ከሃዋሳ -ጐፋ ፣ ከሃዋሳ – አርባ ምንጭ፣ ሃዋሳ -ተርጫ አዳዲስ የትራንስፖርት መስመሮች ተከፈቱ



አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2004 (ዋኢማ) - በደቡብ ክልል ባለፈው የበጀት ዓመት የተከፈቱት 11 አዳዲስ የትራንስፖርት መስመሮች የአካባቢውን ሕዝብ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ አስችለውታል። ነዋሪዎቹም ይህንን የሚመሰክሩት አዳዲስ የትራንስፖርት መስመሮች እንዲከፈቱና የተከፈቱትንም እንዲጠናከሩ በማሰባሰብ ጭምር ነው።

መነሻቸውን ሃዋሳ መናኸሪያ ካደረጉና ወደተለያዩ አካባቢዎች ከሚጓዙ ተሳፋሪዎች መካከል ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ለማቅናት በዝግጅት ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ መሰለች መስቀል ከዚህ በፊት ከነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት ጋር ሲያነፃፅሩት በአሁኑ ወቅት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ይጠቁማሉ።

«ከዚህ በፊት ከሃዋሳ ወደ አርባ ምንጭ በተቆራረጡ መስመሮች ነበር የምንጓዘው። በዚህ ምክንያት ላልተፈለገ ወጪ፣ ለጊዜ ብክነትና ለእንግልት እንዳረግ ነበር» የሚሉት ወይዘሮዋ፤ በአሁኑ ወቅት ግን አዲስ መስመር ተከፍቶ አገር አቋራጭ አውቶቡስ በመመደቡ ችግሮቹ መቃለላቸውን ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ መሰለች ገለፃ፤ ከዚህ በፊት በቅጥቅጥ ተሽከርካሪ ወይም በተለያዩ የተሽከርካሪ ዓይነቶች ከሃዋሳ – አርባ ምንጭ ከ85 ብር በላይ ክፍያ ይጠየቅ፣ ጉዞውም ከስምንት ሰዓት በላይ ይወስድ ነበር። በአሁኑ ወቅት በአገር አቋራጭ አውቶቡሶቹ ለመጓዝ የሚጠየቀው ክፍያ 81 ብር መሆኑንና ጉዞውንም ከስድስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ይቻላል።

ከዚህ በፊት ተገልጋዩ ከተሣፈረ በኋላ ከታሪፍ ዋጋ በላይ ጭማሪ የሚደረግበት ሁኔታ እንደነበር አመልክተው፤ የአዳዲስ መስመሮች መከፈት እነዚህንና መሰል ችግሮች ማስወገዱን ይገልፃሉ። ተገልጋዩ ጥሩ መስተንግዶ እንደሚያገኝም ይናገራሉ።

«አዳዲስ የትራንስፖርት መስመሮች ከተከፈቱ በኋላ የተመደቡት አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች የተሳፋሪው ምቾት እንዲጠበቅና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሎታል» የሚለው ደግሞ ወደ ወላይታ ከተማ ለማምራት በዝግጅት ላይ ያገኘነው ወጣት ዮሐንስ ዋዳ ነው። 

«አገር አቋራጭ አውቶቡስ መብትህ ተከብሮልህ የምትጓዝበት ተሽከርካሪ ነው» የሚለው ይኸው ወጣት፤ በበዓላትና አልፎ አልፎ የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊው ቁጥር በሚበዛበት ወቅት የሚያጋጥሙ የአገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችን እጥረት መፍታት እንደሚገባ ነው ሃሳቡን የገለጸው።

በጋሞ ጐፋ ዞን አሳው ወረዳ ከተማ ሳውል ወደ ወላይታ ከተማ በማምራት ላይ ያገኘነው ወጣት ተስፋዬ እስጢፋኖስ ደግሞ የመስመሮቹ መከፈት በአካባቢው ለሚገኘው ሕዝብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ማስገኘታቸውን ይገልፃል።

«በመለስተኛ አውቶቡሶች ከሳውላ ወላይታ ለመጓዝ የ55 ብር ክፍያ ይጠበቅብን ነበር» የሚለው ተስፋዬ፤ በአሁኑ ወቅት ለአገር አቋራጭ የሚጠየቀው ክፍያ 45 ብር ብቻ እንደሆነም ይጠቁማል።
ወጣት ተስፋዬ እንደሚለው፤ ከሳውላ ወላይታ የአገር አቋራጭ መኪኖች በፍትሐዊ ዋጋ እየሰጡ ያሉት አገልግሎት የነዋሪውን ሕዝብ የሚያረካ ቢሆንም አልፎ አልፎ የመቋረጥ ሁኔታ አለ። ይህንን ችግር በማስወገድ የትራንስፖርቱን አቅርቦትና አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል።

ከሃዋሳ ወላይታ ተርሜ መስመር የአገር አቋራጭ አውቶቡስ አሽከርካሪ አቶ በላቸው መሣይ በበኩላቸው «በመስመር ሥምሪት የተመደቡ ተሽከርካሪዎች ሕጉና ሥርዓት አክብረው በታሪፉ መሠረት በማስከፈል ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው» ብለዋል።

በደቡብ ክልል በትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የትራንስፖርት አቅርቦት አደረጃጀትና ስምሪት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ተሾመ ዩጌ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፈው ዓመት የተከፈቱት አዳዲስ መስመሮች ከዚህ በፊት የትራንስፖርት እጥረት የነበረባቸውን አካባቢዎች ችግር ፈትተዋል።

ከዚህ በፊት «ሩቅ ነው መንገዱ አይመችም» በማለት አንዳንድ አሽከርካሪዎች ሰበብ ያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፤ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት ከአገር አቋራጭ ተሽከርካሪ ማኅበራት ጋር ውይይት ተደርጐ አዳዲስ መስመሮቹን ከመክፈት በተጨማሪ የመስመር የዕጣ ድልድል መውጣቱንም ይገልፃሉ።

በቀጣይ በክልሉ ከ20 እስከ 30 አዳዲስ የትራንስፖርት መስመሮችን ለመክፈት መታቀዱን ገልጸው፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ሽፋንና ጥራት ለማሣደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ። ሕዝቡ ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ ሚኒባሶች እስከ 150 ኪሎ ሜትር፤ መለስተኛ አውቶቡሶች እስከ 250 ኪሎ ሜትር እንዲሁም አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎቹ ከ300 በላይ ኪሎ ሜትር ርቀት ባላቸው መስመሮች እንዲሠሩ መደረጉንም ይናገራሉ። አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችን እንደየባለሀብቶቹ ፍላጐት ከ300 ኪሎ ሜትር በታች ባሉ ርቀቶች ማሣተፍ እንደሚቻልም ይጠቁማሉ።

አቶ ተሾመ እንደሚናገሩት፤ በክልሉ አዳዲስ የተከፈቱ የትራንስፖርት መስመሮች ኩተሬ - አዲስ አበባ፣ ቂልጦ – ጉመሬ - አዲስ አበባ ቂልጦ – ላፍቶ ሌንቃ – አዲስ አበባ፣ ቂልጦ - አዳማ እንዲሁም ጦራ – ዝዋይ፣ ሃዋሳ -ጐፋ ፣ ሃዋሳ – አርባ ምንጭ፣ ሃዋሳ - ተርጫ - ጭዳ - ጅማ፣ ሆሳዕና - ጅማ፣ ሆሳዕና አዳማና ሳንኩራ - አዲስ አበባ ናቸው።
የትራንስፖርት ባለሥልጣን የማስታወቂያ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቤልነህ አግደው እንደሚገልጹት፤ የመስመሮቹ መከፈት፣ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመፍታት የሕዝቦችን ትስስር እያጠናከረ ነው። ልማትን ለማፋጠን የሚያግዝ በመሆኑም ባለሥልጣኑ ከክልል መስተዳድር ጋር በመተባበር በሚገነቡ መንገዶች የትራንስፖርት መስመሮችን በመክፈት ተደራሽነቱን ለማሣደግ እየሠራ ነው ሲል አዲስ ዘመን ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር