መለስ ዜናዊ ሲዘከሩ

New

የኢትዮጵያን የአምስት ሺሕም ሆነ የሦስት ሺሕ ዓመታት የመንግሥትነት ታሪክን አቆይተን ከ19ኛው ምእት ዓመት ብንነሣ፣ ጎልቶ የሚታየን ለ86 ዓመታት በመሳፍንት ተከፋፍላ ለነበረችው ኢትዮጵያ “ዘመነ መሳፍንት” ማብቃቱ በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መበሰሩ ነው፡፡
በተከታታይ የመጡት ነገሥታት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አፄ ምኒልክ፣ ልጅ ኢያሱ፣ ንግሥት ዘውዲቱና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደየዘመናቸው ይብዛም ይነስ ተልዕኮቻቸውን ፈጽመው አልፈዋል፡፡

ተፍጻሜተ ዘውድ የሆኑትን የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ለመገርሰስ የተነሣውና የፈነዳውን የየካቲት አብዮትን ተከትሎ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው በወቅቱ ጥሪው “ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) በመለወጥ 17 ዓመት አገሪቱን መርቷታል፡፡ ይህ ከሆነም በኋላ ገና ሥልጣኑን በጨበጠ በመንፈቁ የትጥቅ ትግል የጀመረው የትግራይ ብሔር ድርጅት ሌሎች አጋሮቹ ከጎኑ አሰልፎ ለ17 ዓመት ያከናወነው ውጊያ በድል መጠናቀቁ ሌላኛው የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡

የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባሕሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983” ብለው ባሳተሙት መጽሐፋቸው ፍፃሜውን እንዲህ ገልጸውታል፡፡

“የኢሕዲሪ ምስረታን ያጀበው ሽብርቅና ሽርጉድ የደርግ ሥርዓት የተጠናወተውን መሠረታዊ ችግር ደብቆት ነበር፡፡ አራት ዓመትም ሳያስቆጥር፣ እንዲያ በረቀቀ ጥበብና በአያሌ ደምና ዕንባ የተገነባው ሥርዓት እንደ አሸዋ ክምር ተናደ፡፡ ደርግ ውስጥ የነበሩትን ባላንጣዎቹንና የከተሜውን ግራ ክንፍ ኃይል የሸወደው አምባገነን፣ የገጠር ሽምቅ ተዋጊዎቹን ምሕረት የለሽ የጥይት ውርጅብኝ መቋቋም አቅቶት ወደቀ፡፡ ደርግ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ብሔርተኛ አመፅ ለመግታት ከዐሥር ዓመት በላይ ተከታታይ ዘመቻዎች አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ከቶም ሳይበገሩ፣ አማፅያኑ በድል ጎዳና ግስጋሴያቸውን ቀጠሉ፡፡ መንግሥቱም ራሱን ለማዳን ለመሸሽ ተገደደ፡፡ የሻዕቢያና የኢሕአዴግ ጦርም በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. በየፊናው አሥመራንና አዲስ አበባን ለመቆጣጠር በቃ፡፡ በዚያውም የአካባቢው የኃይል ሚዛን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ቅኝቱም ወሳኝ በሆነ መልኩ ተቀየረ፡፡ ኅብረ ብሔራዊውን ተቃዋሚ ኃይል ቀደም ሲል ያስወገደው ደርግ፣ አሐዳዊ የሆነውን የፖለቲካ ባህል ላንዴም ለሁሌም ለመቀየር ቆርጦ በተነሣ የብሔርተኛ ኃይል ከታሪክ መድረክ ተባረረ፡፡”

የደርግ ሥርዓትን ያንኮታኮተው ኢሕአዴግ የተሰኘውን ግንባር በመነሻነት በ1981 ዓ.ም. የፈጠሩት ሕወሓትና ኢሕዴን ሲሆኑ በዓመቱም ኦሕዴድ ተቀላቅሏቸዋል፡፡ የግንባሩም መሪ ሆነው ድሉን ያበሰሩት፣ ለ23 ዓመታትም እስከ ሕልፈታቸው የመሩትም አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡

ከደደቢት እስከ ምኒልክ ቤተ መንግሥት

በ1966 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋኩልቲ ተማሪ የነበሩት ለገሰ ዜናዊ በወቅቱ የተፈጠረው አብዮት አቅጣጫውን በመሳቱና ደርግ ሁሉንም ጨፍልቆ ሥልጣኑን በመጨበጡ ለነፃነት ትግል ትግራይ በረሃ ይወርዳሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ሳሉ በተቋቋመው የትግራይ ብሔር ተራማጆች ማኅበር (ማሕበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) በምሕፃሩ “ማገብት” ትግል ውስጥ አልፈዋል፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፣ የዘመኑ ተሳታፊዎችም እንደሚያወጉት በአራዳ ጊዮርጊስ በ1967 ዓ.ም. መስከረም ወር ጀምሮ ይሰበሰቡ ከነበሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የያኔው ለገሰ ዜናዊ አንዱ ነበሩ፡፡

የካቲት 1967 ዓ.ም. ደደቢት ላይ ተመሥርቶ የትጥቅ ትግሉ መጀመሩን ያወጀው ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) ከጊዜ በኋላ ካሰባሰባቸው ታጋዮች አንዱ ለገሰ ዜናዊ ወደ ትግሉ ሲሰማሩ መጠርያቸውም ወደ “መለስ” ተለውጧል፡፡ ስሙም የተገኘው አዲስ አበባ ላይ ደርግ ከገደለው ታጋይ መለስ ተክሌ ነው፡፡ ተጋዳላይ (ታጋይ) መለስ እስከ 1971 ዓ.ም. ድረስ ከወታደርነት እስከ ልዩ ልዩ ክፍሎች አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገሩት የመጀመርያው ድርጅታዊ ጉባኤ ሲካሔድ ነው፡፡

የካቲት 1971 ዓ.ም. የተካሔደው ጉባኤ ድርጅቱን ከተሓህት ወደ ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) ሲለውጥ ከመረጣቸው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከልም ታጋይ መለስ ዜናዊ ይገኙበታል፡፡

ከ “ተጋድሎ” ይልቅ “ወያነ” የተመረጠበት ምክንያትም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከ1935-36 ዓ.ም. የተካሔደውን ትግል ካስተባበረው ቃል “ወያነ” ጋር ለማስተሳሰር እንደሆነ ይነገራል፡፡ የፊተኛውን ከኋለኛው ለመለየትም “ቀዳማይ ወያነ” (የመጀመርያው ወያኔ) “ካልዓይ ወያነ” (ሁለተኛው ወያኔ) የሚልም አነጋገር አለ፡፡

የተጋዳሊት (ታጋይ) የውብ ማር አስፋው “ፊኒክስዋ ሞታም ትነሣለች” የሚለው መጽሐፍ እንደሚተርከው የመጀመርያው ወያነ ተዳፍኖ አልቀረም፣ አይቀርም ለትግል ተነሡ ለማለት ዘፈኖችም ይቀነቀኑ ነበር፡፡

“ቓሎ ስንዳይ በሊዕኻዩ ቓሐርየ
ሓሺኻ እመበይ ወያነዩ ይስዓርየ”
(የስንዴ ቆሎ ሲበላ ያቅራል
ውሸትህን ነው እንጂ ወያኔ መች ይሸነፋል)
“ወርሒ ወፀት ኮኾብ ተተርኢሳ
ዓይነይ እምበይ ልበይዶ ሃሪሳ”
(ጨረቃ ወጣች ኮከብ ተንተርሳ
ዓይኔ እንደሆነ እንጂ ልቤ መች ተኛ)

በሁለተኛው ድርጅታዊ ጉባኤም በ1975 ዓ.ም የፖሊት ቢሮ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) አባል ሆነው እስከ 1981 ከሠሩ በኋላ ሊቀመንበር ሆነዋል፡፡ በዚያው ዓመት የተፈጠረው ኢሕአዴግ የተሰኘው ግንባርም ሊቀመንበር ሆነዋል፡፡ ድርሳናት እንደሚያትቱት ህወሓት በማርክሳዊና ሌኒናዊ ርዕዮተዓለም አማካይነት አብዮቱን ካላራመደ ግቡን አይመታም በሚል በ1977 ዓ.ም. በተምቤን ወርዒ ወንዝ ዳር የተመሠረተው ማሌሊት (ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ) ዋና ጸሐፊው የነበሩት ብፃይ (ጓድ) መለስ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) ውስጥ በተመሠረተውና ጓድ ታምራት ላይኔ ዋና ጸሐፊው ከነበሩለት ኢማሌኃ (የኢትዮጵያ  ማርክሲስት ሌኒኒስት ኃይል) እና ኦሕዴድም በተመሳሳይ ባቋቋመውና ጓድ ኩማ ደመቅሳ ዋና ጸሐፊው በነበሩለት ኦሜሌን (ኦሮሞ ማርክስ ሊኒናዊ ንቅናቄ) ጋር አንድነት የፈጠሩበት ኢላድአ (የኢትዮጵያ ላባደር ድርጅቶች አንድነት) ለመመሥረት አስችሏል፡፡

አንድነቱ በ1983 ዓ.ም. ባደረገው የፓርቲ መሥራች ጉባኤው የኢትዮጵያ ላብ አደሮች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢላአፓ) መስርቶ  ጓድ መለስ ዜናዊን ዋና ጻሐፊው አድርጎ እንደመረጣቸው ይነገራል፡፡ መሥራች ጉባኤው በተካሔደበት አዳራሽ ፕሬዚዲየም ጀርባ ላይ የተሰቀሱት ፎቶግራፎች የማርክስ፣ ኤንግልስ፣ ሌኒንና ስታሊን እንደነበሩ ማስረጃዎች  ይጠቁማሉ፡፡ የኢላአፓ አመራሮች የሶቭየት ኅብረቱን መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭና አመራሮቹን “ከላሾች” እና “አድሃርያን” እያሉም ይጠራቸው እንደነበር ይነገራል፡፡  በወቅቱ ይዘመሩ ከነበሩት አብዮታዊ መዝሙሮች መካከልም የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

“ዘይንዲይቦ ገቦ     (የማንወጣው ተራራ)
ዘይንሰግሮ ሩባ      የማንሻገረው ወንዝ
ፍጹም ወይኮ የለን      ፍጹም አይገኝም
ሕዝቢ’ዩ ኃይልና      መስመር ነው ኃይላችን
መስመር’ዩ ኃይልና”     ሕዝብ ነው ኃይላችን)
የሬዲዮ ሞገድ አሳብሮ በሚያሰራጨው ፕሮግራሙም ህወሓትም ሆነ ኢሕአዴግ፤ “ህዝባዊ ወያነና ነዊህን መሪር እዩ ዓወትና ናይ ግድን እዩ” (ትግላችን ረዥምና መራር ነው፤ ድል ማድረጋችን የማይቀር ነው) ብለው እንደፎከሩት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተው የምኒልክን ታላቁን ቤተ መንግሥት ተቆጣጠሩ፡፡

“የዘመናት የሕዝባችን ብሶት የወለደው ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባ ሬዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል፡፡ ጉምበት ሃያ ሺ ዘጠኝ ሞቶ ሰማንያ ሦስት ዓመተ ምሕረት” ሲል አንድ ታጋይ ድሉን አበሰረ፡፡

ቀጣዩ የትግል ምዕራፍም ቀጠለ፡፡ ኢትዮጵያን ዳር እስከዳር የተቆጣጠረው ህወሓትን፣ ኢሕዴንን፣ ኦሕዴድን፣ ኢዴመአን (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ)፣ አዴትን (አፋር ዴሞክራቲክ  ትግራይን) ያቀፈው ኢሕአዴግ ለአንድ ወር የቆየውን የኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግሥትን መሠረተ፣ ፕሬዚዳንቱም አቶ መለስ ዜናዊ ሆኑ፡፡ ከሰኔ 24 እስከ ሰኔ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ከተካሄደው የሰላምና የዴሞክራሲ ኮንፈረንስ በኋላ ከሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች (ካንዳንዶች በቀር ) የሽግግር መንግሥትን የመሠረተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቋቋም ሊቀመንበሩና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡትም አቶ መለስ ናቸው፡፡ ኅዳር  29 ቀን 1987 ዓ.ም. በጸደቀው ሕገ መንግሥት መሠረትም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ሲመሠረትና ምርጫ ሲደረግ ኢሕአዴግ በማሸነፉ ሊቀመንበሩ አቶ መለስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ በተካሔዱት ሦስት ተከታታይ ምርጫዎችም ግንባሩ በተደጋጋሚ በማሸነፉ መራሔ መንግሥት ሆነው ለ17 ዓመት ዘልቀዋል፡፡

ኢሕአዴግ መሩ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በልዩ ልዩ ዘርፎች መሠረት ልማትን በመዘርጋት ያስመዘገባቸው ስኬቶች ግዘፍ ይነሳሉ ፡፡ በዚህ ረገድ የመራሔ መንግሥቱ መለስ ዜናዊ ሚና በዐቢይነት ይወሳል፡፡ ቀደምት መንግሥታት በየአምስትም ሆነ 10 ዓመት  መሪ እቅድ ሲያወጡ እንደነበሩት ሁሉ ቀጣይ እቅዶች ቢቀጥሉም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተነደፈውና በአምና ጀምሮ በተግባር ላይ ያለው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን (ውላጤ) እቅድ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ካለው ታላቅ የሕዳሴ ግድብ ጀምሮ የተለያዩ ክልሎችን እስከሚያገናኘው የባቡር ትራንስፖርት  ዝርጋታ ቸር ወሬ እየተሰማ ነው፡፡ 2001 ዓ.ም. የገባውን ሦስተኛውን ሚሌኒየም (ሺሕ ዓመት) ተከትሎ በዋዜማው (ጳጉሜን 2000) ጎጃምንና ሸዋን በሚያዋስነው የዓባይ ወንዝ መሻገሪያ ከነበረው ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድልድይ›› አጠገብ የተገነባው ‹‹ሕዳሴ›› የተሰኘው አዲሱ ድልድይም በምረቃው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንዳሉት ‹‹የቁሳዊው ሕዳሴ›› ተምሳሌት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያለንበትን ሦስተኛውን ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) በእርሳቸው መሪነት ስትቀበል፣ ያለንበት ስምንተኛው ሺሕንም በ1501 ዓ.ም. ከተቀበሉት አፄ ልብነ ድንግል ጋር የሚሌኒየም መባቻ ታሪክ ተጋርተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሰብእና 

ኢትዮጵያ በሁለት አሠርት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያላት አገር በማድረግ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለአህጉራዊውና ለቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአሁኑ አፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ስኬት በግንባር ቀደምትነት ከተሰለፉት ይጠቀሳሉ፡፡ በተባበሩት መንግሥታትም ሆነ በቡድን 8 እንዲሁም በቡድን 20 መድረኮች ያልተሳተፉበት የአፍሪካን ድምፅ ያላሰሙበት ጊዜ የለም፡፡ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የተከናወኑት ተግባርም ጉልህ ቦታ አላቸው፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያን ጥቅም በማስጠበቅ ጽሕፈት ቤቱን ወደ ሌላ አገር ለማስወሰድ የተደረገውን ደባ በመበጣጠስም አንቱ ያሰኘ ተግባር አከናውነዋል፡፡

በሊግ ኦፍ ኔሽን (የዓለም መንግሥታት ማኅበር) በ1920ዎቹ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እነ ብላቴን ጌታ ሎሬንሶ ትእዛዝን ይዘው የተሟገቱበት፣ ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስለኢትዮጵያ ክብር ያደረጉት ተጋድሎ፣ በንጉሡ ዘመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ ለማስነሣት እነ ሊቢያ ሲጥሩ እነ አቶ ከተማ ይፍሩ ያደረጉት ተጋድሎ ዱላ ቅብብሎሹ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደርሷል፡፡ ቀጥሏል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ከተመሠረተ በኋላ መቀመጫውን በተመለከተ ከአዲስ አበባ እንዲወጣ ለማመቻቸት በቶጎው ስብሰባ (1991) የሴኔጋሉ መሪ በይደር ይታይ ላሉት አቶ መለስ የሞገቱት ሙግት አፍ ያስያዙበት ንግግራቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲናነትን እንዳታጣ አድርጓታል፡፡

“ኧረ ለመሆኑ ማንዴላን ማነው ያሠለጠናቸው? አፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ አብዮታዊው ማንዴላ በአድኃሪው ኃይለ ሥላሴ ነው የሠለጠኑት፡፡ ማንዴላ ሥልጠና ያገኙት በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሙጋቤ ከኢያን ስሚዝ ሮዲሺያ አገሩን ነፃ ለማውጣት ማን ነበር ከጎኑ? መንግሥቱ ነው፡፡ መንግሥቱ በአገር ውስጥ አምባገነንና ጨፍጫፊ ነበር፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ጉዳይ ላይ እሱም እንደ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላት ቁርጠኝነት በመንግሥታት ለውጥ ፈጽሞ የሚቀየር አይደለም፡፡ “በመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ጠረጴዛ ዙሪያ ብቻችንን ነበርን፡፡ በወቅቱ ምን እንደደረሰብን አንዘነጋውም፡፡ አሁንም ብቻችን አይደለንም፡፡ 53 የአፍሪካ አገራት ከጎናችን ናቸው፡፡ እና የአንድነትን ትርጉም ከማንም በላይ እንረዳዋለን፡፡ ሌሎች አንቀጾችን አጽድቀን ይህን ግን እንደ አንድ ውስብስብ ጉዳይ በይደር መተው በኔ አስተያየት የኪራይ ሰብሳቢነት ፍርፋሪ ነው፡፡››

ደራሲው መለስ
የትግርኛ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ረዥም ዘመን አላስቆጠረም፡፡ በወጉ በመደበኛነት ከተጀመረም ከ150 ዓመታት ጥቂት እልፍ ቢል ነው፡፡ የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ኃይሉ ሃብቱ እንደጻፉት የትግርኛ ሥነ ጽሑፍ ጀማሪ ደብተራ ፍሥሐ ጊዮርጊስ ዓብየዝጊ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከየሐው ተወላጅ ከደብተራ ፍሥሐ ጊዮርጊስ የሚቀድመው የትግርኛ መጽሐፍ ግን በ1858 ዓ.ም. በደብተራ ማቴዎስ ከግእዝ  ወደ ትግርኛ የተተረጐመውና በስዊዘርላንድ የታተመው “ወንጌል ቅዱስ ናይ ጐይታና ናይ መድኃኒትና ናይ ኢየሱስ ክርስቶስ ብትግራይ” የሚል ነው፡፡

በ19ኛው ምእት ዓመት መጨረሻ ደብተራ ፍሥሐ ጊዮርጊስ በትግርኛ ከደረሷቸው አምስት መጻሕፍት ቀዳሚው “ጦብላሕታ” ይሰኛል፡፡ በ1879 ዓ.ም. በሮማ ታትሟል፡፡ “ጦብላሕታ ብዛዕባ ወሬ መንገዲ እንካብ ጦብያ ንኢጣልያ”፣ ደራሲው ከኢትዮጵያ ወደ ኢጣልያ ስላደረጉት ጉዞ የሚያትት የጉዞ ማስታወሻ (ትራቭሎግ) ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍም የመጀመሪያው የጉዞ ማስታወሻ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡

የደብተራ ፍሥሐ ጊዮርጊስ አሠር የተከተሉ በርካታ የትግርኛ ደራሲዎች በየዘመኑ ከመረብ ወንዝ ወዲህም ከመረብ ወደዚያም ታይተዋል፡፡ አንዱ አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ ሲወለዱ “ለገሰ”፣ በወያኔነት ዱር ቤቴ ብለው ሲጋደሉ በ“መለስ” የተኩት አቶ መለስ፣ በአብዮታቸው ዘመን የጻፏቸውን ልብወለዶችም ሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሐቲቶች (ዲስኮርስ) ያሳትሙና ያሰራጩ የነበሩት “ተስፋይ የኋላሸት” በሚል የብዕር ስም ነው፡፡ ቀዳሚው ልብ ወለዳቸው  በ1977 ዓ.ም. በረሃ ሳሉ ያሳተሙትና ዳግመኛ አዲስ አበባ በ1986 ዓ.ም. የታተመው  “ምኹሕኻሕ ዘይፈል የሉ ማዕፆ” ነው፡፡ ሁለተኛው ሥራቸው ደግሞ “ገነቲና” ይሰኛል፡፡

ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተኮር ድርሳናትም ከማርክሳዊ ርዕዮት አንፃር የተነተኑባቸው ልዩ ልዩ ጽሑፎችም እንዳሰራጩ ይነገርላቸዋል፡፡ በሦስት ቋንቋዎች በአማርኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዝኛ ሲጻፉ ኖረዋል፡፡ በ1977 ዓ.ም. የጻፉት መጽሐፍም “The Eritrean Struggle: from where to where?” ይሰኛል፡፡

ስለ ኤርትራ ሕዝብ ትግል የሚያወሳ ‹‹አፈሙዝ ሕዝብ ኤርትራ ንቊልቊል አይድፋዕን›› (በዝርው ትርጉሙ የኤርትራ ሕዝብ የትግል ብረት ቁልቁል አይደፋም) ሌላው መጽሐፋቸው ነው፡፡ ልብወለዶቻቸው አቶ መለስን ከቀደምት ነገሥታት ደራስያን ከእነ አፄ ዘርአ ያዕቆብ፣ አፄ እስክንድርና ከሌሎቹ ተርታ እንዲሰለፉም አድርጓቸዋል፡፡

“ደቂቃነ ጠቢባን” [ንኡሳን ጠበብት]

እሑድ ሚያዝያ 30 ቀን 1947 ዓ.ም. በቀድሞ አጠራር ጠቅላይ ግዛት ዓድዋ አውራጃ፣ ዓድዋ ከተማ ከአባታቸው አቶ ዜናዊ አስረስና ከእናታቸው ወይዘሮ ዓለማሽ ገብረ ልዑል ሦስተኛ ልጅ ሆነው ሲወለዱ የወጣላቸው ስም ለገሰ ነበር፡፡ ከአርባ ቀን በኋላ ሰኔ 9 ቀን ክርስትና ሲነሱ ገብረ እግዚአብሔር የሚል የክርስትና ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዓድዋ ንግሥተ ሳ፣ባ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በአዲስ አበባ ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤቶች ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡ ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤትም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚረዳቸውን የገንዘብ ሽልማት (ስኮላርሺፕ) እርሳቸውን ጨምሮ ለዘጠኝ ተማሪዎች ተሰጥቷል፡፡ የሽልማቱ መጠሪያም “ደቂቃነ ጠቢባን”  [ንኡሳን ጠበብት] ይሰኛል፡፡

የሽልማት ድርጅቱ 10ኛ ዓመቱን 1966 ዓ.ም. ሲያከብር በወጣው መጽሐፍ እንደተገለጸው፣ “ልዩ ተስፋ ከተጣለባቸው ተማሪዎች ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፋካሊቲዎች በስኮላር ሺፕ ሲያስተምር በእያንዳንዱ ዓመት ቢበዛ ለአሥር ተማሪዎች እያንዳንዱ ከአንድ ሺሕ ብር የማያንስ የትምህርት አበል ይሰጣል፡፡”

መጽሐፉ የ1965 ዓ.ም. ስኮላርሺፕ አበል የተሰጣቸው ለገሰ ዜናዊን ጨምሮ ዘጠኙ ደቂቃነ ጠቢባን የጋራ ፎቶግራፍ ይዟል፡፡ ፎቶ የተነሡበት ቦታም በሽልማት ድርጅቱ ጽሕፈት ቤት በራፍ (ያሁኑ የፓርላማው ቤተ መጻሕፍት) ላይ ነው፡፡

ከግንቦት 20 ድል በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በ1988  ዓ.ም. በቢዝነስ አስተዳደር የማስትሬት ድግሪ፣ በ1997 ዓ.ም. ኔዘርላንድስ ከሚገኘው ኢራስመዝ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የማስትሬት ዲግሪና ከደቡብ ኮርያ ሃናም ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡

“ገብረ እግዚአብሔር”
ጎጇቸውን ከትግል አጋራቸው ከወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር የመሠረቱት አቶ መለስ ሦስት ልጆች ያፈሩ ሲሆን በሃይማኖታቸው የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታይ ናቸው፡፡ በክርስትና ስማቸው “ገብረ እግዚአብሔር” ተብለው በቤተ ክርስቲያን የሚታወቁት አቶ መለስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስመ እግዚአብሔርን ሲጠሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከአሜሪካ የመጣው “ኢትዮ ፈርስት” ቴሌቪዥን ድረ ገጽ ጋዜጠኛ ቃለመጠይቁን እንደፈጸመ “አመሰግናለሁ” ሲላቸው ምላሻቸው “እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ነበር፡፡ በሌላ ጊዜም የግልገል ጊቤ ቁጥር ሁለት የኃይል ማመንጫ ሲመረቅና በቴሌቪዥን ሲተላለፍ እንደታየው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንግግራቸውን ሲያበቁ “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ” ሲሉ፣ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትሩም “እግዚአብሔር ይባርካችሁ” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ገብረ እግዚአብሔር) ንግግራቸውን ያሳረጉትም ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልኝ›› በማለት ነበር፡፡

የመሪዎች ሥነ ቃል
በኢትዮጵያ ነገሥታት፣ ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ዙርያ ኅብረተሰቡ በርካታ ሥነ ቃሎች ሲናገር፣ ሲተርት፣ ሲቀልድ ኖሯል፡፡ አንዱ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ ሥልጣን ላይ በወጡ መሪዎች ላይ ከዶሮ ጋር የተያያዘው ቀልድ ነው፡፡

ዶሮዋ
ጥያቄ፡-  ዶሮዋ መንገዱን አቋረጠች ለምን?
የሀገራችን መሪዎች ሲመልሱ፡-
አፄ ቴዎድሮስ 
‹‹ይህች እብድ ዶሮ መሄድ የለመደች፣
ባታውቀው ነው እንጂ ራቴ ነበረች፤
ነይ ተመለሽ በሏት ርቃ ሳትሔድ
ነበረች ራቴ ይቺ የዶሮ እብድ››
አፄ ዮሐንስ
‹‹ማቋረጡንስ ታቋርጥ ግን ይቺ ዶሮ ተጠምቃለች?
ማተቧንስ እንዳሰረች ነበር?››
አፄ ምኒልክ
‹‹ስማኝ ያገሬ ሰው ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን እምነት ማዘለፍ ነውና ለሀገርህና ለማተብህ የምትቆረቆር ሁሉ በምትወደው ታቦት ይዤሀለሁ፤ ዶሮዋን መልሳት፤ ይህን ሳታደርግ ባገኝህ ግን  ወላዲተ አምላክ ምስክሬ ትሁን አልምርህም፡፡››
አፄ ኃይለ ሥላሴ
‹‹የምንወድህና የምትወደን ሕዝባችን ሆይ! ዶሮዋ መንገዱን ስታቋርጥ በቸልታ መመልከት የለብህም፡፡ ባንዲት ዶሮ መንገድ ማቋረጥ ምክንያት አገርን፣ንጉሥን፣ዘርን ማሰደብና ታሪክን ማበላሸት የለብህም፡፡››
ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም
‹‹ጓዶች ተደፍረናል! ተዋርደናል! ዶሮዋ መንገዱን አቋርጣለች፡፡ ይህ ደግሞ አድሃርያን አብዮቱን ለመሸርሸር አብዮታዊ ትግላችንን ለማደናቀፍ  የሸረቡት ሴራ ነው፡፡ ዶሮዋ እስክትመለስና አንድ ሰውና አንድ ጠመንጃ እስኪቀር ድረስም እንዋጋለን፡፡››
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ
‹‹በመሠረቱ ያንዲት ዶሮ መንገዱን ማቋረጥ የልማት እንቅስቃሴያችን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለ ወይ? ነው ጥያቄው መሆን ያለበት፡፡ የለም፣ ስለዚህ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላት፤ አራት ነጥብ፡፡
ስንብት 
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባደረባቸው ሕመም በየጊዜው ሕክምናቸውን  ቤልጂየም ብራሰልስ በሚገኘው ቅዱስ ሉቃስ ሆስፒታል ሲከታተሉ የነበሩት አቶ መለስ ‹‹እያገገሙ ነው›› ቢባልም ከነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ግን ማለፍ አልቻሉም፡፡ እዚያው አርፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በማግስቱ ነሐሴ 15 ቀን ሕዝቡን በቴሌቪዥንና ራዲዮ ያረዳው ባገር ባህል ወግና ልማድ መሠረት ንጋት 12 ሰዓት ላይ ነው፡፡ በምሽቱም እስከሬናቸውን የያዘው አውሮፕላን ቦሌ ደረሰ፡፡ አገር በነቂስ ወጥቶ ከል መስሎ ተቀበለው፡፡ በሠረገላ ላይ  አርፎ የነበረው አስክሬኑም ወደ መኪና ተላልፎ መኖርያቸው ወዳለበት ምኒልክ ቤተ መንግሥት (ታላቁ ቤተ መንግሥት) እኩለ ሌሊት ላይ አመራ፡፡ እሑድ ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  የሚፈጸምበትን ገብአተ መሬት እየጠበቀ ነው፡፡

ከ21 ዓመት (ሦስት ሰባት) በፊት ከለንደን ሆነው ሀገር ሰላም (ተምቤን)  ከሚገኘው ጠቅላይ ማዘዣ ጣቢያ ጋር በሳተላይት ስልክ ከተነጋሩ በኋላ በካርቱም (ሱዳን) በኩል ከአስደንጋጭ የአውሮፕላን ሞተር መጥፋት ጋር አዲስ አበባ በድል አድራጊነት ቦሌ የደረሱት አቶ መለስ ዜናዊ ወደ ማረፊያቸው ያመሩት በታንክ አጅብ ነበር፡፡ ከ21 ዓመት በኋላ ከብራሰልስ አስክሬናቸው ደርሶ ወደ ቤተ መንግሥት ያመራው በዋይታና በሙሾ፣ በፉከራና በሐዘን ዜማ ታጅቦ ነው፡፡ በአንዱ ኅሊናም የነፍስ ኄር ገጣሚና ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ‹‹ሀገሬ›› የተሰኘው  ግጥም አንድ አንጓ ተመላለሰች

‹‹ ለምለም ነው አገሬ
ውበት ነው አገሬ
ገነት ነው አገሬ፤
ብሞት እሔዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ፤
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ፡፡››

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር