የቡና ዋጋ ቅናሽ ማሳየት እያነጋገረ ነው



ቃልዲ በኢትዮጵያ ምድር የገዘፈ ታሪክ ባለቤት ነው፡፡ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ይሆናል። ከከፋ መንደር ፍየሎች ጥዑም ፍሬን አገኙ። የመንጋው እረኛ ብላቴናው ቃልዲ ከዛን ዘመን ጀምሮ ስሙ በታሪክ ማኅደር ሰፈረ። ምክንያት የሚያግዳቸው ፍየሎች ለሀገሬውና ለዓለም ሕዝብ ቡናን በማሳወቃቸው ነው። ምስጋና ለእነርሱ ይሁንና ይኸው ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ከጥዑም ቡናዋ እረኛው ቃልዲም ከታላቅ ስሙ ጋር ተቆራኝተው ለዘመናት መዝለቅ ችለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ሰባት ታዋቂ ቡና አምራች ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉርም በዘርፉ የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳለች። በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ሰፊ ድርሻ ያለው ቡና ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ የጀርባ አጥንት ነው። ከሌሎች የግብርና ምርቶች ቡና ከአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች አልፎ ለበርካታ ሀገራት በመቅረብም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያለተቀናቃኝ በአውራነት ሊዘልቅ ችሏል።
ኢትዮጵያ ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ ለባህር ማዶ ገበያ ያቀረበችው በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር 1838 በምጽዋ ወደብ በኩል እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለት የቡና ዓይነቶችን ( ሐረር እና አቢሲኒያ) ለንደንን ጨምሮ ወደ ኒውዮርክ እና ማርሴል ከተሞች በመላክ የኤክስፖርት ንግዱን ተያያዘችው።
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኤክስፖርት ግብይት በአሁኑ ወቅትም በጥራት እና ብዛት ዕድገት እያሳየ ዘልቋል። ሆኖም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚፈጠሩ የተለያዩ መሰናክሎች ሳቢያ አርሶ አደሮች የጥረታቸውን ያህል ተጠቃሚ ነበሩ ለማለት ያዳግታል።
ከፍተኛ የቡና ምርት መገኛ እንደሆኑ በሚነገርላቸው የተለያዩ አካባቢዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት መመሥረትን ተከትሎ አርሶ አደሩ ከምርቱ ተጠቃሚ በመሆን በኩል ለውጦች መምጣት ጀመሩ። ይሁንና ማኅበራቱ ያስተናግዱ ከነበረው ውስጣዊና ውጪያዊ ተጽዕኖዎች መላቀቅ አለመቻላቸው ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት ሊሆን ችሏል። ለእዚህ ደግሞ እንደ አመራረት ሥርዓቱ ሁሉ የግብይት ሰንሰለት አብሮ አለመዘመን ለችግሩ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። 
ከአራት ዓመት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በቡና እና ሌሎች የቅባት እህሎች ላይ ያለውን የወጪ ንግድ በበላይነት ለማሳለጥ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥራ መጀመር ለዘርፉ ተጠቃሚነት ዳግም ትንሳዔ ሆኗል። የድርጅቱን መቋቋም ተከትሎ የሀገር ውስጥ አምራቾች ገቢ ከማደጉም በላይ ለዘርፉ መጐልበት በምክንያትነት ይጠቀሳል። ያደጉት አገራትን ዘመናዊ የግብይት ሰንሰለት መሠረት አድርጐ መቋቋሙ ፍትሐዊ የገበያ ድባብ እንዲሰፍን አድርጓል። የባህር ማዶ ገበያ ፍላጐት መሠረት አድርጐ በሰፊው መንቀሳቀሱ ለውጭ ምንዛሪ መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል። ለእዚህ ደግሞ በአገር ውስጥ የነበረው የቡና ዋጋ በእጅጉ መናር ለለውጡ ማሳያ ይሆናል።
ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ ባለው ንቁ ተሳትፎ የአገር ውስጥ አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ዋጋን ማግኘት ችለዋል። ነገር ግን ከጥቂት ወራት በፊት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የተፈጠሩ መንገራገጮች እንደዘርፍ የቡናንም ገበያ ሳይገዳደሩት አልቀሩም። በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊ ዕውነታ አንዱ ችግር እንደሆነ ቢገለጽም በተጨማሪ ለቡና ገበያ መዳከም በአገር ውስጥ ያሉ የዘርፉ አካላት የሚያነሷቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ለቡና ዋጋ መውረድ የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቅሱም የቡና ላኪ ማኅበራት እና አርሶ አደሮች ዛሬም የቡና ዋጋ ዳግም ማንሰራራት ጉዳይ የማያባራ ጥያቄያቸው ሆኗል።
በደቡብ ክልል የሚገኘው የፌሮና አካባቢው መሠረታዊ ማኅበር ቡናና ሌሎች ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ያቀርባል። ማኅበሩ ከአባላቱ የሚሰበሰበውን ቡና በቀጥታ ወደ ምርት ገበያ በመላክ ለቡናው ደረጃ ያስወጣለታል። በተጨማሪም የአረቢካ ቡናን ለሲዳማ ቡና ዩኒየን ያስረክባል። ቀደም ሲል ከነበረው የቡና ዋጋ ከአሁኑ ገበያ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ዋጋው መውረዱን የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን ጋርሳሞ ያስረዳሉ።
ሊቀመንበሩ እንደሚሉት ቀደም ሲል አንድ ፈረሱላ ( 20ኪሎ) አንድ ሺ 400 ብር በመግዛት ወደ መጋዘን ቢያስገቡም ለገበያ ሊያቀርቡ በተዘጋጁበት ወቅት ግን የዋጋ መውረድ እንደተከሰተ ይገልጻሉ። ይኸውም ሁለት መቶ ብር ቅናሽ በማድረግ አንድ ሺ200 ብር ድረስ መሸጣቸውን ያስታውሳሉ። ለቡና ዋጋ መውረድ ደግሞ አቶ ጥላሁን እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ከብራዚል የሚመጣ ምርት መጨመር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በጥርጣሬ ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን በግላቸው ለዋጋ መውረዱ የተጨበጠ ምክንያት አላገኙም።
እ.ኤ.አ በ2012 ሐምሌ ወር ላይ የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። ካለፈው ወራት ጋር ሲነፃፀርም በ9 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው የወጪ ንግድ 9 ነጥብ 11 ሚሊዮን ከረጢት ሲሆን ፣ አሁን ወደ 9 ነጥብ 58 አድጓል። ይህ አኀዝ ከዓመት በፊት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ተከታታይ ወራት ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮው ዓመት 0ነጥብ 3 በመቶ መቀነስ አሳይቷል። 
ይህ ማለት 81 ነጥብ 41 ሚሊዮን ከረጢት የነበረው አጠቃላይ ወጪ ንግድ ወደ 81 ነጥብ 16 ሚሊዮን ከረጢት ዝቅ ብሏል። በአጠቃላይ እ.ኤ.አ በ2011 ደግሞ 68 ነጥብ 76 ሚሊዮን ከረጢት የነበረው የአረቢካ ቡና ሽያጭ ዘንድሮ ወደ 64 ነጥብ 48 ሚሊዮን ቅናሽ አሳይቷል። ሮቡስታ በበኩሉ በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ39 ነጥብ 98 ሚሊዮን ከረጢት ሽያጭ ወደ 37 ነጥብ05 ሚሊዮን አሽቆልቁሏል።
ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው አረቢካ ቡና ታዋቂ መሆኑን የሚገልጹት የዳሞታ ወላይታ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተከተል ታደሰ ናቸው። ነገር ግን አገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች አለመሆኑን ያስረዳሉ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያጋጠመውን ሁኔታ ሲገልጹም ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተወዳዳሪነት ጋር ተያይዞ በኒውዮርክ ገበያ የተፈጠረ ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው፡፡ በመሆኑም እንደእርሳቸው ሃሳብ እውነታው በኢትዮጵያ ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው። 
«...የዓለም ቡና አቅራቢዎች የምርት ጫና ፈጥረዋል። ይሄም ከፍላጐት በላይ ክምችት እንዲኖር ሆኗል» በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ በሆነ ጥናት ብራዚል በአረንጓዴ ቡና ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ናት። ቬትናም፣ ኢንዶኔዥያ እና ኮሎምቢያ ቀጣዩን ሥፍራ ይይዛሉ። «ኢትዮጵያ የቡና ምርት በርካታ ተወዳዳሪ ሀገራት አሏት፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ ጥሩ የቡና ጣዕም ባለቤት መሆኗ ጫናውን ተቋቁማ መቆየት አስችሏታል» ይላሉ። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቡና ላኪዎች ማኅበር አባል። እንደእርሳቸው አባባል ይሄን የቡና ጣዕም ለመጠበቅ ከአርሶ አደሩ ምርት አሰባሰብ ጀምሮ እስከማቆያ መጋዘን ድረስ ያለው ሂደት ግብርና ሚኒስቴር ባወጣው መስፈርት ማለፍ አለበት።
አስተያየት ሰጪው የዋጋ ልዩነትን በተመለከተም ቡና ገዢ ድርጅቶች ለየአገራቱ የሚሰጡት ደረጃ መኖሩን ያነሳሉ። በመሆኑም የደረጃ አሰጣጡ ቀጣይነት ያለው የጥራት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ መሆኑ እስከኒውዮርክ ገበያ ድረስ ያለው ቅብብሎሽ ጥንቃቄን ይፈልጋል ይላሉ። አርሶ አደሩ ምርቱን ሲሰበስብ ሲፈለፍል እና ሲያጥብ ባለው ጊዜ የጥራቱን ኃላፊነት መውሰድ ይገባዋል። ቡና ላኪዎች / ኤክስፖርተሮች / በበኩላቸው በመጋዘን እና በጉዞ ወቅት ላለው ጥራት ቁጥጥር ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ባይ ናቸው አስተያየት ሰጪው። 
«... ይህ ካልሆነ እኛ ደረጃ ሁለት የሰጠነው ቡና ባህር ተሻግሮ ደረጃ አራት መሆኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ ዘርፉን ያቀጭጨዋል» የሚል እምነት አላቸው።
በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን አገር ውስጥ ያለውን የቡና ምርት በማቀነባበር እና ማጓጓዝ ገቢውን ፍትሐዊ ማድረግ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪው ያስረዳሉ፡፡ «... ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ቡና ከማጓጓዝ ይልቅ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ማድረስ ይቀላል። እንደ ኤክስፖርተር ከየክልሉ የምናደርገው የቡና ሸመታ ጫናውን ከፍተኛ አድርጐታል» ይላሉ፡፡ በማጓጓዝ ሂደት ውስጥ የትራንስፖርት ባለቤቶች ብቻ መወሰናቸው ችግሩን ይበልጥ እንዳናረውም ያስረዳሉ። ቡና በዓለም ደረጃ ዋጋ ይቀንስ እንጂ በሀገር ውስጥ አሁንም ለኤክስፖርተሮች የማይቀመስ እንደሆነ ይናገራሉ። 
የዓለማችን የቡና ገበያ ማዕከል ኒውዮርክ ከተማ ነች። የተለያዩ አገራት ቡናዎችም በእዚችው የግብይት ማዕከል እንደጥራታቸው ደረጃ ዋጋ ይቆረጥላቸዋል። የአውሮፓዊቷ አገር ጀርመን ከተማ ሀምቡርግ በበኩሏ በወደቧ አማካኝነት የዓለማችን ግዙፍ የቡና ምርት ማስተላለፊያ በመሆን ትጠቀሳለች። ኢትዮጵያም ወደእነዚሁ የግብይት አካባቢዎች ምርቷን በመላክ ጉልህ ተሳትፎ ከሚያደርጉት አገራት መካከል አንዷ ነች።
የግብይት ሰንሰለቱን በማሳለጥ በኩል ኃላፊነቱን የሚወስደው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነው። ምርት ገበያው በዋናነት ከሚያገበያያቸው ምርቶች ውስጥ ቡና፣ ሰሊጥ እና ነጭ ቦሎቄ የሚጠቀሱ ናቸው። በእዚህ ዓመት ብቻ በአጠቃላይ ወደ 600 ሺ ቶን የሚመዝን የተለያዩ ምርቶችን ማገበያየት ተችሏል። ከእዚህ ውስጥ ደግሞ ቡና 38 በመቶ ወይንም 227 ሺ ቶን አካባቢ የሚደርሰውን ይይዛል። በመሆኑም ለቡና ዋጋ ወቅታዊ ጉዳይ ቀጥታ የሚመለከተው ተቋም ነው።
በእዚህ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ሸማቾች ፍላጐት መቀዛቀዝ መኖሩን የሚነግሩን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ዋና የኦፕሬሽን ሥራ ኃላፊ አቶ አንተነህ ምትኩ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት መቀዛቀዙን ተከትሎም የዋጋ ከፍተኛ የቡና ዋጋ መውረድ ተስተውሏል።
«... ከዓለም አቀፍ ገበያ አኳያ ቡና ከ2004 ዓ.ም መስከረም ወር ጀምሮ የዋጋ መውጣትና መውረድ ቢታይበትም በተለይ ሰኔ ወር ላይ የቡና ዋጋ ቅናሽ አሳይቷል» የሚሉት አቶ አንተነህ፤ ለክስተቱ ምክንያት ከሚሆኑት ውስጥ የብራዚል ምርት መጠን በእጅጉ መጨመር ማሳየት አንዱ ነው። ለአብነትም ብራዚል በእዚህ ዓመት ብቻ ወደ 43 ሚሊዮን ጆንያ ቡና ለግብይት አቅርባለች። ይሄን ተከትሎ በዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት አማካኝነት ይቀርባል የሚለውን 128 ሚሊዮን ጆንያ ቡና ግምት በማስለወጥ ወደ 131 ሚሊዮን አሳድጐታል። በመሆኑም የአቅርቦቱ መብዛት ገበያው ላይ ጫና ፈጥሯል የሚል እምነት አላቸው። 
አቶ አንተነህ ለቡና ዋጋ መውረድ በሁለተኝነት የሚያስቀምጡት ምክንያት አለ። ይኸውም እ.ኤ.አ በ2008 አካባቢ መከሰት የጀመረው የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ ነው። በተለይ የአውሮፓ ቀጣና ሀገራት ያጋጠማቸው የበጀት ጉድለት ጋር ተያይዞ የቡና ፍላጐቱን አቀዝቅዞታል። በመሆኑም እንደባለሙያው ገለጻ ከእነዚህ ሁለት አንኳር ምክንያቶች በመነሳት የዓለም ቡና ዋጋ መዋዥቅን አስከትሏል። «... ከእዚህ ውጪ በኢትዮጵያ ቡና ላይ በተናጠል ምንም ዓይነት የፍላጐት መቀዛቀዝ የለም» ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ምርት ገበያው አምና በእዚህ ወቅት ካስመዘገበው ከፍተኛ የኤክስፖርት መጠን የማይተናነስ ቡና ዘንድሮም ለሽያጭ አቅርቧል።
«በዓለም አቀፍ ደረጃ ቡና መወዳደር የተሳነው ከአመራረት ጋር ተያይዞ የጥራት ማነስ ነው» የሚለውን ሃሳብ የማይስማሙበት እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይ የቡና የምርት ጥራቱ ወርዷል ለማለት የሚያስችል ምክንያት የለም ባይ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በምርት ገበያ መረጃ መሰረት ከባለፉት ሦስት ዓመታት አኳያ ሲታይ ለሽያጭ የሚቀርቡት የቡና ዓይነቶች ጥራት እየተሻሻለ መጥቷል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጐረቤታችን ኬንያ ቡናን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በዓመት ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች። ነገር ግን በኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የነበረው እውነታ ከኬንያ በሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደሚቀንስ ነበር። የዳሞታ ወላይታ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅም በእዚህ የማስተዋወቅ ሥራ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ይስማማሉ። አቶ ተከተል «... ቡናን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ ሌላ የውድድር አካል መሆን አለበት። እኛ ዘንድ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአገር ውስጥ ገበያ ዋጋ ከምርት ወጪ ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን ለቡና ዋጋ መቀነስ በቀጥታ ተጠቃሽ የሚሆነው ዓለም አቀፍ ቀውስ ነው» ይላሉ። 
ለአርሶ አደሮች ከቡና ጥራት እና ግብይት ጋር በተያያዘ ስልጠና እንደሚሰጡ የሚናገሩት አቶ ተከተል፤ ይሄ በሀገር ደረጃ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል አቅጣጫ መሆኑን ያምናሉ። «... የወቅቱ ቡና ዋጋ የብዙ ማህበራት አባላትን ያስደነገጠ ነው» ብለው፤ ይሁንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሲፈታ የኢትዮጵያም ቡና ወደ ቀድሞ ዋጋው ይመለሳል የሚል እምነት አላቸው። ለእዚህ ግን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ያሰምሩበታል።
ማስተዋወቅን በተመለከተ የምርት ገበያው ዋና የኦፕሬሽን ሥራ ኃላፊው አቶ አንተነህ እንደሚሉት የኢትዮጵያን ቡና ማስተዋወቅ የምርት ገበያ ዋና ተግባር አይደለም። ይልቁንስ ድርጅቱ በዋናነት ለቡና ላኪዎች (ኤከስፖርተሮች) እና አምራቾች ምቹ የመገበያያ መድረክ መፍጠር ላይ ይሰራል። ለወደፊት ግን ቡናን በማስተዋወቁም ረገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ይሰራል ብለዋል። በእዚህ እና ይሄን በመሳሰሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ዕድሜ ጠገብ ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ «አረንጓዴ ወርቅን» ወደ ቀድሞ ዝናው መመለስ ላይ ያተኮረ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
ከባህር ማዶ ሀገራት ጀርመን ቁጥር አንድ የኢትዮጵያ ቡና ሸማች ሀገር ናት። በእዚህ ዓመት ብቻ እንኳን 29 በመቶ የኤክስፖርቱን ድርሻ ትወስዳለች። በመቀጠልም ሳውዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቤልጂየም እና ፈረንሳይ በከፍተኛ ደረጃ የኢትዮጵያን ቡና የሚጠጡ አገራት ናቸው።
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/economy.php?instruction=&economyId=1135

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር