POWr Social Media Icons

Tuesday, August 28, 2012

በኤልያስ ዶጊሶ 
ከደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ 

እጅግ እየዘመነ በመጣው የዓለማችን የኑሮ ሁኔታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሕልውና ጥያቄ ሆኗል። በተለይ ሕዝቦች ከከፋ ድህነት ተላቅቀው የተሻለ ሕይወት መምራት እንዲችሉ በኢኮኖሚው መስክ ንቁ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ እንደ ንግድ ያሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ደግሞ አንዳንዴ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት የተለያየ ስፍራ መገኘትን ይጠይቃል። የሰው ልጅ ደግሞ በተፈጥሮው በጊዜና በቦታ ውሱን ከመሆኑ አንፃር በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ጥቅሙን በሚመለከቱ ስፍራዎች ሁሉ ተገኝቶ ተግባሩን መከወን አይችልም፡፡
እነዚህ መሰል ጉዳዮችን አስመልክቶ የሰው ልጅ የሚኖረው ብቸኛ አማራጭ እንደራሱ ሆኖ በእርሱ እግር ተተክቶ ጉዳዮቹን ወይም ሥራዎቹን የሚከውንለትን ሰው መወከል ግድ ይሆንበታል፡፡ ሥራዎችን በውክልና ማሰራት አስፈላጊ የሆነው በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ የሕይወት መስክም ካለው ጠቀሜታ አኳያ ነው፡፡ በየትኛውም ዘርፍ የሚደረጉ የውክልና ውሎች ማዕቀፋቸው በፍትሐብሔር ሕግ ከአንቀጽ 2179 እስከ 2285 ባሉ ድንጋጌዎች ነው፡፡
በዚሁ ሕግ መሠረት የውክልና ሕግ የእንደራሴነት ሕግ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሁለቱንም ቃላት መጠቀም በፍቺ ረገድ ልዩነት የላቸውም፡፡ በአማርኛ መዝገበ ቃላት «ወኪል» የሚለውን ቃል እንደዋና ሆኖ የሚሰራ፣ ተጠሪ፣ ኃላፊ፣ ዋናውን ተክቶ እንዲሰራ የተመረጠው ሰው፣ አካል የሚል ሲሆን «ውክልና» ማለትን ደግሞ ለአንድ ሰው ወይም ድርጅት ወኪል፣ ተጠሪ መሆን የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል፡፡ በፍ/ሕ/ቁ 2199 መሠረት ደግሞ «ውክልና» ማለትን በሚከተለው መልኩ ይተረጉመዋል፡፡ «ተወካይ የተባለ አንድ ሰው ወካይ ለተባለው ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ሕጋዊ ሰራዎችን በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ነው።»
ከዚህ የሕግ ትርጓሜ የምንረዳው ውክልና በወካይና በተወካይ የሚደረግ ውል መሆኑን፣ ተወካዩ የወካዩ እንደራሴ መሆኑን፣ ተወካዩ ሕጋዊ ሥራዎችን በወካዩ ስም የማከናወን ግዴታ ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ውክልና የመስጠትም ሆነ የመቀበል ጉዳይ በግልጽ ወይም በዝምታ ሊፈፀም የሚችል ሲሆን ሕጋዊ ፎርም የሚያስፈልገው ሆኖ ሲገኝ ግን ሕግ በሚያዘው መሠረት መሆን እንዳለበት በሕግ ተደንግጓል፡፡ (የፍ/ሕ/ቁ 2200ና 2201)፡፡ በኢትዮጵያ የእንደራሴነት ሕግ መሠረት የውክልና ስልጣን ከሁለት ነገሮች ሊመነጭ ይችላል፡፡ ይኸውም ከሕግና ከውል፡፡
(ፍ/ሕ/ቁ 2179) ከሕግ የሚመነጭ የውክልና ስልጣን በሕግ ተለይቶ ሲቀመጥ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አባትና እናት 18 ዓመት ላልሞላው ልጃቸው ሞግዚትና አሳዳሪ መሆናቸው በደቡብ ክልል ቤተሰብ ህግ ቁ. 234 ላይ በግልጽ ስለተደነገገ ልጁን በሚመለከቱ ጉዳዮች አባትና እናት ተገቢ ሕጋዊ ተግባራትን የመፈፀም ስልጣን ይኖራቸዋል፡፡
ከውል የሚመነጭ የውክልና ስልጣን ደግሞ በወካዩና በተወካዩ መካከል በሕግ አግባብ ከሚደረገው ውል የሚመነጭ ሥልጣን ነው፡፡ የውክልና ውል ሳይኖር የውክልና ስልጣን ሊኖር አይችልም፡፡ በውክልና ሕጉ መሠረት ሁለት ዓይነት የውክልና ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህም 
1. ጠቅላላ ውክልና (General agency)፡- ጠቅላላ ውክልና የተሰጠው ተወካይ የወካዩን የአስተዳደር ሥራ ብቻ የሚያከናውን ነው (ፍ/ሕ/ቁ 2203)፤ ከዚህ ሌላ ተጨማሪ ሥልጣን አይኖረውም፡፡ የአስተዳደር ሥራ ማለት ደግሞ የወካዩን ሀብት የማስቀመጥ፣ የመጠበቅ፣ ከ3 ዓመት ለማያልፍ ጊዜ የማከራየት፣ በብድር የተሰጠውን ሀብት መሰብሰብ፣ ከሀብቱ የሚመጣውን ገቢ ተቀብሎ የማስቀመጥ፤ ለተከፈሉ ዕዳዎች ደረሰኝ መስጠት፣ ሰብልን መሸጥ፣ ለሽያጭ የተመደቡ የንግድ ዕቃዎችን ወይም ይበላሻሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን መሸጥ የመሳሰሉትን ለመሥራት የሚያስችል ነው (ፍ/ሕ/ቁ 2204)፡፡
2. ልዩ ውክልና (Special agency)፡- ከዚህ በላይ የአስተዳደር ሥራ ተብለው ከተጠቀሱት ሥራዎች ውጪ ሌላ ሥራ ለመሥራት ልዩ ውክልና እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ፣ ዋስትና አስይዞ መበደር፣ የአክሲዮን ወይንም በሌላ የንግድ ማህበራት ካፒታሎችን ማስገባት፣ የለውጥ ግዴታን ውል መፈረም፣ መታረቅ፣ ለመታረቅ ውል መግባት፣ ስጦታ ማድረግ፣ በፍርድ ቤት ቀርቦ ለመከራከር ልዩ ውክልና ሥልጣን አስፈላጊ ነው(ፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2205)፡፡ 
በፍርድ ቤት ለሚቀርብ ክርክር ለመወከል ተወካዩ የሕግ ባለሙያ ጠበቃ መሆን አለበት፤ ወይም የተከራካሪው ወገን ሚስት፣ ባል፣ የልጅ እናትና አባት፣ እህት፣ ወንድም መሆን እንዳለበት በፍ/ህ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 58 ላይ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውጪ ተወካይ ወኪል አድራጊውን ወክሎ በራሱ ያለጠበቃ ፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር አይችልም፡፡ ልዩ ውክልና የተሰጠው ሰው በውክልናው ላይ በዝርዝር ከተመለከቱት ጉዳዮች ሌላ ከእነዚሁ ጉዳዮች ጋር ተከታታይና ተመሳሳይ የሆኑ በልማድ አሰራርም አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወን ይችላል፡፡ ለምሳሌ መሸጥ መለወጥ የሚችል ተወካይ የሸጠውን ነገር ገንዝብ መቀበልም ይችላል፡፡ ካፒታሎችን በንግድ ማህበር ማስገባት የሚችል በማህበሩ ሰነድ ላይ የመፈረም ሥራም መሥራት ወዘተ … ይችላል ማለት ነው፡፡
ተወካዩ ከተሰጠው የውክልና ሥልጣን ውጪ አልፎ የፈፀመውን ተግባር ወካዩ ካላፀደቀው ወይንም በሥራ አመራር ደንብ መሠረት መሰራት ያለበት ካልሆነ በስተቀር ወካዩን አያስገድደውም፡፡ ተወካዩ ከሥልጣኑ አልፎ የሰራውን ሥራ ወካዩ የማጽደቅ ግዴታ የሚኖርበት ተወካዩ የሠራው በቅን ልቦና ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም ወካዩ የሥራውን አረማመድና መልካም አካሄድ ሁኔታ ቢረዳው ኖሮ ለተወካዩ የሰራውን የሥልጣን ወሰን ሊያሰፋ ይችል ነበር፤ ተብሎ ሲገመት ነው፡፡ ሆኖም ተወካዩ ያልተፈቀደለትን ሥራ ከመሥራቱ በፊት ወካዩ ሥልጣኑ እንዲያሰፋለት መጠየቅ እየቻለ ቸል ብሎ በራሱ ሃሣብ ሰርቶ ከሆነ ወካዩን አፅድቅልኝ ብሎ የመጠየቅ መብት የለውም (ፍ/ሕ/ቁጥር 2207)፡፡ 
አንድ ሰው በአንድ ነገር ላይ ለአንድ ወይንም ለብዙ ተወካዮች በአንድ ላይም ሆነ በተናጠል ውክልና መስጠት ይችላል፡፡ በአንድ ውል ብዙ ሰዎች የተወከሉ ከሆነ የውክልና ሥልጣኑን ሁሉም በአንድነት መቀበላቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፤ ካላረጋገጡ ውክልናው እንደፀና አይቆጠርም፡፡ እንዲሁም በአንድ ውል ብዙ ሰዎች የተወከሉ ከሆነ የሰሩዋቸው ሥራዎች ወካዩን ሊያስገድዱት የሚችሉት ተወካዩች ሁሉ አብረው ሰርተው ሲገኙ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአንድ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች በተናጠል ተወክለው ከሆነ እያንዳንዳቸው የሚሰሩት ሥራ ወካዩን ሊያስገድደው ይችላል፡፡ 
የወካይ ግዴታዎች (Duty of the prin cipal)
- በውላቸው ስምምነት መሠረት ለተወካዩ የድካም ዋጋ የመክፈል፣ የሚከፈለው የድካም ዋጋ ከተሰጠው አገልግሎት ጋር እኩል ወይም ተመጣጣኝ መሆን ይገባዋል፡፡ ከተሰጠው አገልግሎት የበለጠ ከሆነ ዳኞች መቀነስ ይችላሉ፣ በውል ያልተቀመጠ ከሆነ በአካባቢው ልማድ መሠረት የመክፈል፣ 
- ለሥራ ማስኬጃ ቅድመ ክፍያ መስጠትና የወጣውን ወጪ የመሸፈን፣
- ተወካዩ ለወካዩ ጥቅምና ለሥራው መልካም አካሄድ ሲል በወኪልነቱ ከገባው የውል ግደታ ተወካዩን ነፃ ማውጣትና ለደረሰበት አደጋ ኪሣራ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል፡፡ 
የተወካይ ግዴታዎች(duty of the agent)፡- ከፍ/ብ/ሕ/አንቀጽ 2208-2213
- የወካዩን ጥቅም ለማስጠበቅ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና እንዲኖረው ያስፈልጋል፤
- ውክልናውን ማሻሻል አስፈላጊ ሲሆን ለወካዩ ሃሣብ ማቅረብና ማሳወቅ፤
- በወኪልነቱ የሚሰራውን የተገኘውን ገቢ ትርፍ ሂሣብ በመያዝ ወካዩ በጠየቀው ጊዜ የሥራውን አካሄድ መግለጫና ሂሣብን ማቅረብ፤
- ተወካዩ ለወካዩ ሊከፍል የሚባውን ገንዘብ ለራሱ ጥቅም አውሎት ከሆነ እስከወለዱ ለወካዩ የመክፈል ግዴታ አለበት፤
- ተወካዩ በውክልና የተሰጠውን አደራ እንደመልካም የቤተሰብ አባት በትጋትና በጥንቃቄ መጠቀም አለበት፤
- ወካዩ ካልፈቀደለት በስተቀር ተወካዩ የተወከለበትን ሥራ እሱ ራሱ መፈፀም አለበት፡፡
ስለውክልና መቅረት (Termination of Agency)፡-
የውክልና ሥልጣን በመሻር፣ በሞት፣ በፍርድ መብት ማጣት፣ በጤና ችግር ቀሪ ሊሆን ወይንም ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ወካዩ አስፈላጊ መስሎ በታየው ጊዜ የውክልናውን ሥልጣን ለመሻር ይችላል፤ የውክልና ውል ጽሁፉንም ተወካይ እንዲመልስለት ሊያስገድደው ይችላል፡፡ የውክልናውን ጽሁፍ እንዳይመለስ ውል ቢደረግ እንኳን ፈራሽ ነው፡፡ 
ወካዩ ወይንም ተወካዩ በሞት ቢለይ የውክልና ሥልጣኑ ወዲያውኑ ይቋረጣል፡፡ የተወካዩ መሞት ወይም ሥራ ያለመቻል፣ በሥፍራው አለመኖሩ ከተረጋገጠ፣ ችሎታ ያጣ እንደሆነ ወይንም በንግድ ኪሣራ ደርሶበት ከሆነ የውክልና ሥልጣን ወዲያውኑ ቀሪ ይሆናል፡፡ ሆኖም የሟች ወራሾች መብታቸውን አረጋግጠው እስከሚመጡ ድረስ ተወካይ ወካይ በሕይወት በነበረ ጊዜ የጀመረውን የአስተዳደር ሥራ ለአጭር ጊዜ ሊሰራ ይችላል (ፍ/ሕ/ቁጥር 2232 (2))፡፡ 
ብዙ ወካዮች በአንድነት ሆነው ለጋራ ጉዳያቸው የወከሉትን ተወካይ አንዱ ወካይ ብቻ ሊሽረው አይችልም (ፍ/ሕ/ቁጥር 2228)፡፡ በሌላ በኩል ተወካዩ የውክልና ሥልጣኑን በራሱ ለመተው የሚችል ሲሆን ነገር ግን የውክልና ሥራውን ሲተው ለወካዩ ማሳወቅ አለበት፡፡ ተወካዩ በጥቅም የሚሰራ ከሆነና የተወካዩ ሥራውን መተው በወካዩ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ተወካዩ ለወካዩ የደረሰበትን ኪሳራ መክፈል አለበት፡፡ በሌላ በኩል ተወካይ ሥራውን ቢቀጥል ከፍ ያለ ጉዳት የሚያደርስበት መሆኑ ከታወቀና ሥራውንም ለመቀበል በፍፁም የማያስችለው ምክንያት ካለ የጉዳት ኪሳራ መክፈል አይገደድም፡፡
ለሦስተኛ ወገን (ተተኪ ተወካይ) ስለሚሰጥ ውክልና፡- 
ወካዩ ለተወካዩ በሚሰጠው የውክልና ሥልጣን ሦስተኛ ወገንን መወከል እንዲችል ሥልጣን ሊሰጠው ይችላል፡፡ ሆኖም ሦስተኛ ወገን ተወካይ የሚኖረው የውክልና ሥልጣን ለመጀመሪያ ተወካይ ከተሰጠው ሥልጣን ያነሰ ወይንም እኩል ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ተወካይ ሥልጣን ባልተሰጠው ጉዳይ ሦስተኛ ወገንን ሊወክል አይችልም፡፡ ተወካዩ ወካዩ ሳያውቅ ተተኪ ተወካይ ሊወክል የሚችለው በሕመም ወይም በሌላ ከባድ ምክንያት ስራውን ራሱ ማከናወን ካልቻለና በወካዩ ጥቅም ላይም ጉዳት ሊያመጣ የሚችል ሲሆን ነው፡፡ በዚህን ጊዜ በተተኪው ተወካይና በዋናው ወካይ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለ ሕጉ ግምት ይወስዳል፡፡ 
ውክልና የሚሰጥባቸው ተቋማት፡- 
ውክልና ውል ነው፡፡ ስለሆነም ውሉ ወይም ስምምነቱ የሚደረገው ውል ለማዋዋል በሕግ ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት መፈፀም ይኖርበታል፡፡ በክልሎች ውል የማዋዋል ሥልጣን የተሰጠው ለፍትህ ቢሮ ሲሆን እነኚህ ውሎችም በዞን ፍትህ መምሪያና በወረዳ ፍትህ ጽ/ቤቶች ውስጥ አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የውልና የክብር መዝገብ ማስረጃ ምዝገባ አገልግሎት በክፍለ ከተሞች የፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ጽ/ቤቶች ነው፡፡
ስለኢትዮጵያ ውክልና ሕግ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች በጣም በአጭሩና ዋና ዋናዎቹን ድንጋጌዎች በዳሰሰ መልኩ ሲሆን በዚህ ሕግ ዙሪያ ለወደፊት ወይም በቀጣይ ሰፋ ያለ ጥናትና ማብራሪያ ለመስጠት የምንሞክር መሆኑን አንባቢው እንዲረዳልን ይሁን፡፡ 

http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/politics.php

0 comments :