የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የቀብር ስነሰርዓት ተፈጸመ



አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17፣ 2004 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ ።
በቀብር ስነ ሰርዓቱ ላይ  ተጠባባቂ  ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ሚኒስትሮች ፣  የተለያዩ አገራት አብያተ ከርስቲያናት መሪዎች ፣ አምባሳደሮችና  በሺዎች የሚቆጠሩ  የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል ።
በስነ ስርዓቱ ላይ  አቶ ሀይለማሪያም ብፁዕ  ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ተሳታፊ የነበሩ አባት ናቸው ብለዋል ።
በቤተ ክርስቲያኗም ሆነ በአገሪቱ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከነበራቸው ተሳትፎ ባለፈ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት  ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም የአገራቸውን  በጎ ገፅታ ያሳወቁ ብልህ አባት ነበሩ ሲሉም ገልጸዋቸዋል።
የአቡነ ጳውሎስን የበጎ አድራጎት ተግባር ተሳትፎን  ያስታወሱት አቶ ሀይለማሪያም ፥ በኤች አይ ቪ /ኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን በመደገፉ እንዲሁም የቫይረሱን ስርጭት በመከላከሉ ረገድ ያከናወኗቸው ስራዎች የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል ።
የዓለም አብያተ ክስርስቲያናት ምክር ቤት ፀሃፊ በበኩላቸው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ  ጳውሎስ ለዓለም ሰላም የሰሩና የአመራር ብቃታቸውንም ብዙዎች አርዓያ የሚያደርጉት መሆኑን ተናግረዋል ።
በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቡነ ጳውሎስ ከ1985 ዓመተ መህረት ጀምሮ የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አምስተኛ ፓትሪያሪክ  ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል ።
በ1999 ዓመተ ምህረት በብራዚል በተካሄደው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጉባኤ ላይም የምክር ቤቱ ሰባተኛ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል ።
ቅዱስነታቸው በህይወት ቆይታቸው በኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩል የግብረ ሰናይ ተግባራትን ፈፅመዋል።
በተለይም በጦርነትና  በድርቅ የተፈናቀሉ  ኢትዮጵያውያንን መልሶ በማቋቋሙ ረገድ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር ።
ለአፍሪካውያን  ችግሮች  አፍሪካዊ  መፍትሄ  መፈለግ በሚል  መርህም  ብፁዕነታቸው  ወደ  ሱዳን በማቅናት  ለዳርፉር ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት ሰርተዋል።
ቅዱስነታቸው ከሃምሌ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ 20ኛ አመት በአለ ሲመታቸውን ሲያከብሩ ቆይተዋል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር