ሲዳማ ዞን “አስተዳዳሪ” ሚሊዮን ማቴዎስ ሐምሌ 04/2004 የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫን በተመለከተ ህዝቡ ያለውን ስሜት ለመግለጽ የተሰጠ መግለጫና አቅጣጫዎቻችን



ሲዳማ ህዝብ ክልል ለመሆን ያስተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ሰሞኑን የዞኑ “አስተዳዳሪ” ሚሊዮን ማቴዎስ በሐምሌ 04/2004 እትም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ደኢህዴን ጋዜጣ ላይ እንደወትሮው የጓዶቹ መግለጫዎችና ዜናዎች ሁሉ ንቀት የበዛበትና ተራ ስድብ ያዘለ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ የጋዜጣው ተነባቢነት ከሚገመተው በላይ መጥበቡና በአጠቃላይ በህዝብ ዘንድ እንኳንስ አሁን ባለንበት ሁኔታ ቀድሞውንም ቢሆን ተቀባይነት የለሌው ከመሆኑ የተነሳ ወደሰፊው ህዝብ ጆሮ መድረስ በነበረበት ፍጥነት በሰፊው ባይደርስም ከአጀንዳው አንገብጋቢነት አንጻር አሁን የመነጋገሪያ ርዕስ በመሆኑ ይሄንን ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ጋዜጣ በፊት ገጹ ላይ “የሐዋሳ ከተማ ነዋሪውን ህዝብ የሚወክል አመራር እንዲኖሩት የቀረበውን አቅጣጫ በመቃወም በቅርቡ የሐዋሳ ከተማ ተሸጠች የሚል ውዥምብር በመንዛት ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት ሲሯሯጡ የነበሩ ፀረ-ልማት ኃይሎች በመላው ህብረተሰብ ትብብርና በድርጅቱ የጠራ መስመር ሊከሽፍ ችሏል” በማለት የነበረውን የህዝብ ቁጣ “ውዥምብር” ብለው በማጣጣል እርሱም ቢሆን በሲዳማ ህዝብና በድርጅታቸው መክሸፉን አስነብበውናል፡፡ እዚህ ላይ ተቃውሞው መነሻ እንዳለው ካለመካዳቸውም በላይ በተቃውሞው የተሳተፉት እነርሱ እንደሚሉት “ፀረ-ልማት ኃሎች” ሳይሆኑ ሰፊው የሲዳማ ህዝብ መሆኑን “ውዥምብር” የሚለው ቃላቸው ያሳብቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ጥቂት “ፀረ-ልማት ኃሎች” “ውዥምብር” መፍጠር አይችሉምና፤ ሊፈጥሩ የሚችሉት ሹክሹክታ፣ ሀሜትና ጥቂት “ንፋስ” ነው፡፡ “ውዥምብር” ሊኖር የሚችለው ሃይለኛ የሆነ እንቅስቃሴና ተቃውሞ ሲኖር ነው፡፡ ይሄንንም እውነታ ለመግለጥ እየሞከርን ያለነው ከሲዳማ ውጭ ላሉ አንባቢያን ነው እንጂ የሲዳማ ህዝብ ይቅርና ሲዳማ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም በእውነት የሚያምንና ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ ተቃውሞው ህዝባዊ መሆኑን ሊክድ አይችልም፡፡ እውነቱን እንናገር ቢባል “የሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ውሳኔ የእኔ ውሳኔ ነው፤ የመጣውን ‘ሜትሮፖሊታን…’ የሚለውን የመንግሥት አጀንዳ እቃወማለሁ…” የማይል የሲዳማ ተወላጅ የሆነ ሽፈራውና አሁን ባለንበት ሁኔታ ሚሊዮንን ጨምሮ ቢቆጠር ከአምስት የማይበልጡ የደኢህዴን ካድሬዎች (ባንዳዎችካልሆኑ ሌላ ሰው እንደማይገኝ በእግዚአብሔር ስም እንምልላችኋለን፡፡ ይሄንን እውነታ እነርሱም ያውቁታል፡፡
በመቀጠልም በገጽ ዋና “አስተዳዳሪ” የተባለው ግለሰብ የሰጠውን ቃለምልልስ ያቀረቡ ሲሆን ጋዜጠኛው ያቀረበው የመጀመሪያው ጥያቄ “ሰሞኑን በሀዋሳ ከተማና በአንዳንድ የሲዳማ ወረዳዎች መነሻው ከየት እንደሆነ የማይታወቅ ውዥምብር ሲናፈስ ነበር፡፡ ለመሆኑ የዚህ ውዥምብር መነሻ ምክንያቱ ምንድነው? የሚል ነበር፡፡
እዚህ ላይ ልብ ሊባልልን የሚገባው ጉዳይ ከላይ እንደገለጽነው ጋዜጣው በመጀመሪያ ገጹ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪውን ህዝብ የሚወክል አመራር እንዲኖሩት የቀረበውን አቅጣጫ በመቃወም ጥቂት ፀረ-ልማት ሃይሎች ውዥምብር መፍጠራቸውንና ይህም መቀልበሱን ካስነበበን በኋላ አሁን መነሻው የጠፋውና የማያውቀው መሆኑን ገልጾ መነሻ ምክንያቱን የመጠየቁ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው መነሻው ከየት እንደሆነ የማይታወቅ ውዥምብር ከሆነ እንዴትስ አውቆ እንዲመልስለት አስተዳዳሪውን እንደጠየቀው ልብ ካልን እውነታውን እያወቁ ያላወቁ ለማስመሰልና የውሸት ወሬ/ፕሮፓጋንዳበመፍጠርና በመጻፍ በሚጥሩበት ወቅት አካሄዱ እንደጠፋባቸው በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ መቼም መልሱ ግልጽ ቢሆንም ወደጥያቄው ስንመለስ “አስተዳዳሪው” ሲመልስ በሐዋሳ ከተማ የእድገትንና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግም የከተማዋን የአመራር ጥያቄ በሚመለከት ለውይይት የቀረበ ሰነድ መኖሩን በመጥቀስ በሰነዱ ላይ ማእከላዊ ኮሚቴውና ሥራ አስፈጻሚው በሰፊው ከተወያየ በኋላ በከተማ፣ በዞንና በክልል ደረጃ ያሉ የሲዳማ ጓዶች እንዲወያዩ ተደርጎ በየደረጃው የተነሱ ጉዳዮች ተገምግመው ወደፊት መቀጠል ያለባቸው መድረኮች የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት ላይ እንዳሉ አሉባልታው በአንድ ጊዜ መናፈስ መጀመሩን በማስረዳት ይህም የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ በውይይት መድረክ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮች ለእነርሱ ብቻ ለውይይት የቀረበውን ሰነድ ሀሳብ አዛብተው ውጭ በተለያየ መልኩ አኩርፈው ለተቀመጡ “ፀረ-ልማት ኃይሎች”ና በግምገማ ላኮረፉና ስልጣን ናፋቂዎች አሳልፈው በመስጠታቸው እንደሆነ ገልጸው እነእከሌ ሐዋሳን ሸጡ እያሉ እዳስወሩ በመግለጽ የተሸጠ ነገር እንደለለ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ቀርቦ ስለነበረው ሰነድ አስፈላጊነት ሲገለጽ በሐዋሳ ከተማ የእድገትንና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለተባለው የሲዳማ ህዝብ ሲህዴድ ፈርሶ (ተጋብቶደኢህዴን ከሆን በኋላ ያተረፈው ነገር ቢኖር በልማትና ዕድገት ቦታ መፈራረስና ሥራ መፍታት በመልካም አስተዳደር ቦታ በደል፣ ሁከት፣ እልቂትና ስደት ሆኗል፡፡ የልማት ተቋማቱ በደኢህዴን አፈቀላጤዎችና አውደልዳዮች እየተመሩ ፈራርሰዋል፡፡ የልማት ማህበሩ ወደፊት ከመሄድ ያለበት ሰልፈ በመርገጥ ላይ ይገኛል፡፡ ወትሮም ቢሆን የእነሽፈራው ሰላዮች፣ ጆሮ ጠቢዎች፣ ታማኞችና ዘመዶቻቸው የሚቀጠሩበት፣ የሚሾሙበት፣ ሽፈራውን ጨምሮ ሲቸገሩ የማይመለስ ገንዘብ የሚበደሩበትና አበል የሚበሉበት ነበር፤ አሁንም ይህ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ሌላው ልማት የማይታሰብ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ሽፈራው በክልሉ ሌሎች አከባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን እያስመረቀ ጊዜ ስላጣ ሳይሆን አይቀርም በሲዳማ ዞን ግን አንድ መንገድ እንኳ ሊሠራ አልቻለም፡፡ ከአለታ ወንዶ በንሳና ሌሎች አከባቢዎች አስፋልት ይሠራላችኋል ተብሎ የክልል ውሳኔው እንዲዘገይ ሲደረግ ቃል በተገባው መሰረት ከአራት አመታት በፊት የተጀመረው መንገድ ዛሬ “አስፋልት ሳይሆን 4ኛ ደረጃ ኮንክሪት ነው የተባለው” ተብሎ ያውም አንድ ሦስተኛው እንኳ ሊሠራ አልቻለም፡፡ ተሠራ የተባለው የከብቶች በረት የሚመስል ነገር ሲሆን አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር እየፈረሰ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ደጋግመን ለመጻፍ እንደሞከርነው የሐዋሳ ከተማ ከ1995 እስከ 1997 በኃይለማሪያም አመራር ሥር የተመራ ሲሆን በዚህ ወቅት በህዝባችን ላይ የነበረውን መከራ፣ ፍትህ ማጣት፣ እንግልትና ወከባ በቃላት ለመግለጽ ከሚቻለው በላይ ሲሆን ይሄንኑ ለህዝባችን ለማስረዳት መሞከር ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው፡፡ በክልል ደረጃም ቢሆን የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት አብሮ ከኖረው ህዝብ ጋር ለአንዴና ለመጀመሪያ ጊዜ ያዋጋና በህዝባችን መሬት ላይ የራሱን ወገን አምጥቶ ያሰፈረ ደፋር ሰው ነው፡፡ ኃይለማሪያም፡፡ ሌላው ቀርቶ ተራ የእንሰት ኮባ ጀርባቸው ላይ ተሸክመው ሐዋሳ ከተማ ይወጡ የነበሩ እናቶች መሬት አታስቀምጡም ተብለው እንደተሸከሙ ከተማ ለከተማ ይዞሩ የነበረው የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ (ትራጀዲድራማ ነው፡፡ በዚህ በተገለጸው ወቅት የከተማዋ እድገትና ልማትም ተመሳሳይ ነበር፡፡ የፒያሳ አንዷ አስፋልት እንኳ የተጀመረችበት ቆማ ከተማዋ አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን ከእጃቸው ከወጣች በኋላ ነው ተሠርቶ ያለቀው፡፡ ደኢህዴን/ኃይለማሪያም ማለት በ1994/ም ተመሳሳይነት ያለውን አጀንዳ ባለመቀበል ሰላማዊ ተቃውሞውን ሊያሰማ የወጣውን የሲዳማ ህዝብ ከፌዴራል ለመጣው ሠራዊት አመራሮች (“ህዝቡ ሰላማዊ ስለሆነ አንመታም በሠላማዊ መንገድ እንመልሰው…” በማለታቸውየትዕዛዝ ደብዳቤ በመስጠት ያስጨፈጨፈ ሰው ነው፡፡ ታዲያ የቱን ልማት የመሥራት ተሞክሯቸውን፣ የቱን አቅማቸውንና ዓላማቸውን ሊነግሩን ነው፡፡ የቱንስ ልማት አሳይተው ሊያሳምኑን ነው፡፡ የቱን አስፋልት፣ የቱን የገጠር የጠጠር መንገድ ሠርተው ያውቃሉየቱን ልማት ነው የሚነግሩን ወይስ እነርሱ ተቀይረው ሌላ ደኢህዴን ተፈጠረለመሆኑ ሌሎች ኃይለማሪያም ወዘተ የሚባሉ ሰዎች አሉ ወይስ ያው “የእኛው” ኃይለማሪያም ነውያው “የእኛው” ኃይለማሪያም መሠለን፡፡ የእርሱ ልማትና ሰላም የለም እንጂ ካለም በአፍንጫችን ይውጣ፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተባለው ተራ ማስመሰልና ውስጠ ወይራ የነሚሊዮን ጌቶች ውሸት እንጂ ሊያረጋግጡ ያቀዱት የህዝብ ተጠቃሚነት የለም፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሐዋሳን ሙሉ ለሙሉ ራሳቸው ሲያስተዳድሩ የነበረው ሁኔታ ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ሳይሆን አንድን ወገን ለይቶ የሚያውክና የሚያደኸይ ነው የነበረው፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ገበያ ውስጥ እንኳ ሳይቀር የሚነግዱበት ቦታ ቀርቶ ሴት ወንዱን መቆሚያ መቀመጫ የሚያሳጣ አሠራር ነው የነበረው፡፡ ተጠቃሚ ይሆናል የሚሉት ህዝብ ሲዳማን የሚጨምር ከሆነ እውነታው ይህ ነበር፡፡ በርግጥ የራሳቸው ብሄር የሆኑ የትየለሌ ሰዎች በሚገርም ፍጥነት ተጠቃሚ የሆኑበት ሁኔታ ቢካድም ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ይሆናል፡፡ የእከሌ ብሄር መንደር ተብሎ እስኪጠራ የአንድና ሁለት ብሔር አባል የሆኑ ብቻ የሚኖሩበት መንደሮችና ብሎም ቀበሌዎች ተፈጥረው አልፈዋል፡፡ ከነኃይለማሪያም ወገኖች በቀር ሌላ ኢትዮጵያዊ የማይታይባቸው ማህበራትና የመንገድ ዳር ሱቆች ቁጥር ስፍር አልነበራቸውም፡፡ ሀዋሳ ሐይቅ ዳር የአንድና ሁለት ብሔር አባላት ሲሳይ እንደሆነ ቀርቷል፡፡ ታዲያ የህዝብ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚለው ማደናገሪያቸው የትኛውን ህዝብ እንደሚገልጽ አሁን ላይ ሆነን ግልጽ ይመስለናል፡፡
እስኪ ሚሊዮንን እንጠይቅ ለመሆኑ አንተ ይሄንን እውነታ አታውቅምበውይይት መድረክ የተገኙ “አንዳንድ” አመራሮች ሰነዱን አዛብተው ህዝቡን እንዳሳሳቱ ተናግረሃ
፤ ለመሆኑ ከዚህ ቀደም እንደጻፍነው ሰነዱ ወዲያው እጃችን እንደገባ ታውቃለህ? ከአንተ አሥር እጅ መረዳት የሚችል ሰው ሊኖር እንደሚችል እንኳ አልተረዳህም፡፡ ሰነዱን በሚገባ አንብበን ገምግመናል፡፡ ስለሰነዱ ባለ 24 ገጽ ጽሁፋችንንና አመራሩ ሰነዱን አዛብተው ተረጎሙት ላልከው ደግሞ ባለ ገጽ የእኛን ጽሁፍ ብትችል ብታነብ ደስ ይለናል፡፡ ሰነዳችሁ ግን ተራ ስድብ፣ ሸርና ሲዳማ በሀዋሳና በአከባቢው ባሉ ከተሞችና የኢኮኖሚ ፋይዳ ባላቸው የገጠር ቀበሌዎች ላይ ያለው ሚና እንዲከስም የተወጠነ ውል እንጂ ምን ሳይንስ አለውስለዚህ አመራሮቻችሁን አታሸማቋቸው፡፡ እርግጥ ነው እዚህ ላይ “አስተዳዳሪው” አንድ እውነት ተናግሯል፡፡ በአመዛኙ አመራሮቻቸው አልተቀበሏቸውም፡፡ ስለዚህም አልተሳካላቸውም፡፡ በርግጥ ልናመሰግናቸው ሲገባ አላመሰገናቸውም፡፡ እነዚህ የዞኑና የሐዋሳ ከተማ አመራሮች አመራሮቻችን ናቸው፣ አጽድቀናቸዋል፣ የእሥራኤል አምላክ ብሎም የሲዳማ አምላክ አብሯቸው እንዲሆን ሁሌም ጸሎታችን ነው፡፡ ሁሌን ከጎናቸው ነን፤ ብቻቸውን እንዳይደሉም በደንብ እንደሚያውቁ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ህዝብና እግዝአብሄር አብሯቸው ካለ ብቻውን ያለው ሽፈራው ዛሬ ሚሊዮንን ቢጨምር ምን ያስፈራል፡፡ ስለዚህ ሚሊዮን እዚህ ላይ ሊያስተውል የሚገባው ሰነዱን የተቃወሙት “አንዳንድ” አመራሮች ሳይሆኑ የተቀበሉት (እርሱንም ወደው ሳይሆን ተቸግረው ሆዳቸውንና ስልጣናቸውን አስበልጠውእጅግ በጣም ጥቂት አመራሮች ብቻ መሆናቸውን ነው፡፡
በጣም የገረመን የከተማዋ የአመራር ጥያቄ ሌላኛው ሰነዳቸው መሰረት ያደረገው መሆኑ የመገለጹ ጉዳይ ነው፡፡ መቼም የከተማዋ የአመራር ጥያቄ ማለት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማለት አይመስለንም፡፡ የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ያኔ እነኃይለማሪያም ሲያጨማልቁ ከነበረበት በእጅጉ እንደሚሻል ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው አይክድም፡፡ ያኔማ ተወልደን ባደግንበት ቀያችን ቤታችንና መኖሪያችን ባለበት ቀበሌ መታወቂያ ማግኘት ዳገት ሆኖብን ነበር፡፡ ፍጹምነት ያለው ለውጥ ለማምጣት ግን የእነርሱ እጅ ሙሉ ለሙሉ መውጣት አለበት፡፡ አሁንም በቀጥታም ሆነ በስልክ ግራ እያጋቡ ያሉት የእነኃይለማሪያም እንደራሰዎች እነአለማዬሁ ናቸው፡፡ የከተማዋ አመራር በራሱ አቅዶ እንዳይሠራ በእጅ አዙር ተከልክሏል፡፡ ለዛሬው የህዝብ ቁጣ ሌላኛው ማራገቢያ የሆነውም ይሄው ጉዳይ ነው፡፡ እያየንና እየሰማን እያዘንንና ወደውስጥ እያለቀስን ነበር የቆየነው፡፡ ሰላማዊ ህዝብ እንደመሆናችን መጠን አይተን ያላየን ሰምተን ያልሰማን ለመምሰል ሞከርን፡፡ ይሄንን እንደሞኝነት የቆጠሩ ብልጣብልጦች ግን ለዛሬዋ ቀን አደረሱን፡፡ ለእነርሱ “የብብታቸው” የሚወርቅበት ለእኛ ግን የድል ዋዜማ ለሆነችው ለዚህች ቀን፡፡ ለዚህ ነው ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው የምንለው፡፡ ስለዚህ የከተማዋ የአመራር ጥያቄ ማለት የይገባኛል ጥያቄ፣ የባለቤትነት ጥያቄ፣ ሐዋሳን ጨምሮ ሌሎች የኤኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ከተሞችንና የገጠር ቀበሌዎችን ማን ይምራው የሚል ጥያቄ እንደሆነ ይገባናል፡፡ “አስተዳዳሪው” ይሄንንም አያውቅም ማለት ነው ወይስ አሁንም የስልጣን ነገር ሆነበትእስኪ እርሱን ለጊዜው እንተወውና ወደ ውስጠወይራ እቅዳቸው እንመለስ፡፡ ማን ይምራው የሚለው ጥያቄ እኮ በህገ-መንግሥታችን የተረጋገጠ ነው፡፡ መቼም ይሄንን የህግ ኪዳን መንግሥት ለራሱ እንደሚመቸው መተርጎም ከጀመረና ሳይመቸውም ሲቀር እንዳሻው ተውኝ ማለት ከጀመረ የቆየ ቢሆንም ኪዳን ነውና እኛ መጥቀሳችንንና በርሱ እየተቃኘን መመራታችንን አንተወውም፡፡ ለመሆኑ ይህ የህግ ኪዳን በተለይ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚለው ዋናው ያገናኘንና የህጉ ምሰሶና እስትንፋስ መሆኑን ኢህአዴግ አጣው እንዴእንዲህ መሠረታዊነት ባለው ነገር ዙሪያ ደኢህዴን/እነኃይለማሪያም በእሣት ሲጫዎቱ ኢህአዴግ አያውቅም ማለት የዋህነት ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ኢህአዴግ ሲዳማን አጥቷል ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ የባሰ መለያየት እንዳይመጣ የበለጠ ሳይረፍድ አሁን በረፋዱም ቢሆን ቢያስብበት ጥሩ ነው፡፡ እነኃይለማሪያም በሐዋሳ ላይ እግዝአብሔር ምስክራችን ነው ከእንግዲህ አይወስኑም፡፡ ስለዚህ የሐዋሳ አስተዳደር ጥያቄ የሲዳማ ጥያቄ እንጂ የማንም አይደለም፡፡ የሶዶ አስተዳደር የሲዳማ ጥያቄ ሆኖ አያውቅማ፡፡ አሁን ግን ጥያቄው የሐዋሳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጥያቄው የሲዳማ ክልል ጥያቄ ነው፡፡ በእውን ሲዳማ ክልል ሳሆን ከዚህ በኋላ ቤቱ የሚገባ ይመስላችኋልአሁን አቅዳችሁ ተነስታችሁ እንዳላችሁት ለአንዱ ገንዘብ በመስጠት፣ ለሌላው ስልጣን፣ በዚህ ያልተሸነፈውን በአሸባሪነትና ህዝብን በመቀስቀስ ስም እያሰራችሁ የምትዘልቁና ሲዳማን የምታሸንፉ፣ የሲዳማንም ክልል እውን ከመሆን የምታስቀሩ ይመስላችኋልአይምሰላችሁ አሁን ሁሉም ቆርጦ ተነስቷል፡፡ እነኃይለማሪያምን ከፊታችን ገለል ለማድረግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አምነናል፡፡ ልብ በሉ ከኢህአዴግ ጋር ከዚህ ቀደም የተባበርነው በጠቀስነው የህገመንግሥቱ ምሰሶ አንቀጽ ነው፡፡ እርሱ ከተሸራረፈ ለምን የምንጨነቅ ይመስላችኋልሲዳማ ክልል የሚሆነው በደኢህዴን መቃብር ላይ ነው አለ አሉ የደኢህዴኑ አለማየሁ፡፡ ወይ አለማወቅ፡፡ ደኢህዴንማ አሁንም መቃብር አፋፍ ላይ ነው ያለው፡፡ እኛማ አፈረስነውኮ፡፡ የርሱ ሞት ሰርጋችን ነው አልንኮ፡፡ የደኢህዴን ሞት ለቅሶ የሚሆነው ለእናንተ ለተጠቃሚዎቹ እንጂ ለእኛ ሰርጋችን ነው፡፡ በበርካታ ወረዳዎች የደኢህዴን አባላትና ካድሬዎች (ህዝብንና ህገ-መንግሥቱን የሚወግኑመታወቂያ መልሰዋል፡፡ ባይሆን አንድ ጉዳይ እንንገራችሁ፡፡ አሁን ጊዜው ለኢህአዴግ ጥሩ አይደለም የሚለው ወሬ ከእንግዲህ አይሠራም፡፡ ራሳችንን ማስተዳደር ከተከለከልንና የህገ-መንግስቱ እስትንፋስ ያልነው አንቀጽ ከተሸራረፈ አይደለም ደኢህዴን በኢህአዴግ መቃብርም ቢሆን ሲዳማ ክልል ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ሲዳማ አሁንም ክልል ነው፡፡ ከደኢህዴን ላይ እውቅና ካነሳን፣ ከናቅነውና አይወክለንም ካልን ቆየን፡፡ በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል ይለናል ቅዱስ ቃላችን፡፡ ደኢህዴንን ለቀብር አጭተነዋል አሜን፡፡ እየተጠባበቅን ያለነው የቀብር ሥነ-ስርኣቱን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚጠራ ፊትህ ፈላጊ ሲፈራ፣ ሲደነግጥ፣ አላማውን ሲተውና ሲሸነፍ አይታችሁ ወይ ሰምታችሁ ታውቃላችሁየእግዝአብሄርን አሠራር የሚታውቁ ከሆነ መልሳችሁ አይደለም ነው የሚሆነው፡፡ እኛ ተነስተናል፡፡ ጌታ ይሠራልናል፡፡ አሜን፡፡ ስለዚህ ለሐዋሳ ከተማ አተዳደር ጥያቄ ሌላ ሰነድ አያስፈልገንም ሰነድ አለን፡፡ ህገ-መንግሥቱ፡፡
በመጀመሪ ጥያቄና “አስተዳዳሪው” በሰጡት መልስ ዙሪያ ብዙ ውይይት ያደረግን ቢሆንም እነእከሌ ሐዋሳን ሸጡ እያሉ አንዳንድ አመራሮች ህዝቡን በተሳሳተ መንገድ እንዳስነሱ ለተገለጸው አንድ ነገር ማለት እንዳለብን ተሰማን፡፡ እዚህ ላይ ለጋዜጣው ምላሽ የሰጠው ግለሰብ በርግጥ መልሱ የራሱ ከሆነ ያልተረዳው ጉዳይ ቢኖር አንድ ነገር ሲሸጥ ገዢው ከሻጩ ላይ ንብረት፣ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛው የግድ በካሽ ገንዘብ ተቆጥሮ፣ በቼክ ወይም በዓይነት (in kindብቻ አይደለም፡፡ አሁን አሁን በስልጣን መሸጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሽፈራው ባማረ ወንበር ስልጣን ላይ እንዲቆይና ጊዜውም ሲያልቅ በክብር በህዝብ ስም አምባሳደር ተደርጎ ውጭ አገር እንዲሄድ ከኃለማሪያም ጋር ይደራደራል፡፡ የክልል ጥያቄ የለሌና “የፀረ-ልማት ሀይሎች” ቀቢጸ-ተስፋ መሆኑን እንዲሰብክ፣ እንዲያጠፋና ሐዋሳንና አከባቢውን ይገባናል ለሚሉ ደኢህዴኖች አሳልፎ እንዲሰጥ ይስማማል ማለት ነው፡፡ በርግጥ ያንን ነው እያደረገ ያለው፡፡ ተመሳሳይነት ያለው ክህደት እየፈጸመ እስከአሁን ስልጣን ላይ ቆይቷል፡፡ የሚቀረው በሰላም ውጭ አምባሳደር ሆኖ መሄድና ተሠራለት የተባለውን ህንጻ መረከብ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ አቶ ሚሊዮን እዚህ ጋ በገንዘብ የማይገመትና የማይተመን የህዝብ መብት (ለዚያውም የወላጆችህና የልጆችህን መብት ጨምሮአልተሸጠምየክልል ጥያቄው አልተሸጠምሐዋሳ ተሸጠ የተባለው በፊት ነው፡፡ አሁን ልትሸጡ ያልተዋዋላችሁት ምን አለአንተስ መጀመሪያ መልካም አቋም ያለህ ብትመስልም የኋላ ኋላ በሽፈራው ሽንገላና ሁሌም በሚነገርብህ ፍራትህ ይሁን ወይም አንተም ስልጣን ፈልገው ይሄው ተደራደርክኮ፡፡ ይሄ ነው መሸጥ፡፡ ስልጣን ፈልገህ ከሆነ የሚከፈልህ ዋጋ ስልጣን ነው አይሳካላችሁም እንጂ፡፡ ፈርተህ ህይወትህን ለማዳን ከሆነም ያው ለእድሜ መብትህን፣ የልጆችህንና የህዝብህን ክብርና መብት ለዘላለም ለማይኖር ህይወት ቀየርከው ማለት ነው፡፡ መሸጥ ማለት በግርድፍ አማርኛ መቀየር ማለት ነው፡፡
በአሉባልታ መናፈስ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ቢገለጹልን” ለሚለው 2ኛ ጥያቄ “አስተዳዳሪው” ሲመልስ ህዝቡ ዋና ዓላማው ከሆነው ከልማትና መልካም አስተዳደር እንዲፈናቀል ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ሲዳማና ሌሎች የክልሉ ህዝቦች እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ ተደርጓል፡፡ በሐዋሳ ከተማና በአከባቢው የስጋት ድባብ እንዲያንዣብብ ለማድረገግ ተሞክሯል፡፡ ከተማዋ የመቻቻል ተምሳሌትነቷን እንዲታጣና ገጽታዋን ለመቀየር የተደረገ ሴራ መኖሩን አመልክተው ይህና መሠሉ “የጥገኞች ምኞትና ሩጫ” ህዝባዊ ዓላማን ባነገቡ የአመራር አባላት ባደረጉት ብርቱ ጥረት መበተኑን አመልክቷል፡፡
አቶ ሚሊዮን ደኢህዴን ሲዳማ ውስጥ ልማት ሊሠራና ሊያሠራ ቀርቶ ህዝቡና አስተዳደሩ በራሱ ጥረት ልማት እንዲሠራ ሊፈቅድ አልወደደም፡፡ ለዚህ የልማት ማህበሩ ያለበትን ሁኔታ ማየቱ በቂ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ልማት ማህበሩን በተመለከተ እንደሚከተለው ብለን ነበር፡፡
የሲዳማ ልማት ማህበር የሕዝብ ልማት አጋርነቱን በተግባር ማሳየት የቻለው የሲዳማ ዞን መስተዳድር ሙሉ በሙሉ ከአስተዳደርና ፖለቲካ ስልጣን እስካልወጣበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ሲህዴድ ማንነቱን አሳልፎ እንደሸጠ ደኢህዴን የወሰደው አፋጣኝ እርምጃ የሲዳማ ልማት ማህበር ያለውን ገንዘብ ወደ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲያዛውር ማስገደድ ነበር፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በብድር ስም የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ወስዶ ነገደበት፡፡ ማህበሩ ግን የበይ ተመልካች እንዲሆን ተፈረደበት፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ሕዝቡ በቁጭት ማህበሩን መልሶ ለማቋቋም በመነሳሳት ከአርሶ አደር እስከ መንግስት ሠራተኛ የአንድ ወር ደመወዝ መዋጮ ድረስ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ የልማት ስራ እንዲሰራ አልተፈቀደም፡፡ ሕዝቡ ያዋጣው በርካታ ሚሊዮን ብሮች በዝግ አካውንት በባንክ ተቀምጧልም ይባላል፡፡ ነገር ግን ሕዝባዊ ልማት ለማካሄድ የደኢህዴን መልካም ፈቃድ ይጠይቃልና እነሆ እስከ ዛሬ ስለዚህ ገንዘብ እንዲወራ አይፈለግም፡፡
ወደ እናንተ እንመለስና ታዲያ እናንተ በርግጥ አሁን ልማት እየሠራን/እያለማን ነን ብላችሁ ታምናላችሁይሄንን የምታስቡ ከሆነ ራሳችሁን እያታለላችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ህዝባችን እያሰማ ካለው ቁጣና የመብት ጥያቄ የተነሳ ከናንተ የቀረበት ልማት የለም፡፡ ወትሮም አልነበረምና፡፡ እራሱ የሚያለማውን/የሚሠራውን ግን ባለው ጊዜ እየሠራ ነው፡፡
ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር አብሮ በመተሳሰብ፣ በመከባበርና በመቻቻል መኖርን በተመለከተ ማንም ለሲዳማ አስተማሪ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ያለ አይመስለንም፡፡ ከዚህ አንጻር ህዝባችን ጠብታ የምታክል ችግር ታይቶበት አያወቅም፡፡ ሌላውን በማክበርና በፍቅር አብሮ የሚኖር ስለመሆኑ ሌላው ህዝብ እራሱ ምስክር ስለመሆኑ ጥርጥር የለንም፡፡ ስለዚህ ከህዝባችን ጋር ኖሮ የሚያውቅ የሐዋሳ ነዋሪ በርግጥ ከዚህ ህዝብ ችግር ይደርስብኛል ብሎ ይሰጋል ብለን አናምንም፡፡ አልሰጋምም፡፡ ከከፋ በደልና ብሶት የተነሳ ተማሮ የመብት ጥያቄ ማንሳት ሌላውን ወገን መበደል ሊሆን አይችልም፡፡ ጥያቄውን ያነሱት ተቃውሞውንም እየገለጹ ያሉት እናንተ እንደሚትሉት “አንዳንድ ፀረ-ልማት ሀይሎች” አይደሉም፡፡ የሲዳማ ህዝብ ነው፡፡ ከዚህ ከጋዜጣዊ መግለጫችሁ በኋላ 31 የሲዳማ ሽማግሌዎች ከ17 ወረዳዎች ተውጣተው “አስተዳዳሪው” ጋ መጥተው ጥያቄያችን ለምን ዘገየበጋዜጣ ለምን ሰደብከን ብለው ነበር፡፡ መልሱ ዝምታ ነበር፡፡ ለክልል ጥያቄው መልስ ግን ወደክልሉ “መሪ” ተልከው ነበር፡፡ ታዲያ የሄዱት ጥያቄያቸው ተመልሶላቸው ሳይሆን “የቀሩንን የህዝብ ተወካይ አዛውንቶች ከቀሩት ወረዳዎች አሟልተን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንመለሳለን…” ብለው ነው የሄዱት፡፡ ታዲያ ይህ አዛውንት ነው ፀረ-ልማት ሀይልየሐዋሳ የመቻቻል ተምሳሌትነቷ ቀድሞውንስ ቢሆን የህዝባችን ማንነት መገለጫ አይደለም ወይካልሆነ ከየት ተማርነውከደኢህዴንደኢህዴንማ ያስተማረን መገፋፋትን፣ ጥላቻን፣ የጎሪጥ መተያየትን፣ የሌላውን መብት መሻማትና ሁሉንም ጠቅሎ የመያዝ ራስወዳድነትና መሰል ትምክቶችንና ጠባብነቶችን ነው፡፡ የሲዳማ ዞን ሐዋሳን ጨምሮ ክልል እንዲሆን ህዝባችን የመፈለጉ ዋናው ዓላማም ከዚህ ችግር መላቀቅና በምትኩም በክልሉ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ተመኝቶ ያጣው ልማትና ሰላም እውን እንዲሆን፣ ከተማዋ እንድታድግና እንዳውም የመቻቻል ተምሳሌትነቷ የበለጠ እንዲጠናከርና እንዲዳብር ነው፡፡ ቤቱ ጥሩ ነው እንዳይባል የሚፈልግ፣ እንዲቆሽሽና እንዲጠላ የሚፈልግ ማን አለ ወገን፡፡ ጠላት ካልሆነ ይሄንን ለራሱ ማንም አይመኝም፡፡ ይሄንን የተመኙልን ማለትም የመብት ጥያቄው ከተማዋ የመቻቻል ተምሳሌትነቷን እንድታጣና ገጽታዋ እንዲቀየር የተወጠነ ሴራ እንደሆነ አድርገው የሚያስወሩብን ያሉት ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ከዚህ ቀደም ባወጣነው የአቋም መግለጫችን ውስጥ እንደሚከተለው አስነብበን ነበር፡፡
የባለአጀንዳዎቹ (የደኢህዴኖቹወገኖች ምንጫቸው ከማይታወቅ ሌቦችና የሁከት ወሬ አናፋሾች ጋር ሆነው አንዳንድ የወላይታ ተወላጆችን ብቻ ሳይሆን ህዝባችንንም ሲያውኩ ተስተውለዋ
፡፡ ለምሳሌ ሰኔ 15 አርብ ቀን በከተማዋ ውስጥ ረብሻና ብጥብጥ አለ፣ ከቤት አትውጡ ብለው የተማሪ ወላጆችንና ህ/ሰቡን ሲያውኩ ቢውሉም እኛ ግን ከተማ ውስጥ ሆነን ምንም ረብሻ አላየንም፡፡ በማግስቱ ሰኔ 16/2004 /ም (ቅዳሜከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል፣ ታይቶ የማይታወቅ ረብሻና ብጥብጥ ይኖራል ብለው ቢያስወሩም ግን በሰላም አሳልፈናል፡፡ “ግርግር ለሌባ ይመቻል” ይባል የለም፡፡ ቁጣና ተቃውሞ የለም አላልንም እርሱማ አሁንም አለ፡፡ ጥያቄያችን መልስ እስከሚያገኝ ከዚህ በኋላ መቼም አይቆምም፡፡ በአሁን ጊዜ እንኳ “ሲዳማ የክልል ጥያቄው ይመለስለታል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ግን የሚተዳደረው በፈዴራል ነው… ሀዋሳ የኦሮሚያ ናት…ወዘተ” እያሉ ከማስወራት አልፈው ወረቀት በትነዋል አስበትነዋል፡፡ “እኔ ከሞትኩ …” እንዳለችው አህያ፤ ታዲያ ይሄን ሁሉ የሚያስወሩ እነማን ሊሆኑ ይችላሉያው የህዝባችን ባላንጣዎችና ግብረአበሮቻው ናቸው እንጂ፡፡ ያለውና የሚኖረው ግን ሰላማዊ ተቋውሞ ነው፡፡ ይሄንን አቋማችንን በጽሁፎቻችንም በተለያዩ ወቅቶች ግልጽ አድርገናል፡፡ የእኛንም ሆነ የወላይታን ህዝብ ወገኖች ያወካችሁ እናንተው ደኢህዴኖች ናችሁ ብለን እናምናለን፡፡ ነውም፡፡ ይሄንን አጀንዳ ከማምጣታችሁ በፊት ሁከት ኖሮ ያውቃል ወይ አያውቅም፡፡ ከየትኛውም አብሮን ከሚኖር ሌላው ህዝባችን ጋር ወላይታን ጨምሮ በሠላም፣ በመተሳሰብና በፍቅር ከመኖር በቀር ተናቁረን እናውቃለን? አናውቅም፡፡ ታዲያ አሁን ምን ተፈጠረ? ተጠያቂውስ ማነው? መልሱን ለእናንተውና ቅን ዓእምሮ ላለው ሁሉ ተውን፡፡
ስለዚህ ከዚህ የተነሳ ግን በሐዋሳ ከተማና በአከባቢው የስጋት ድባብ አንዣቦ እንደነበር እኛም አንክድም፡፡ በዚያ ሁሉ በፈጠራችሁት ትርምስ ውስጥ ግን የከፋ ነገር ያልተፈጠረው ህዝባችን ለሰላም ካለው ቆራጥ አቋም፣ ይዞ የነበረውና ያለውም ስልት ሰላማዊ በመሆኑና በተለይም ሌላውን ወገን እንዳይጎዳና እንዳይበደል ምሎ ተገዝቶ የተነሳ ከመሆኑ በላይ አዋቂዎች፣ ሽማግሌዎችና የሀይማኖት መሪዎች ወጣቱን በአንክሮ ሲከታተሉትና ሲመክሩት ስለነበረና የምንመካበትም አምላክ ከእኛ ጋር ስለነበረ ነው፡፡ በእርግጥ ህዝቡ ችግር ሊፈጥር ፈልጎ ቢሆን ኖሮ ማን ያስቆመው ነበርእናንተ ናችሁ አሁን የከፋ ጉዳት እንዳይፈጠር ያደረጋችሁበያንዳንዱ የሐዋሳ ነዋሪ ደጅ ላይ ዘብ ቆማችሁሀሰት፡፡ እኛ ተበድለን ፍትህ ፍለጋ እየማሰንንና እየታገልን ብሎም የፈጣሪን ስም እየጠራን በርሱ እየተመራን ሌላውን ልንበድል አይቻለንም፡፡ የከዚህ ቀደም ጽሁፎቻችንን ያየ ይሄንን አቋማችንን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ሁሌም ማጠቃለያ ላይ ከምናስቀምጣቸው የትግል ስልቶች ዋናውና የመጀመሪያው ነጥብ ሰላማዊ ትግል ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ ነው፡፡ ይሄንን እያልን ያለነው ለደኢህዴኖች ሳይሆን ለሌላው ሰላማዊ ወገኖች ነው፡፡ እናንተማ “እያወቀ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማ” እንዲሉ ሆነ እንጂ መች እውነቱን አጣችሁትና፡፡ በጣም የገረመን ህዝባዊ ዓላማን ባነገቡ የአመራር አባላቶቻችሁ ብርቱ ጥረት ህዝብ የፈጠረው ሴራ መክሸፉን የመግለጻችሁ ጉዳይ ነው፡፡ የእናንተ በርካቶቹ አመራሮች በእናንተ ቋንቋ “ፀረ-ልማት” ሃይሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነርሱ ደግሞ ከእኛ ጋር ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ አመራሮቻችሁ ህዝባዊነት የት አላቸውእናንተኮ ለራሳችሁ ወንበርና ክብር የምትሠሩ ከህዝብ የተለያችሁ ናችሁ፡፡ አሁን ስለናንተ ለጊዜው ይብቃን፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በተከታታይነት ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች ተመሳሳይነት ስላላቸው አንድ ላይ አይተናቸዋል፡፡ ጥያቄዎቹ፡ -
የድርጅቱን መሥመር አጥብቆ ለመቀጠል ምን መደረግ አለበትከአመራሩ ምን ይጠበቃልሊተገበሩ ይገባሉ የሚሏቸው ጉዳዮች ካሉ ቢገልጹልንበአመራሩ፣ በአባሉና በምሁሩ አከባቢ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ይኖሩ ይሆንየሚሉ ሲሆን አስተዳዳሪው ሲመልስ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለህዝባችን የሰጠው መብትና ያመጣው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ጠቅሶ መስመሩ ለህዝቡ ቅድሚያ የሚሰጥና በህዝብ ጥቅም ላይ የማይደራደር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህዝባችን የኢህአዴግን ሥርአት ላለፉት አሥርት ዓመታት የተቀበለበት ዋናው ምክንያት ራስን-በራስ የማስተዳደር መብትን እውን ለማድረግ ካለው ብርቱ ዓላማና ፍላጎት የተነሳ ነበር፡፡ ራሱን የሚመራ ህዝብ ክቡር ነው፤ ለራሱ ያስባል፣ ለራሱ ያቅዳል፣ እራሱ ይሠራል፣ ለራሱ የሚሆን ህግ ያወጣል፣ በቋንቋው ይሠራል ይዳኛል፣ ባህሉን ያሳድጋል፣ በአጭሩ የራሱ የሆነች መንግሥት ትኖረዋለች፡፡ ትንሽዬ መንግሥት፡፡ “ለአንተ ከአንተ የተሸለ ስላወኩልህና ስለተገለጠልኝ ይሄንን ትተህ ይሄን አድርግ…” የሚል ፖለቲከኛ ነብይ የለሌበት መንግሥት፡፡ ታዲያ ይህ እውን ሆኖ ነበርአልነበረም፡፡ ባይሆን የነበረው በዞን ደርጃ እስከ 1992 /ም ድረስ አንጻራዊ ለውጥ ነበር፡፡ በቋንቋችን እንሠራና እንማር ነበር፣ ከደቡብ ምዕራብ እስከ ምስራቅ ያለ ብሔር ብሔረሰብ ተሰብስቦ አንድ ላይ እስከሚታጎር ድረስ ከጥቂት ወገን ህዝቦች ጋር ክልልም ነበረን (ሌሎቹ ወገን አይደሉም አላልንም ያልነው ቤቱ/ክልሉ ጠበበን ነው)፣ ሐዋሳን እናንተ አትመሩም ዋናውን የአንበሳ ድርሻ ለእኛ ተው የሚሉ ብልጣብልጦች አብረውን አልነበሩም፣ እውነት ነው አንጻራዊ ለውጥ ነበር፡፡ ስለዚህም ህዝባችንም ሥርዓቱን መከተሉ አይደንቅም፤ ተገቢም ነበር፡፡ ከሌሎች ጭቁን ህዝቦች ጋር ማበሩ መልካም ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር አዎን መስመሩ ጠቃሚ ነበር ብለን ተቀላቅለን ነበር፡፡ ነገር ግን ሲህዴድ ከደኢህዴን ጋር ከተጋባና በተለይ ደግሞ ጭራሽ ለይቶለት ፈርሶ ደኢህዴን ብቻውን ልዕልና ካገኘ በኋላ ይህ ሁሉ መብት መና ቀረ፡፡ በእጅ አዙር ሐዋሳ አይገባችሁም ተባለ፤ አንድ ልክ እነርሱን የሚመስል ህዝባችንን የሚጠላ ሲዳማ የሆነ ባንዳ ይፈለግና ከንቲባ ይደረጋል፤ ከዚያ በኋላ ቀሪው ቦታ በሙሉ በእነርሱ ይያዛል፡፡ ይህ ነው ራስን በራስ ማስተዳደርየቱ ጋ ነው ባህላችንን ማሳደግ የምንችለውከገብርኤል ፊት ለፊት ያለው የሲዳማ ባህል ሀውልት ተሰርቶ ምን ተብሎና ተወርቶ ነበር? “እንዴት እዚህ መሀል ላይ ሲሠሩ ዝም ይባላልላያችን ላይ መራት አልነበረበትም…ከቤተክርስቲያን ፊት ለፊት መሠራቱ ስህተት ነው…” አላሉምሳይገባቸው ይሄንን ሁሉ ካሉ በእኛ ቦታ ቢሆኑ ኖሮ ምን ይሉ ነበር፡፡ ይልቅ አይገቡ ገብተው ሆዳችን እንድሻክር የሚያደርጉ እነዚህን ወገኖች ሀይ በሏቸው፡፡ አካሄዳቸው ውጤቱን መልካም አያደርገውም፡፡ በሲዳማ ባህልና ቋንቋ ስምፖዚዬም ላይ ሁሌ እየተነሳ መልስ አጥቶ የቆየውና መጨረሻ ላይ በዞን ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኖ የነበረው የሲዳማ ባህልና ቋንቋ ተቋም ይቋቋም ተብሎ ተጠንቶ ሰነዶቹ ላይና መተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተወሰነ ውይይት ከተደረገ በኋላ ተከልክሎ አልቀረምይሄንን ያደረገው ጠባብ ቤት ውስጥ 56 ህዝቦች የመኖራቸው ጉዳይ አይደለምእኛ የራሳችን የሆነ ቤት በማጣታችን አይደለምአይ ራስን የማስተዳደር መብቴ ህገ-መንግሥታዊ መብቴ ነው፣ ሐዋሳ ማንነቴ ነው ብሎ ሰላማዊ ድምጹን ሊያሰማ የወጣ ህዝብ ልጅ አዋቂ ሳይለይ በክልል መንግሥት አልተጨፈጨፈምአልታሰረምአልተዋከበምይህ አልበቃ ብሎ ከዚህና ከዚህም ከከፋ በደል የተነሳ ህዝባችን “አሁንስ በቃኝ ራሴን ችዬ በህገ-መንግሥቱ ስርዓት መሠረት ክልል ልሁን…” ብሎ ውሳኔ ሲያስተላልፍ አልተከለከለም፡፡ ይህ ሁሉ ድርጊት መንግሥት ህገ-መንግሥቱን እንደጣሰ አያሳይምታዲያ የቱ ጋ ነው የኢህአዴግ መሥመር በህዝብ ጥቅም ላይ የማይደራደር ነው የምትሉንህገ-መንግሥቱ ላይ የተጻፈን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያስከበረውን አንቀጽ እኛ ብቻ ሳንሆን መሰል የቤንሻንጉል፣ የኦሮሞ፣ የአፋር፤ የሱማሌ፤ የጋምቤላ፣ የጌደኦ፣ የቡርጂ የአማሮ፣ የጋሞ፣ የጎፋና ወዘተ መሰል ጭቁን ህዝቦች ሥርዓቱን እንድንቀላቀል ምክንያት የሆነንንና የህገመንግሥቱም ሆነ የሥርዓቱ ምሰሶና እስትንፋስ የሆነን አንቀጽ የናደው ማነውመሥመሩ እራሱ አይደለምመሥመሩ ራሱን በራሱ እያፈረሰ መሆኑ አይታያችሁምንታዲያ ይህ አንቀጽ ከተናደ ህገ-መንግሥቱ ውስጥ የሌለ ያህል አይደለምንበእኛ በኩል ‘አይ እነርሱ ህገ-መንግሥቱን ባያከብሩም (ቢጥሱምህገ-መንግሥቱ ለእኛ ይጠቅመናልና እንታገስ’ ብለን አላለፍንም? “ጥያቄያችሁ/ውሳኔያችሁ ህጋዊ ነው፣ ማንም የመከልከልም ሆነ የመፍቀድ ስልጣን የለውም፣ ስልጣኑ የእናንተው ነው፣ ነገር ግን ለኢህአዴግ ጊዜው ጥሩ አይደለም፡፡ ስለዚህ አቆዩልን…ለጊዜው ይሄ ይሄ መብታችሁ ይከበራል…” ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎቻችንን ሊመልሱ ቃል በገቡልን መሠረት አልታገስንምታዲያ ይሄንን ውል ማን አፈረሰሲዳማ ወይስ መሥመሩለመሆኑ መሥመሩ ማነውኢህአዴግ ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትሩበዚህ ሁኔታ መስመሩ ከደርግ በምን ተለየየቱ የልማትና የሠላም ፍላጎትና ጥያቄ ተመለሠለሁሉም መልሱ አንድም የተመለሰ ጥያቄ የለም የሚል ነው፡፡ ይሄንን እውነታ እናንተም አታጡትም፡፡ ስለዚህ ህዝባችን የሚያሰምርበት አንዱና ብቸኛው ጉዳይ መሥመሩ መሥመሬ ነው የሚለው ጥያቄው በወቅቱ ሲመለስለት ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ጥያቄው ካልተመለሰና የህገመንግሥቱም ሆነ የሥርዓቱ ምሰሶና እስትንፋስ የሆነው አንቀጽ (እራሱ ህገመንግሥቱከተጣሰና ካልተከበረ ምን አንድነት አለን፡፡ በአንድ በኩል አመራሩ የብዙሃኑን ሀሳብ የማስፈጸም ግዴታ አለበት ትላላችሁ፤ ለነገሩ እውነት አላችሁ መተዳደሪያ ደንባችሁ ይሄንን ይላል፤ ታዲያ ህዝባችን አንሶ ከታያችሁ ማነው በአመራሩ መሀከል ብዙሃኑየህዝብ ወገን የሆነውና የአሁኑን የእናንተን አካሄድ የተቃወመው አመራር አይደለምወይህድ ከነመሥመርህ ወዲያ በል፣ ወይ ጥያቄያችን ይመልስ!! ለነገሩ እናንተ ራሳችሁ መሥመራችሁን ስታችኋል፡፡ ህገመንግሥቱ የተጣሰ ቀን ነው መሥመሩ የጠፋባችሁ፡፡ ህገመንግሥቱ እኮ ብቸኛ መሥመራችን ነበር፡፡ ስለዚህ የድርጅቱን መሥመር አጥብቆ ለመቀጠል እንዲህ አንዲያ መደረግ አለበት የሚል ወሬ አይሰራም፡፡ መሥመሩ እንዲጠበቅ መጀመሪያ መሥመሩ ራሱ መኖር አለበት፡፡ መስመሩ በሌለበት ስለመጠበቅ ማውራት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ ይሆናል፡፡ ስለዚህ መሥመሩ ተንዷል፡፡ ቀድማችሁ እርሱን ጠግኑና ቤተኞቹን ከውጭ አስገቡ፡፡ ከዚያ ስለመጠበቁ አብረን እናወራለን፡፡ ካልተጠገነ እንኳንስ እኛ ውጭ ያለነው ቤት የሌለን ቤት ያላቸውም ነግ በኔ ብለው ጥሏችሁ ሽምጥ ይጋልባሉ፡፡ ተጠንቀቁ፡፡ ለምሳሌ ቤንሻንጉልና ሱማሌ ዛሬ ራሳቸውን እያስተዳደሩ ናቸው፤ ነገ ነዳጅ ሲወጣና የመሃል አገሩ መሪዎች ጥጋብ ሲሰማቸው፣ ኒዩክሌር ቦንብ ባይሆንም ሚሳኤል ሲሠሩ ‘አሁን አንተ አቅም የለህም ክልልህን እኔ እመራዋለሁ ከተማህም ተጠሪነቱ ለፌደራል ነው…’ ለምን አይሉም፡፡ ልክ እንደኛው ዛሬ እነርሱን እንዲህ እንበል ቢሉ እነርሱ ድንበር ላይ ስላሉ ስርዓት ያሲዟቸዋል፡፡ አቅም መገንባትና ጊዜ መግዛት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሊባል እንደሚችል ከመንግሥት ከአሁኑ አካሄድ፣ በየክልሉና በየቦታው ከሚታየው ማንአለብኝነት፣ መብት ረገጣና የህገ-መንግሥት ጥሰት ቤንሻንጉሉ፣ አፋሩ፣ ጋምቤላው፣ ሱማሌው ወዘተ ይረዳል፡፡ ከዚያ ምን ይሆናል ከተባለ ያው ልክ እንደኛው መታገል ነዋ፡፡ ይታገላሉ፡፡ በአጭሩ የእኛ ጥያቄ “አወኩሽ ናኩሽ” እንዲሉ ሆነ እንጂ በጊዜው ካልተመለሰ ሌላም መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ማለታችን ነው፡፡ ይህ ትንሽዬ ግምገማ ነው፡፡ በአጭሩ ጊዜ በተገዛ ቁጥር የትግልና የቁጣ አድማስ የታጋዩና የተቆጭው ቁጥር እያሻቀበ ይሄዳል… ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ብታስቡበት ጥሩ ነው እንላለን፡፡
በመቀጠል “አስተዳዳሪው” እንደሰሞኑ ዓይነት ሁኔታ ሲከሰት የትግል ጓዶች ቆም ብለው ማሰብ እንዳለባቸው፣ የድርጅቱን ህልውና ለአደጋ የሚያጋልጡ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች መቆም እንዳለባቸው አስምረው በአጠቃላይ በሁለት ቢላ መብላት መቆም አለበት በማለት ካስጠነቀቀ በኋላ ሲቀጥል ህዝቦችን በማጋጨት የግል ጥቅም ማሳካት እንደማይቻል ከሂደቱ ትምህርት የተገኘበት ይመስለኛል ብሏል፡፡ እዚህ ላይ ነው ዋናው ቀጣይ ጨዋታ ያለው፡፡ በሁለት ቢላ መብላት መቆም አለበት ሲል ህዝቡን ወግነው የተነሱትን አመራሮች በግምገማ እናስወግዳቸዋለን ማለታቸው ነው፡፡ መንግሥት ያመጣውን ሰነድ የተቃወሙትንና ‘ህዝባችን በየጊዜው በዚህ መልኩ የሚታወክ ከሆነ እየተታለልን እንደሆነ ገብቶናል፡፡ አንድ ቀን ህዝባችንን አሽቀንጥረው በመጣል ከጫወታ ውጭ ያደርጉታል፡፡ ስለዚህ የክልል ጥያቀው መልስ ማግኘት ያለበት ጊዜ አሁን ነው…’ በማለት መሄጃ ያሳጧቸውን ብዙሃኑን አመራሮች ከጫዎታ ውጭ ሊያደርጓቸው ነው እቅዳቸው፡፡ ይሄንን የበለጠ ግልጽ የሚያደርገው ከበር መልስ አብረን እንሄዳለን የሚለው ነገር አይሠራም የሚለው የ“አስተዳዳሪው” መልስ ነው፡፡ እውነት ነው ከበር መልስ አብረን መሄድ አንችልም፡፡ ምርጦቹ አመራሮቻችን ይሄንን ያጡታል ብለን አናምንም፡፡ በክፉ ቀን ተሸክመን ያሳለፍነው ሥርዓት ዛሬ ለመስመሩ ህዝባችን የዋለውን ውለታ በመርሳት መሥመሩ ለህዝባችን የዋለውን ውለታ ብቻ በመቁጠር መብትህን ብትገፈፍም ዝም በል፣ ራስህን ማስተዳደር አትችልም ከተባልክም ዝም በል፣ ከአንተ በላይ ሌላው ባለመብት ነው በገዛ አገርህና ቀዬህና ዝም በል፣ ህገ-መንግሥቱን ባናከብርም መስመሩ ይበልጥብሀልና ዝም በል እያሉን ነው፡፡ ታዲያ ለምድነው ዝም የምንለውመሥመሩ ከካደን በኋላ የቱ ጋ ነው ከመብታችንና ከክልላችን የሚበልጥብን? የለም እንዲህ ከሆነ እንኳንስ ከእናንተ ጋር መስመራችሁም ይቅርብን፡፡ ስለዚህም ከበር መልስ አብረን መሄድ አንችልም፡፡ ስለዚህ ኑ እንገማገም በሉ አመራሮቻችን፡፡ ለነገሩ እነርሱም ይሄንን መች አጡትና ይሄንን እያሉ ናቸው አሉ፡፡ ማነው አሁን መገምገም ያለበትየሚያበጣብጠው ነዋ፣ “ከተማው የእከሌ ነው…የሲዳማ አይደለም ህዝብ ተበጣበጠ፣ ሲዳማ ሌላውን እንዲህ አደረገ ወዘተ” እያለ ወረቀት የሚበትነውና የሚያስበትነው ነዋ፣ ህዝባችንም ሆነ ሌላው እንዲታወክ የሚያደርገው ነዋ፣ ህዝባችን ያወራውንና የጠየቀውን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው በውሸታሙ ራድዮ፣ ቴሌቪዢንና ጋዜጣ ተቃራኒ ሀሳብ ያስተላለፈና ህዝቡን “ፀረ-ልማትና ፀረ-ሰላም ሀይል” የሚለው ነዋ፣ በህዝባችን ስም እየነገደና መብቱን እየሸጠ “የተሸጠ ነገር የለም፣ በህዝብ ስም መነገድ የለበትም፣ ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ መሠጠት ነበረበት..” እያለ ለህዝብ ያሰበና የተቆረቆረ በመምሰል ህዝባዊ መሠረት ያላቸውንና ለህዝብ ወገንተኛ የሆኑ አመራሮችን ለመምታትና ለማስመታት እያመቻቸ አዛኝ መስሎ የአዞ እምባ የሚያለቅሰውን ነዋ መገምገም፡፡ አዎን ህዝቦችን በማጋጨት የግል ጥቅም ማሳካት እንደማይቻል ማወቅ አለባቸው፡፡ ችግሩ እነርሱ የሚገባቸው በተቃራኒው ነው እንጂ ከሂደቱ ትምህርት ማግኘት ነበረባቸው፡፡ ግድ የለም በግምገማ ይማሩታል፡፡ ይሄንንስ የኛዎቹ አመራሮች መች አጡት፡፡ አዎን ጊዜው ይምጣ እንጂ ከበር መልስ አብረን መሄድ አንችልም፡፡ እነ ሰንባላጥና ጦቢያ መለየት አለባቸው፡፡ እኛን አይወክሉንም፡፡
ሌላው “አስተዳዳሪው” ካነሳቸው አቤይት ጉዳዮች መነሳት ያለበት ስለወጣት አመራር ልምድ ማነስ ያነሳው ጉዳይ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ሰፊ ቁጥር ያለው በዞኑ ውስጥ በአመራር ቦታ ያለው ወጣት የሰሞኑ ዓይነት ፈታኝ ጉዳዮች ሲከሰቱ በድርጅቱ መሥመር ላይ ሆኖ ሁሉንም ነገር ከዚህ አንጻር የመፈተሽ ተሞክሮ የለሌው መሆኑን ጠቅሷል፡፡ እዚህ ላይ ሚሊዮን ያላስተዋለው እንኳንስ በአመራር ቦታ ያለውና አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን ልምድ ያለው ወጣት ይቅርና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንኳ ሳይቀር መበለጡን ነው፡፡ ተማሪዎቹም ሆኑ ልምድ አነሳቸው የተባሉ አመራሮች መነሻ አድርገው እየታገሉ ያሉት ህገ-መንግሥቱን ነው፡፡ መመሪያቸው ይሄ ነውና፡፡ ታዲያ የቱን መሥመር ነው የሚለው ሚሊዮንየቱ መሥመር ላይ ይቁሙሌላ መሥመር አለ እንዴስለዚህም እኮ ነው መስመሩን ናዳችሁት እያልን ያለነው፡፡ እኛም ሆንን እነርሱ ሌላ የምንቆምበትና ከመብታችንና መመሪያችን ከሆኑ የህገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች አስቀድመንና አስበልጠን የምንቆምለትና የምንቆምበት መሥመረር የለንም፡፡ ያገናኘንም ይሄው ህገ-መንግስትነና የጠቃቀስናቸው ህገ-መንግስታዊ መብቶቻችን ናቸው፡፡ እናም መሥመራችን ያ ነው፡፡ እርሱ ከተናደ የት ላ ይቁሙላችሁና የቱንስ መስመር ይጠብቁእናንተስ የየራሳችሁ መስመር እንዳላችሁ አየን፡፡ የስልጣን መስመር፣ የሀብት መሥመርና የክብር መሥመር፡፡ እነርሱ ግን ይሄንን አልመረጡም፡፡ እነርሱ የመረጡት ህገ-መንግስቱን፣ ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱንና የወከላቸውን ወገን ነው የመረጡት፡፡ ታዲያ የቱ ሚዛን የሚደፋ ይመስልሃልአሁን ካልገባህ ነገ ወድቀህ ስትከሰከስ ይገባሀል፡፡ የናካቸው ወጣት አመራሮች በአቅም ከአንተ የሚበልጡ ናቸው፡፡ ቢያንስ እንዳንተ ፈሪ እንዳይደሉ አስመስክረዋል፡፡ በአመራርነትም ከአንተ በብዙ የሚሻሉ ብዙ አሉ፡፡ አንተ ለዚያ ቦታ የታጨህበት ዋናው ምክንያት ከመነሻው ስህተት ቢሆንም ሁለት ነው - 1) “የክልሉ መሪ” እንደምትመቸውና ፈሪ መሆንህንና ከዓላማህ ነፍስህን እንደምታስበልጥ መረዳቱና 2) የአባትህ ስመ ጥሩ መሆን በሰዎች ፊት ይሁነታን የሰጠህ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ከአቅም አንጻር የሚበልጡህ በርካታ ወጣቶች አብሮህ እያዘኑብህ አሉ፡፡ ስለዚህ ታሪክ ሳይሆን ህገ-መንግሥትና ህጋዊነት ብቻ ነው የምያኖረንና የሚያስተሳስረን፡፡ ባይሆን ይሄንን እውነታና ህዝባችን ያለበትን አከባቢና ማንነቱን እንዴት ይዞ እንዳቆየ ለእናንተ የሲዳማን ህዝብ የትግል ታሪክ በአግባቡ ማስጨበጥ ማስፈለጉን እጅግ አምነንበታል፡፡
ሌላው የገረመን የጋዜጣዊ መግለጫው መልዕክት ክፍል በበራሪ ጽሁፎች የሰዎች የመናገር ህገ-መንግሥታዊ መብት እስከመጋፋት የተደረሰበት ሁኔታ ስላለ መስተካከል አለበት የተባለው ነው፡፡ እውን አሁን በአገራችን የመናገር መብት አለየመናገር መብት ካለ የፍትህ ጋዜጣ ህትመቶች ሰሞኑን ለምን ታፈኑለምንስ ለዚያውም ግልጽነት በጎደለው መልኩ እንዳይታተሙ ተከለከሉየክልሉ አስተዳዳሪ ስብሰባ ጠርቶ እርሱ ካሰበው ውጭ የሚናገርና የሚጠይቅን ሰው ሁሉ የሚሳደበውና የሚያሸማቅቀው ታዲያ ለምንድነውየመናገር መብት ስላለ ነውበርግጥ ይሄንን የተጠቀሰውን ጽሁፍ ባናውቅም እኛ መብታችን ተነካ፣ የመናገር መብታችንንም አጣን እያልን ሌላውን አትናገር ልንልም አንችልም፡፡ ህዝባችን ይሄንን ሊል አይችልም፡፡ ምን ያልጻፋችሁትና ያልበተናችሁት ወረቀት አለና ህዝባችንን ትወነጅላላችሁውስጣችሁ ያለውን መሰሪ ሴራና እርሱን ለማሳካት የምትፈነቅሉትን ድንጋይ ሁሉ አጥብቀን ስለምናውቅ የቧጥ የቋጡን አትቀባጥሩ፡፡ እኛስ የመናገር መብት ሰዎች የሰጡት መብት ሳይሆን እግዝአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር አብሮ የሰጠው መብት እንደሆነ እናምናለን፡፡ የሰው ልጅ የመናገር መብት አብሮት ተፈጥሮ ባይሆን ኖሮ ሁላችንም ተመሳሳይ አነጋገርና አስተሳሰብ በኖረን ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አልሆነም፡፡ አየር እንደፈለግነው እንደምንተነፍስ ሁሉ እንደፈለግነው የመናገርም ጸጋ አብሮ ተሰጥቶናል፡፡ እናንተ ሀገ-መንግሥቱ ሳይነፍገን ነፈጋችሁን እንጂ፡፡ ታዲያ ከዚህ ተፈጥሯዊ መብታችን እንኳ ሳይቀር የሚገድበንን የተናደ መሥመር ነው ጠብቁ የምንባለውና ላዩ ላይ ቆመን ያለንበት እንድንቀር የምንመከረውአቶ ሚሊዮን ግድ የለም እርሱ መሥመር ለጊዜው ይቆይልን ለአንተው ይመችህ፡፡
ከማስገረምም አልፎ በእጅጉ ያሳቀን “አስተዳዳሪው” ሲናገር በጉዳዩ ላይ አርሶ አደሩ ከምሁሩና ከአመራሩ በተለየና በተሻለ መልኩ ያሳየውን ቁርጠኝነት እናደንቃለን ማለቱና እየተሄደበት ያለው አግባብ ከመስመራችን አካሄድ ውጭ ነው፣ በልማታዊ መስመሩ አልደራደርም ብሎ አሉባልተኞችን ገትሮ አቁሟቸዋል የመባሉ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እዚህ ላይ የቱን ብለን የቱን እንደምንተውም አልገባምን፡፡ ምክንያቱም ያሉት እውነታዎች ሁሉ፣ ልንል የምንችላቸው ነገሮች ሁሉ ከባለአጀንዳዎች አስመሳይ አባባል በተቃራኒ ያሉ ናቸው፡፡ እስኪ ቀድመው ወደአእምሮአችን የመጡትን ነጥቦች ብቻ ለማስተናገድ እንሞክር ምክንያቱም ይህ ሰነድ በሰፋ ቁጥር ተነባቢነቱ እያነሰ ይሄዳልና፡፡ ቀድመው የተነሱ ጥያቄዎችን ስንመልስ ለማስረዳት እንደሞከርነው ከ17 ወረዳዎች የተውጣጡ 31 ሽማግሌዎች ወደ ሚሊዮንንና ሽፈራው ቢሮዎች ሄደው ሰፊ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ በዚህን ወቅት ሽማግሌዎቹ ሚሊዮንን በጋዜጣ ለምን እንደሰደባቸው ከመጠየቃቸው በፊት ክልል ለመሆን ያስተላለፍኩት ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን ለምን ዘገየ የሚል ጥያቄ አንስተው ለስድቡ ራሱን አቀርቅሮ ያሳለፈ ሲሆን ለክልል ጥያቄው ግን መልስ ከአኔ አታገኙም ሽፈራውን ጠይቁ ብሎ መልሶ እንደነበር ገልጸናል፡፡ ከሽፈራው ጋርም እስከምሽቱ ሰዓት ሲሟገቱ ቆይተው ስላልተግባቡ የቀሩትን ወረዳዎች ሽማግሌዎች ይዘን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንመለሳለን ጠብቁን ብለው ተለያይተው ሄደዋል፡፡ ቀጥሎ የሚሆነው ነገር እየተጠበቀ ያለ ሲሆን ተቃውሞውና ጥያቄው ግን ቀጥሏል፡፡ በሁሉም ወረዳዎች ሰላማዊ ስብሰባዎችና ተቃውሞዎች አንዳንድ ቦታ ሰላማዊ ሰልፎች “ቄጣላ” እየተደረገ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ማልጋ ወረዳ ህዝብ ወጥቶ ተሰባስቦ ሳለ ከዞን ፖሊሶች ሄደው ለማስቆም ሲሞክሩ ህዝቡ “ሐዋሳ እንዳንሰባሰብ ስለከለከሉን ለሠላም ብለን ትተን በደጃችን በባህሉ መሠረት የምንሰባሰበውን ሊከለክሉን አይችሉም…” በማለት በቁጣ ተነሳስተው ያልነበረ ሰላማዊ ሰልፍ “ቄጣላ” ማድረጋቸው የታወቀ ሲሆን ማን እንዳደረገው ለጊዜው በውል ባይታወቅም በመኪና የሄዱ ከ10 በላይ የሆኑ ፖሊሶች ትጥቃቸው ተፈቶ ተወስዷል፡፡ መኪኖቹ ተሰባብረው እንዳልነበሩ ሆነዋል፡፡ ጠመንጃዎቹን ማን እንደፈታና እንደወሰደ ሲጠየቅ ህዝቡ ያለው “አናውቅም ምናልባት የወረዳ አመራሮች ሊሆኑ ይችላሉ” የሚል ነበር መልሳቸው፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ነገር ቢኖር ይህ ሁሉ ሲሆን ራሱን በራሱ በመቆጣጠርና በማረጋጋት የከፋ አደጋ በወታደሩም ላይ ሆነ መሰል ግለሰቦች ላይ አላደረሰም፡፡ ይሄንን ለማርገብ ከፌደራል የመጡ ፖሊሶች እንዳይገቡ መንገድ ተዘግቶ በኦሮሚያ ክልል በኩል የኦሮሚያ የገጠር ህዝብ “የሲዳማ ጥያቄ ትንሽ ነው፣ ክልል ነው የጠየቁት፣ ችግር ውስጥ ከምትገቡ ለምን ክልል አትመልሱላቸውም..” እያሉ እንደተሳለቁባቸው ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል በሁሉም ወረዳዎች ያሉ አርሶአደሮች “አትምጡብን፣ ልናነጋግራችሁ አንፈልግም…በሚመጡ ሰዎቻችሁ እየተረበሽን ነው” ብለው ለዞንና ወረዳ አመራሮች መልክት አስተላልፈዋል፡፡ እንኳንስ ከዞን የተሳደቡ አመራሮች ሄደው ሊያነጋግሯቸው በየወረዳዎቹ ያሉ አስተዳዳሪዎች ህዝቡ ተሰባስቦ ያለበት ሲሄዱ “እንዴት ሳንጠራችሁ መጣችሁበባህላችን መሰረት ያልተጠራ ሰው ሸንጎ ውስጥ ሰተት ብሎ ይገባል ወይ…?” እያሉ ሲያስወጧቸው ተስተውሏል፡፡ ታዲያ የቱ አርሶ አደር ነው ከምሁሩና ከአመራሩ በተለየና በተሻለ መልኩ ቁርጠኝነት ያሳየውና ‘እየተሄደበት ያለው አግባብ ከመስመራችን አካሄድ ውጭ ነው፣ በልማታዊ መስመሩ አልደራደርም’ ብሎ አሉቧልተኞችን ገትሮ ያስቆመውአቤት ውሸት፡፡ ውሸት መቼ ይሰለቻችሁና ያሳፍራችሁ ይሆንአቤት ቅሌት!! ቀለላችሁኮ፡፡ ይህን ያህል ቀሎና ከህዝብ ተለይቶ የሚገኝ ስልጣን ፋይዳው ምን ይሆንለልጆቻችሁስ ምን ልትሉ ነው? “ለስልጣንና ገንዘብ ብለን ክብራችንን ሸጥነው…” ልትሉክብርና ክብደት የለሌው ስልጣን፣ ያልተባረከና የማይበላ ሀብት፣ ተቀባይነት የለሌው ስምና ዓላማ የለሌው ትግልና ጉዞ ምነው በቀረባችሁ፡፡ በነገራችን ላይ ሳናመሰግን የማናልፈው ነገር ሳታስቡትም ቢሆን ምሁሩና አመራሩ እንዳልተቀበላችሁ የማመናችሁ ጉዳይ ነው፡፡ የናንተማ ዓላማ እነዚህ ሁለቱ ከተማ የሚኖሩ ስለሆኑ ተቀብሎናል ብትሉ ስለምትጋለጡ እንደወትሯችሁ ሁሉ ሰፊው አርሶአደር ከእኛ ጋር ነው ብላችሁ ልትሸውዱ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተጠቀሰው ከሁለቱ ወገኖች ይልቅ ዛሬ ዓላማውና አካሄዱ እናንተ እንዳላችሁት ሳይሆን በተቃራኒው የክልል ጥያቄዬ ይመለስ የሚል ሆኖ በየቢሮአችሁ እየመጣ፣ በየወረዳው በራሳቸው ጉባኤና መሰል መንገዶች ያለውን ጥያቄ እያቀረበ እየታገለ፣ ጋዜጣችሁ ገና ተነቦ ሳያልቅ ለምን በጋዜጣ ሰደባችሁኝ እያለ መቆሚያና መቀመጫ እያሳጣችሁ ነው፡፡ እንግዲህ አርሶ አደሩ አብሯችሁ ሊሆን ቀርቶ ዋና አጀንዳው ከሆነው ከክልል ጥያቄ ፍንክች እንደማይል ከማሳየቱም በላይ ባለፈው ወደሽፈራው ቢሮ ሄዶ “ለምን ቃላችሁን ቀየራችሁያኔ የክልል ጥያቄ ጊዜው ለኢህአዴግ ጥሩ አይደለም በሚል ይዘግይ ተባለ እንጂ ይቅር መች ተባለለምን ሲዳማ ክልል አልጠየቀም አልክ?” ብለው ሲጠይቁት “እኔ አላልኩም…አምላካችሁ እንዲህ እንዲያ ያድርገኝ” ብሎ እዛው ሁለት ጊዜ ቃሉ ሲቀያየርና ሲምል አይተው “ዝም በሉ ይህ ልጅ ጤነኛ አይመስለንም፡፡ ግድ የለም አምላካችን አይለቀውም ዝም በሉ ይማል…” እያሉ ሲታዘቡትና ስዘባበቱበት እንደነበር ለማስተዋል ተችሏል፡፡ ይህ ማለት ህዝቡ “የክልሉን መሪ” ልጄ አይደለም የፈለገውን ይሁን ማለቱን ያሳያል፡፡ እንግዲህ ይህ የሚያሳየው አሉባልተኞችን ገትሮ አስቆመ የተባለው አርሶ አደር እነሽፈራው በምንም መልኩ ከፊቱ ገለል ብለውለት ጥያቄው ብቻ እንዲመለስ የሚፈልግ ከሆነ፣ በሁሉም ወረዳዎች በሙሉ ድምጽ ጥያቄውን የሚያሰማ ከሆነና ከምሁሩና አመራሩ ተሻለ የተባለው ደግሞ እርሱ ከሆነ እነርሱን የሚሰማ ሰው ቀርቶ ሊያያቸው የሚፈልግ አለመኖሩን ያሳያል፡፡ ብቻቸውን ናቸው ማለት ነው፡፡ ብቻቸውን ስለመሆናቸው ለነገሩ እንኳንስ እኛ እነርሱም በደንብ ያውቁታል፤ ይሄንኑ ለማስተላለፍ እየሞከርን ያለነው ለሌላው አንባቢ ነው እንጂ፡፡
በመጨረሻም “አስተዳዳሪው” የትኩረት አቅጣጫ ምን እንደሆነና የሚያስተላልፈው መልክት እንዳለ ሲጠየቅ እንደሚከተለው አጠቃሏል፡፡
የአባላት መድረክ፣ ህዝባዊ ኮንፎራንስና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ቅራኔዎች በህዝብ ለህዝብ ኮንፎራንሶች እንደሚፈቱ ታምኖበት እየተሠራበት መሆኑን በመግለጽ “አፊኒ” የሚለው ባህል ከወጣቱ ዘንድ እየጠፋ መምጣቱን ጠቁሟል፡፡ ቀጥሎም ድርጅቱ ህዝባዊ መሰረት ያለው መሆኑን ለኛው ሊነግረን ከሞከረ በኋላ ህዝባችን ተጠቃሚ የሚሆነው ሰላምና ድርጅታቸው ሲኖር መሆኑን አስምሮበታል፡፡ “የተነሳበትን የማያውቅ የሚሄድበትን አያወቅም” እንደሚባል አስታውሶ ታሪኩን የማያውቅ የወደፊቱን አያውቅም ብሏል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች ህዝባችን የበይ ተመልካች መሆኑን ገልጾ ምርቱን የሚቀማበት፣ ባህልና ታሪኩን እንዳያሳድግ ትልቅ ተፅዕኖ ነበረበት ካለ በኋላ በዚህ ሥርዓት ግን ባመረተው ልክ እየተጠቀመ መሆኑን፣ በራሱ ልጆች እየተዳኘ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ በራሱ ቋንቋ እየተማረና የሥራ ቋንቋ አድርጎ፣ በማንነቱ ኮርቶና ከሌሎች ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ እየኖረ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በመጨረሻም እነዚህን እሴቶች ያጎናጸፈውን ልማታዊ መስመር ከአፍራሽ ኃይሎች መጠበቅ እንዳለበት ገልጾ ዓይኑን ትኩረቱን ካደረገበት ከድህነት ጋር ከሚያደርገው ትግል ለአፍታም ሳይነቅል ከዚህ ዓይኑን እንዲያነሳ የሚማስኑ ኃይሎች ጠላቱ መሆናቸውን አውቆ ሊታገላቸው ይገባል በማለትና “ልጅ ለናቷ ምጥ አስተማረች” እንዲሉ የአከባቢን ሰላም በማረጋገጥ ከሌሎች ህዝቦች ጋር አብሮ የመኖርና ወንድማዊ ትስስሩን ለማጠናከር መትጋት እንዳለበት ህዝቡን ለማስተማር በመሞከር አጠናቋል፡፡ በአጭሩ መልክቱ ይህ ነበር፡፡
እኛም ለዚህ ማጠቃለያ የሚኖረን መልስ በአመዛኙ ከላይ ካነሳናቸው ነጥቦች ጋር ተያያዥ ስለሆነ በተቻለ መጠን ለማሳጠር ሞክረናል፡፡ ለህዝባችን ከሌላው ወገን ህዝብ ጋር አብሮ እንዴት በሠላም መኖር እንዳለበት መምከርም ሆነ በህዝብ ለህዝብ ኮንፎራንሶች ይቅርና አንድ ኮንፎራንስ ለማካሄድ ማሰብ በራሱ ከላይ እንደተረትነው አይነት ነው የሚሆነው፡፡ ልጅ እናቷን ምጥ
ታስተምር አትችልም፡፡ ስለዚህ ቢቀርባችሁ ጥሩ ነው፣ ህዝባችን ከሌላው ህዝብ ጋር ምንም ቅራኔና ቁርሾ የለበትምና፡፡ የሲዳማ ህዝብ ኮንፈራንስም የማይታሰብ ነው፡፡ ስለምን ለማውራትህዝባችን የሚፈልገው አሁን ወሬ ሳይሆን ውሳኔው እንዲከበርና መልስ እንዲመለስለት ነው፡፡ ሳይሸራረፍ እንዲመለስለት ነው የሚፈልገው፡፡ በርግጥ ጌቶቻችሁ ህዝባዊ ጥያቄውንና ቁጣውን ጊዜያዊ ድንፋታ አድርገው እንደቆጠሩት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሄንን ህዝባችንም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ጊዜያዊ ጫጫታ (በእናንተው ቋንቋመሆን አለመሆኑን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ኮንፎራንስ ባታስቡ ይሻላችኋል፤ ማድረግ ያለማድረጉንማ ጉዳይ ለእኛው ተውት፡፡
ይህ ሥርዓት በርግጥ ካለፉት ሥርዓቶች ይሻለኛል ብሎ ተከትሏችሁ ነበር፡፡ ይህ ሲባል ምርቱን የሚቀማበት፣ መማር ያልቻለበትና የከፋ በደልና ግፍ ይደርስበት የነበረው ግን በንጉሱ ሥርኣት ነው፡፡ ሰው በላ የተባለው ደርግ እንኳ በመሬት ላራሹ መሬቱን መልሶለታል፣ መማር ችሏል፣ ባመረተው ልክ መጠቀም ችሎ ነበር፡፡ በማንነቱ ኮርቶና ከሌሎች ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ ይኖር ነበር፡፡ አንድ ሰው ከንቲባ አድርጎ የቀረውም ማሽከርከርማ ደርግም ከዚህ የተሻለ መብት ሰጥቶ ነበር፡፡ በደርግ ወቅት ለአብነት ያህል በሁሉም የሲዳማ አውራጃዎች አስተዳዳሪዎችም ሆኑ አመራሮች የሲዳማ ተወላጆች ነበሩ፡፡ ያጣው የነበረው ነገር ቢኖር ራስን በራስ ማስተዳደርን፣ በቋንቋው መሥራት፣ መዳኘትና ባህሉን ማሳደ
ን ነበር፡፡ በቃ ይሄው ነው፡፡ ቢበደልና ቢገፋ እንኳ ተለይቶ ሳይሆን ከሌላው ወገን ኢትዮጵያውን ጋር አብሮ ነበር፡፡ እሰከ 1992 /ም ድረስ ይህ በአንጻሩም ቢሆን ምላሽ አገኘ ብሎ ትንሽ አርፎ ነበር፡፡ ከ1992 ጀምሮ ግን እየተሸራረፈ ቆይቶ ከ1994 /ም ጀምሮ ጭራሽ ለይቶለት እየተቦዳደሰ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ተመለሰ፡፡ ባህልና ታሪኩን ሊያሳድግ ላቋቁም ያለው ማዕከል ሊሆን አልቻለም ተከለከለ፣ የክልል ውሳኔው ተከለከለ፣ ሌላው ቀርቶ ጊዜ እየተጠበቀ “ዋና ከተማው ይበዛብሀል ስለዚህ ይ/ዓለምም በኛው ሥር ስለሚሆን አለታ ወንዶ ሂድ…” ተብሎአል፡፡ ከ1994 ወዲህ የተሠሩ መንገዶች አሉ ልትነግሩን ትችላላችሁመሀል አገር ሳለን ልማት ናፈቀን፡፡ ዛሬ ወደሩቅ ወረዳዎች ትንሽ ዝናብ ካካፋ መሄድ የማይታሰብ ሆኗል፡፡ መሪ ተብየዎቹ የወጡባቸው ወረዳዎች እንኳ መንገዶች ተዘግተዋል፡፡ ለምሳሌ አሮሬሳ መሄድ አይታሰብም፡፡ በንሳም እንዲሁ፡፡ ጭሬማ ጭራሽ የማይታሰብ ከሆነ ቆየ፡፡ እነዚህን ወረዳዎች ለአብነት ጠቃቀስን እንጂ ሁሉም ወረዳዎች ያው የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡ እውነት ነው ሥርዓቱ ለጥቂቶቻችሁና ጥቂት ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ተመችቷል፡፡ ነገር ግን ዘመዶቻችሁ እንኳን ተሟልተው መጠቀም አልቻሉም፡፡ ከዘመድም ዘመድ የምትመርጡ የምትገርሙ ፍጡራን ናችሁ፡፡ ታዲያ የእናንተም መሥመር ከደርግ ጊዜ በምን ተሸለአሁን ላይ ሆነን ስናየው የለም ያው ነው ፡፡ ህዝባችን የመጣበትንና የሚሄድበትን ጠንቅቆ የሚውቅ ነው፡፡ የመጣችሁበትንና የምትሄዱበትን የማታውቁ እናንተ ናችሁ፤ መነሻችሁ ኢህአዴግ፣ መጦሪያችሁ እርሱ፤ መንገዳችሁ እርሱ፣ ኼሬ እስትንፋሳችሁም እርሱ እየመሰላችሁ ያለ ኢህአዴግ መንግሥተሰማያትም የማይገባ የሚመስላችሁና ሌላ የተሻለ መንገድ መኖር አለመኖሩን እንኳ የማትገመግሙ እናንተው እንጂ ህዝባችን ያውቃል፡፡ መስመሩ ተሳስቶ እንኳ ስህተቱን አይቶ ማረም እንዳይችል ትክክል ነን እያላችሁ ከፊቱ ተደንቅራችሁ ገደሉን ከልላችሁ ገደል እየከተታችሁት ያላችሁ እናንተው ናችሁ፡፡ ሥርዓቱ ገደሉን ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም እንዳያይ የከለላችሁት እናንተው ናችሁ፡፡ ዓላማችሁን እንኳ በውል የማታውቁ ማየት የተሳናችሁ በዓይነስውራን የምትመሩ እናንተ ናችሁ፡፡ አንድ ያደረገንን ዋናውን ድልድይ ፈርሶ እንኳ የማታስተውሉ አካለስንኩላን ከገደል አፋፍ ናችሁና ተጠንቀቁ፡፡
እውነት ነው በባህላችን አዛውንቱና አዋቂው ጥላ ሥር ይቀመጣል፤ ወጣቱም አብሮ ይሆንና ይመክራሉ፡፡ ዋናው የሚደመጠው ግን ሽማግሌው ነው፡፡ “አፊኒ” ይልና ለወጣቱም ሆነ ለአዋቂው ያደርሳል፡፡ በእንዲህ ሳይሰማና ሳይመክር ወጥቶ የሚሄድ የለም፡፡ ታዲያ እናንተ መች ይሄንን “አፊኒ” ተብላችሁና ብላችሁ መስማቱን መረጣችሁ፡፡ በሰሞኑ ቁጣ ተገፋፍተው ቢሯችሁ የመጡ ሽማግሌዎች እንኳ ልታዳምጡት መች ወደዳችሁ፡፡ ስለዚህ በወጣቱ ላይ ጣት ስትቀስሩ የቀሩት አራቱ ጣቶቻችሁ እናንተ ላይ ስለሚያመለክቱ አስተውሉ፡፡ ስለድርጅታችሁ ህዝባዊ መሠረት ያላችሁትን አሁን እርሱት፡፡ ህዝብ ቀርቶ በግለሰብ ደረጃ ማንም ከእናንተ ጋር እንደለሌ እናንተ ያሳተማችሁትን ጋዜጣ በአንክሮ ያስተዋለ ይረዳዋል፡፡ አሁን ህዝባችን እውነተኛ ጠላቱን ለይቶ ስለሚያውቅ ግድ የለም አትጨነቁ፡፡ ፀረ-ልማት ሃይልም ማን እንደሆነ ለርሱ መንገር ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው፡፡
በአጠቃላይ ይህ ቃለምልልስ የዞኑ “አስተዳዳሪ” አቶ ሚሊዮን የበሰለ ፖለቲከኛ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ ውሉ የጠፋበትና ብልጠቱ ያለቀበት የክልሉ “መሪ” ሽፈራው ይዞት ገደል እየገባ ያለ ይመስላል፡፡ ለምን ቢባል አቶ ሽፈራው የሚተነፍሰው በአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሳንባ ነው፡፡ ይህ የሆነው ፍቅር ጠንቶባቸው ወይም የዓላማ አንድነት ኖሯቸው አይደለም፡፡ ይልቅ ሽፈራው ለሃይለማሪያም አጀንዳውን ካሳካ (ሐዋሳንና አከባቢዋን ለኃይለማሪያም ካስረከበበኋላ ከስልጣን ኮርቻ ሳይሽቀነጠር በክብር ከዚህ አገር ፎቅ ቤት (G+1) ወደተሠራለት ውጭ አገር በሠላም መሸኘት ይፈልጋል፡፡ ከተቻለም አምባሳደር ሆኖ፡፡ ይሄንን ለማሳካት ሲጥር ድሮም ቢሆን በቋፍ ያለው ከሲዳማ ህዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ለአንደና ለመጨረሻ ጊዜ ከስሟል፡፡ አሁን ሽፈራው የሚባል ሰው ህዝብ ጋ መውረድ አይችልም፡፡ መንገዱ ዝግ ነው፡፡ የተበላሸበት የሚመስለው ወደታች (ወደ ህዝብያለው አቅጣጫ ብቻ አይደለም፡፡ ወደላይም ተበላሽቶበታል ምክንያቱም ሃይለማሪያም ለውለታው ወሮታውን መክፈል አይችልምና፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በጻፍነው መጣጥፋችን ለመገምገም እንደሞከርነው የሃይለማሪያም የስልጣንና የበላይነት ዕድሜ ማብቂያው ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታመዋላ፡፡ ወደሥራ የመመለሳቸው ሁኔታ ያጠራጥራል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሁኔታዎች የሚበላሹት ለሁለቱም ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለቱ ሰዎች ዙሪያቸውን በገደል በተከበቡ ማየት የተሳናቸው ሰዎች ይመሰላሉ፡፡ የፈደራሉ ዓይነስውር የክልሉን ይመስጋል፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ሁለቱም ቁልቁል መደፈቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነፍሳቸውን ይማርልን አሜን፡፡ የስጋ ሞት አላልንም፡፡ ያው ለእነርሱ ስልጣን ማጣት ማለት ሞት ማለት ነውና፡፡ አለመሰልጠን እንዲህም አይደል፡፡ ስልጣንን በህዝብ ይሁኔታ መቀበልና መስጠት ብሎም ለተረኛው በፍቃደኝነት መተው ጫፍ መሰልጠን መሆኑን እነኦባማን መቼም የት አግኝተው ይንገሯቸው፡፡ አሁን እንግዲህ ጉዳዩ እዚህ ላይ ነው፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪ ተብየው ሚሊዮን እነዚህን ማየት የተሳናቸውን ሰዎች መከተል ምርጫው እንዲሆን የወሰነው በሳል ቢሆን ነው ማለት እንችላለንአይደለም፤ ባይሆን በሳል ስላይደለና ከህዝብ ጥቅምና ፍላጎት የራሱን ስልጣንና ፍላጎት ስላስቀደመ ነው፡፡ ብልጥ ራስወዳድ እንኳ አይደለም፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ ማጠቃለያ ሥር የጽሁፉን ማጠቃለያ ለማቅረብ አልተሞከረም፡፡ ስለ መግለጫውና መልሱ ማወቅ የፈለገ ውስጡን ማንበብ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ለማቅረብ የሞከርነው ትግላችን መና የሚቀር ሳሆን የቱን ዋጋ ያስከፍል የቱንም ያህል ይቆይ የሲዳማ ክልል እውን መሆኑ የማይቀር ሀቅ መሆኑን የማስረገጥ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል “አስተዳዳሪው” ደግሞ ደጋግሞ ሊነግረንና ሊያስተምረን የፈለገው የኢህአዴግ መሥመር ብቻውን ለህዝባችን በቂ መሆኑን፣ ጥያቄያችን ከመሥመሩ ጋር መደራደር የለሌበት ስለመሆኑ፤ ያለን አማራጭ መሥመሩና መስመሩ ብቻ መሆኑን፤ ከዚህ ውጭ ጥያቄ የሚያነሳ ሁሉ ጥያቄው ህገ-መንግሥታዊ ይሁንም አይሁንም ጠያቂው ግለሰብ ይሁን ህዝብ እርሱ “ፀረ-ልማትና ፀረ-ሰላም” ሀይል ስለሆነ ጥያቄያችንን ትተን መሥመሩ ላይ ሆነን የልማት ሥራችንን ብቻ እንድናፋጥንና ከዚህ ውጭ ስለመብት የሚያነሳልን ሁሉ “ጠላታችን” ስለሆነ በአንክሮ እንድንጠብቀውና ከሌላው ወገን ህዝብ ጋር በሰላም መኖር እንድንለማመድና በመተሳሰብና በመቻቻል እንድንኖር መክሮናል፡፡ እኛም ለዚህ ያለንን ምላሽ በሰፊው የሰጠን ሲሆን ቀድሞውንም “ከመሥመሩ” ጋር ያገናኘን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄያችን ስለሆነ፤ ይህም የህገ-መንግሥታችን ዋናው ምሰሶና እስትንፋስ ስለሆነ፤ ይህም በተደጋጋሚ “በመሥመሩ” በራሱ ስለተናደ፤ ህገ-መንግሥቱ ሲናድ ጭራሽ እንዳይጠፋና “መሥመሩም” እንዳይፈራርስ በመስጋት ለመቻል ቢሞከርም “መሥመሩም” እራሱ ደጋግሞ ራሱን በመብላት ደርግ ደርግ ከመሽተት አልፎ መፈራረስ ስለጀመረ፤ መሠረታዊ የሆኑ “የመሥመሩ” መሪህዎች ከተናዱ “መሥመሩ” ሊኖር ስለማችል፤ ከህገ-መንግሥት የሚበልጥ የመሥመሩ ምሰሶ ስለማይኖርና ይህም ስለፈራረሰ፤ የከፋ ነገር ተፈጥሮ ውጭ ሳለንና ቤት ኖሮን ወደቤታችን ሳንመለስ ጭራሽ የቀረው የህገ-መንግሥቱ አካል ተንዶ ሳይበላን የራሳችንን ቤት የምናዘጋጅበት መንገድ መምረጡን አስቀድመናል ብለናል፡፡ የሲዳማን ቤት፡፡ አዎን የሲዳማን ክልል፡፡ እዚህ ላይ የኢህአዴግ መስመር ዋና ምሰሶ የሆነው ህዋኃት የጭቆናን ብርታትና ክፋት፣ የመብት ጥያቄ አንስቶ ማጣት ከሞትም የበለጠ የበረታ መሆኑን ስለሚውቅ ችግራችንን እንዲረዳልን ከወድሁ ሰላማዊ የሰቆቃ ጥሪያችንን እናስተላልፋል፡፡ ተጨቁኖ ታግሎ ስልጣን ይዞ መጨቆንና የጭቆና ጣር ሲኖር ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት በእውነት ይቅር የማይባልለት ሀጢአት መሆኑን ሳይረፍድ አስተውሉ፡፡ ሞት ከጭቆና ቢበረታ፣ የመብት ጥያቄ ከሞት ባይበረታ በዚያ በሰሜን ተራሮች እሳት ውስጥ አልፋችሁ ስልጣን ባልያዛችሁ ነበር፡፡ ከልብ በምክንያት የተቆጣን ከመልስና ከአሸናፊነት በፊት መላሽ ቢኖረው ባላሸነፋችሁም ነበር፡፡ ታዲያ የእኛን ጥያቄና የኋለኛውን ቁጣ ከምን ናቃችሁአትሳሳቱ ትንሽ እርሾ ሊጥ እንደሚያቦካ አስተውሉ፣ አስቡበት ብለናል፡፡ በመቀጠልም ቀሪው ወገንና ድርጅቶች ማለትም ጌደኦ፤ አማሮ፤ ቡርጂ፤ ጋሞ፤ ጎፋ፤ አላባ፤ ወዘተ ብሎም ኦህዴድ፤ ብአዴን፤ የጋምቤላ፣ የሱማሌ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል ወዘተ ህዝብ ድርጅቶች ነግ በኔ ብለው ጩ ኸታችንን እንዲያዳምጡ ዳግም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ ከዚህ ቀደም ባስተላለፍነው ጥሪ ምላሽ ብናጣም መቼም ወገን ነውና ዳግም በራቸውን እናንኳኳለን፡፡ እስከዛሬ ጥያቄ ስናነሳ የነበረው ለኢህአዴግ ነበር፣ በመስመር ላይ ሆነን ማለታችን ነው፡፡ ዛሬ ግን ይህ መልክ እየተቀየረ ነው፡፡ በእኛ ስህተት ግን አይደለም፡፡ የባሰ መፈራረስ ሳይመጣ ቢረፍድም ጭራሽ ሳይጨልም እንድታስቡበትና በፍጥነት እንድትመክሩ አደራ እንላለን፡፡
ቀድሞውንም ቢሆን ህዝብ ወደ ትግል የሚገባው ሲበደል፣ ፍትህ ሲያጣ፣ የራሴ ያለው ሲወሰድበት በአጠቃላይ በልማትና አስተዳደር ጉዳዮች የበኩሉን ድርሻ እንዳይጫወት ሲገደብና የስልጣን ባለቤት ሳይሆን ሲቀር ጫንቃው መሸከም እስከሚያቅተው ችሎና ትቶ በደሉ ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ነው፡፡ በታሪክ ለማየት እንደሚቻለው ህዝብ አንዴ ጥያቄ አንስቶ ሳይመለስለት ቀርቶ ወደትግል ከገባ በኋላ መንግሥት (የእኛን አገር ጨምሮከራሱ ህዝብ ጋር ታግሎ ያሸነፈበት አገር የለም፡፡ ህዝብም ተሸንፎ ቤቱ የገባበት አገር የለም፡፡ አይኖርምም እንዳውም “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንዲሉ መንግሥት ምላሽ ባዘገየ መጠን የህዝብ ቁጣ ገንፍሎና አድማሱም ሰፍቶ ሌሎች ተበድለው በየቤቱ አምላካቸውን እየተማጸኑ ያሉ ወገኖች ሁሉ ወደትግሉ ይከቱና ሁሉንም በእጁ ጨብጦ ትንሿን የህዝብ መብት ለመቀማት የቋመጠው መንግሥት የራሱንም አጥቶ ከስልጣን ይወርዳል፡፡ ዋናዋን ኬክ ያጧታል (በራሳቸው ቋንቋ)፡፡ ይሄነ ሌላው አምባገነን እስከሚመጣ ስልጣን የህዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በወቅቱ መልስ ካልተሰጠው የህዝባችንም ትግል ውጤት ይህ እንደሚሆን እርግጠኞች ነን፡፡ ቆይ እስኪ እንጠይቃቸው ለመሆኑ ከእኛ ሌላ ሲዳማ አለ ማነው ሲዳማሲዳማ የክልል ጥያቄ አላነሳም የምትሉን ጥያቄው ቀርቦ የነበረው ያውም ከምክር ቤቱ የወትሮው አሠራር በተለየ መልኩ በፊርማ ነበር፡፡ ያ ፊርማ አሁንም አለ፡፡
የሲዳማ ህዝብ ዋናና መሠረታዊ ጥያቄው አንድ ብቻ ነው፡፡ የሲዳማ ክልል አስተዳደር ጥያቄ፡፡ ያለው አጀንዳ አንድ ብቻ ነው፡፡ የራሱ የሆነ የሲዳማ ክልል አስተዳደር አጀንዳ፡፡ ከማንም ስላልተጣል የእርቅ አጀንዳ የለውም፡፡ የህዝባችን የወቅቱ ጥያቄና አካሄድ ዋና ዋናው የሚከተለው ስለሆነ አብረን ለመተግበር እንሞክር፡፡
ጥንቃቄ የሚሹ መሠሪ ተግባሮቻቸው
  1. በአሁኑ ጊዜ እንደትልቅ ጥበብ ይዘው እየሠሩበት ያለው አካሄድ በወጣቱ ተቀባይነት ይኖራቸዋል ተብለው የሚታመኑ የወጣቱ ጓደኛ የነበሩ ወጣቶችን በመሾም እነዚህ አዲስ ወጣት አመራሮች የክልል ጥያቄውን አንግበው ህዝብ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን በጓደኝነትና በጥቅም ይዘው እንዲያዘናጉ፣ እንዲያረሳሱና ጥያቄው እንዲዳከም ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ፣ ከተቻለም በተቃራኒው እንደራሳቸው ካድሬ አድርገው እንዲጠቀሙ ታቅዶ ተሠማርተው እየሠሩ ያሉ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡ እነዚህ አዲስ አመራር ወገኖች መጀመሪያ ለሲዳማ የክልል ጥየቄ አይመለስም የሚለውን ሀሳብ እንዲያምኑ የተደረጉ ናቸው፡፡ ለዚህም ማባበያና አፍ ማስያዣ ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦ መምጣቱ ተደርሶበታል፡፡ ምንም እንኳ ወጣቱ በዚህ ተታሎ መብቱን ይሸጣል ተብሎ ባይጠበቅም በራሱ በወጣቱ፣ በምሁሩ፣ በሽማግሌውና በሁሉም በህ/ሰቡ ትኩረት ተሰትጥቶና በአንክሮ ሊመከርና ውድቅ ሊደረግ የሚገባ አደገኛ አካሄድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል እንላለን፡፡ በመቀጠልም ክልል ሰው የሚሰጠንና የሚነሳን ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥትም ሆነ መስመር የሚሰጠንና የሚከለክለን ዳቦ አይደለም፡፡ ክልል የመሆን መብት ህገ-መንግሥቱ የሰጠንና እኛም የወሰነው መሠረታዊ መብት ነው፡፡ ካልተከበረም የትኛውንም ዋጋ ከፍለን የምናስከብረው ዋናው የመኖር ያለመኖር ህልውናችን ነው፡፡ ቤቱ ተወስዶበት ወይም በመሬቱ ላይ በሀገሬው ህግ መሠረት ቤት ለመቀለስና ለመሥራት ፈልጎ ተከልክሎ እሽ ብሎ ትቶ የሚቀመጥ ማነውይሄንን የሚቃወም አካሄድ ከየትም ይምጣ መንግሥትን ጨምሮ ኢህገ-መንግሥታዊ አካሄድ ነው፡፡ ለህገ-መንግሥት መገዛት ያለበት ህዝብ ብቻም አይደለም መንግሥትና መስመርም ነው፡፡ ይህ ህግ ከየትኛውም ህግና መስመር የበላይ ህግ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ሲዳማ ክልል ሆነናል፡፡ የቀረው እውቅና የማግኘት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው እየታገልን ያለነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ማባበያ ልንታለል እንደማይገባ መረዳት አለብን፡፡
  2. ጥሩ ሲዳምኛ ተናጋሪ የሆኑና ሲዳማ ውስጥ አድገው የህዝቡን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ ነባር የደህንነት ሰዎች ከያሉበት ከሀገሪቷ የተለያዩ አከባቢዎች ተጠራርተው ሲዳማ ከተዋል፡፡ ሀዋሳን ጨምሮ ሁሉም የዞኗ ከተሞች በነዚህ ወገኖች ተጨናንቀዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ሙሉ በሙሉ የህዝባችን ጠላቶች ናቸው ብለን ባናምንም ግን በርካቶቹ ሰላዮች ግን ጡቱን ጠብተው ያደጉበትን ህዝብ እየበሉትና አሳልፈው ለጠላት እየሰጡት ነው፡፡ የእናት ጡት ነካሾች፡፡ በርግጥ ከፍሎቹ ይሄንን እውነታ አያጡም ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ ባንሸማቀቅና ባንፈራቸውም መጠንቀቅ ጥሩ ነው እንላለን፡፡
ወቅታዊ አቅጣጫዎቻችንና አቋሞቻችን
  1. መሠረታዊ ጥያቄያችን የሲዳማን ክልል መንግሥት እውን ማድረግና በውስጡ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሠረት የመጣል ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህም አጀንዳ ውጭ የትኛውንም የማስመሰልና የማሞኛ አጀንዳ አንስተን መነጋገር የለብንም፡፡ አሁንም አቋማችን አንድ ነው፡፡ ጥያቄያችን እስከሚከበር ድረስም በርትተን እንሠራለን፡፡
  2. ከህዝባችን ሆድና ጀርባ የሆኑ፣ ህገ-መንግሥቱንም ሆነ መስመሩን ከመጠበቅ ይልቅ እየናዱ ያሉ፣ መንግሥት ትክክለኛውን የህዝብ ስሜትና ጥያቄ እንዳያውቅ መሀል ገብተው ደንቃራ በመሆን ሥርዓቱን እየናዱ ያሉ አሁን ስልጣን ላይ የሚቆዩበት ምክንያት የለም፡፡ በርግጥ የሚታገሉት ለራሳቸው ወንበርና ጥቅም እንደሆነ ቢታወቅም አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህም የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቢረፍድም ሳይጨልም በራሳቸው ፍቃድ አመልክተው ስልጣን እንዲለቁ(resignation) እናሳስባለን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለህዝባችን ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ስለማይበጅ ሀሳቡን ሳይንቁ ቢያስተውሉና ቢወስኑ ጥሩ ነው እንላለን፡፡ በፍቃደኝነት ስልጣን መልቀቅ መሰልጠን መሆኑን እውነተኛውን ስልጣን እንኳ ከሚለቁ ከጃፓን፣ ከአሜሪካና ከእንዶኔዥያ መሪዎች ሊማሩ ይገባል፡፡
  3. የህዝባችንን ህገ-መንግሥታዊ ጥያቄ አንስተው የታሰሩና የሚታሰሩ ወገኖች ካለምንም ቅድመሁኔታ እንዲፈቱና ጥያቄው በአስቸኳይ እንዲመለስ ባገኘው አጋጣሚና መንገድ ሁሉ ሰላማዊ ጫና እንዲፈጥር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ ከዚህ ቀደም በገባነው ቃል መሠረት (አብሮን የሚታገል ማንኛውም ሰው ሲታሰር እስከሚፈታ ቀጣይነት ያለው ጥያቄ ማቅረብና እስከመጨረሻው ከጎኑ/ኗ መቆም በሚለው ኪዳናችን መሠረትአሁን ታስረው ያሉት ወገኖች በአስቸኳይ እንዲወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋል፡፡
  4. ሲአን ህዝባዊ መሠረት ነበረው፡፡ ህዝብን አታግሎና ታግሎ እንደነበር አይካድም፡፡ ህዝብ የሞተለትና ደሙን ያፈሰሰለት ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ የግለሰቦች ድርጅት አይደለም፡፡ በሲዳማ ደም የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡ አሁን ያለበት ሁኔታ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ ራሱን ገምግሞ፣ በብቁ አመራር አደራጅቶ ወደትግል የማይገባ ከሆነ በታሪክ ከመጠየቅ አይድንም፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ የተሃድሶ እርምጃ እንድወስድ በሲዳማ ህዝብ ስም እናሳስባለን፡፡
  5. እነሽፈራው ከዚህ በኋላ የሚታመኑበት ምክንያትና ሁኔታ የለም፡፡ እነርሱን ፍለጋ ህዝባችን ሓዋሳ የሚመጣበት ምክንያት የለም፡፡ ሊያነጋግሩት ከፈለጉ ያለበት መሄድ አለባቸው፡፡ ስለዚህ አንድም ተሰብሳቢ ወደሐዋሳ መምጣት የለበትም፡፡
  6. ስብሰባ የትም ይደረግ የት ዋናው አጀንዳችን ሁሌም “የክልል ውሳኔው ተግባራዊነቱ ለምን ዘገየ?” የሚል ብቻ መሆን እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ ከዚህ ሌላ የመነጋገሪያ አጀንዳ የለንም፡፡
  7. ከማንም ጋር ስላልተጣላን ይቅርታ የምንጠይቀውም ሆነ ስለዚህ ጉዳይ የምንነጋገረው አካል የለም፡፡ ስለዚህ ማንም ሲዳማን እወክላለሁኝ የሚል ይሄንን ስህተት እንዳይሠራ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ይልቅ በመንግሥት፣ በእነኃይለማሪያምና በነሽፈራው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት የሲዳማ ህዝብ መሆኑ ሊሠመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
  8. በዞን ደረጃ ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የሽማግሌዎች ሸንጎ ተቋቁሟል፡፡ በባህሉ ድሮም ቢሆን ከየወገንና ከየጎሳ የተውጣጣ ሸንጎ የነበረውና ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአሁኑ የሚለየው ከሁሉም ወረዳዎች የመውጣጣቱ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ሸንጎ ያቋቋመው ማንም አይደለም፡፡ ያው ሽማግሌው ራሱ ነው፡፡ በርግጥ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቢያንስ ውሳኔያቸውን መዝግቦ የሚይዝና በጽሁፍም ጉዳዩ ለሚመለከተው ወገን የሚያቀርብ ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ሸንጎ መቼም ቢሆን የማይፈርስ መሆን አለበት፡፡ ቀጣይነት ባለው መልኩ በሲዳማ ክልል “አፊን” ሳይባል ወሳኝ በሆኑ የህዝብ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዳይተላለፍና አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ህዝቡን ሳያማክሩ ሄደው እንዳይሳሳቱ ጥላና ከለላ መሆን አለበት ተብሎ ይታመናል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ሸንጎው ተቀምጦ የሚመክርበት ቦታ ችግር ሆኖበታል፡፡ ስለዚህ ቋሚ ጽ/ቤትና የተደራጀ አሠራር ይኑረው የሚሉ ወገኖች እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጽ/ቤታቸው የሚይዝና ጸሃፊ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው፡፡ ጽ/ቤቱ በበጀት የተደገፈ መሆን እንዳለበትም ታምኖበታል፡፡
    1. አሁን ባለንበት ሁኔታ የሽማግሌዎቹ ጥያቄና ውሳኔ “የክልል ጥየቄው መልስ ይሰጠን፡፡ ለምን ዘገየበጋዜጣና በራድዮ የሰደቡንና ህዝባችንን ያወኩ ወገኖች ህዝባችንን በይፋ በዚያው በሰደቡትና ባወኩት መንገድ ይቅርታ ይጠይቁ…” የሚል ነው፡፡
    2. ባለፉት ጊዜያት ጥቂት የሥርዓቱ ካድሬዎች ሽማግሌዎቹ እንዳይገናኙ ያላደረጉት ደባ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ቱላ ለመገናኘት ቀን ቆርጠው ከየቦታ ሲሰባሰቡ መንገድ ላይ ጠብቀው “ቦታ ተቀይሯል እዚያ ሂዱ፣ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል…” ወዘተ እያሉ አሳስቷቸው ስብሰባቸው ፍሬ አልባ ሆኖ እንዲበተን አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህም የተነሳ ሽማግሌዎቹ “እንዲህ የምረበሽ፣ የምታወክና መሰብሰቢያ ቦታ የማጣ ከሆነ እንዳውም ሐዋሳ ጉዱማሌ እገናኛለሁኝና ቦታ አዘጋጅልኝ…” ብለው ለዞኑ አስተዳደር መልዕክት ልከው እንደነበር የሚታወቅ ስለሆነ የቀረበው ጥያቄ በአስቸኳይ ተግባራዊ መደረግ አለበት እንላለን፡፡
    3. እኛም የምንለው ሽማግሌዎች ወደየአመራሩ ቢሮ እየተጎተቱ ከሚቸገሩ በርግጥ አመራሩ ህዝቡን እወክላለሁኝ የሚል ከሆነ ሽማግሌዎቹ ተዘጋጅተው አመቺ ቦታ ተመርጦና ተመቻችቶ አመራሮቹም እነርሱ ያሉበት ሄደው እንዲያነጋግሯቸው መደረግ አለበት፡፡
    4. የአመራሩ ውሸታምነት ያሳዘነውና እየተኬደ ያለው አካሄድ መሰሪ መሆኑንና ጥያቄው በዚህ መልኩ ከቀጠለ ላይመለስ እንደሚችል የተጠራጠረው አርሶአደር አመራሩን (የዞኑንም ሆነ የወረዳዎቹን) “አትምጡብኝ፣ ላነጋግራችሁ የምችለው ጥያቄዬ የሚመለስ ከሆነ ብቻ ነው፣ ሌላ የትኛውንም አጀንዳ ይዛችሁ አትምጡ…” ብሎ መልዕክት ልኮ አሳውቋል፡፡ ስለዚህም ዛሬ ወደህዝብ የሚወርድ ደፋር የለም፡፡
  9. በመጨረሻም ልናነሳ ግድ የሆነው ጉዳይ ከመጀመሪያ አቋማችንን ከገለጽንበት ጽሁፋችን ጀምሮ እርስ በርስ ወደመታገል እንዳንገባ፤ እንዳንከፋፈልና እንድንጠባበቅ የተሳሳቱትን ጥቂት አመራሮች እንኳ ሳይቀር እንድንመክርና በዘመድ አዝማድ እንድናስመክር የተስማማንና የአቋም መግለጫ ያወጣን ሲሆን ሆን ብለው ግን እርስ በርስ እንድንጋጭ እያደረጉን ናቸው፡፡ እስከአሁን ድረስ ለምሳሌ ሽፈራው ላይ እንኳ ምንም እዚህ ግባ የሚባል መሠረታዊነት ያለው በመረጃ ላይ የተደገፈ ጽሁፍ አላቀረብንም፡፡ ይህም የሆነው እርስበርስ ላለመናቆር ሆን ተብሎ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ስማቸውን እያነሳን ያለነው ያው በሬድዮ፣ በቲቪና በጋዜጣ ሲሰድቡንና ስለህዝባችን የተሳሳተ መረጃ ሲያስተላልፉ ይሄንኑ ለመቃወምና ለማስተካከል ስማቸውን ማንሳት ተገቢ ስለሚሆን ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ የተነሳ ከዚህ በኋላ በተቻለ መጠን ስማቸውን ባናነሳ መልካም መሆኑ ስለታመነበት ይሄንኑ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ማሳሰቢያይህ ሰነድ ኮፒ የደረሰው ማንም የብሔሩ ተወላጅ በዛሬው ቀን ኮፒ በማድረግ ይሄንን ሴራ ለመቀልበስ የሚደረግ ትግል እንዲደግፍ እንጠይቃለን፡፡ በአገሪቱ ለሚገኙ የብሔሩ ዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች በትክክል እንዲደረሳቸውና በአከባቢያቸው በቂ ግንዘቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል እንላለን፡፡ ሐምሌ 20/2004

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር