የሲዳማ ሕዝብ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው


ሃዋሳ ነሐሴ 9/2004 የሲዳማ ሕዝብ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ ተክብሮለት ለአገር ዕድገትና ብልፅግና ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡
የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ የፍቼ ጫምባላለ በዓልና የብሔሩ 18ኛው የቋንቋና ባህል ስምፖዚየም በሲዳማ ባህል አዳራሽ ትናንት በድምቀት ተከብረዋል፡፡
የፍቼ ጫምባላለ በዓልን ባህላዊ የአከባበር ስነ ስርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ለማስመዝገብ ዝግጅት መደረጉም ተመልክተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሲዳማ ብሔረሰብ ከሌሎች ብሔር ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት በመገርሰስ በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን የድርሻውን ተወጥቷል፡፡
የሲዳማ ህዝብ በሀገሪቱ እየተገነባ ባለው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ማንነቱ ተክብሮ በቋንቋው የመናገር፣ የመዳኘትና የመማር መብቱ ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ማግኘት ችሏል ብለዋል፡፡
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ የሲዳማ ህዝብ በሥርዓቱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በመከበሩ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ባለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ለተመዘገበው ፈጣን ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
የሲዳማ ህዝብ የኢትዮጵያን ህዳሴ በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት እየተደረገ ላለው ሁለንተናዊ ጥረት ስኬት ከሌሎች ብሔር ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመሆን እያካሄደ ያለውን ፀረ-ድህነት ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
የሲዳማ ተወላጆች የፍቼ ጫምባላለ በዓልን ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍና የሌሎችንም ባህል በማክበር በድህነት ላይ እየተደረገ ያለው ትግል ውጤታማ እንዲሆን ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው የሲዳማ ሕዝብ ከ1983 ወዲህ በቋንቋው የመጠቀም ፣ ባህሉን የማሳደግ አኩሪ ድል መጎናፀፉን ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ቋንቋና ባህልን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት የሲዳምኛ ቋንቋ ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም በብሄራዊ ፈተና እንደ አንድ ትምህረት ከመሰጠቱም በላይ በኮሌጆችም በቋንቋው በዲፕሎማ ማስመረቅ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመጪው የትምህርት ዘመን በሲዳምኛ ቋንቋ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር ሥልጠና ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም የሲዳማ ሕዝብ ባለፉት 21 ዓመታት በሁሉም መስክ ያስመዘገባቸውን ድሎችና ውጤቶች ጠብቆ ለበለጠ ዕድገትና መሻሻል በትጋት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
የዞኑ አስተዳደር የፍቼ ጫምባላላ በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ለማስመዝገብ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል፡፡
በሲዳማ በህል አዳራሽ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ በየደረጃው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና በውጭ አገር የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጆች የተሳፉ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር