ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

 ማክስኞ, 21 ንሐሴ 2012


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣

የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባላትና መላ የትግላችን ወደጆች

በዛሬው እለት ድርጅታንን ገና ከውልደቱ በመምራት ለታላቅ ሀገራዊ ለውጥ ያበቃንና በሀገራችን ታሪክ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስቻለንን ታላቁ የድርጅታችን መሪ ጓድ መለስ ዜናዊ ለህልፈተ ሕይወት በመብቃቱ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰማውን ከፍተኛ ሀዘን ይገልጻል፡፡ ዛሬ በእርግጥም ድርጅታችንና መላ የሀገራችን ህዝቦች ታላቁን የለውጥ መሪያችንን ተነጥቀናል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በድርጅታችን ሊቀመንበር በጓድ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማውን ልባዊ ሃዘን እየገለጸ ለመላ የሀገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላት እንዲሁም ለመላ ቤታሰቦቹ ከፍተኛ መጽናናትን ይመኛል፡፡

የድርጅታን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ገና ከውልደቱ አመራር እየሰጠ ለዚህ ያበቃው ኢህአዴግና መላ አባላቱ በድርጅታችን ታላቅ መሪ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ከፍተኛ ምሬትና ሃዘን የሚሰማን ቢሆንም በታላቁ መሪያችን አኩሪ ስራና ጥሎልን ባለፈው ትክክለኛና የጠራ የትግል መስመር ፀንተን በመታገል ራዕዩን እውን ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት መነሳታችንን እንገልጻለን፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣
የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባላትና መላ የትግላችን ወዳጆች

የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ከምንም ነገር በላይ የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና እነዚህን ተግባራዊ የሚያደርግ ጠንካራ ድርጅትና መንግስት በመገንባት የሚያምንና ይህንኑም በተግባር ላይ ያዋለ ፅኑ የህዝብ ልጅ ነበር፡፡ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን በእውቀትና በዘመናዊ መንገድ ብቻ መምራት እንደሚቻል አውቆ ሁሌም ራሱን ለማስተማርና በጥረቱም ያካበተውን እውቀትና ልምድ ኢትዮጵያን ለመለወጥ በከፍተኛ የትግል ፅናት ተግባራዊ ያደረገ ታላቅ መሪ ነበር፡፡ ከድህነትና ከመሃይምነት በላይ ጠላት የለም ብሎ የሚያምነው ጓድ መለስ ዜናዊ እድሜውን በሙሉ ድህነትን፣ መሃይምነትንና ኋላቀርነትን ሲፋለም ኖሯል፡፡ ድህነት የሚረታው በጠራ የትግል መስመር እየተመሩ በመታገል ነው ብሎ በማመን ድርጅቱን ጥራት ያለው የትግል መስመር ባለቤት ያደረገ ታላቅ የለውጥ ሐዋርያ ነበር፡፡ የመሃይምነት ተራራ የሚናደው በትምህርት ጥይት ነው ብሎ በማመን በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርትን ወደር በሌለው ደረጃ ያስፋፋ ታላቅ የህዝብ ልጅ ነበር፡፡

ታላቁ የድርጅታችን መሪ ጓድ መለስ ዜናዊ ድርጅታችን በየምዕራፉ ያጋጠሙትን ፈተናዎችን ሁሉ በብስለትና በፅናት እንዲያልፍ ያስቻለ በሳልና አርቆ አስተዋይ መሪ ነበር፡፡ በሀገራችን አምባገነናዊ አገዛዝ ተወግዶ ህዝቦች ለፍትህና ለእኩልነት እንዲበቁ በተካሄደው ትግል ጓድ መለስ ዜናዊ ብቁ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ድርጅታዊ አመራር ሰጥቷል፡፡ የደርግ መንግስት ተገርስሶ በሀገራችን የሽግግር መንግስት ከተመሰረተ በኋላ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለአዲስ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት እንድትበቃ ፣ በሌላ በኩል ከእዝ ኢኮኖሚ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ የሚደረገው ሽግግር ሰላማዊና ህብረተሰባዊ መናጋት በሌለበት አኳኋን እንዲፈፀም ለማድረግ ያስቻለ ብቁ አመራር ሰጥቷል፡፡

ጓድ መለስ ዜናዊ በሀገራችን የሽግግሩ ሂደት አብቅቶ በህዝብ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ፌዴራላዊ ስርዓት በመገንባትና የመጀመሪያውና ሁለተኛው የልማት መርሐ ግብር በተግባር ተተርጉሞ ሀገራችን በፈጣን እድገት አቅጣጫ እንድትረማመድ ውጤታማ አመራር ሰጥቷል፡፡ በመቀጠልም እኛን በመሰለ ህብረተሰብ የሚያጋጥመውን የእድገት መገታት መሰረታዊ መንስኤ በማጥናት ድርጅታችንና ሀገራችን በማያቋርጥ የተሃድሶ አቅጣጫ እንዲራመዱ በሳል አመራር ሰጥቷል፡፡ ጓድ መለስ መቼም ቢሆን ከትምህርት የማይቦዝነውን ብሩህ አእምሮውን በመጠቀም ሀገራችን ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያረጋገጠችውን ፈጣን እድገት በመሃንዲስነትና በቀያሽነት ብቻ ሳይሆን ሰርቶ በሚያሰራ ብቁ አመራር ተግባራዊ ለማድረግ አስችሎናል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ታላቁ የድርጅታችን መሪ ሀገራችንን ለመለወጥ ያስችላል ብሎ ያመነበትንና ኢትዮጵያውያን ተረባርበን ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለውን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ነድፎ ለሁለት ዓመታት ያህል ከህመሙ ጋር እየታገለ ተግባራዊ ለማድረግና ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ሲረባረብ ቆይቷል፡፡

የድርጅታን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ድህነትንና ኋላቀርነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ወሳኙን ርብርብ ለዘመናት በተዘነጉት ገጠሮችና በአርሶ አደሩ አካባቢ እንዲጀመር አበክሮ አስተምሯል፣ ተግባራዊ አመራም ሰጥቷል፡፡ እነሆ ኢትዮጵያ የረሃብ ተምሳሌትነቷ ማብቃት አለበት ብሎ የተነሳው መሪያችንና ድርጅታችን ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ድህነትን ከገጠር ለመመንገል ያልተቆጠበ ርብርብ በማድረግ ኢትዮጵያ በርግጥም የዳቦ ቅርጫት የምትሆንበትን አረንጓዴ ልማት በገጠር አቀጣጥሏል፡፡ አርሶ አደሩን ከመሬቱ ለማፈናቀል የተደረጉ ጥረቶችን ሁሉ በጽናት ተፋልሞ በማሸነፍ ዛሬ የሀገራችን አርሶ አደሮች የዘመናዊ ግብዓትና ማዳበሪያ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ኑሯቸውንም ደረጃ በደረጃ እንዲለውጡ በሳል አመራር ሰጥተዋል፡፡

ጓድ መለስ ዜናዊ በከተሞችም የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ሴክተሩ እንዲነቃቃና ተወዳዳሪ እንዲሆን፣ ዜጎች ሰርተው የሚበለጽጉባት ኢትዮጵያ እንድትፈጠርና በካፒታላቸውና በእውቀታቸው ተጠቅመው በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት የሚያቀርቡ ሀገራዊ ባለሃብቶች እንዲፈጠሩ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡ ዜጎች በራሳቸው ተማመነው ከድህነት ለመውጣት በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተደራጅተው እንዲረባረቡና ለሀገራቸው ልማትና እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ መሰረት የጣለ መሪም ነበር፡፡

የመላ ኢትዮጵያውያን የዘመናት ህልም የሆነውን የአባይን ወንዝ ለኢትዮጵያ ልማት ለማዋል ባዘጋጀው እቅድና ባካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ«አባይን የደፈረ ጀግና» የሚል ስም ያተረፈው ታላቁ የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የዘመናዊ መሰረተ ልማት ባለቤት እንድትሆን ሌት ተቀን ተረባርቧል፡፡ የስልክና የኤሌክትሪክ ፣ የመኪና መንገድና የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲጀመርና እንዲስፋፋ ያስቻለ ብቁ አመራር ሰጥቷል፡፡ ጓድ መለስ ዜናዊ በሰጠው አመራር ኢትዮጵያ የድህነትና የኋላቀርነት ተምሳሌት መሆኗ እየቀረ በዓለማችን በፈጣን እድገታቸው ከሚታወቁ ጥቂት ሀገሮች አንዷ እንድትሆን አብቅቷታል፡፡

የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ በድርጅታችንና በሀገራችን ውስጥ ከተጫወተው የበሰለ የአመራር ሚና ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካ ህዝቦች ድምጽ እንዲሰማ የተሟገተ ፣ በዚህ ታላቅ የአመራር ሚናውም በመላ የአፍሪካ ህዝቦች ዘንድ ታላቅ አክብሮት ያፈራ በዓለምም ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተረፈ ታላቅ መሪ ነበር፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
መላ የኢህአዴግ አባላትና
መላ የትግላችን ወዳጆች

ጓድ መለስ ዜናዊ መታመሙ ከተሰማ ጀምሮ ስለደህንነቱ ጭንቀታችሁንና መልካም ምኞታችሁን ስትገልጹ መቆየታችሁ የሚታወስ ነው፡፡በዚህ ወቅት የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መላ የሀገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላት በመሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ለደረሰባችሁ መሪር ሃዘን መጽናትን ይመኛል፡፡

በታላቁ መሪያችን በጓድ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማን ሃዘን እጅግ ጥልቅ ቢሆንም በርሱ ራዕይና ብቁ አመራር በሀገራችን የተጀመረው የለውጥ እና የእድገት ብሩህ ተስፋ ህያው ሆኖ እንደሚቀጥል የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያረጋግጣል፡፡ በሀገራችን የተጀመረው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በላቀ ውጤታማነት እንዲቀጥል ለማድረግ ከዚህ በፊት ከታላቁ መሪያችንና ከድርጅታችን ጎን ተሰልፋችሁ አንፀባራቂ ድሎችን እንዳስመዘገባችሁ ሁሉ ዛሬም ለበለፀገችና ለዳበረች ኢትዮጵያ ግንባታ የጀመራችሁትን ተጋድሎ በፅናት እንድትቀጥሉ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባላት

መሪያችንን በማጣታችን ከፍተኛ ሃዘን ቢሰማንም እርሱ ጥሎልን ያለፈውን ጠንካራ ድርጅትና መንግስት አጥብቀን ይዘን በፅናት ራዕያችንን ለማሳካት የመረባረብ ድርጅታዊ ባህላችንን ዛሬም ተግባራዊ እንደምናደርግ እሙን ነው፡፡ የመሪያችን የጓድ መለስ ዜናዊ ራዕይ ዛሬ የመላ ድርጅታችን አባላትና የ80 ሚሊዮን የሀገራችን ህዝቦች ራዕይ ሆኗል፡፡ በፈጠርነው ጠንካራ ድርጅትና በመሰረትነው ልማታዊ መንግስት እየተመራን የድርጅታችንን መሪ ፈለግ ተከትለን የጋራ ራዕያችንን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ዛሬም በፅናት እንራመድ፡፡

የመለስና የኢህአዴግ ራዕይ ህያው ሆኖ ይቀጥላል!!
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር