የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በ579 ሚልዮን ብር ግንባታ አጠናቀቀ



አዋሳ መስከረም 18/2005 የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ በ579 ሚልዮን ብር የጀመረው የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማዘጋጀቱን ገለጸ፡፡ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በ2 ቢልዮን 460 ሚልዮን ብር ወጪ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡ የዩኒቨርስቲው የቢዝነስና ዲቨሎፕመንት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጋቱ ረጋሳ ከትናንት በስቲያ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በዩነቨርስቲው ሜዲካልና ይርጋዓለም ካምፓሶች እንዲሁም በዋናው ግቢና ግብርናና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ከአንድ አመት በፊት የተጀመሩት አዳዲስ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቀዋል፡፡ ከተጠናቀቀው ፕሮጀክቶች መካከል በተለምዶ ኋይት ሀውስ የሚባለው የተማሪዎች ማደሪያ ፣ የመማሪያ ክፍሎች ቤተ መፃህፍት፣የአስተዳደርና የመምህራን ቢሮዎች ጨምሮ ሌሎችም ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መገልጋያዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል፡፡ በሜዲካልና በይርጋለም ካምፓስ ብቻ በእያንዳንዳቸው 780 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስማር የሚያስችሉ መሆናቸውን አመልከተው የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተናገድ እየተዘጋጁ ናቸው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሰቲው በ460 ሚልዮን ብር ወጪ ባለፈው ዓመት ግንባታው ያስጀመረው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አምስት ትላልቅ ዶርሚቴሪዎች በመያዝ እያንዳንዱ ዶርሚተሪ 780 ተማሪዎች ለማስተናገድ የሚያስችሉ ህንፃዎች ማካተቱን ተናግረዋል፡፡ በሁለት ሀገር በቀል ተቋራጮች የሚካሄደው የቴክኖሎጂ እንስቲትዩት 145 የመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የአስተዳደር ቢሮዎች እና ሌሎችም ዲፓርትመንቶች ያካተተ ግዙፍ ህንፃ መሆኑን ከሁለት ዓመት በኋላ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስታውቀዋል፡፡ የቴክኖሎጂ እንስቲትዩቱ የሚቀበሉአቸው ተማሪዎችን 40 በመቶ የኢንጀነሪግ 30 በመቶ ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ለማስተናገድ የሚያስችል ግዙፍ ተቋም እና በውስጡ በርካታ ላብራቶሪዎች፣ የመማሪያ ክፍሎች እንደሚያካትትም ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ዋናው ግቢና አምስቱም ካምፓሶች በ2 ቢልዮን ብር በሚጠጋ ወጪ 24 ትላልቅ ግዙፍ ህንፃዎች የያዙ አዳዲስ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለመጀመር የዲዛይን ስራው አልቆ ተቋራጮችን ለመምረጥ በጨረታ ሂደት ላይ እንዳለና ግንባታቸው ዘንድሮ ተጀምሮ በአራት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትና የአስተዳደር ቢሮዎች በርካታ የመማሪያ ክፍሎች ፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ ካፍቴሪያና ሌሎችም ለመማር ማስተማሩ ስራ የሚያስፈልጉ ክፍሎች ማካተቱን ተናግዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው የሚያካሂዳቸው የማስፋፊያ ፐሮጀክቶች ግንባታ አሁን በመደበኛ ፕሮግራም ብቻ ያሉትን 16ሺህ ተማሪዎች በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመት መጨረሻ የቅበላ አቅሙን ወደ 30 ሺህ ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት መሆኑን ዶክተር ንጋቱ አብራርተዋል፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የቅበላ አቅሙ በየዓመቱ እያሳደገ ዘንድሮ የሚቀበላቸው አዳዲሶችና የተከታታይ ትምህርት ፕሮግራምን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚኖሩት ገልጸዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=2620

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር