለሚኖረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታና ስለ አተካኩ የሚለው ነገር አለ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር በሕይወት እያለ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን መሥራት ባልቻለ ጊዜ የሚሆነው ነገር ሲሆን፣ ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞቱ ጊዜ ሊፈጸም ስለሚገባው ሥርዓት ነው፡፡ 

የመጀመሪያውን ሁኔታ በተመለከተ በሪፖርተር ጋዜጣ ባለፉት ሳምንታት ሲገለጹ በነበሩት ሐሳቦች የተለያየ አቋም ሲያዝባቸው አስተውለናል፡፡ የተወሰኑት ሕገ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕመም ላይ ሲሆኑ ወይም ሥራቸውን ለመሥራት ባልቻሉ ጊዜ ክፍተቱ ሊሞላበት የሚችለው ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ ባለመቀመጡ ማሻሻያ ይፈልጋል ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 75 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክቶት ይሠራል በሚል ስለሚደነግግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲታመሙ ምክትላቸው እንደሚተኳቸው በመግለጽ ሕገ መንግሥቱ ክፍተት የሌለው ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ጸሐፊው ሕገ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕይወት እያሉ በሕመም ወይም በተለየዩ ጊዜያዊ ምክንያቶች በማይኖሩበት ጊዜ ስለሚኖረው ሁኔታ ሁለት መፍትሔ እንዳለው ያምናል፡፡ የመጀመሪያው አንቀጽ 75 ሲሆን፣ ሁለተኛው አንቀጽ 54፣ 55 እና 72 የጋራ ንባብ የሚገኘው መፍትሔ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታመው ሥራቸውን መሥራት ካልቻሉ በአንቀጽ 75 መሠረት ምክትላቸው ተክተዋቸው እንደሚሠሩ ማሰብ አሳማኝ ነው፡፡ አንቀጽ 75 ‘ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ’ የሚለው በሕመም ምክንያት ሥራቸውን ለመሥራት ባልቻሉበት ጊዜ ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራቸውን በፈቃዳቸው ቢለቁ፣ ወይም በተለየዩ ምክንያቶች በመረጣቸው ሕዝብ አመኔታ ካጡ (በአንቀጽ 54(6) መሠረት) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሾም ወይም ሊመረጥ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይህ ሥርዓት በግልጽ በሕገ መንግሥቱ በዝርዝር ባይገለጽም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደመሆኑ መጠን ምክር ቤቱ በእነዚህ አሳማኝ ምክንያቶችም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማንሳት የሚሾምበት ወይም የሚመርጥበት የሕግ አግባብ አለ፡፡ ተጠሪነት (Accountability) በመሾም፣ በመቆጣጠርና ከሥልጣን በማንሳትም የሚገለጥ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ዜና ዕረፍት ከተሰማ በኋላ ግን ከላይ የቀረቡት ግራ ቀኝ ክርክሮች ፋይዳ ስለማይኖራቸው ጉዳዩን ከዕረፍታቸው አንፃር እንደገና መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር በሞት በመለየቱ ምክንያት ስለሚፈጸም የመተካት ሥርዓት (Succession procedure) ሕገ መንግሥቱ በግልጽ የሚያስቀምጠው ነገር ባለመኖሩ ለተለያየ ትርጉም የተጋለጠ ይመስላል፡፡ እነዚህ ሐሳቦች በመረጃ መረብና በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘገቡ ይስተዋላል፡፡ በአቋም ልዩነቱ ከላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜያዊ ችግር ምክንያት ሥራቸውን መሥራት ባልቻሉ ጊዜ ስለሚፈጸመው ሥርዓት ከሚነሳው ክርክር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሐሳቦቹን ጨምቀን ካቀረብናቸው አራት ዘንግ ይኖራቸዋል፡፡ አንደኛው ሕገ መንግሥቱ መተካትን (Succession) የሚገዛ ድንጋጌ ስለሌለው ካልተሻሻለ ክፍተት አለው የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 75 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞት ምክንያት በማይኖሩበት ጊዜ ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው አቋም ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሞቱ የሚተካቸውን የተመለከተ ድንጋጌ ባይኖርም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሾም ይችላል የሚል ሐሳብ ነው፡፡ አራተኛው ጉዳዩ በሕገ መንግሥቱ ስለማይሸፈን በአሁኑ ወቅት ያሉት የፖለቲካ ኃይሎች በሚፈጥሩት ኅብረት (Coalition) መፍትሔ ሊሰጡበት የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ የመጨረሻው አማራጭ የሕገ መንግሥት መሠረት የሌለውና ‘ፖለቲካዊ’ ሐሳብ ብቻ በመሆኑ ውኃ የሚቋጥር አይመስልም፡፡ ሌሎቹን አቋሞች በተመለከተ ግን አጭር ምልከታ እናድርግ፡፡

የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 75 መሠረት አድርጎ የሚነሳው ክርክር ድንጋጌው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞቱ ጊዜም ምክትላቸው እንዲተኳቸው ሥልጣን ይሰጣል ወይስ አይሰጥም የሚለው ነው፡፡ በአንድ በኩል አንቀጽ 75(1) (2) ‹‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶት ይሠራል፤›› ስለሚል ድንጋጌውን አስፋፍቶ (Broadly) ለተረጎመው ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞት በተለዩ ጊዜም ተፈጻሚ ይሆናል ሊባል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን የድንጋጌው ጠባብ (Narrow) አተረጓጎም መተካቱ ተፈጻሚ የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕይወት ኖረው በተለያዩ ጊዜያዊ ችግሮች ምክንያት በማይኖሩበት ጊዜ ነው የሚል መከራከሪያ ማንሳት ይቻላል፡፡ በተለይ አንቀጽ 75(2) ‘ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል’ በሚል ስለሚደነግግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሉበት (በሞት በተለዩበት) ሁኔታ መተካቱን ያለተጠያቂነት ማሰብ ስለማይቻል ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህ በጸሐፊው የሚደገፍ ነው። ሆኖም በመጀመሪያው አቋም መሠረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ማኒስቴሩን እንደሚወክሏቸው ለሚያስብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንም ይሁንታ አይፈልግም፤ ሹመቱም ጊዜያዊ ሊባል አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ውክልናው ሕገ መንግሥታዊ ውክልና በመሆኑ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ ሁሉም ሰው ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ የሚያውቀው፤ የሚጠብቀውም በመሆኑ ነው፡፡ 

ሁለተኛው አማራጭ ግን አንቀጽ 75 ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚ እንደማይሆን በማሰብ ሕገ መንግሥቱ ሌላ መፍትሔ እንዳለው መረዳት ነው፡፡ ይኸውም ጠቅላይ ሚኒስቴሩን የሚሾመውና የሚቆጣጠረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሞት ምትክ የመሾም ወይም የመምረጥ ሥልጣኑ የምክር ቤቱ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱ ይህንን ሥልጣኑን እስከሚጠቀም ድረስ ግን ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ያለው በአንቀጽ 72(2) መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመሆኑ ክፍተቱን የሚሞላ ሥራ ይህ ምክር ቤት ሊሠራ ይችላል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሚሠራው ሥራ ውስጥ አንዱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም ሌላ የምክር ቤቱን አባል ‘ጊዜያዊ የጠቅላይ ሚኒስትርነት’ ሥልጣን መስጠት ነው፡፡ ይህ ጊዜያዊነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰብስቦ ባፀደቀው ጊዜ ወይም ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር በሾመ ወይም በመረጠ ጊዜ ቀሪ ስለሚሆን ክፍተት የመሙላት (Gap filling) ድርሻ ይኖረዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በጥንቃቄ ላስተዋለው ይህ ክርክር አሳማኝ ነው።

ሦስተኛው አማራጭ ሕገ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞት በተለዩ ጊዜ ስለሚኖረው መተካት (Succession) በግልጽ የሚለው ነገረ ባለመኖሩ ክፍተት አለው የሚለው አቋም ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ስለ ፕሬዚዳንቱ አሿሿምና ሥልጣን ሲደነግግ ሰዎች ናቸውና በሞት ቢለዩ ሊሆን ስለሚገባው ነገር አለመግለጹ ክፍተት አለው ሊያስብል ይችላል፡፡ የሕገ መንግሥት ዝምታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሾም ለመምረጥ ባለው ሥልጣን እንደሚሞላ ጸሐፊው ስለሚያምን አቋሙን አይጋራም። ሆኖም ክፍተቱ መኖሩን ለሚያንም መፍትሔው ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ካልሆነም በሕገ መንግሥቱ ለመተርጎም ሥልጣን በተሰጠው አካል ገዥ ትርጉም እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡ ሁለቱንም የሚደግፍ አቆም በሪፖርተር መስተናግዱን ጸሐፊው ያስታውሳል። ማሻሻሉ ከሚጠይቀው ጊዜና ጠበቅ ያለ ሥርዓት አንፃር ግን ተመራጭ አይደለም፡፡ ይህ በአሜሪካ የሕገ መንግሥት ታሪክ ያጋጠመ ክፍተት ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻልና አማራጭ የመተካኪያ መስመር በማበጀት መፍትሔ ሰጥተውታል፡፡ 

የሌሎች ተሞክሮ 


አገሮች ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች (ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር) በሞት በተለዩ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች በማይኖሩበት ጊዜ ስለሚኖረው መተካት (Succession) የተለያዩ ድንጋጌዎች ያስቀምጣሉ። በቅርቡ በሰሜን ኮሪያ እንደተመለከትነው በዘር ሐረግ መተካት የሚኖርበት አጋጣሚ አለ፡፡ በአገራችንም በንጉሡ ዘመን ሕገ መንግሥቱ እንዲህ ዓይነት መተካት በግልጽ ይፈቀድ ነበር፡፡ በቻይናና በአሜሪካ ዘርዘር ያለ ሕገ መንግሥታዊ ደንብ አለ፡፡ በቻይና የፕሬዚዳንቱ ቦታ ሞትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ክፍት ከሆነ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተክቶ ይሠራል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተመሳሳይ ሁኔታ ካጋጠመው ኮንግረንሱ (National People’s Congress) አዲስ ምክትል ፕሬዚዳንት በመምረጥ ክፍተቱን ይሞላል። ፕሬዚዳንቱም ምክትል ፕሬዚዳንቱም በተመሳሳይ ጊዜ ከሌሉ ደግሞ ኮንግረሱ አዲስ ፕሬዚዳንት ይመርጣል፡፡ 

አሜሪካም መተካትን (Succession) የተመለከተ ድንጋጌ አላት። ፕሬዚዳንቱ ከሥራው ከተወገደ፣ በሞት፣ ሥራ በመልቀቅ ወይም ችሎታ በማጣት ቦታው ክፍት ከሆነ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር ወደ ምክትሉ ይተላለፋል ። ሆኖም ይህ ድንጋጌ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ሙሉ የፕሬዚዳንቱን ቢሮ የመረከበ ሥልጣን እንደሚሰጠውና እንደማይሰጠው ግልጽ ስላልነበር አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ሃሪሰን እ.ኤ.አ. በ1843 በሞቱ ጊዜ ምክትል ፕሬዚዳቱ ጆን ቴይለር ሙሉ የፕሬዚዳንት ሥልጣኑን ጠይቀው ስለተወሰነላቸው ገዥ ልምድ (Precedent) ሆነ። ከዚህ በኋላ እ.ኤ.አ በ1967 በ25ኛው ማሻሻያ ዝርዝር ደንብ ወጣ፡፡ በዚሁ መሠረት ፕሬዚዳንቱ ከሞቱ ወይ ከለቀቁ ምክትሉ፣ ምክትሉ ከሞቱ ወይም ከለቀቁ ደግሞ ኮንግረንሱ የመተካት መስመሩን እንዲወስን ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚሁ መሠረት ኮንግረሱ በ1986 ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በሌሉበት ወቅት መተካቱን አከናውኗል፡፡ ኮንግረንሱ ምክትሉ በሌለበት ጊዜ ለሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባዔ እሱም ከሌለ ለተለያዩ የካቢኔ ሚኒስትር አባላት ሥልጣኑን የሚያስተላልፍበት ሥርዓት አለው፡፡ 

ከላይ የተመለከትናቸው አገሮች የመንግሥት አወቃቀራቸው ከእኛ ጋር ቢመሳሳልም ባይመሳሰልም ለሥልጣን አተካካ (Power Succession) ሥርዓት ሊበጅለት  እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ምክንያት በሌሉበት ጊዜ ስለሚኖር መተካት ዝርዝር  ደንብ ያስፈልጋል። መተካቱ በዝርዝር በሕግ የሚገዛ ከሆነ ለትርጉም አይጋለጥም፤ ሁሉም ቀድሞ ኃላፊነቱን አውቆት የሚሠራው ይሆናል፡፡ ዕረፍት ዘመናቸው በሞት የተገታው የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎቻችንን የሚተኩ ግለሰቦች የሟቿቹን ራዕይ እንደሚያስቀጥሉ በመመኘት ጹሑፉን እንቋጭ።

‹ምነው ሞት ዛሬ ተሞኘ፣ ተተኪ እንዳለ ባወቀ፣ ሞት እንዲህ ባልተጨነቀ› የሚለውን እንጉርጉሮ በበሳል ተተኪ እንተግብረው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/306-law/7550-2012-08-25-09-43-13.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር