ክልል ለምን?

(ከማህበራዊ መረብ ላይየተገኘ ጽሁፍ)


ለአለቆቻቸው የኖሩ ጥቂት የሲዳማ ኢህአዴግ ካድሬዎች በእነርሱ አመራር የሲዳማ ሕዝብ ኑሮ አሻሽለናል፣ ልማትና ዕድገት አምጥተናል ብለው ሕዝቡን የሚያታልሉበትን ሁኔታ ውስጥ ገብተን ስንመለከት ተቃራኒውን ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ለምሳሌ በሐዋሳ ከተማ የታየው ዕድገትና ለውጥ የሲዳማን ሕዝብ ለውጥ ያሳያል ማለት በድሀው ሕዝባችን ማላገጥ ነው፡፡ ልመና ነውር የሆነበትን የሲዳማን ባህል፣ ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖበት በከተማው እየተበራከተ የመጣውን የሲዳማ ለማኝ መቁጠር ይቻላል፡፡ የሕዝባችንን ዕድገትና ኑሮ ለማወቅ እነዚህን በልመና የተሰማሩ ወገኖችንና በከተማው የተበራከቱ የሲዳማ ጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን ታርክ እንዲሁም ከከተማው ዙርያ ጀምሮ የገጠሩ ሕዝብ ያለበትን የኑሮ ሰቆቃ ማየት ይበቃል፡፡ ሲዳማ ከ90% በላይ በገጠር የሚኖር ሕዝብ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ከሕዝቡ ቁጥር መጨመር ጋር የመሬት ጥበት እና የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ በልቶ ለማደር፣ ልጆቹን ለማስተማር እንዲሁም አስፈላጊውን ቁሳቁስ ለመግዛት ከዋጋ ንረት የተነሳ ለሕዝቡ የሚቀመሱ አልሆኑም፡፡ 60 ከመቶ የሚሆነው ሕዝባችን ከድህነት ወለል በታች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 20 ከመቶው ራሱን መመገብ የማይችል ሲሆን የቀረው ድሀው ሕዝብ በቀን ከአንድ ዓይነት ምግብ (ደረቅ ዋሳና ቅጠላቅጠል) በመመገብ በዚህ ዓለም ኑሮውን ለማርዘም የሚጥር ነው፡፡
በሃዋሳ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪ ቤተሰብ


ዕድገት ማለት ሁለንተናዊ እና ሕዝቡን ያማከለ እንጂ የጥቂት ሰዎች (በስልጣን ላይ ያሉት፣ የት/ት ዕድል አግኝተው በከተሞች የተሻለ ስራ ያላቸውን እንዲሁም እጅግ ጥቂት ነጋዴዎችን) ኢኮኖሚ መዳበር አይደለም፡፡ ሕዝቡ ከድህነት ወለል በታች ባለበት፣ የምግብ ዋስትና ባልተረጋገጠበት፣ ሕጻናት በምግብ እጥረት በየቀኑ የሚሞቱበት፣ እንዲሁም ከአብራኩ የወጡ ካድሬዎች የኢህአዴግ ፓለቲካ ጠባቂ እንጂ ለሕዝቡ ያልቆሙበትን (መብቱን የጠየቀውን እስከመግደል የሚያዙበትን) አመራር ይዘን ሕዝቡን እንለውጣለን ማለት ዘበት ነው፡፡ የሲዳማ ህዝብ በታሪኩ ለረሀብ የተጋለጠው በዚህ አገዛዝ ዘመን መሆኑን አንዘንጋ፡፡ አረንጓዴው ረሀብ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነና በሲዳማ ብቻ የተከሰተ እንደሆነ የቢቢሲ ዘጋቢ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሲናገር ተሰምቷል፡፡ ዘጋቢውን የገረመው ነገር ቢኖር በሐዋሳ ከተማ ያለውን ሕዝብ አይቶ በጥቂት ኪሎ ሜትር ለዚያውም አረንጓዴ በሆነ ምድር በረሀብ ሕጻናት ይሞታሉ ብሎ ማሰብ ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ሲናገር በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡

የኢኮኖሚ አቅም ላለውም ሆነ ለሌለው ሕዝብ ትምህርት ለዕድገት መንገድ ከፋች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በዚህም በኩል ያለው ሁኔታ አንገት የሚያስደፋ እንደሆነ መመልከት እንችላለን፡፡ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ የሲዳማ ዞን ከአገሪቱ በመጨረሻና በዝቅተኛ ደረጃ ያለ እንደሆነ በቂ መረጃ አለ፡፡ ለሪፖርት ትምህርት ቤት ተከፈተ ለማለት ካልሆነ በስተቀር ለት/ት ጥራት ምንም ስላልተሰራ ሲዳማ ያልተማሩ ‹የ10ኛ ክፍል ትምህርት የጨረሱ› ወጣቶች የበዙበት ሆኗል፡፡ የት/ቱ ጥራት ዜሮ ስለሆነ 90 ከመቶ የተማሩት ተማሪዎች ተወዳዳሪ ስላልሆኑ በአብዛኛው ገጠር የ8ኛን ክፍል ሚንስትሪ የሚያልፈው 10 ከመቶ አይሆንም፡፡ መምህራን ተቸግረው መልስ ስለሚሰሩላቸው የውሸት ውጤት ይዘው ራሳቸውን መግለጽ የማይችሉ የ10ኛን ብሔራዊ ፈተና ይፈተናሉ፡፡ 10ኛ ክፍልም 80 ከመቶ የሚሆኑ ልጆች ያለዕድሜ ትምህርታቸውን ተቀጭተው በመቅረት የአገር ሸክም ይሆናል፡፡ ይህንንም ቤቱ ይቁጠረው፡፡ 

እንደ ትግራይ ያሉ ክልሎች ነጻ ወጥተው በነጻ ማሰብ የሚችሉበትን መንገድና ስልጣን ስለዘረጉ በትምህርት ጥራትና ብዛት ብዙ ሰርተው በተሸለ መንገድ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፣ ‹የኛዎቹ› ደቡብ ሳንሆን እንደክልሉ ሁሉ በአቅጣጫ ስም የተሰየመውን የዩኒቨርስቲውን ስም ለመቀየር ወኔው ስላልነበራቸው ረጅም ጊዜ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ከ30 ዓመት በፊት የደርግን መንግስት ለመፋለም የራሱ ራድዮና ተሌቭዥን ከሞቃድሾ የነበረውን የሲዳማን ሕዝብ ያ እንኳን ቢቀር በከተማው በቋንቋው FM ራድዮ እንዳይኖር በማድረግ ሲዳማ ማለት በአካባቢውም ሳይቀር minority እንዲሆን ከአለቆቻቸው ጋር ተባብረው አደረጉት፡፡ በሐዋሳ የሚገኘውን የአማርኛውን FM ራድዮ የሐዋሳ FM ብሎ ለመቀየር ምናልባት ሲዳምኛው ይገባል ብለው ስለፈሩ ይመስላል ደቡብ ሳይሆን ደቡብ ብለው ጸንተዋል፡፡ ለማለት እንኳንሕዝቡ እራሴን በራሴ እንዳስተዳድር ይፈቀድልኝ ሲል የዛሬ 10 ዓመት በጠራራ ጸሐይ ዓለም ጉድ እስኪል ድረስ ከ50 ሰዎች በላይ ፈጁ፡፡ በዚህ ጭፍጨፋ ሁለት የሚገርሙና ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አሉ፡፡-1ኛ/ ‹የኛዎቹ› በሕዝብ ተመርጠናል ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ካድሬዎች ሰላማዊው ሰው ሲጨፈጨፍ አለመቃወማቸው 2ኛ/ መንግስትም አንዱን ወታደር እንኳን ተጠያቂ አለማድረጉ ለሕዝቡ ያለውን ንቀት ያሳያል፡፡

በሲዳማ ያለው ግን የተገዢነትና በራሱ ምድር ሁለተኛ ዜጋ በመሆን የሌላውን አመራር የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ በራሱ ከተማ ባሉት ተቋማት እንኳን የደህዴን ካድሬዎችና ጠባቂዎች በቋንቋውና በማንነቱ የሚያፍር ሁለተኛ ዜጋ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ በኢህአዴግ የመጀመሪያ አገዛዝ ዘመን የነበረው የአካባቢው ባህልና ቋንቋ መነቃቃት በአሁኖቹ ደህዴን ካድሬዎች ግብአተ መሬት ተፈጽሞለታል፡፡ ሰው በሌላው ተጽዕኖ ስር ሲሆን በራስ መተማመን ስለማይኖረው በራሱ ከመቆም ይልቅ ሌላውን ለመምሰል ወይም ለማስመሰል ይጥራል፡፡ ለአብነት ያህል ወደሐዋሳ በሄድኩ ጊዜ ወደ 2 ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ወደ አንድ ኮሌጅ ሄጄ እዚያ የምትማረውን እህቴንና ጥቂት የሲዳማን ተማሪዎች ቃለመጠይቅ አድርጌ ነበር፡፡ በገዛ ምድራቸው የሲዳማ ልጆች በቋንቋቸው ለመናገር የሚያፍሩበት ሲሆን በተቃራኒው የኦሮሞ ልጆች በልበ ሙሉነት ቋንቋቸውን የሚናገሩበት እንደሆነ አይቼ ያዘንኩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የኛዎቹ በኛ ስም የተሾሙ፣ በአለቆቻቸው በኩል ስልጣናቸውን ለማረዘም የሚተጉ፣ የዴህዴን ካድሬዎች ሕዝቡ በገዛ አገሩ ቋንቋውን እንዲያቀጭጭና አንገቱን እንዲደፋ አድርገውታል፡፡ እነርሱ በስልጣን ላይ ያሉት ይህንን ሕዝብ ወክለው በቋንቋውና በሲዳማነት እንደሆነ የዘነጉት ይመስላል፡፡ 

በአጠቃላይ ክልል አያስፈልገውም የሚሉት ‹የኛዎቹ› ባለስልጣናት በአንድ በኩል ከላይ ያሉትን አለቆቻቸውን ለማስደሰት፣ በሌላው ጎን የራሳቸውን ኑሮና ሁኔታ እየተመለከቱ የሕዝቡን ነባራዊ ሁኔታ የሚያዩበት ዓይን ስለሌላቸው ይሆናል፡፡ እነርሱ የክልልን ጥቅምና ጉዳት ይነግሩናል፡፡ ከላይ እንዳሉት አለቆቻቸው የተማረና አማራጭ የሚያቀርቡ የሲዳማ ተወላጆችን ከተቻለ በማባረር ካልተቻለም ስራ ቀይረው ከፖለቲካውና ከመንግስት ስራ እንዲወጡ በማድረግ ተሳክቶላቸዋል፡፡ የሕዝቡን ድምፅ ያስተጋቡትን ተባርረው አልቀው የቀሩትን ጥቂት የተማሩ የሲዳማን ልጆች ማሰር ለሕዝቡ ማሰብ ይሁን ሕዝቡን ማዳከም ታሪክ የሚገልጠው ይሆናል፡፡ እነርሱ እራሳቸው መልሰው ክልል ለመሆን አሁን እየተማረ በቂ ሰው የለንም፣ በባጀት እጥረት እንጎዳለን ወዘተ ይሉናል፡፡ ክልል ስለሆነ የሲዳማ ህዝብ በሌላው ላይ ተነስቶ ልማቱን ያበላሻል ብለውም የሚያስቡ አሉ፡፡ ሕዝቡ ከታሪክ እንዳየነው ሌላውን የሚያከብርና በፍቅር የሚይዝ እንጂ ሌላውን ለመጉዳት የሚነሳ አይደለም (ምንም እንኳን ይህንን የሕዝቡ ጨዋነት ለገዢዎች መጠቀምያና ለሕዝቡ ጭቆና መሳሪያ ቢሆንም)፡፡ ክልል አለመሆን ጥቅም ካለው ታዲያ ለምን ትግራይና ሌላው ራሱን ችሎ ክልል ስለሆነ ተጎድቷልና ከሌላው ጋር ሆኖ የሰሜን ብሔር ብሔረሰቦች ክልል እንዲባል ለኢህአዴግ ሐሳብ አያቀርቡም፡፡ በሌላው ጠርዝ ላይ የቆሙ ቢወዱም ባይወዱም የሲዳማ ሕዝብ በስርዓት የሚኖር የተከበረና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ይሆናል፣ ጥቂት የደህዴን ካድሬዎች እባካችሁን አመለካከታችሁን መቀየር ካልቻላችሁ እናንተ ዘወር በሉና ሕዝቡ ክልል መሆን እንደማይችል፣ ራሱን ማስተዳደር እንደማያውቅ፣ እና እናንተ የምትሉት ትርፉ ጉዳት ብቻ እንደሆነ ታያላችሁ፡፡

ድል ከምንልክ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ለተጨቆነው ሕዝብ!

አዲሱ ከአዲስ
http://www.facebook.com/addisu.getachew.7

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር