በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ጎልማሶች የመሰረተ ትምህርት ፕሮግራም


አዋሳ መስከረም 12/2005 በኢትዮጵያ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን በተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተስጥቶ እየሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ አለም አቀፍ የመሰረተ ትምህርት ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ " የጎልማሶች ትምህርት ለዘላቂ ሰላም " በሚል መሪ ቃል በሀዋሳ ከተማ ከትናንት ጀምሮ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ በበአሉ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም እንደገለጹት ጎልማሶች ከዕለት ተዕለት ስራቸውና ህይወታቸው ጋር የተያያዘ ጤናቸውን በመጠበቅ ምርታማነታቸውን እንዲያሻሻሉ ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ የምዕተ አመቱን የልማትና የትምህርት ግቦችን ከዳር ለማድረስ በተለይም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት ጎልማሶች ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንደሚያበርክቱ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአለማችን 796 ሚሊዮን በሀገራችን ደግሞ 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ጎልማሶች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ አመልክተው በተለይ በትራንስፎርሜሽን እቅዱ አመት መጨራሻ ሁሉንም ጐልማሶች ለማብቃት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለድህነት መወገድና ለሀገራችን ዕድገት በጽኑ ይመኙና ለስኬታማነቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀያሽ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ " ሁሉም ትምህርት ቤቶች ፣ የገበሬ ማሰልጠኛ ጣቢያዎችና የጤና ኬላዎች ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ለማዳረስ ከፍተኛ አስተዋጾኦ ይጠበቅባቸዋል ያሉትን ሚኒስትር ዴኤታ በማስታወስ ለተግበራዊነቱ ባለድርሻ አካላት፣ አጋሮች ብሎም ህብረተሰቡ እጅ ለእጅ ተያይዘው መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ መሀመድ አህመዲን በበኩላቸው የተማሩ ጎልማሶች ካልተማሩት በበለጠ ምርታማና ጤናማ እንደሚሆኑ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ጠቁመው በዓሉ በሀዋሳ ሲከበር በጎልማሶች ትምህርት ክልሎች የደረሱበት ደረጃ ፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ ልምድ ለመለዋወጥና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ለ2 ቀናት በሚቆየው በዓል ላይ የሁሉም ክልሎች የጎልማሶች ትምህር ዘርፍ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ተጠቃሚ ጎልማሶች ተሳትፈዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃና የየክልሎችን ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ሪፖርትና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ የጋር ውይይት ይካሄዳል፡፡ ለክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ተጠቃሚ ጎልማሶችና አመቻቾች የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥም ከወጣው ፕሮግራም ለመረዳት ተችሏል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር