የሕገ መንግሥታት ያላቻ ንፅፅርና የኢ-ዘላቂነት ዳንኪራ


በበሪሁ ተወልደ ብርሃን

አንድን ነገር ከመጻፌ በፊት ራሴን እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ መጻፌ ጥቅም ይኖረው ይሆን? የምጽፈው ነገር ምክንያታዊ ነውን? ይህ ካልሆነ ግን ዝምታን እመርጣለሁ፡፡ ዛሬ ለመጻፍ ስነሳም ለጥያቄዎቼ በቂ ምላሽ ከሰጠሁ በኋላ ነው፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ በሐምሌ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ዕትሙ በአገራችን ዕውቅ ከሆኑ የሕግ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም በማስታከክ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ሕመም ቢያጋጥመው ማን ተክቶት ይሠራል ለሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ክፍተት አለበት›› በሚል ርዕስ የቀረበውን ጽሑፍ አንብቤ የተነሳው ጭብጥ፣ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ብዙም ባላምንበትም፣ በተነሱት አንዳንድ ሐሳቦች ላይ ከተነሱት ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችና ድንጋጌዎች ምክንያታዊ እሳቤ (rationale)፣ ይዘት (content)፣ መልእክት (message)፣ ትርጓሜ (interpretation) እና ማብራርያ ምሳሌዎች (illusturation) ረገድ የምስማማባቸውን ትቼ፣ በማልስማማባቸው ሐሳቦች ላይ ይን መጣጥፍ ስጭር፣ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ምላሽ ለመስጠትና ለእሰጥ አገባ በር ለመክፈት እንዳልሆነና በሠለጠነው ሐሳብ የማንሸራሸር ውቅያኖስ ላይ ጠበል ጠዲቅ ከመቃመስ አኳያ ብቻና ብቻ እንደሆነ ግንዛቤ እንዲወሰድበት እፈልጋለሁ፡፡

ስለዚህ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት፣ ሕገ መንግሥት ከሌሎች ሕጎች የሚለይበት መሠረታዊ ባሕርያት፣ የፓርላማ ሥርዓትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን መሠረታዊ መገለጫዎችና ከፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚመሳሰሉበትና የሚለያዩበት ሁኔታ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ማዕቀፍ፣ ሕገ መንግሥታዊ ክፍተትና የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰያየምና ያንፀባረቀው አቋም፣ እንደ መንደርደርያነት በመመልከት እውን ይህ የተባለው የሕገ መንግሥት አንቀጽ 75 ክፍተት ያለበት ነውን? የጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመምና የተለያዩ የእክል ክስተቶች በሕገ መንግሥት መመለስ ያለባቸው ጉዳዮች ናቸውን? የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት እውን በተነሳው ጭብጥና ተያያዥ ነጥቦች ላይ ከቀደምት ሕገ መንግሥቶች የሚነፃፀር ነውን? የደርግ ወይም የኃይለ ሥላሴ ሥርዓት የወላድ መካን የሆኑት በሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት መርሆዎች በተነሳ ጉዳይ ነውን? የሌሎች ሚኒስትሮች ቢሮዎች እውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸውን? የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሥልጣን ወሰንና እንደ አንድ አካል መቆጠር እርግጠኛ መሆን አይቻልምን? የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ሕመም ለኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግር ምክንያት ሊሆን ይችላልን? የሕገ መንግሥቱ ዘላቂነት በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጭብጦችን እንደሚከተለው አብረን እንመርምራቸው፡፡

ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት
በዘመናችን ሁለት መቶ የሚሆኑ ሉዓላዊ አገሮች እንዳሉና ከእነዚህም በጣም የበዙት የተጻፈ፣ በጣት የሚቆጠሩት ደግሞ ያልተጻፈ ሕገ መንግሥት እንዳላቸው በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ሰዎች ስለሚኖሩበት አገር ወይም ስለሌላው አገር ሕገ መንግሥት በአንዱ ወይም በሌላው መልኩ ሲገልጹ፣ ሲከራከሩና ሲወያዩ መስማት ወይም ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት የሚወያዩ ሰዎች ሁሉ ስለሚወያዩበት ሕገ መንግሥት ትክክለኛና የተሟላ ግንዛቤ አላቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ግን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ከደረሰበት የትምህርት ደረጃ፣ ከኖረበት ሥነ ቁጠባዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ባህል፣ ከተሰማራበት የሙያ ዘርፍና ሌሎች ምክንያቶች ስለ ሕገ መንግሥት ያለው ግንዛቤ አንዱ ከሌላው ሰው የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ ጽንሰ ሐሳቡን ለመረዳት ይረዳን ዘንድ ከትርጓሜው እንነሳ፡፡ ብላክስ ሎው የተባለው የሕግ መዝገበ ቃላት የሰጠውን ትርጓሜ ስንመለከት “Constitution is the fundamental and organic law of Nation or State establishing the conception, character, and organization of its government, as well as prescribing the extent of its sovereign power and the manner of its exercise” የሚል ፍቺ ሰጥቶት እናገኘዋለን፡፡ ይህን ፍቺ ስንመረምረው፣ ሕገ መንግሥት መሠረታዊ የሆነ፣ አንድ አገር ወይም መንግሥት የሚመራበትና የሚተዳደርበት፣ በዋነኛነት ስለሕገ መንግሥት አወቃቀር፣ የመንግሥት አካላት አደረጃጀት፣ የመንግሥቱን ባህሪና ስለ መንግሥት ሥልጣን ሊያዝ የሚገባውን ገዢ አስተሳሰብ፣ የመንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን ወሰን፣ መንግስት ሉዓላዊ ሥልጣኑን ሥራ ላይ ስለሚያውልበት አግባብ ወይም ሥርዓት፣ የመንግሥት ሥልጣን አጠቃቀም ላይ ልጓም በማድረግና ገደብ በማበጀት፣ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣኑን እንዴትና በምን መንገድ መጠቀም እንዳለበት ገዢ የሆነ ደንቦች የሚያስቀምጥ ሕግ ብቻ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረዊና ፖለቲካዊ ባህል የሚገለጽበት ፖለቲካዊና ሕጋዊ ሰነድ ጭምር ነው፡፡ ሕገ መንግሥት በትርጉሙ የሕግና የፖለቲካ ሥርዓትን ቁልፍ ማዕቀፍና መሠረት የሚጥል (Framework and Skeleton) ሆኖ እንዲያገለግል የአውጪዎቹ የጋራ እምነት፣ እሴትና ስምምነት እንዲሁም የሥልጣነ መንግሥት ክፍፍልና በመንግሥት አካላት ውስጥና መንግሥት ከሌሎች ድርጅቶና ዜጎች በአጠቃላይ የሚኖረው ግንኙነት የሚወስንና አንዲት  አገር በረዥም ጊዜ ውስጥ ዕውን ልታደርገው የምትፈልገውን ራዕይ፣ አገራዊ ራዕዩን ዕውን ለማድረግ መሳካት የሚገባቸው ሕገ መንግሥታዊ ግቦችንና ዓላማዎችን በረቀቀ ሁኔታ የሚገለጽበት ሰነድም ጭምር ነው፡፡

ይህ ማለት ግን የሕገ መንግሥት ተግባር ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥት የመንግሥት ስያሜ፣ ዝርዝር ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን፣ የአሠራር ደንቦችና ሥነ ሥርዓቶችን አጠቃልሎ ሊይዝ ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትም ተቋማዊ ልጓምና አለንጋ ወይም የቁጥጥርና ምዝዝን (Check and Balance) አሠራር ያለበት፣ የሕግ ሉዓላዊነት የሰፈነበት፣ የመንግሥት ተግባርና ሥራ በሕግ ሥርዓቱ ቁጥጥር ሥር የሆነበት የሥርዓተ መንግሥት ምሶሶ ማለት ነው፡፡

የአንድን አገር የሕግ ሥርዓት፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ኃይሎች የሚወሰኑት በሕገ መንግሥት መርሆዎች ነው፡፡ ሕገ መንግሥት በተፈጥሮው ከሥልጣነ መንግሥትና ሥርዓተ መንግሥት ይዘትና አመሠራረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ሕግ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ መሣሪያም ጭምር ነው፡፡ በአንድ ጂኦግራፊያዊና ሕገ መንግሥታዊ ወሰን ክልል ያለው አገር ውስጥ የሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በሕግ ሥር የሚደረጉ ከሆነ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ ማለት ነው፡፡ የአንድን አገር ሕገ መንግሥት በማጥናት ብቻ በንድፍ ሐሳብ ደረጃ ፖለቲካውንና የሕግ ሥርዓቱን ማወቅ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥት ለአንድ የፖለቲካና የሕግ ሥርዓት የማዕዘን ድንጋይ፣ ምሰሶና ማገር ሆኖ የሚያገለግል ሰነድ ነው፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት (Constitutionalism) ሥርዓተ መንግሥቱ ለአንዲት አገር ሕገ መንግሥት ያለው ታማኝነትና እምነት የሚገለጽበት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ የመንግሥት አካላትና የመንግሥት ባለሥልጣናት በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ መሠረታዊ መርሆዎች እሴቶች በሙሉ ልብ በመቀበል እነዚህን ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች፣ እሴቶችና ድንጋጌዎች በመላ ተግባሮቻቸው እንዲገለገሉበትና ሕገ መንግሥቱን በማክበር፣ በማስከበርና በመጠበቅ ያለውን ተፈጻሚነት የሚገለጽበት ዘውግ ነው፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት በአንዲት አገር በሕገ መንግሥትነት የታወጀ ሰነድ ከመኖሩ ባሻገር፣ በሕገ መንግሥቱ ጥላ የተደራጁ አካላት ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ሆነው መገኘታቸውን ይመለከታል፡፡ የዘርፉ ሊቃውንት ሕገ መንግሥታዊነትን ‹‹The phenomenon of government conforming to the dictates of a settled constitution is known as constitutionalism›› በማለት ይገልጹታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአገሪቱ ውስጥ የመንግሥት ሥልጣን ምንጭና መሠረት መሆኑና መንግሥት ዜጎችና ሌሎች ተቋማት የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ገዥ የሆነ የአገሪቱ የበላይ ሕግ መሆኑን በመቀበል፣ ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ሆኖ በመገኘትና ሕገ መንግሥቱም እንዲከበር የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣትንም የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊነት ስንል የተለያየ ሐሳብና ፍላጎት ያላቸው አካላት ያሏቸውን ልዩነቶች በሕገ መንግሥቱ ጥላ ሥር ተሰባስበው የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች መሠረት አድርገው ለመፍታት ያላቸውን እምነትና ቁርጠኝነት ሁሉ የሚያመለከት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡

ሕገ መንግሥት ከሌሎች ሕጎች የሚለይበት መሠረታዊ ባህርያት
ሕገ መንግሥት ከሌሎች ሕጎች የሚለይበት መሠረታዊ ባህርያት እጅግ በጣም በርካታ ቢሆኑም የተወሰኑትን ለመመልከት ያህል፣ የሕገ መንግሥት ዓይነተኛ ተግባርና ዓላማ የመንግሥትን ተግባራት ሁሉ መቆጣጠር ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ከሌሎች ሕግና አዋጆች በተለየ ሁኔታ የሚወጣውና የሚሻሻለው በሕግ አውጪ አካል ሳይሆን ከሱ በላይ በሆነ ምልዓተ ሕዝብና ምልዓተ ሕዝቡ በቀጥታ በሚወስነው ውሳኔ መሆኑ፣ ህያውና መሠረታዊ የሆነ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ መሆኑ፣ ማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩና ከሕገ መንግሥቱ ጋር ከተቃራኑ ውጤት አልባ እንዲሆኑ የሚያደርግ፣ ከሥልጣነ መንግሥትና ሥርዓተ መንግሥት ይዘትና አመሠራረት ጋር የተያያዘ ሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መሣሪያም ጭምር ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ማናቸውም ሕግ (አዋጅ ወይም ደንብ) ሊያሳካው የሚፈልገው መሠረታዊ ግብና ዝርዝር ዓላማዎች በሕገ መንግሥቱ እንዲመሠረት ያደረገ የሕግ ሰነድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት በአዋጅ ወይም በደንብ ሊገለጽና ሊካተት የማይችል ጥቅል መሠረታዊ ቁም ነገር የሚገልጽና ያካተተ ሰነድ ነው፡፡ ከግቦቹና ዝርዝር ዓላማዎቹ በላይ የረዥም ጊዜ አገራዊ ራዕይም የሚገለጽበትና የሚካተትበት መሠረታዊ ሰነድ ነው፡፡

በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን መሠረታዊ መገለጫዎችና ከፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚመሳሰሉበትና የሚለይበት ሁኔታ
በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማናቸውም መንግሥት ሲደራጅ ይብዛም ይነስ በመራጩ ሕዝብ በሚመረጡ ሰዎች እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት መንግሥት በመራጩ ሕዝብ በቀጥታና ነፃ በሆነ ምርጫ በሚመረጡ ተወካዮች የሚቋቋም እንደመሆኑ መጠን ከሌሎች አካላት በተሻለ ሁኔታ ሕዝቡን ይወክላል፣ የሕዝቦች ፍላጎትን ያንፀባርቃል ተብሎ እምነት የሚጣልበትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውነተኛ መገለጫ መሆን አለበት፡፡ በተለያዩ አገሮች የሚገኙት መንግሥታት የተለያየ አደረጃጀት ያላቸው ሲሆን፣ እንደ ናሙና (ሞዴል) ሆነው ያገለግላሉ የሚባሉት አደረጃጀቶች ፓርላሜንታዊ (parliamentary system) እና ፕሬዚዳንታዊ (presidential system) የሚባሉት ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዝ የፓርላሜንታዊ አስተዳደር ቅርፅ የተከተለ ሲሆን፣ የኤሜሪካ ኮንግረስ ደግሞ ፕሬዚዳንታዊ የአስተዳደር ሥርዓት ቅርፅ የተከተለ ነው፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አረንድ ሌይፍርት የተባሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፓርላሜንታዊ የመንግሥት ሥርዓት  በዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ክፍፍል የተመሠረተ ሲሆን፣ መንግሥት (government) የሕግ አውጪው (የመንግሥት ከፍተኛው የሥልጣን ደረጃ የያዘ አካል)፣ የሕግ ተርጓሚና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ አስፈጻሚ ክፍል የሚያደራጅ ነው፡፡ በእዚህኛው ሥርዓት በሕዝብ በቀጥታ የተመረጡ የሕግ አውጪ (ፓርላማ) አባላት ሕግ በማውጣትና ሌሎች የሥልጣን አካላቶችን በመሾምና በመቆጣጠር የበላይ ሥልጣን እንዳላቸው የሚያረጋግጥ የመንግሥት ሥርዓት ሲሆን፣ የሥራ አስፈጻሚው አካል ዋና ኃላፊዎች የፓርላማው አባላት የሆኑበት ወይም ፓርላማው በቀጥታ እንዲቆጣጠራቸው የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ የሕግ አስፈጻሚው የሚመረጠው አብላጫ ወንበር ከያዙ ወይም የተጣመሩ ፓርቲዎች ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ አስፈጻሚ ክፍል የሚያደራጀውም እንደ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በግለሰብ ጥላ ሥር ሳይሆን፣ በድርጅቱ (ፓርቲው) ጥላ ሥር ብቻ ነው፡፡ ለስኬቱም ሆነ ለውድቀቱ በጋራ ፓርቲው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሚኒስትሮች እኩል ኃላፊ የሚሆኑበት ሥርዓት ነው፡፡ ‹‹…in a parliamentary system, the prime minister is merely the first of the team-hence the term prime minister, or in Latin primus inter pares (the first among equals)… the relevant actors are not individual members of parliament, but the parties.››


በተቃራኒው በፕሬዚዳንታዊ የአስተዳደር ሥርዓት የሥራ አስፈጻሚ ክፍል (cabinet) የሚያደራጀው በፕሬዚዳንቱ ጥላ ሥር ነው፡፡ ለስኬቱም ሆነ ለውድቀቱ ኃላፊ የሚሆነው ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የአስፈጻሚው አካል ፓርላማውን መቆጣጠር የሚያስችለው ሥልጣን የለውም፤ ራሱ ተጠሪነቱ ለፓርላማው ነው፡፡ ይህ በመሆኑም የአስፈጻሚው አካል የሕግ አውጪን ብሎም አንዱ ሌላኛውን የሚቆጣጠርበትና የሚከታተልበት ሥርዓት ከፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት አንፃር ሲታይ እጅግ የጎላ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን የሕግ አውጪው በአስፈጻሚው ላይ የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር የለም ማለት አይደለም፡፡ በፓርላማዊ ሥርዓት የሕግ አውጪው የበላይነት (legislative supremacy) ያለበት ስለሆነ፣ በአገሪቱ ግዛት ሥር ባሉ ሰዎች በራሱም ላይ ሳይቀር አዛዥነት፣ አስገዳጅነትና ተፈጻሚነት ያላቸውን ሕጎች ያወጣል፡፡ በፓርላማዊ ሥርዓት የፓርላማ ሥልጣን ከርዕስ ብሔሩም (Head of State) ከርዕስ መስተዳድሩም (Head of Government) በላይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፓርላማዊ ሥርዓት የሕግ አውጪው የበላይነት የሰፈነበት የሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር ነው የሚባለው፡፡ የፓርላማዊ ሥርዓተ መንግሥት ዋነኛ መሠረተ ሐሳቡ ከግለሰባዊ ሥልጣን ክምችት (እንደ ፕሬዚዳንታዊ) ይልቅ ተቋማዊና ብዙ ተወካዮች ያሉበት ምክር ቤት ላይ ሥልጣን ቢከማች መተማመን (ኮንፊደንስ) መፍጠር ይችላል የሚል ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ የሕግ ማዕቀፍ 
የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ መርህ የወል እሴት በሆኑና በአገርና ሕዝብ የተጋረጠ አደጋ ለመቀልበስ የሚደነገግ መርህ ነው፡፡ የአገር ሉዓላዊነትን ከውጭ ወራሪ ጠላት ለመጠበቅ፣ የተፈጥሮ አደጋ ለመመከትና ሕዝብና ዜጎችን ከበሽታና ሰቆቃ ለመታደግም ጨምሮ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዳይናጋ ለማድረግ ነው የአስቸኳይ ጊዜ የሕግ ማዕቀፍ የሚቀረፀው፡፡ ግለሰባዊ አንድምታ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ የሕግ ማዕቀፍ የዳበረ የሥልጣኔ ዘንግ አላቸው በሚባሉ አገሮችም የለም፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አደረጃጀት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰያየምና የሕግ አስፈጻሚው አካል አወቃቀር
በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ 6 አንቀጽ 53 ላይ እንደተጠቀሰው የፌዴራሉ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶች ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ናቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥቱን ዓበይትና መሠረታዊ ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ ከተቋቋሙት በርካታ ተቋማት መካከል በአንቀጽ 55 መሠረት በተሰጠው ሥልጣን ተግባራት መሠረት በአገሪቷ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ምክር ቤቱ ለፌዴራል መንግሥቱ ተለይተው በተሰጡ ሥልጣኖች ዙሪያ ሕግ የማውጣትና አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠር ሥልጣን ተሰጥቶቷል፡፡ በአንቀጽ 55 (13)፣ (17) (18) መሠረት ሹም ሽር መፈጸምን ጨምሮ የሕግ አስፈጻሚው አካል አሠራር የመመርመርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠ ነው፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 45 መሠረት ኢትዮጵያ የምትከተለው ሥርዓት የፓርላሜንታዊ ሥርዓት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይህ ማለት በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የሚገኙትን በጎ ትሩፋቶች በሙሉ ትጋራለች ማለት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 እና 73 (2) መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ከማውጣት ሥልጣን በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት መሆኑ ነው፡፡ ይህም የሚገለጸው በምክር ቤቱ ከፍተኛ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል (ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት) በማደራጀትና በመምራት ነው፡፡

የሕግ አስፈጻሚው የሚመራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት የበላይ አስፈጻሚና የአገሪቷ ርዕሰ መስተዳድር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡ ይህ ሥልጣኑ ግን ከፓርቲው የሚመነጭ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የሕግ አስፈጻሚው የቆይታ ዘመን የሚወሰነው ሥራውን በአግባቡ እየመራ ነው ተብሎ እስከታመነበት ጊዜ ድረስ ነው፡፡ በፓርላማዊ ሥርዓተ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሥልጣን ያበቃውን ፓርቲ በመወከል የሥራ አስፈጻሚው አካል ቁንጮ በመሆን ያገለግላል፡፡ የፓርላማ አባል ነው፡፡  
ይህ ምርጫ የሚመሠረተው በፓርቲ ይሁንታ እንጂ በግለሰብ አይደለም፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ 8 አንቀጽ 72 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥታዊ ሥራ በጋራ ለሚወስኑት ውሳኔ በጋራ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህ የሕገ መንግሥት ምዕራፍና አንቀጽ የሚያደራጀው የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደ ቡድን በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 56 እና 72 ያስቀመጠው መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአንቀጽ 73 እስከ 77 የአባላቱ የወልና የተናጠል ዝርዝር ኃላፊነቶች በልዩ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ ይህ በልዩ ሁኔታ የተሰጠ ኃላፊነት ግን መርሁን የሚሸረሽርና ለውድድር በር የሚከፍት ሳይሆን በአንድ መንግሥታዊ መዋቅር ጥላ ሥር፣ በጋራ ኃላፊነት፣ በጋራ አቋም፣ ለጋራ ግብና ዓላማ እንዲሠሩ የሚያደርግ መዋቅራዊ ቅርፅ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአንቀጽ 72 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥታዊ ሥራ በጋራ ለሚወስኑት ውሳኔ በጋራ ተጠያቂዎች ናቸው የሚለው፡፡ 

ለዚህም ነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥታዊ ሥራ በጋራ ለሚወስኑት ውሳኔ ሁሉም ሚኒስትሮች እንዲተገብሩት የሚገደዱት፡፡ የአንድ አምሳልነት ማረጋገጫ፡፡ እዚህ ላይ እ.ኤ.አ በ2003 በእንግሊዝ ካቢኔ ሮቢን ኩክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በኢራቅ ላይ የወሰዱትን አቋም ደግፈው መቀጠል ስላልቻሉ ከሥራ መልቀቃቸውን ልብ ይሉታል፡፡

የሕገ መንግሥት አንቀጽ 75 እውን ክፍተት ያለበት ነውን? 
በፍፁም፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በመርህ ደረጃ ሕገ መንግሥት መርህ እንጂ ልዩ ሁኔታና የአፈጻጸም ድንጋጌዎች መያዝ አይጠበቅበትም፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 75 ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካስቀመጣቸው ኃላፊነቶች በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ እንደሚሠራ ደንግጓል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ አንድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ በላይ ምክትሎች እንዳይሾም በሌላ መልኩ ደግሞ ምክትል አያስፈልገኝም በማለት ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን ለማስቀረት አልሞ በተመጠነ ይዘትና ግልጽ በሆነ መልዕክት የተቀመጠ ድንጋጌ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ ካገኘ ፓርቲ ወይም ካገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የሕግ አስፈጻሚው እንዲያደራጅ በአንቀጽ 56 እና 73 (2) የተሰጠው ሥልጣን ቢኖርም፣ የሕግ አስፈጻሚው አካል ይህን መርህ እንደፈለገ እንዳያደርገውና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋርም ሆነ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ድልድዩ በግልጽ መለየት ስላለበት፣ በሕግ አስፈጻሚው ውረድ ተዋረድ ልጓም ያበጀ ድንጋጌ ነው፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አንድምታ ሕጉ ክፍት ነው ያስባላቸው ምክንያት ‹‹በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ›› የሚለው ለትርጉም ተጋላጭ ነው የሚል ነው፡፡ በመሠረቱ የሕገ መንግሥት ሰነድ በጣም በጥቅል ከመቀመጡ የተነሳ ሕገ መንግሥት የተወሰኑ ጉዳዮችን ብቻ ሊዘረዝር ይችላል፡፡ በአብዛኛው መርህን ብቻ ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ዝርዝር ጉዳዮችን ባይዝም አጠቃላይ ይዘቱን ወይም መንፈሱን ከሕገ መንግሥቱ በመረዳት ሕገ መንግሥቱን መተርጐም ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህል አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የባህላዊ ፖሊሲዎች ሕገ መንግሥታችን ከአንቀጽ 85 ቀጥሎ በምዕራፍ አሥር ሥር ተለይተው በአጭሩ ተቀምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ድንጋጌዎች በጣም ውስንና ጥቅል ሆነው በአጠቃላይ አቀማመጥ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ መርሆዎች በመነሳት በዝርዝር ያልተቀመጡና  ያልተሸፈኑትን ጉዳዮች አጠቃላይ የሰነዱን ይዘት በመፈለግ የመተርጐም ሥልጣን ያለው አካል ሊተረጉም ይችላል፡፡ 

አሁን እየዳሰስነው ባለነው ጉዳይ ግን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተካው ከሰነዶች ማረጋገጫ በሚሰጠው የውክልና ሰነድ አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥታዊ ውክልና ነው፡፡ ይኼው የመተካት ሁኔታ ግን ተግባራዊ የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦታው እስከሌለ ድረስ ነው፡፡ ግልጽ፡፡ አገር ውስጥ፣ ውጭ አገር፣ ለረጅም ጊዜ ዕረፍት፣ አጭር ጊዜ ዕረፍትና መልቀቅን ጨምሮ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በእክል ምክንያት ባልነበሩበት ጊዜ የርዕሰ መስተዳደር ሥራው ቀጥሏል፡፡ ይህ ማለት ግን የሥልጣን ሽግግር እየተካሄደ ነው ማለት አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለመኖሩ የሕግ አስፈጻሚው ወይም በሥሩ የተደራጁት የመንግሥት አካላት ሥራ አቁመዋል፤ የሥልጣን ክፍተት ተፈጥሯል ማለት አይደለም፡፡ በመሠረቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸው የመሪነት ሚና ከፓርቲያቸው አሸናፊነትና የፓርቲው ሕገ ደንብ የመነጨ፣ ፓርቲውና ፓርላማው ባለው እምነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አንቀጽ 75 ብቻውን ተነጥሎ የሚቆም አይደለም፡፡ አንቀጽ 56 እና 72 ላይ በተቀመጡት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመምና የተለያዩ የእክል ክስተቶች በሕገ መንግሥት መመለስ ያለባቸው ናቸውን? 
ከሕገ መንግሥት ከገጽታዎቹ አንዱ የወል እሴት በሆኑና በአገርና ሕዝብ ላይ የተጋረጠ አደጋን ለመቀልበስ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ፣ ሁኔታውን ለመቋቋም መንግሥት ስለሚወሰዳቸው ልዩ ዕርምጃዎችና ዕርምጃዎቹ ስለሚቆዩበት የጊዜ ገደብ፣ ዕርምጃዎቹ ትክክለኛ ስለመሆናቸው ክትትልና ቁጥጥር ስለሚደረግበት ሁኔታ፣ ገዥ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የፌዴራልና ክልል የመንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ስላላቸው፣ ሥልጣናቸውን እንዴት መጠቀም እንደለባቸውና በጉዳዩ ላይ ክትትልና ቁጥጥር ስለሚደረግበት ሥርዓት በምዕራፍ አሥራ አንድ አንቀጽ 93 ላይ በመደንገግ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ተፈጻሚነት ያለውን የአሠራር ሥርዓት ዘርግቷል፡፡

ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም አንደ ዜጋና እንደ ሰው በማናቸውም ጊዜና ወቅት ባልመኘውም የአስቸኳይ ጊዜ ለመሆን የሚያበቃ ክስተት አይደለም፡፡  በመሠረቱ ይህ ጥያቄ መመለስ ያለበት በግለሰቡ፣ በፓርቲውና ቢበዛ በውስጣዊ አሠራር ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የወል ሰነድ ነው፡፡ ማስተናገድ ያለበት የወል የሆኑ መርሆዎችን ነው፡፡ የንጉሡ ዘመን የግለሰብ ሕገ መንግሥት ስለነበር የግለሰብ ጉዳይ አስተናግዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥትን የሚያክል ክቡር ሰነድ ወደ ግለሰባዊ ማዕቀፍ መቀየሩ ግን ከሕግም ሆነ ከሞራል አንፃር ተቀባይነት የለውም፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ይህንኑ አለማድረጉ ደግሞ ትክክል ነው፡፡ ይህንኑ ሕገ መንግሥት ላረቀቁና ተወያይተው ይሁንታቸውን ለሰጡት ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በመሠረቱ አሁን ግለሰብ ላይ የተንጠለጠለ መንግሥት የለም፡፡ ሥርዓትና በሥርዓቱ ሥር የተደራጁት ሕገ መንግሥታዊ ተቋሞች የሚመሩት መንግሥት እንጂ፡፡ ለዚህም ነው በፓርቲያቸው ጥላ ሥር የተሰበሰቡ ሰዎች እንጂ፣ በግለሰብ ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ፓርቲዎች የማይኖሩት፡፡ 

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት እውን በተነሳው ጭብጥና ተያያዥ ነጥቦች ላይ ከቀደምት ሕገ መንግሥቶች የሚነፃፀር ነውን? የደርግ ወይም የኃይለ ሥላሴ ሥርዓት  የወላድ መካን የሆኑት በሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት መርሆዎች በተነሳ ጉዳይ ነውን? 

እንደ ዜጋ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በተነሳው ጭብጥም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ነጥቦች ላይ ከቀደምት ሕገ መንግሥቶች የሚነፃፀር አይደለም፡፡ የደርግ ወይም የኃይለ ሥላሴ ሥርዓት የወላድ መካን የሆኑትም በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥታዊነት መርሆዎች በተነሳ ጉዳይ ሳይሆን፣ ሥርዓቶቹ በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥታዊነት መርሆዎች ያልተቃኙና ዘመኑ የሚጠይቀውን ምላሽ ባለመስጠታቸው ነው የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ታሪካዊ ዕድገት ስንመለከት ክብረ ነገሥትና ፍትሐ ነገሥት እንደ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ከወሰድናቸው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ሥርዓት የአምላክ ትዕዛዝ ነው ይሉናል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ነገሥታት በሚለው ምዕራፍ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች እንዳለው ‹‹መሪ በእግዚአብሔር ብቻ የሚሾም በመሆኑ፤ ሁላቹሁም ለመሪዎቻችሁ ሥልጣን ተገዢ መሆን ይኖርባችኋል፡፡ ሁሉንም መሪዎች ሥልጣን ሰጥቶ የሾማቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለሆነም መሪን የሚቃወምና መሪ ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ፈቃድና በመሪው ላይ ያመፀ ነው፡፡ በመሪዎቻቸው ላይ የሚያምፁ ከፈጣሪያቸው ቅጣትን ይቀበላሉ፤›› በማለት የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር በዘርና በደም ላይ መሠረት ያደረገ እንዲሆን አደርጎታል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከ1923 ዓ.ም. በፊት የተጻፈና በሕገ መንግሥትነት በይፋ የታወጀ ሕገ መንግሥት እንዳልነበራትና የመጀመሪያው እንደሆነ ተቀብለን፣ ይህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት ከመውጣቱ በፊትና ሲወጣ በአገሪቱ ውስጥ ደም ያፈሰሱ አንገብጋቢ የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች የነበሩ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱ ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀና የወጣ ሳይሆን፣ በወቅቱ ወራሴ መንግሥቱ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተወላጆች ብቻ እንዲተላለፍ በሕግ ለመደንገግና የዘውዳዊው ሥርዓት የግዛት ሉዓላዊነት ሕጋዊ መሠረት ለመጣልና የመኳንንቱና የመሳፍንቱን ጥቅም ለማስከበር የተደነገገ ሕገ መንግሥት እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም፡፡ እንደ ፊታውራሪ ደምስ ወልደ አማኑኤል ከሆነ ይኼው ሕገ መንግሥት የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን መመለስ የቻለ ሥር ነቀል የአስተዳደር ለውጥ ይቅርና ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንኳን አላመጣም፡፡ ለውጥ አመጣ ቢባል የየክፍለ ሀገሩ ባላባቶችና መሳፍንት በአዲስ አበባ እንዲቀመጡ በማድረግ በአፄው ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ንጉሠ ነገሥቱ በመሰላቸው መንገድ ቀርፀው ለሕዝቡ በስጦታ መልክ ያወጁት እንደሆነ በመግቢያው ላይ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በአንቀጽ 3፣4፣5 እና 17 የንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን ከኢየሩሳሌም ንጉሥ ከሰለሞንና ከኢትዮጵያዊትዋ ንግሥት ንግሥተ ሳባ ከተወለደው ቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ ተያይዞ ከመጣው ከንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ዘር ከተወለደው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትውልድ እንዳይወጣ፣ ለልጅ ልጆቻቸው እንዲተላለፍ ታመውና ሞተው አይደለም ከዘራቸው ሰው ቢጠፋ እንኳን በማህፀን ውስጥ ያለ ሽል እንዲወርስ በሕግ የወሰነ ሕገ መንግሥት ነው፡፡

በ1948 ዓ.ም የተሻሻለው ሕገ መንግሥት እንዲሁ በንጉሠ ነገሥቱ ታወጀ፡፡ ይህ ሕገ መንግሥትም እንደ ቀዳሚው የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ ያልፈታ፣ በአገሪቱ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ትግል ለማብረድና ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ መስጠት የማይችል፣ በተቃራኒው በአንቀጽ 4፣5፣ 11፣ 12 እና 13 የንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን ከኃይለ ሥላሴ ትውልድ እንዳይወጣ፣ ለልጅ ልጆቻቸው እንዲተላለፍ ታመውና ሞተው አይደለም ከዘራቸው ሰው ቢጠፋ እንኳን በማህፀን ውስጥ ያለ ሽል በሞግዚቱ በኩል እንዲወርስ በሕግ የወሰነ ነበር፡፡

‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› በሚል መጠሪያ የሚጠራ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት ራሱ ባወጣው ቀላጤ የ1948 ዓ.ም. አዋጅ ከማገዱም በተጨማሪ የመሰለውን ሕግ እያወጣ፣ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በስብዕናና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀሎችን በመፈጸምና የጦርነትን ሕግጋት የሚጥሱ ወንጀሎችንና የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመ ብዙ ማጣቀሻና ማስረጃ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ እስከ 1980 ዓ.ም ድረስም ቀላጤ እንጂ ሕገ መንግሥት የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥትም ቢሆን ኢሠፓ ብቸኛ የፖለቲካ ፖርቲ መሆኑን ከመደንገጉም  በላይ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በአሃዳዊ መንግሥት ሥር የራስ ገዝ አስተዳደር እንደሚኖራቸው ከመደንገግ ያለፈ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ መሠረታዊ መልስ የሚሰጥ ሕገ መንግሥት አልነበረም፡፡ ታድያ እንዴት ነው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ከእነዚህ ሕገ መንግሥታት የሚነፃፀረው? ለግለሰቦች በግለሰቦች ከታወጁት ጋር? ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ፡፡

የአንድን አገር የሕግ ሥርዓት የፖለቲካ እንቅስቃሴና ኃይሎች የሚወስኑት ሲሆን፣ የሕግ ሥርዓቱ በተራው የፖለቲካ ሥርዓቱን ይቀርፀዋል፤ ይወስነዋል፡፡ ሕገ መንግሥት ሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መሣሪያም ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ራዕይ ሲቀርፁና ሕገ መንግሥታዊ ግቦችንና ዓላማዎችን ለይተው ሲያወጡ የሚያማልሉ ንድፈ ሐሳባዊና ፍልስፍናዊ ሐሳቦችንና ትንታኔዎችን መነሻና ማጣቀሻ በማድረግ አይደለም፡፡ ይልቁንም ለዘመናት በጋራ በኖሩባቸው ጊዜዎች በአገሪቱ ውስጥ አንገብጋቢና ቁልፍ የሆኑትን ችግሮች በመለየት፣ ችግሮቹ በወቅቱ በቂና አጥጋቢ መፍትሔ ባለማግኘታቸው የደረሰውን ሰቆቃና እልቂት እንደዚሁም ቁሳዊ ውድመት፣ ካለፉበት የሕይወት ዘመን ተሞክሮና ከተጨባጭ መረጃዎች በመረዳት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነውን በሰከነ ሁኔታ በማሰብ ነው፡፡ 

‹‹በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ የሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤›› የሕገ መንግሥቱ ዓላማ በመግቢያው ላይ እንዳሰፈረው፡፡

ይህ ማለት እንደ ዘውዳዊውና አምባገነኑ መንግሥታት የግል ፍላጎት የሚንፀባረቅበት ሕገ መንግሥት ሳይሆን፣ የጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ለሕዝብ የሚሆን ክቡር የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡  ሕገ መንግሥቱ የግለሰብ ሳይሆን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት መገለጫ፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት የሚያስከብር፣ የመንግሥትን አሠራር ለሕዝብ ግልጽ የሚያደረግና ከቀደምት ሕገ መንግሥቶች በተለየ ሁኔታ የፓርላማ ሥርዓት ያስተዋወቀ በመሆኑ፣ ቢያንስ በእነዚህና በሌሎች ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች ከቀደምቶቹ እጅግ በጣም ይለያል፡፡  ለዚህም ነው የሥልጣን ሽግግር ቢኖር እንኳን በዘር ወይም ደማዊ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅድው መርህ ሊሆን ይገባል ሲል የደነገገው፡፡ ግለሰብ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትና ሥርዓት አለ የሚለው፡፡ የጋራ እሴቶች ላይ በማጎልበት የተመሠረተው፡፡ የደርግና የኃይለ ሥላሴ ሥርዓት የወላድ መካን የሆኑት ግን ግለሰባዊ መርህ ላይ ስለተንጠለጠሉ፣ በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥታዊነት መርሆዎች ላይ ስላልተመሠረቱና ራዕይ አልባ ስለሆኑ ነው፡፡

የሌሎች ሚኒስትሮች ቢሮዎች እውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸውን? የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሥልጣን ወሰንና እንደ አንድ አካል መቆጠር እርግጠኛነት በሕገ መንግሥቱ አልተንፀባረቀም? 

ይህ አባባል ለእኔ አዲስ ግኝት ነው፡፡ ነገር ግን የተሳሳተ ግኝት፡፡ መሳሳት ነውር አይደለም ሊታረም ግን ግድ ይላል፡፡ ለመሆኑ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ በውረድ ተዋረድ ለይቶ የሚያውቃቸው የሕግ አስፈጻሚው ከፍተኞቹ የሥልጣን እርከኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትላቸው አይደሉም እንዴ? ናቸው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 73 እና 75 ብቻ ማየቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ሚኒስትሮች እኩል ኃላፊነት የተጣለባቸው፣ በአንድ መንግሥታዊ መዋቅር ጥላ ሥር፣ በጋራ ኃላፊነት፣ በጋራ አቋም፣ ለጋራ ግብና ዓላማ እንዲሠሩ የሚያደርግ አደረጃጀት ነው ያለው፡፡ አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ የሚያደርግበት አግባብ የለም፡፡ ለማጣቀሻ የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 72 ይመልከቱ፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ሕመም ለኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግር ምክንያት ሊሆን ይችላልን?  የሕገ መንግሥቱ ዘላቂነትስ? 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ሕመም ለኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግር ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9(3)፣ 45፣ 55(13)፣ (17)፣ (18)፣ 56፣ 72 እስከ 77 ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግር እንዳይኖር የሚከላከሉ ፈውሶች ናቸው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የተቋቋመው መንግሥት ፓርላሜንታዊ የመንግሥት ሥርዓት የሚከተል፣ ባለሙያዎቹ እንደ ምሳሌ ካቀረቡት የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚያራምዱ አገሮች (አሜሪካና ፖላንድ) ፍፁም የተለየ፣ በአንድ ግለሰብ (ፕሬዚዳንት) የተንጠለጠለ ሳይሆን፣ በጋራ ኃላፊነት (collective reponsiblity) ላይ የተመሠረተ፣ መንግሥት ከመሠረተው ፓርቲ መርህ ጋር የተቆራኘ፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትና ሥርዓት ያደራጀ፣ ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻውን የተተወ ሳይሆን፣ ለሥልጣን ባበቃው የፓርቲው መርህና በዚሁ ጥላ ሥር በተደራጀው የአስፈጻሚ አካላትን ጨምሮ ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት (ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሌሎች ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች)  ጭምር ነው፡፡ ሥርዓት አለን እስካልን ድረስ ግለሰቦች በዚህ ሥርዓት ይስተናገዳሉ፡፡ ይህ ስጋት ለእኔ ምክንያቱ አልታየኝም ሕገ መንግሥቱ በቂ ፈውስ ነው፡፡

በመጨረሻ የሕገ መንግሥቱ ዘላቂነት ላይ አስተያየት ልሰንዝርና ላብቃ፡፡  ሕገ መንግሥት ማሻሻል ማለት በአጭር አነጋገር ለሕገ መንግሥት ማስተካካያ የሚደረግበት ሒደት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ሕገ መንግሥት መሻሻል እንደሚችል ሁሉ በቀላሉና በማናቸውም ጊዜ የሚሻሻል ባለመሆኑ፣ በእያንዳንዱ አገር ነባራዊ የዕድገት ሒደት በሕገ መንግሥት ያልተሸፈኑ ጉዳዮች እየተሸፈኑ ይሄዳሉ፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ሒደት ክለሳ (Revision) ወይም አብዮት (Revolution) ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም መሻሻል ማለት የለውጥ ሒደት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ሒደት በአንድ ሕገ መንግሥት ሰነድ ውስጥ የለውጥ ዕርምጃ ወይም ዕድገት የሚታይበት ሒደት ነው፡፡ አብዛኛው ጊዜ ማሻሻያ የሕገ መንግሥቱን ቃላት፣ ሐረግ፣ ዓረፍተ ነገር ወይም አንቀጾችን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ በሚሻሻሉት ፈንታ በከፊል መጨመር፣ በከፊል መቀነስ ወይም ሙሉ በሙሉ መለወጥ ሊሆን ይችላል፡፡  ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ለውጦች ከሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ ዓላማ፣ ግብና መንፈስ ጋር በሚጣጣም ሁኔታ ነው የሚደረገው፡፡  የሕገ መንግሥት ማሻሻል ሒደት ሕገ መንግሥቱ ሕይወት ኖሮት ለረጅም ጊዜ እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ሕግም ሆነ ሕገ መንግሥት ከኅብረተሰብ ዕድገት ጋር አብረው ማደግ የግድ ይላል፡፡  ይህ ማለት ሕገ መንግሥቱ ዘላቂ ሆኖ እንዲበለጽግ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን ባከበረ መንገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚቻል በአንቀጽ 104 እና 105 የደነገገው፡፡

http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/303-commentary/7239-2012-07-28-11-06-24.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር