በባህላዊ ማዕድናት ልማት ዘርፍ የታቀደውን ያህል ምርት አልተገኘም፤ ኣዲሱ እቅድ የሲዳማን ወርቅ ኣምራቾች ይጠቅም ይሁን?



የባህላዊ ማዕድናት ምርትና ግብይትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በተደረገው ውይይት እንደተመለከተው፤ ከጋምቤላ ክልል ውጭ በሁሉም ክልሎች የባህላዊ ማዕድናት ምርት ከዕቅድ በታች ነው። ከ2001 ዓ.ም ወዲህ የባህላዊ ማዕድናት ምርት ጭማሪ እያሣየ ቢሆንም በ2004 በጀት ዓመት ግን እንደታቀደው አይደለም።
በዘርፉ የ2004 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2005 በጀት ዓመትን ዕቅድ ያቀረቡት በማዕድን ሚኒስቴር የባህላዊ ማዕድናት ምርትና ግብይት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞጆ እንደሚናገሩት፤ ከተወሰኑ ክልሎች በስተቀር የባህላዊ ማዕድናት ምርት በአብዛኛዎቹ ክልሎች የመቀነስ ሁኔታ ታይቶበታል።
በዘርፉ የምርት መቀዛቀዝ እንደታየና የ2004 በጀት ዓመት አፈፃፀም 63 በመቶ እንደሆነ አመልክተው፤ ከገቢ አንፃር ከዕቅድ በላይ የሆነ አፈፃፀም መመዝገቡን ግን ያመለክታሉ። ለገቢው መጨመር እሴት ተጨምሮላቸው የሚላኩ ምርቶች ማደግና የወርቅ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር በአብነት ተነስቷል።
እንደ አቶ ታምራት ገለፃ፤ በዘርፉ ችግሮች እያጋጠሙ ሲሆን በተለይም የሚመለከታቸው አካላት በሚፈለገው መንገድና ፍጥነት በቅንጅት አለመሥራት፣ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ማነስ፣ የባለሙያ መፍለስ፣ ፈቃዶችን በአግባቡ አለማስተዳደር ዋና ዋናዎቹ ችግሮች ናቸው። ሕገ ወጥ የማዕድናት ምርት እንዲሁም ወርቅ በባህላዊ መንገድ የሚመረትባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ችግሮች መኖራቸውም ሌሎች የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው።
«በዘርፉ ማኅበራትን ማደራጀት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሮያሊቲ ክፍያ ያለው የግንዛቤ ማነስ ተጨማሪ ችግር ነው» ሲሉም ይናገራሉ።
በውይይቱ ተሣታፊ የሆኑ የክልል የማዕድን ቢሮ ተወካዮች በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ለዘርፍ ዕድገት ከላይ እስከታች በቅንጅት መሥራት ይገባል። ሮያሊቲ ክፍያን ሥርዓት ማስያዝና ሕገ ወጥ አምራቾችን መከላከል እንደሚገባም ያመለክታሉ።
እንደ ተሣታፊዎቹ ገለፃ የማዕድን እሴት በመጨመር ለውጭ አገር ለመላክ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። «ይህም አሠራር የውጭ ምንዛሪ ከማሳደጉ በተጨማሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል» ይላሉ። የተሰጡ ፈቃዶች በአግባቡ ለማስተዳደር በቅንጅት እንዲሰራም ይጠይቃሉ።
የማዕድን ሚኒስትሯ ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ የባህላዊ ማዕድናት ምርትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው። «የባህላዊ ወርቅ ምርትን የበለጠ ውጤታማ በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል በአደረጃጀትና በአሠራር ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት የሚያስችል ሁለንተናዊ የባህላዊና የአነስተኛ ደረጃ ማዕድናት ልማት ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል» ሲሉም ይናገራሉ።
ማዕቀፉ በሁሉም ክልሎች ለውጥ ያመጣል ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተው፤ በመሆኑም ማዕቀፉን ተግባራዊ በማድረግ በ2005 ዓ.ም በዘርፉ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
የወርቅ ግዥ ጣቢያዎች ከማዕከል ወደ ምርት አካባቢዎች ቀረብ ለማድረግ ታቅዶ በሃዋሳ፣ በአሶሳ፣ በጅማና በሽሬ ንግድ ባንኮች አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። በቀጣይም በጥናት ላይ የተመሠረቱ የግዥ ጣቢያዎችን ወደ ምርት አካባቢዎች የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደ ሚቀጥልም ያመለክታሉ።
በዕለቱ እንደተገለጸው በዘርፉ ያሉትን ማነቆዎችን በመፍታት በ2005 ዓ.ም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ታቅዷል።
በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በባህላዊ ማዕድናት ዘርፍ በሥራ ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ ይገመታል። በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በዘርፉ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ዜጐች ተሰማርተው እንደሚገኙም ተመልክቷል።
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php? newsLocation=home&newsInstruction=more&newsId=9018

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር