ለመሆኑ ደኢህዴን የምር ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋትና የማድረቅ ፍላጎት አለው ወይስ በሙስና ስም የሲዳማ ብሔር ተወላጆችን ለይቶ መምታት ነው ኣላማው ? ለመሆኑ የኪራይ ሰብሳቢዎችስ ማዕከል የት ነው? እስከ አሁን በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎች ምንድናቸው?




ሳይገባን ቀርቶ አይደለም የህዝብን ደም የመጠጠ ባለስልጣን ሆኖ ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት ሲዳማን የሚያፈንቅልላቸቸው ከሆነ ከሙስና የፀዳ የስርአቱ አርበኛ ተደርጎ መቆጠሩ አይደንቅም፡፡ በአጠቃላይ ለደኢህዴን ሙስናን መዋጋት ማለት በወረዳ ህዝብን የበዘበዘ የህዝብ ጩሄት ሲበዛ በዞን ላይ መሾም፤ የዞኑን በክልል፤ የክልሉን ወደ ፈዴራል አዛውሮ መሾም መሆኑ ከማንም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህ አይነት ከደቡብ ዞኖች ወደ ክልልና  ወደ ፈዴራል ተሸጋሽገው  ለስልጣን ሽልማት የበቁት ባለስልጣናትና ለሹመት ሽልማት ያበቃቸውን ስራ ለግንዘቤ እንዲረዳ ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1 የደኢህዴን መጨረሻ ስልጣን ደረጃ ላይ የተቀመጡ በአሁኑ ጊዜ በፌዴራል የተሾሙ ባለስልጣናት በልዩ ትዕዛዝ ከሊዝ ደንብና መመሪያ ውጪ ለራሳቸው 425 ካ/ሜ በተጨማሪ ማስፋፊያ ሳይጠይቁ 250 ካ/ሜ ጨምረው በህገ ወጥ መንገድ የያዙት መሬት ከሙስና የጸዳ ይባል ይሆን?
2 እኚው ባለስልጣን ለጓደኞቹና ለብሔሩ ተወላጆች በተመሳሳይ ትዕዛዝና መንገድ ለኢንቨስትመንት የተሸነሸነውን መሬት ወደ መኖሪያ ቦታነት አስቀይረው ለእያንዳንዳቸው 500 ካ/ሜ ያሰጡበትና የመሬት አገልግሎት አጠቃቀም እንዲዛባ ማድረጉ ምን ያስጠይቃል ጃል? ያሸልማል እንጂ፡፡

3 ለደቡብ ፖሊስ ባንድ መሣሪያ ግዥ ምክንያት 5000,000 ብር የተመዘበረና በተጨባጭ ተደርሶበት ክስ ተጀምሮ ሳለ በልዩ ትዕዛዝ የታፈነ፤ ይባስ ብሎ ይህን ምዝበራ የፈፀመውን ኮሚሽነር መልሶ በመሾም ይህን አድራጎት የታገሉ የፖሊስ አባላት ብላቴ ተወስደው በእኚ ባለስልጣን በበቀል እንዲባረሩ መደረጉ ሽልማት ቢያሰጥ ለምን ይገርማል፡፡

24 ይህ ኮሚሽነር በዳቶ ኦዳሄ ቀበሌ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል 1000 ካ/ሜ የግሉ በማድረግ ሽጦ በህገ ወጥ የበለፀገበት ሙስና ወይስ ድቁና ተደርጎ ታሰበላቸው?

5 በሀዋሳ ከተማ የተሰራ አስፋልት ስራ ሳይጠናቀቅ በልዩ ትዕዛዝ ክፍያ እንዲፈፀም ተደርጎ ቦዮቹ ሳይከደኑ በመቅረታቸው በተደጋጋሚ በሰውና በንብረት ላይ የሚደረስው አደጋ ያደረሱ የክልሉ ቁንጮ ባለስልጣናት እንደ ወንጀል አይቆጠር ይሆን፡፡

6  የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ባለስልጣን የነበሩትና የፈዴራል መንግስት ቁንጮ ባለስልጠን የሆኑት ከሀዋሳ ከተማ በጉልበታቸው በህገ ወጥ መንገድ በአስፋልት መንገድ ላይ የወሰዱትን መሬት 1.5 ሚሊዮን ብር ሽጠው ያካበቱት ገንዘብ ወንጀል ሳይሆን ወደ ፈዴራል ሲዛወሩ ለሽኝት የተሰጣቸው ገጸበረከት ይሆንን?

7 አንዳንድ የደኢህዴን ቁንጮ ባለስልጣናት የህዝብን ሀብት በዝብዘው በቤተሰቦቻቸውና በጥገኛ ባለሀብት ስም ያፈሩት ሀብት በፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲደረስባቸው ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሀዋሳ ከተማን ከብሔሩ ለማስነጠቅ መስማማታቸው ደኢህዴን ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ያቋቋመው ለምን ኣላማ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር እንዲሆን አድረጎታል፡፡   እንዲህ ነው ኪራይ ሰብሳቢነትን/ሙስናን መዋጋት!!!

8 የክልሉ ቤቶች ልማት እንተርፕራይዝ ከሚያጠናቅቃቸው መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 25% ወይም 104 ቤቶች ለሲዳማ ዞን ያለቅድመ ሁኔታ ከተሰጣቸው ቤቶች ውስጥ 49 ቤቶችን በሚስጢር በሲዳማ ስም የተከፋፈሉና በአሁኑ ወቅት ሚስጢሩ ታውቆ በመተረማመስ ያለው ጉዳይ የእነ ማን ተግባር ነው? እነዚህንና ሌሎች መሰል ደባዎች ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ያለበት አካል ማነው?
9 ማንነታቸው በውል በማይታወቁ ሰዎች በ26 በማህበራት እንደተደራጁ በማስመሰል በተናጠልም በዘመድ አዝማዶቻቸው ስም በሀዋሳ ከተማ ባልተለመደ መልኩ የወላይታ ሰፈር፣ የካንባታ ሰፈር ወዘተ እየተባለ በህገ ወጥ መንገድ የተመዘበረ መሬት ምን ቆርጦት ወንጀል ይሆናል፡፡ በእነዚህ ማህበራት ስም 644 የቤት መስሪያ መሬት ወስደው ተቀራምተዋል፡፡ እንደ ዜጋ ማንም ኢትዮጵያዊ በግልም ሆነ በማህበር ተደራጅቶ የከተማ ቦታ መጠየቅና ማግኘት የዜግነት መብት አለው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ማህበራት ፋይል እንጂ የሰዎቹ ማንነት በግንባር ተፈልጎ አለመገኘታቸው ጉዳዩ ሙሰኛ ባለስልጣናት ረጅም እጅ ያለበት መሆኑን ልዩ የሚያደርገው ነው፡፡ ይህ ማለት በወቅቱ በግርግሩ የሚፈልጉትን ወገን ለመጥቀም ሲባልና የማህበሩ አባላት በግንባር መገኘት ሳያስፈልግ በአንድ ግለሰብ እና በባለስልጣናት አማካይነት ተቀነባብሮ የተዘረፈ መሬት ነው፡፡ ታዲያ ይህን የምዝበራ ወንጀል የፈፀሙትን ባለስልጣናት ማን ይጠይቃቸው? አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ነውና፡፡

በማህበር ስም ከተቀራመተው ከከተማ መሬት ውጭ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቅርብ ዘመዶቻቸውን ከያሉበት ዞን በመጥራት እንደ እሳት አደጋ መከላከያ ስራ በዘመቻ መሬት በመከፋፈል የዚህ ብሔር ቀበሌ፣ የዚያ ብሔር መንደር እየተባለ ዛሬ በጥቂት ባለስልጣናት ብሔረሰቦች ስም የተሰየመው መንደሮች የተመሰረቱት በሲዳማ አስተዳደር ወቅት አይደለም፡፡ታዲያ ሲዳማ ሲያስተዳድር እኮ በተቻለ መጠን የሁሉንም የደቡብ ብሔር አባላትን ብቻ ሳይሆን ማንንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በከተማው አስተናግዷል፡፡የሲዳማ ብሔር አባላት ትንኝ የምታህል ጉድፍ በትልቁ ተጋንኖና ተባዝቶ ˝ ከቁንጫ ሌጦ እንደማውጣት˝ ያክል ተደርጎ ህዝቡ እንዲታወክ ይደረጋል፡፡የእነሱ ምሰሶ የሚያክል ጥፋት በዓይናቸው ውስጥ ተደንቅሮ አይቆረቁራቸውም፡፡እውነታውን ህዝብ የሚሰማበት መንገድ የለም፡፡ የደቡብ መገናኛ ብዙሀንም ቢሆን እውነቱን ፈልፍሎ ለህዝብ ከማቅረብ ይልቅ የባለስልጣናትን የውሽት ፕሮፖጋንዳ ከማናፈስ የዘለለ ስራ የለውምና፡፡የደቡብ መገናኛ ብዙሀን የሚበረታው የሲዳማን ህዝብ ለመሳደብ በሚዘጋጅ ፕሮግራሞች ላይ ምላሳቸውን ማርዘም እንጂ ለእውነትና ለፍትህ በመቆም ሀቁን ቆፍሮ ለማውጣት የሙያ ስነምግባር የላቸውም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለእውነት የቆሙ ወገኖች ወይም የፍትህ አካላት ደኢህዴን አስተዳደሩን ከሲዳማ በመቀማት ባጭር ጊዜ በማደራጀት መሬት እንዲቀራመቱ የተደረጉ ማህበራት ስም የተጠቀሰ ስለሆነ የያንዳንዱ ማህበር አባላት ከተጠቀሰው ቁጥር አንፃር ሰዎቹን (አባላቱን) በግንባር ተቆጥሮ ማረጋገጥ ይቻል ይሆን? ከሌሉስ መሬት እንዴትና ለማን ተከፋፈለ? ይህ ወንጀል እንዲሰራ አመራር የሰጡ ባለስልጣናት እነማን ናቸው? ያስፈፀሙትስ?

ሠንጠረዥ 1. የሀዋሳን መረት ለመቀራመት ሽፋን የሆኑ አባላቱ በውል የማይታወቁ ማህበራት ዝርዝር



እጅግ የሚገርመው ነገር ቢኖር ከላይ ከተጠቀሱት ማህበራት ውስጥ አንድም የሲዳማ ብሔር እንዳይገባበት መንገዶች ሁሉ ዝግ መደረጉ ነው፡፡ይህ በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ታዲያ እነዚህ ናቸው ወይ ስለ ህዝቦች አንድነትና እኩልነት የሚደሰኩሩት? ስለ መልካም አስተዳደር ተቆርቋሪ መስለው የፍትህና የልማት አርበኛ ሊሆኑ የሚቃጣቸው? ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል አሉ፡፡

ሌላው የሀዋሳ ከተማ መሬት በደኢህዴን ካድሬዎች ተቀራምተው ወደ ደቡብ አፍሪካ፣አውሮጳ እና ሌሎች አገሮች መሄጃ የትራንስፖርት ገንዘብ እንዲያገኙ ሆን ተብሎ በተደራጀ መልኩ በአንድ ሌሊት በመቶዎች የሚቆጠር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰርቶ ተስጥቶ ወዲያው በሚያሻሽጡ ደላሎች እየተቸበቸበ የብሔር አባላቶቻቸውን ብቻ ተጠቃሚ ያደረጉ እነማን ናቸው? ለምን የእነሱ ጉዳይ በደኢህዴን ባለስልጣናትና ካድሬዎች አጀንዳ ሆኖ ሲቀርብ አይሰማም? የሲዳማ ጉዳይ ሲሆን ግን ለምን ይንጫጫል?

ምንጭ፦የሲዳማ ምሁራን የማወያያ ጽሁፉን በተመለከተ በተለያዩ ማህበራዊ መረቦች ላይ ካቀረቡት ትችት ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር