የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር እስከሚፈጸም ድረስ በመላው አገሪቱ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሆኖ ይቆያል


አዲስ አበባ ነሐሴ 15/2004 የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር እስከሚፈጸም ድረስ በመላው አገሪቱ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሆኖ እንደሚቆይ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ገለጹ።
በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሠረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አገሪቱን የመምራት ኃላፊነት መረከባቸውን ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሥርዓተ ቀብርን የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን አስታውቀዋል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር እስከሚፈጸም ድረስ በመላው አገሪቱ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሆኖ ይቆያል።
"ዛሬ ለኢትዮጵያ አሳዛኝ ቀን ነው። ላለፉት 21 ዓመታት አገሪቱ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓትና የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታመጣ ያስቻሏትን ታላቅ መሪዋን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አጥታለች።" ብለዋል አቶ በረከት።
በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሠረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አገሪቱን የመምራት ኃላፊነት መረከባቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክር ቤት /ኢህአዴግ/ ጠቅላላ ጉባዔ በሚካሄድበት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ የሚደረግ ሲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፓርቲውንና የመንግስትን ኃላፊነት ይዘው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በተቀመጠው የአምስት ዓመት የአዲስ አመራር የመተካካት ሥርዓት መሠረት የአዲስ አመራሮች ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክር ቤት /ኢህአዴግ/ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚከናወን አመልክተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የሚፈጠር ምንም አዲስ ነገር እንደማይኖር የገለጹት አቶ በረከት ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ራዕይን ለማሳካት ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት ከምንጊዜውም በላይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር