የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ዕረፍት አስመልክቶ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሰጡት አስተያየት



በመገናኛ ብዙኅን የሰማሁት ነገር እጅግ ልብ የሚነካና የሚያሳዝን ነው፡፡ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትልቅ ራዕይና አቅም የነበራቸው መሪ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ይኼ ነው የማይባል ጊዜያቸውን መስዋዕት አድርገው፣ አምባገነኑን የደርግ ሥርዓትን መክቶ ማሸነፍ የቻለ ፓርቲ መመሥረት የቻሉ ግለሰብ ናቸው፡፡
ከዚያም በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ነው የማይባል የፖለቲካና የኢኮኖሚ መነቃነቅን የፈጠረ አቅም የነበራቸው ግለሰብ ነበሩ፡፡ ወደፊትም በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ርቀትን ለመሄድ የሚያስችል አቅም የነበራቸው ግለሰብ ናቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ለኢትዮጵያ ካቀዱትና ይዘውት ከተነሱት ዓላማ አኳያ መታጣታቸው እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ በተረፈ እንደ አባት ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው እጅግ ትልቅ እጦት ነው፡፡ ለአፍሪካ ማኅበረሰብም አፍሪካን በማስተሳሰርና አንድነትን በማምጣት፣ በልማት መስመር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ቀላል የማይባል ሚና የተጫወቱ ግለሰብ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ስናያቸው እንደ አገር መሪ ይዘውትና ሰንቀውት የተነሱት ነገር ረጅም ርቀት የሚወስደን መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ወደፊትም ቢሆን በጀመሩት ነገር ላይ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት አቅም የነበራቸው ግለሰብ ነበሩ፡፡ እስከዛሬ ድረስ የሰበሰቡት ዕውቀት፣ ያከማቹት ግንዛቤና ተሞክሮ ወደሚቀጥለው ኃይል ተላልፎ አለማየትም ትልቅ እጦት ነው፡፡ በቀጣይ የሚጠበቀው ነገር ከኢሕአዴግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ በሰፈረው መሠረት ኢሕአዴግ የሥልጣን ሽግግሩን በአግባቡ መወጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ፣ በማያሻማና በሚታይ ሁኔታ መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ አገርን በማልማትና በማሳደግ ሒደት ውስጥ ቀዳዳ እንዳይኖረው እመኛለሁ፡፡ ተቀራርቦና ተቻችሎ ለመሄድ ብዙ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የተፈጠረው ነገር አሳዛኝ ቢሆንም ቆም ብለንና ወደ ኋላ መለስ ብለን እንድናይ፣ እንድናስብና እንድናጠነጥን ያስገድዳል፡፡ ሁላችንም ለአገራችን ቀናኢዎች ነን፡፡ በዕድገቷና በልማቷ ላይ የራሳችን አስተሳሰብ አለን፡፡ ይኼንን ሁሉ ተጋርተን ይህችን አገር ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን አስጠብቀን መቀጠል የምንችልበት ዕድል እንዲኖር ነው ምኞቴ፡፡ በምንም ዓይነት ውስጣዊ ግጭትና አለመስማማቶች ቢኖሩ ቅድሚያ ለሕዝቡ ሊሰጥ የሚገባው አክብሮትና ትኩረት መኖር አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ ኢሕአዴግ ሥራውን ሠርቶ መገኘት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ



---------------------- //-------------------

እንደማንኛውም ፍጡርና ሰው በመሞታቸው አዝኛለሁ፡፡ እኔና እሳቸው በትግል ወቅትም አብረን ብዙ ጊዜ ስለነበርን ሕይወታቸው ማለፉ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ወስጥ ደግሞ በሚቀጥለው ጊዜ እሳቸው ከነበሩበት ጊዜ የተሻለ መግባባትና ነፃነት እንዲፈጠር ፍላጐቴ ነው፡፡ የተሻለ ነገር እንዲኖር በተለይ ፓርቲያቸው በጥብቅ እንዲያስብበት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት ብዙ ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ነበሩ፡፡ የታሰሩ ሰዎች የሚፈቱበትና በአገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ መግባባት የሚፈጠርበት ሁኔታ መኖር አለበት የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ ማንም ቢሆን ሕይወቱ እንዲያልፍ ወይም እንዲሞት አልመኝም፡፡ እንኳን አብሮ ብዙ የሠራ ሰው ቀርቶ ማንም ሰው ሲሞት ሐዘን ይሰማኛል፡፡ እሳቸው ደግሞ በትግልም ወቅት አብረን ነበርን፤ ላለፉት አሥር ዓመታት ብንለያይም፡፡ በተለይ በትግል ወቅት በነበርንበት ጊዜ በነበረው ሁኔታ የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡

የአረና ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አሥራት

---------------------- //-------------------

እኔ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገራችን ባህል ሰው እንዲህ ዓይነት ነገር ሲገጥመው ነፍሱን ይማረው እላለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጠዋት (ትናንትና ማለዳ) ስሰማ ደንግጫለሁ፡፡ ነገር ግን አገሪቷ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመፍጠር እጅግ አጣብቂኝ የሆነ ነገር ውስጥ ስለገባች፣ የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ ለመፍጠር ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲኖር አጋጣሚውን እንዲጠቀም ገዥውን ፓርቲ አደራ እላለሁ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና
---------------------- //-------------------

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞት አዝኛለሁ፡፡ ሰው ናቸውና እንደ ሰው መታመምም፣ መሞትም እንደሚኖር አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ አስተምረውት ሊያልፉ ይገባል ብዬ የማስባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ሥልጣንን በሞት ሳይሆን በፈቃደኝነት ለቆና ሲቪል ሆኖ ያለአጃቢ ከሕዝብ ጋር መንቀሳቀስና የመሳሰሉ ነገሮችን፡፡  በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ምን ዓይነት ኑሮ እየኖር እንደሆነ መረጃ ከሚያቀርቡላቸው ሹማምንት ውጭ በራሳቸው እይታ ካዩ በኋላ የሚኖራቸው ምላሽ ቢታይ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በሞተ ሰው ላይ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሳይሞቱ ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገር መማማር ይቻል ነበር፡፡ በሕይወት እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባገነን፣ ጨካኝ፣ ወዘተ በማለት ብዙ ኃይለ ቃል ተጠቅመን ገልጸናቸው ይሆናል፡፡ አሁን በሞተ ሰው ላይ ምንም ማለት አስፈላጊም አይደለም፡፡ አይቻልምም፡፡ ከዚህ በኋላ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለው ነገር ታሪክ የሚሆንና ታሪክ የሚፈርደው ጉዳይ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ፓርቲያቸው የሚወስዳቸውን አቋሞች በማየት የምንለው ነገር ይሆናል፡፡ አሁን ሹማምንቱ ከሚሰጧቸው መግለጫዎችና ንግግሮች የምረዳው፣ ምናልባትም ፓርቲውን የሚያስገምተው ነው እላለሁ፡፡ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተሳሰብ፣ እይታና ሌሎች ነገሮችን ይዘን እንቀጥላለን›› ሲባል፣ ‹‹ፓርቲው የአንድ ሰው ነበር?›› የሚለውን ነው የሚያሳየው፡፡ ይኼ ትንሽ ኢሕአዴግን እንደ ገዥ ፓርቲ ያስገምተዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው የበላይነት እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ መሪ ሆኖ የሚመጣው ሰው የራሱን እይታ ይዞ የሚመራበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ለምሳሌ የእኔን መኪና እኔ ስነዳውና አንተ ስትነዳው ይለያያል፡፡ እስከምትለማመደው ብቻ አይደለም፡፡ የአነዳድ ሁኔታው ሁሉ ነው የሚለያየው፡፡ ስለዚህ ለሚቀጥለው መሪ መብት ስትሰጠው ‹‹በፈለግኩት አቅጣጫ ነው የምትመራኝ›› ካልከው የፓርቲውን ደረጃ ያወርደዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ የመሪነት ሥልጣን የሚይዘው ሰው የሚመራበትን ሁኔታ ራሱ መምረጥ ይኖርበታል፡፡ የሚመራበትን ሁኔታ በፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ መስጠት የሚመራውን ሰው መናቅ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላሉ አይደለም በሰላምና በፍቅር የሚኖሩት፡፡ አሁንም በሰላም መኖራቸው ይቀጥላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ታመዋልና ምን እንሆናለን?›› ሲሉ ምንም አንሆንም ነው ያልነው፡፡ አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም አይሆንም፡፡ ግን ደግሞ ምንም የማይሆኑ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥላ ጠብቀው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ካሉ ቢፈሩና ቢሰጉ ተገቢ ነው፡፡ የሚያስፈራቸውና የሚያሰጋቸው የሠሩት ሥራ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም፡፡ መልካም እንቅልፍ ለመተኛት ጥሩ ሥራ መሥራት አለብህ፡፡

የመድረክ ፓርቲ ብቸኛው የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ


---------------------- //-------------------

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ከ1983 ዓ.ም. እስከ 1993 ዓ.ም. ለአሥር ዓመታት አብረን ሠርተናል፡፡ ከዚያ በኋላ አንድና ሁለት ጊዜ እንጂ ብዙም አልተገናኘንም፡፡ በእሳቸው አመራርና አካሄድ የማልስማማ ቢሆንም አደንቃቸው ነበር፡፡ አሁንም አደንቃቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ጐበዝ ናቸው፡፡ ብዙ ያነባሉ፡፡ ብቃታቸውን እኔ በማስበው መንገድ ለአገሪቱ በጥቅም ላይ አውለዋል ወይስ አላዋሉም? ለአገሪቱ ጠቃሚ ነበር ወይስ አልነበረም? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በጉብዝናቸው የማደንቃቸው ሰው ናቸው፡፡ ይሠራሉ፡፡ እንደሰው ማረፋቸው (መሞታቸው) በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወገኖቻቸውና ለጓደኞቻቸው እግዚአብሔር እንዲያጠናቸው እመኛለሁ፡፡ መደበቁ ትክክል እንዳልሆነና የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 12 ድንጋጌ መጣሱን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ታመዋል ከተባለ 50 ቀናት አልፈዋል፡፡ አገሪቱን 21 ዓመታት ያስተዳደሩ በመሆናቸው፣ ለሕዝቡ በየቀኑ ስለሳቸው እያንዳንዱ ጉዳይ መገለጽ ነበረበት፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ


---------------------- //-------------------

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞታቸውን ስሰማ ከልብ ነው ያዘንኩት፡፡ በመሞታቸውም ልጆቻቸውን፣ ባለቤታቸውን፣ ዘመዶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን እግዚአብሔር ያጥናችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የአመለካከት አቅም ያላቸው ባላንጣ ነበሩ፡፡ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳይ ያሉት ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው፣ ብዙዎቹን ሐሳቦች በራሳቸው አስተሳሰብ ለመግለጽና ለማሳመን አቅም ነበራቸው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ሆኖም ግን በአንድ በኩል ወደ ኋላ ዘወር ብዬ ስመለከተው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሥር እንዲሰድና አቅም እንዲኖረው፣ ታማኝነት ያለው የፖለቲካ አቅጣጫ እንዲፈጠር የተለያየ አመለካከት ያላቸው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የነበራቸው አስተዋጽኦ ደካማ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጣዩ የኢሕአዴግ አመራሮች ለሕዝብ ታማኝነት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች በማሰባሰብ፣ እኛም ተቃዋሚዎች አገራችን በሰላም ነፃነቷን፣ ክብሯንና ህልውናዋን ጠብቃ ወደፊት እንድትራመድ አስተዋጽኦ እንዲኖረን፣ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ መድረኩን ማስፋት አለበት፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገር ልማትና ዲሞክራሲ እንዲሳተፉ ማድረግ ከገዥው ፓርቲ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማኝን ሐዘን በድጋሚ መግለጽ እወዳለሁ፡፡

የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ተመስገን ዘውዴ

---------------------- //-------------------

እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት አሳዝኖኛል፡፡ ወደፊትም የሰከነና የረጋ አመራር እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች የተከፋ ሰው ሊኖር ስለሚችልና ሐዘንም ሲጨመር ከባድ ነገር ሊሆን ስለሚችል፣ አስተዋይነትና አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የኢሕአዴግ አመራር ይኼንን በብቃት እንዲወጣ እንፈልጋለን፡፡ አቶ መለስ ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በተለይ በሥራ ጥንካሬያቸው እኔም በግሌ ጥሩ ሰው እንደሆኑና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ሰው እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ በሥራዎቻቸውና በሆኑት ጉዳዮች ዙሪያ የሚስማማም የማይስማማም እንዳለ ሆኖ፣ የያዙትን ነገር ይዘው በተከታታይ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በዓላማቸው ፀንተው መቆየታቸው እንደ አንድ ጥሩ ጐን የሚታይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ወደፊት እንደተለመደው የጠቅላይነት አስተሳሰብን ትቶ፣ ኢትዮጵያን የሁሉም አድርጐ ማየትና የማሳተፍ ሰፊ የሆነ የፖለቲካ መድረክ መፍጠር፣ ሌሎች አማራጮችን በመፈለግ ኢትዮጵያውያንን ሊጠቅሙ የሚችሉ ትላልቅ ሰዎችን ማሳተፍ አለበት፡፡ ትልቅ አገርና ትልቅ መሪ ማለት ሌሎቹም እንዲበቁ ማድረግ ስለሆነ፣ የሌሎቹም ችሎታ እንዲወጣ በማድረግ በሳል አመራር እንዲኖር ማድረግ አለበት፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር