‹‹መለስን መተካት ከባድ ነው››


ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
‹‹የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል አደራ››
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኑዛዜ

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕልፈት ምክንያት በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲሠሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹መለስን መተካት ከባድ ነው›› አሉ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል ግን አዲሱ አመራር ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ትናንት አመሻሽ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደ ሻማ ቀልጠዋል፤›› ብለዋል፡፡ ላለፉት 38 ዓመታት በሰው ልጅ ታሪክ የሚጠቀስና በብቃት የሚፈለግባቸውን መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማው ተናግረው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘለዓለም በታሪክ ሊዘክራቸው የሚገባ መሪ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡ በእሳቸው አመራር የተገኘው ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማስቀጠል አዲሱ አመራር ቃል ኪዳን የሚገባበት ፈታኝ ጊዜ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

‹‹በእሳቸው አመራር የተጀመረው የአመራር መተካካት ሒደት አይደናቀፍም ወይ?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ሒደቱ በጥናት ላይ የተመሠረተና በኢሕአዴግ ውስጥ ሙሉ መተማመን ላይ የተደረሰበት ስለሆነ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መሞት የሚደናቀፍ አይሆንም በማለት፣ በእሳቸው ጊዜ የተጀመረው የአዲሱ ትውልድ የአመራር መተካካት በብቃት እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

በማገገም ላይ ሳሉ ከአራት ቀናት በፊት ኢንፌክሽን አጋጥሟቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ እስኪወድቅ ድረስ በስልክ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር በተደጋጋሚ መገናኘታቸውን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የሚናገሩት በሙሉ ሥራ እንዴት እየተከናወነ እንደሆነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሥራ የተገዙ ሰው ነበሩ›› በማለት፡፡ በመጨረሻም አሁን የተነደፈው የኢትዮጵያ መንግሥት የልማት ስትራቴጂ እንዲቀጥልና አዲሱ ትውልድ ይህንን ተግባራዊ እንዲያደርግ ማነሳሳት እንዳለባቸው ከተናገሩዋቸው ኑዛዜዎች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል አደራ ማለታቸውን በማስታወስ፣ ‹‹እኛም ለዚህ እጃችንን የሰጠን ነን፡፡ አደራቸውን ከግብ እናደርሳለን የሚል እልህ በአመራሩ ላይ ሰፍኗል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ግለሰብ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ቦታ ተክተው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ምን ያህል ዝግጁ መሆናቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹መለስን የመሰለ ከፍተኛ የአመራር ብቃትና ክህሎት ያለው ሰው መተካት ከባድ ነው፡፡ ሆኖም እሳቸው ጥለውልን ያለፉትን መሠረት ተከትሎ አመራሩ ሚናውን መጫወት ይችላል ወይስ አይችልም ነው ጥያቄው፡፡ በዚህ መሠረት አመራሩ እንደ ቡድን ከምንጊዜም በላይ በእልህና በብቃት አመራሩን ለመቀጠል ዝግጁ ነው፤›› በማለት የኢሕአዴግ ውስጣዊ አመራር በአንድነት የፀና መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእኛ የሚጠብቀውን መስዋዕትነት ለመክፈልም ዝግጁ ነን፡፡ ሕዝባችን ከጎናችን እንደሚሰለፍም እርግጠኞች ነን፤›› በማለት አመራሩ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር