ጊዳቦ ፍልውሃ ገና ያልተነካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም


ቅዱስ ኃይሉ

ይርጋለሞች፣ ዳሌዎች እንዲሁም እነዚህን አካባቢዎችና የተለያዩ አገልግሎታቸውን ያዩ ሁሉ ሳይቋደሱት አያልፉም። የጊዳቦ ፍልውሃን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት ሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ ይርጋለም ከተማ የሚገኘው ይህ የፍልውሃ ቀደም ሲል በዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች አስተዳደር ሥር ይተዳደር ነበር። አሁን ደግሞ የሲዳማ ልማት ማኅበር ተቋም ነው።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ እዚህ አካባቢ በሄድኩ ቁጥር እኔም ይህንን ሀብት ሳልቋደስ አልመለስም። በቅርቡም ወደዚሁ ፍልውሃ አገልግሎት ዘልቄ ያለፈውን እያስታወስኩ የአሁኑን አገልግሎቱን ቃኘሁ። ወደፊትም ሊኖረው የሚችለውን አቅምም ተንብያለሁ። 
የፍልውሃ አገልግሎቱን ተጠቃሚ የሚያደርገውን ትኬት የሚቆርጡበት ቢሮ ቀድሞ ከነበረበት ወደ መግቢያው አካባቢ መጥቷል። ራሱን የቻለ ቤትም የፍልውሃ አገልግሎት መስጫ ቤቶቹ ከራስጌያቸው ያደረጉት ኮረብታውን ጥግ ይዞ ተሠርቶለታል። 
የፍልውሃ አገልግሎቱ ሁሌም በወረፋ የተጨናነቀ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀን ምሳ ሰዓት ላይ ነው ወደ ሥፍራው ያቀናሁት። በእኔ ቤት ብልጥ ሆኜ ቶሎ አገልግሎቱን አግኝቼ ልመለስ። 
የትኬት መቁረጡ ተራ እስኪደርሰኝ ድረስ ዙሪያ ገባውን ተመለከትኩት። ትኬቱ የሚቆረጥበት ሥፍራ ፍልውሃው የሚገኝበትን አካባቢ በሙሉ ለመቃኘት ያስችላል። 
ቁልቁል ስመለከት የጊዳቦ ወንዝ ግራ ቀኙን በልምላሜ ታጅቦ በርበሬ መስሎ መፍሰሱን ተያይዞታል። ወቅቱ ክረምት ነውና የውሃው መጠን በጣም ጨምሯል፤ የሚጣደፍ አይመስልም። ድምፁ አይሰማም ከወንዙ ባሻገር የአርሶ አደሮች መንደር፣ እንሰት፣ ዛፎች እና የተለያዩ ተክሎች ይታያሉ። ከነዚህ ተክሎች ውስጥ ቡናና የፍራፍሬ ዛፎች ሊገኙበት እንደሚችሉ ጠጋ ብዬ ያየኋቸው የከተማና የገጠር መኖሪያ ጊቢዎች ሁኔታ ይመሰክራል። ከወንዙ ወዲህ ደግሞ የፍልውሃ አገልግሎቱ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ዛፎች፣ ዘምባባዎችና አበባዎች ይታያሉ። 
እኔና አብረውኝ ወደ ሥፍራው ያቀኑት ቤተሰቦቼ ትኬት ቆርጠን ወደ ውስጥ መግባታችንን ተያያዝን። በየዛፎቹ ላይ ሽኮኮዎች ይታያሉ። ጉሬዛ ከአንዱ ዛፍ ወደ አንዱ ይዘላል። ፍልውሃው ራስጌው ያደረገው ኮረብታ ጥግም በተለያዩ የዛፍ ዓይነቶች፣ ሐረጎች ተሸፍኗል። የተጋለጠ መሬት አይታይም። አንድ ቦታ ላይ ብቻ የመሬት መንሸራተት ያስከተለው ችግር ይመስለኛል ድንጋያማ ቦታ በአንድ ወቅት ተጠራርጎ የወረደ የአፈር፣ የሀረግ ወዘተ ቅሬት ይታያል። 
«አገልግሎቱን ቶሎ እናገኛለን» በሚል አሳቻ ጊዳቦ ባልነው ሰዓት ብንገኝም፣ ማመን በማያስችል መልኩ በ70 ሰዎች መቀደማችንን ትኬቱን እየተቀበለ ከሚያስተናግደው ሠራተኛ ተረዳን። ይህ አጋጣሚ አካባቢውን ይበልጥ መቃኘት የሚያስችለኝን ሁኔታ አመቻቸልኝ። 
የመናፈሻ አገልግሎት መስጠት የሚችል አረንጓዴ ሥፍራ ተዘጋጅቷል። ለእኔ አዲስ ነበርና በጣም አደነቅኩት። ይህ ቦታ በተለይ በበጋው ወቅት ምንኛ ሊያምርና ሊያጓጓ እንደሚችል ገመትኩ። ቀደም ሲል ያልነበረ ለመዝናኛ አገልግሎት የተገነባ ሕንፃም አለ። ቦታው የሠርግ አገልግሎት እንደሚሰጥ ቀደም ሲልም አውቅ ነበረና አሁን ደግሞ በዚህ መልኩ ከተደራጀ ጥሩ ገቢ ሊያስገኝ፣ የተገልጋዩንም መንፈስ ሊያድስ እንደሚችል መረዳት አይከብድም
የፍልውሃ አገልግሎቱን ለማስፋፋት የሚረዱ የስድስት መታጠቢያ ቤቶች ግንባታም እየተካሄደ ይገኛል። 
ተራቸውን የሚጠብቁ ሰዎች በመታጠቢያ ቤቶቹ በረንዳዎችና ከዚያም ፈንጠር ባሉ ቦታዎች ላይ ይታያሉ። በጋራ መታጠቢያ ቤት ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ የሚገለገሉበትን ሥፍራ በርቀት አየሁ። ይኸኛው የወንዶች ነው፤ በስተጀርባ የሴቶችም እንዳለ ቀደም ሲልም አውቃለሁ። ሌላም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጥ ሰፊ ክፍል አለ። ወረፋ መጠበቅ የማይፈልጉ ባብዛኛው ወደነዚሁ ሥፍራዎች ነው የሚያመሩት። ከተለያዩ አሸንዳዎች በሚወርደው የሞቀ ውሃ በየተራ መታጠብ ይችላሉና። 
ተራችንን በቅርበት መከታተል ወደሚያስችሉን አንዱ የመታጠቢያዎቹ በረንዳ አምርተን ተራችንን መጠባበቅ ጀመርን። 
ከመታጠቢያ ቤቶቹ መዝጊያዎች ቁልፍ የሌላቸው እንዳሉ ውጫዊ ሁኔታቸውም ያስገነዝባል። በዝገት የተጠቁ መሆናቸውን ውጪያቸውም ይጠቁማል። 
አንድ ክፍል ተለቀቀና በተራ የሚቀድሙን ይገቡበታል ብለን ስንጠብቅ ሊገቡበት እንዳልፈለጉ ተገነዘብን እስቲ በማለት ጐራ ብዬ ተመለከትኩት። የመዝጊያው እጀታ የተነቀለበት ቦታ ትልቅ ክፍተት ይታይበታል። ምናልባትም ከውጪ ወደ ውስጥ ሊያሳይ ይችላል። ብዙ ከመቆየት ብዬ ወሰንኩና ክፍሉ እንዲፀዳ አስደረግሁ። 
ወለሉና ገንዳው የሚፀዳው በአንድ ዓይነት መወልወያ ነው። ወቅቱ ክረምት ነውና ወለሉ ጭቃ ይስተዋልበታል። ይህ ወለል በፀዳበት ገንዳውም ሲፀዳ አስተዋልኩ። 
አንደኛ ማዕረግ በሚል የያዝኩት መታጠቢያ እንደ ጥንቱ ገንዳው ውስጥ እንደፈለገኝ እየሆንኩ መታጠብ እንደማልችል የፅዳቱ ሁኔታ አረጋገጠልኝ።
ሙቅ ውሃው ፊትም የማውቀው ነው፤ ለጉድ እንደ እሳት ይፋጃል። መከለሻ ቀዝቃዛ ውሃ የለም። ይኑር ማለቴ ግን አይደለም።ቀስ እያልኩ ተላመድኩትና መታጠቤን ቀጠልኩ።
ፎጣ አልቀረበም፤ ጨርሶም የለም። የገንዳው ንፅህና አስተማማኝ ባለመሆኑም ሜዳላይ ከሚታጠቡት ሰዎች ባልተለየ መልኩ ቆሜ መታጠብ ግድ ሆነብኝና ይህንኑ አደረግሁ።
ዱሮ ፎጣ ይቀርብ ነበር። እያደር የፎጣው ንፅህና አስተማማኝ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች ፎጣውን መጠቀም የማይፈልጉበት ሁኔታ እንደነበር ትዝ አለኝ። እናም የፎጣው መቅረት ብዙም የሚያስከፋ አይደለም። ይሁንና አንደኛ ማዕረግ በሚለው ላይ ግን አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል።
በግል አንድ ክፍል ይዞ አገልግሎቱን ማግኘት ብቻውን አንደኛ ማዕረግ ያሰኛል ወይ? ንፁህ ፎጣ፣ ንፁህ ገንዳ፣ የቤት ጫማ ወዘተ በሌለበት ሁኔታ አንደኛ ማዕረግ መባሉስ ለምን?
ቀደም ብዬ ሳውቀው አገልግሎቱ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ማዕረግ የነበረው። አሁን ግን ሁለተኛ ማዕረግ የለውም። ሦስተኛው ማዕረግ የጋራ መታጠቢያ ሆኗል። በግል የሚያዙት ክፍሎች በሙሉ አንደኛ ማዕረግ ተብለዋል። አገልግሎቱ ከማዕረጉ ጋር አይጣጣምም።
የፍልውሃ አገልግሎቱ ቀደም ሲል ከጠቃቀስኳቸው ጥቂት የማስፋፊያ ሥራዎች ውጪ ለውጥ ማምጣት የቻለ አይመስለኝም።
ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የጊዳቦ ፍልውሃ አሁን እየሰጠ ባለው አገልግሎቱም ብቻ ተፈላጊ ሆኖ እንደሚቀጥል አልጠራጠርም፤ ፍልውሃው ይፈለጋልና። አገልግሎቱን ቢያንስ ቀደም ሲል ወደ ነበረበት መመለስ ግን ያስፈልጋል። ፎጣና ነጠላ ጫማ ማዘጋጀት ምን ያስወጣል? በርካታ ሰዎች እግረ መንገዳቸውን አገልግሎቱን ብለው ጎራ ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ቢያንስ ፎጣና ነጠላ ጫማ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ አገልግሎቶች ቢያንስ ከአንደኛ ማዕረግ ይጠበቃሉ። ማዕረግ የሚለው ቃል በከንቱ አይጠራም። በአግባቡ የማይዘጋ፣ ጨርሶ የማይዘጋ በር ያለው ክፍል እንዴት በዚህ ማዕረግ ይጠራል? 
የጊዳቦ ፍልውሃ አገልግሎት አሁን ያለው ይህ ሕይወትን የሚያድስ ሙቅ ውሃና የተፈጥሮ አካባቢው ብቻ ይመስለኛል፡፡ የመናፈሻ አገልግሎቱም እንዲሁ።
ከዚህ በመለስ ግን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት አገልግሎቱ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም። ለምን ይሆን? ገቢው ራሱን ማሳደግ ሳያስችለው ቀርቶ ነው ብዬ አልገምትም። በግሌ የጊዳቦን ፍልውሃ ከዚህም በላይ ጥቅም የሚሰጥ ማድረግ እንደሚቻል በጽኑ አምናለሁ። አቅሙ አለውና።
የጊዳቦ ፍልውሃ አገልግሎቱ እየወረደ ቢሆንም ፍልውሃውን ያለ ይፈልገዋል። በዚህ ገበያው ላይ ችግር አያጋጥመውም። ይህ ግን ለዚህ ውብ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የመጨረሻው ግቡ መሆን የለበትም።
ይህ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ሊለማ የሚያስችለው ዙሪያ ገባ አለው፡፡ አሁን ያለውን ይዞታ በሚገባ በማስፋት ደንበኛ ተኮር ተግባር በማከናወን ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ ለጊዳቦ ፍልውሃ ራዕይ በመሰነቅም አካባቢውን በሙሉ በዚህ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ብዙ ጠቅሞ መጠቀም ይቻላል።
የሶደሬ መዝናኛ ዋናው ሀብቱ ምንድነው? ፍልውሃውና ከግርጌው ዘና ብሎ የሚፈሰው አዋሽና ያ ተራራ ናቸው። ዋናው ደግሞ ሙቅ ውሃው ነው። 
ጊዳቦስ ምን አጣ? እነዚህ ሁሉ አሉት። ከዚያም በላይ ባይሆን? ያ በአረንጓዴ ያሸበረቀ አካባቢ እኮ ተጨማሪ ውበቱ ነው።
ጊዳቦ ያጣው አልሚ ብቻ ነው፡፡ አገልግሎቱን የሚፈልግ አዋሳን የመሰለ በመስፋፋት ላይ ያለ ከተማ ሕዝብ፣ የሲዳማና የጌዲኦ ሕዝብ፣ የደቡብና የኦሮሚያ አካባቢ እያለ ከጥንት ጀምሮ የሚያውቀው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖር ሕዝብ እያለ፣ ይህን ሁሉ ሕዝብ አገልግሎ መጠቀም መቻል ለምን አልተሞከረም?
አሁን እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በአንድ ወቅት በራሱ ከበቀለ ዛፍ እየሸመጠጡ ከመብላት የማይለይ ይመስለኛል። ትርጉም ያለው እሴት አልተጨመረበትም። ለገበያ እየቀረበ ያለው ፍልውሃው ብቻ ነው፡፡
ጊዜው ለዕድገት የሚሠራበት ነው፡፡ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው የሀገሪቱ እምቅ ሀብቶችን በተገቢው መንገድ ተጠቅሞ ለዕድገቱ አስተዋጽኦ ማበርከት ሲችሉ ነው። ለዚህ ደግሞ በእጅ ያለን አቅም በሚገባ መጠቀምን አላይም ደሞ አቅምን ከሌሎች ጋር አስተባብሮ መንቀሳቀስን ያስፈልጋል።
ከዚህ አንፃር የጊዳቦ ፍልውሃ ባለቤት የሆነው የሲዳማ ልማት ድርጅት ይህን እምቅ ሀብት በሚገባ ለማልማት መንቀሳቀስ የነበረበት ወቅት የዘገየ መሆኑን መገንዘብ የኖርበታል። ይህም ሆኖ አሁንም ለዕድገት ከተነሳሳና ራዕይ ሰንቆ መንቀሳቀስ ከቻለ ውጤታማ መሆን አያቅትም። ተፈጥሮ ሀብቱን በአግባቡ የመጠቀም አቅምን ማጎልበትም ይኖርበታል።
ድርጅቱ ይህን ፍልውሃ ለማልማት የአቅም ችግር አለበት ብዬ አልጠራጠርም። 
ድርጅቱ ለጊዳቦ ፍልውሃ የሰነቀው ራዕይ ካለም በዚህ ገጽ ላይ ይፋ ያደርግልንና ይበልጥ የለማ የሚናፍቅ ለሲዳማ ዞን፣ ለደቡብ ክልልና ለአገሪቱ ሀብት የበኩሉን ሚና የሚጫወት የጊዳቦ ፍልውሃንና የለማ አካባቢውን በጉጉት እንድንጠብቅ ያድርገን።
እስከዚያው ድረስ ደግሞ የመታጠቢያ ቤቶቹ መዝጊያዎች በዝገት የማይጎዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። መዝጊያዎቹ ቁልፍ እንዲኖራቸው በማድረግ ሰዎችን መዝጊያዎቹን መለስ ብቻ አድርገው እየተገለገሉ ካሉበት ሁኔታ ማውጣት ያስፈልጋል።
ከመታጠቢያ ቤቶቹ በስተጀርባ ያለውን ውብ ተራራና ደኖቹንም በመሬት መንሸራተት እንዳይጠቁ የተፋሰስ ሥራ እንደሚያስፈልግ በአካባቢው ችግሩ ደርሶ እንደነበር የሚያመላክተው የዚሁ ሥፍራ ገጽታ ይጠቁማል። ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር