የሐዋሳ ሞያሌ የመንገድ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያና ኬንያ የንግድ ትስስር ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ (ዋኢማ) - ከኢትዮጵያ የወጭና የገቢ ምርት 90 በመቶ የሚሆነው የሚመላለሰው በጁቡቲ ኮሪደር ነው፡፡ ይሁንና የወጭና የገቢ ምርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም አስፈላጊ ሆኗል፡፡ 

በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገነባው የሃዋሳ ሞያሌ የመንገድ ፕሮጀክትም አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ከሚያስችሉት መካከል አንዱና ዋናው ነው፡፡ ይህ መንገድ የሞምባሳ ናይሮቢ አዲስ አበባ ኮሪደር አካል ሲሆን በ6 ኮንትራቶችም ተከፍሏል፡፡ ከነዚህም መካከል ከሀገረማርያም ያቤሎ እና ከያቤሎ ሜጋ ግንባታው ተጀምሯል፡፡

የሀገረ ማርያም ያቤሎ የመንገድ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሀንዲስ የሆኑት ሚስተር ጌርድ ዌበር ግንባታው በተፈለገው የጊዜ ፍጥነት ባይካሄድም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ነው የሚገለጹት፡፡

«በአሁኑ ሰአት ሁሉንም አይነት እንቅስቃሴዎች እያከናወንን ነው፡፡ በዋናነት መንገዱን በማስፋት የአፈር ስራዎችን እያከናወንን ነው፡፡ የተወሰነውን የመንገዱን ክፍልም ጠጠር አልብሰናል፡፡ ነገር ግን የአስፋልት ስራ ገና አልተጀመረም፡፡ መንገዱን የሚሰራው ድርጅት የግብጽ አረብ ኮንትራክተር አዲስ ነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ከልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ ችግሮች ነበሩበት አሁን እየተቀረፈ ነው፡፡»

98 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና በቻይና ኩባንያ የሚገነባው የያቤሎ ሜጋ የመንገድ ፕሮጀክትም አስከአሁን 17 በመቶ የሚሆነውን ስራ አጠናቋል፡፡

የሁለቱም መንገዶች ደረጃ አስፋልት ኮንክሪት ሲሆን በቀን እስከ 2 ሺህ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ነው፡፡

የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎችን አቋርጦ የሚያልፈው የሐዋሳ ሞያሌ የመንገድ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያና ኬንያ የንግድ ትስስር ወሳኝ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሮፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ የሚገልጹት፡፡

በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ከግብጽ ካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ድረስ ያሉ ሀገራትን በመሰረተ ልማት መገናኘት ወሳኝ መሆኑን ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት ኔፓድ ያስቀምጣል፡፡

ኢትዮጵያና ኬንያን የሚያገናኘው ይህ መንገድ ደግሞ የኔፓድን እቅዶች ለማሳካት ወሳኝ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከግብጽ እስከ ኬፕታውን ባለው ርቀት በመንገድ ካልተገናኙት አካባቢዎች አንዱ ይህ በመሆኑ፡፡ እናም ይህ መንገድ ኢትዮጵያና ኬንያን ከማገናኘቱም ባለፈ ሀገራቱን ከአህጉሪቱ ዋና መስመር ጋር በማገናኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

«እኔ እንደማስበው በኢትዮጵያ መንግስት እየተከናወነ ያለው ስራ እጅግ ጠቃሚ ፕሮግራም ነው፡፡ በዚያኛው በኩልም የኬንያ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርሰውን መንገድ እየገነባ ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል ያለው የተሻለ ነው፡፡ እነዚህ አለቁ ማለት ሀገሪቱ ወደፊት በትልቁ እንድትራመድ ያስችላታል፡፡» ብለዋል አቶ ሳምሶን፡፡

ከሜጋ አስከ ያቤሎ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት በጨረታ ላይ ያለ ሲሆን ከሃዋሳ እስከ አገረ ማርያም ድረስ ያለው ደግሞ በቅርቡ ግንባታው እንደሚጀመር የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል፡፡ ከ500 ኪሎ ሜትር ባላይ ለሚሽፍነው የሃዋሳ ሞያሌ የመንገድ ፕሮጀክትም ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል፡፡ 

ወጭው በኢትዮጵያ መንግስትና በአፍሪካ ልማት ባንክ ይሸፈናል፡፡ የባንኩ የትራንስፖርት ኢንጅነር የሆኑት ሚስተር ዋኬንዱ ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ባለፈ አህጉራዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በባንኩ ድጋፍ ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ የመንገድ ዘርፍ የልማት ፕሮግራም አካል ነው፡፡ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን የሚያዳርሰው ትልቁ የትራንስፖርት በር አካልም ነው፡፡ 

አካባቢያዊ ውህደት በመፍጠር፣ እንዲሁም ባለው የንግድና ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የባንኩን መስፈርት አሟልቷል፡፡ ለዚም ነው ፕሮጀክቱን የደገፍነው  ማለታቸውን የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር