የሲዳማ ፖለቲካ


ወደ ሲዳማ የባሕል አዳራሽ ሲዘልቁ በቀጭኗ መግቢያ ላይ ፊትዎን ወደ ግራና ቀኝ እንዲያማትሩ ይገደዳሉ። በስተቀኝ በኩል ብሔሩን የሚወክለው ትልቁ መሰብሰቢያ የ‹‹ሲዳማ የባሕል አዳራሽ›› በሰፊው ተንጣሎ ይመለከቱታል።
ወደ ግራ አይንዎትን ሲያማትሩ በተለያየ ቅርፅ የተሰሩና ለብሔሩ ‹ማንነት›› ዋጋ የከፈሉ ጀግኖችን የሚታሰቡበት የተለያዩ ሐውልቶች ተሰድረው ያገኛሉ። የግቢው ድባብ የባሕል አዳራሹን ከማየት
ይልቅ ጀግኖቹን ወደመመልከቱ እንዲያጋድሉ ያስገድዳል። እናም ወደ ሐውልቶቹ ተጠግተው ፊትዎን ቀና አድርገው ሲመለከቱ ጀግኖቹ ፊታቸው ኮስተርተር ብሎ የሲዳማን ባሕላዊ ልብስና የክብር መለያ ለብሰው፤ አንዳንዶቹ በፈረስ ላይ፣ አንዳንዶቹ ቀጥ ብለው ቆመው፣ የተለያዩ የጦር መሳሪያቸውን ታቅፈው ይመለከታሉ።
እነዚህን ጀግኖች ፊታቸው ላይ ያለውን ግርማ ሞገስ ብቻ መመልከቱ አያጠግብም። ምን
ቢሰሩ ነው? የሚለው ጥያቄም አእምሮን ማጫሩ አይቀርም። ከታች በእምነበረድ ላይ በተቀረፀ ጽሁፍ
ጀግኖቹ ከማን ጋር ለምን አላማ እንደተዋጉ ተፅፎ ይገኛል። ከሐውልቱ ስር ተቀርፆ የተቀመጠው ፅሁፍ የመንግስትን አቋም የሚያንፀባርቅ ነው የሚል እምነት አለኝ። መንግስት ጀግኖቹ የሰሩትን ገድል እውቅና የሰጠ ብቻም ሳይሆን ተተኪዎቹ የሲዳማ ተወላጅ ህፃናት ይህንን ታሪክ እየሰሙ አርአያ እንዲሆኗቸውም ጭምር ለማስተማሪያ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ትውልዱ ታሪክን መገረብ ብቻ ሳይሆን ‹‹ጠላቶቹ›› እነ ማን እንደሆኑ እግረ መንገዱን ያጠናም ዘንድ በሰፊው ተፅፎለታል- በሲዳማ የባህል አዳራሽ።
ሐውልቱ ስር የተቀረፀውን ፅሁፍ በአንድ ወገን እንደ መንግስት አቋም ተቀብለን፣ በሌላ ወገን የብሔሩ ተወላጅ ምሁራን የፃፏቸውን አስረጂ ፅሁፎች ይዘን፤ ሲዳማዎች ስለራሳቸው እና ስለተቀረው የአገሪቷ ህዝብ ያላቸውን አመለካከት ለመመርመር መሞከር ጠቃሚ እይታዎችን ይሰጣል። ሁለቱም የብሔሩ የ‹‹ታሪክ ወካይ›› ነን የሚሉትን ወገኖች በሚያግባቧቸው ሃሳቦች ዙሪያ እስከመጨረሻው በአንድነት እንደማይዘልቁ ዝቅ ብለን እናያለን።
በጥቅሉ ከኃውልቱ ስር የተቀረፁ ፅሁፎች ታሪካዊ ዳራ አራት የተለያዩ ዘመናትን ይወክላሉ።
የሚኒልክን፣ የአፄ ኃ/ስላሴን፣ የጣልያን ወረራንና የደርግን ስርዓት። እኔም እንደ ዘመኑ ቅደም ተከተል ትንታኔውን ወደዚህ ዘመን አሻግረዋለው።
ምሁራኑ እና ፖለቲከኞቹ
በሲዳማ ህዝብ ታሪክና ፖለቲካ ላይ ሰፊ ትንታኔ ከሰጡት ምሁራን በዋነኝነት ስማቸው ከሚጠቀሱት መካከል ስዩም ሀሜሶ ተጠቃሽ ናቸው። ስዩምና ሌሎች የብሔሩ ተወላጅ ልሂቃን በተለያየ ጊዜ የ‹ሲዳማ› ህዝብ ታሪክ በሌሎቹ ብሔሮች ዘንድ ሲታይ ያለው ግንዛቤ የተዛባ ነው
ብለው የሚያምኑም ናቸው። ሁሉንም የብሔሩ ምሁራን በአንድም ይሁን በሌላ ጠቅለል አድርገን ስናያቸው የሲዳማን ታሪክና ፖለቲካ በሚመለከት የጋራ የሆነ አቋም እና መግባባት አላቸው። በተለይ በሲዳማ የታሪክ ዑደት ከዚህ በታች ባሉ አንኳር በሆኑ ነጥቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ እና መግባባት እንዳለ ለማስተዋል ችያለሁ።
1. የአፄ ሚኒልክ የግዛት ማስፋፋት ተሞክሮ በእነርሱ አገላለፅ የ‹‹ቅኝ ግዛት›› ፖሊሲ የብሔሩን ራስ ገዝ ህልውና በእጅጉ የናደ መሆኑን፤ ባህላቸውና ታሪካቸው በሌሎች የነፍጠኛው ስርዓት ሙሉ በሙሉ በጫና ውስጥ እንደወደቀ፣
2. የአፄው አስተዳደር ቀድሞ የቆየውን ‹‹የአንድ ብሔር የበላይነት ፖሊሲ›› ይበልጥ እንደገፋበትና የፊውዳል ስርዓት ከፍተኛ መሰረት እንደያዘ፣
3. በጣልያን ወረራ ወቅት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን አርሶ አደሮቹ የመሬት ባለቤት በመሆን አንፃራዊ ነፃነት እንዳገኙ፣ 
4. ከአፄው መንግስት መውደቅ በኋላም የተተካው የወታደራዊ መንግስት ከላይ ተያይዞ የመጣውን ጭቆና ማስቀረት አለመቻሉንና እንዲቀጥል ማድረጉን፣
5. የኢህአዴግ መንግስት ‹‹ሲዳማ››ን ከሌሎቹ (ከ45 በላይ ከሚሆኑ ብሔሮች) ጋር በአንድነት በመጨፍለቅ የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄን ዋጋ ማጣቱን… በሚሉት መከራከሪያቸው ላይ የጋራ የሆነ መግባባት አላቸው ።
በአጭሩ የምሁራኑ ትንተና ሲዳማዎች የራስ ገዝ አስተዳደር በኃይል በሚኒልክ ተወርረው ተነጠቁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ እዚህ ዘመን ድረስ ጥንት የነበራቸውን የማንነት  መገለጫዎች፣ መብቶች እና ፖለቲካዊ አስተዳደሮች ከእጃቸው እንደወጡ በቁጭት ይፅፋሉ፤ ይናራሉ…።
በሲዳማ ታሪክ ላይ ሰፊ ጥናት ካደረጉት በሙሉነህ አያሌው muleayalew@yahoo.com ግለሰቦች መካከል ሶስቱ ከፃፏቸው ፅሁፎች መካከል ትንሽ እየቀነጨብን በማስረጃነት በመያዝ ለምን ይህንን ሊሉ እንደቻሉና መውጫ መንገዱ ምን መሆን እንዳለበት እንመለከት።
ብሔሩ ልሂቃን የሲዳማን ታሪክ በአጭሩ በዚህ መልኩ የሚያዩት ሲሆን ክልሉን እያስተዳደረ ያለው መንግስት በዚህ የታሪክ ዳራ ላይ ያለው አቋም በግርድፉም ቢሆን ይኸው ነው። የክልሉ መንግስት የሲዳማ ህዝብ ጭቆና ደርሶበታል ብለው ምሁራኑ በሚያነሷቸው ነጥቦች ላይ ከሁለት ሃሳቦች በስተቀርበአብዛኛው ተደጋጋፊ ሙግቶችን ይዞ እናገኛለን። የመጀመሪያው ምሁራኑ የሲዳማ ህዝብ ጥንት ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ በደል እየደረሰበት ነው በሚለው ጥያቄ ላይ የብሔሩ የፖለቲካ ልሂቃን አይስማሙም። ሁለተኛው የማይስማሙባቸው ነጥቦች የሲዳማ ህዝብን በደቡብ ክልል ውስጥ የሚያዩበት
አተያይ ነው። የብሔሩ ምሁራን ሲዳማ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተብሎ ከሚጠራው
ስብስብ ወጥቶ፣እራሱን ችሎ ክልል መሆን ይገባዋል ሲሉ በብሔሩ የመንግስት ተወካዮች በበኩላቸው አሁን ባለው ስብስብ ውስጥ መብታችን በደንብ ስለተረጋገጠልን በዚሁ መቀጠል አለብን የሚል አቋም አላቸው።
ከሐውልቱ ስር
ሐውልት 1-ባሊቻ ዎራዎ
ከባሊቻ ዎራዎ ግዙፍ ሐውልት ስር፡-
‹‹የሚኒልክ ወራሪ ወደ ሲዳማ እንዳይዘልቅ ድንበር ላይ ተዋግቶ በማዋጋት ታሪክ ሰርቶ ያለፈ ጀግና›› ይላል በአማርኛና በላቲን ፊደል በሲዳሞኛ ቋንቋ የተፃፈው ማብራሪያ፡፡
የመንግስት አቋም፡- በዚህ ሐውልት ስር የሰፈረው ፅሁፍ የመንግስት አቋም የሚኒልክን ‹‹ግዛት ስፋፋት›› ታሪክ እንዴት እንደሚመለከተው ለማየት ያስችለናል። እነዚህን ቃላቶች አስምረን
እናንብብ። ‹‹የሚኒልክ ወረራ፣ ድንበር ላይ ተዋግቶ፣ ታሪክ ሰርቶ ያለፈ ጀግና…›› የሚሉትን።
መንግስት ሚኒልክ የአሁኗን ኢትዮጵያ የሰራበትን (የኢትዮጵያ ታሪክ እና የሚኒሊክ ወረራ) መንገድ የሚመለከተው በጥቅሉ የ‹‹ቅኝ ግዛት ፖሊሲ›› ነው የሚለውን ሙግት የተቀበለ ነው።
ስለዚህ የሚኒልክ ወረራ የቅኝ ግዛት ማስፋፋት ፖሊሲ ስለነበር ባልቻ ዎራዎ ይህንን ከድንበር ለመመከት ታግለዋል የሚል ነው። ነገር ግን አልሆነም። የዚህን ጀግና ታሪክ እና በጊዜው የነበረውን የሚኒልክ ወረራ ምሁራኑ አጥብቀው ይተነትኑታል።
የምሁራኑ አቋም፡- ሲዴ ጐዶ የተባሉ የብሔሩ ተወላጅ ፀሐፊ “There are no people called
Sidamo” በሚለው ፅሁፋቸው ላይ የሚኒልክን ወረራ እና በጊዜው በብሔሩ ላይ ደርሷል የሚሉትን
ጭቆና በስፋት ያብራሩታል።
‹‹የሚኒልክ ወራሪ ኃይል ወደ ሲዳማ ክልል ሲመጣ በጊዜው የመጨረሻው የሲዳማ ንጉስ ከነበረው ባሊኪኪቻ ዎራዎ (Balichicha Worawo) ጋር ስምምነት አድርገው ነበር። ስምምነቱ ልክ የውጫሌ አይነት ውል ነበር። (የውጫሌ አይነት ውል ሲል ምናልባት በቅኝ ገዥና ቅኝ ተገዢ መካከል የተደረገ ስምምነት አይነት ለማለት ይመስለኛል)።
የሚኒልክን ጦር እየመራ ወደ ግዛቲቱ ይዞ የዘለቀው ባሻህ አቦዬ የተባሉ የጦር መሪ ናቸው። እኒህ የጦር መሪ ወደ ንጉሱ ይጠጉና ህዝቡ ማን እንደሚባል ይጠይቃቸዋል። ንጉሱም የሚመሩት ህዝብ ‹‹ሲዳማ›› እንደሚባል ቢነግሯቸውም አዛዥ ባሻህ ግን‹‹ሲዳሞ›› ብለው መጥራት ይጀምራሉ።›› ወራሪው የተወረረውን ህዝብ ለማንቋሸሽ ሁለት መንገዶችን ተጠቅሟል ይላሉ እኒህ ጸሐፊ። አንደኛው መጠሪያ ስማቸውን በመቀየር በማንነታቸው እንዲሳለቁባቸው ማመቻቸት ሲሆን ሁለተኛው ህዝቡን በባርነት ስርዓት ማስተዳደር ነው።
ስለዚህም ነው ባሻህ ‹‹ሲዳማ›› ተብሎ የተነገራቸውን ‹‹ሲዳሞ›› ሲሉ የጠሩት ይሉናል።
‹‹ምንም እንኳን በሁለቱ መካከል አስቀድሞ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም ብዙ ጊዜ መዝለቅ ባለመቻሉ ስምምነቱ ፈርሶ ጦርነት እጣ ፈንታቸው ይሆናል።
በዚህ ጦርነት የባሻህ ጦር ሽንፈት ስለገጠመው ለሚኒልክ ሄዶ ሪፖርቱን ማቅረብ ግዴታው ነበር። ‹‹ሲዳሞ›› የሚባሉ ወገኖችን እንዳልቻላቸው አብራራ። ‹‹ሲዳማ›› የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ሲዳሞ›› በሚል በቤተ መንግስት እውቅና አግኝቶ ከዚህ ጊዜ ወዲህ መጠራት ተጀመረ›› ባይናቸው ፀሐፊው።
ማጠቃለያ፡- የሚኒልክ ወረራ በብሔሩ ምሁራንም ይሁን በፖለቲካ ልሂቃኑ ዘንድ አንድ አይነት አቋም እንዳለ ተረድቻለሁ። የሁለቱም ወካይ ቡድኖች የብሔሩ ታሪክ አቀራረብ ሚኒልክ ጠቅልሎ የሰራት አገርን እውቅና የመስጠት ነገር አይታይባቸውም። የሚኒልክ ወረራ እንዳታሰበው ባይሆን ኖሮ (ምን አልባት ሌላ ወራሪ እስካልመጣ ድረስ) ‹‹ሲዳማ›› የሚባል አገር በአሁኑ ጊዜ ይኖር
ነበር ማለት ነው? እናም በእነርሱ ሙግት ሚኒልክ ብሔሩን በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ መክተቱ 
በጠላትነት አስፈርጅቶታል።
ሐውልት 2- የቴራ ቦሌ
ከሐውልቱ ስር፡- ‹‹ጭቆናን በመቃወም ጠብመንጃውን አንግቦ የነፍጠኛውን ስርዓት የታገለ ጀግና። ደርግን በመፋለም የህይወት መስዋዕትነትን የከፈለ ታጋይ››
የመንግስት አቋም፡- ይሄኛው ሐውልት የወከለው ጀግና ሁለት ስርዓቶችን ተሻግሮ የተዋጋ የብሔሩን አርበኛ ወካይ ነው። የመጀመሪያው የነፍጠኛ ስርዓቱን (አፄ ኃ/ስላሴ) ቀጥሎም የደርግን
ስርዓት፡፡ የሲዳማ ብሔር አገዛዙ በተለዋወጠ ቁጥር ጨቋኞቹም፣ ጭቆናውም አብሮ እንደ ተፈራረቁበት ማሳያ ነው። መንግስት ለእነዚህ ሁለቱ ስርዓቶች እና ገዢዎች በብሔሩ ላይ ላደረሱት ግፍና በደል እውቅና የሰጠ ነው። እንደ ነባሩ ‹‹የቅኝ ግዛት
ፖሊሲ›› ገዢዎች በኋላ የተተኩት አመራሮች ተመሳሳይ ስርዓትን ዘርግተዋል ብሎ ያምናል።
የምሁራኑ አቋም፡- የዚህ ታሪክ ትንታኔ ላይ ስዩም ሐሚሶ የተባሉ ፀሐፊን እናገኛለን። እኚህ ግለሰብ የብሔሩን አጠቃላይ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶችን ተንትኖ በማቅረብ የሚያክላቸው የለም።
አጠቃላይ በብሔሩ ብቻም ሳይሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ በርካታ ፅሁፎችንና መፅሐፍትን
ያሳተሙ ምሁር ናቸው።
እንደ ሌሎቹ የብሔሩ ምሁራን ሁሉ ስዩም ሐሚሶም የሲዳማ ህዝብ ታሪክ የቅኝ ግዛት ታሪክ ነው ብለው ያምናሉ። መፍትሄውም ሲዳማ የ‹‹ራስ ገዝ አስተዳደር›› ያስፈልጋታል የሚል ነው።
አቶ ስዩም ሐሚሶ “Arrested development in Ethiopia” በሚለው ርዕስ ‹‹ተጨቋኝ ብሔሮች››
በመጡ ፀሐፊዎች በታተመው መድብል ውስጥ “Nationalism, democracy and selfdetermination”
በሚል ርዕስ ባሳተሙት ፅሁፍ የሲዳማ ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት እየደረሰበት ያለውን 
ጭቆና በሰፊው ይተርካሉ። አቶ ስዩም የወራሪውን 
ይል በአጠቃላይ ‹‹አቢሲኒያውያን›› ሲሉ 
ይጠሯቸዋል። አገዛዙንም ‹‹የአማራ›› ይሉታል፡፡ እነዚህ ነፍጥ የታጠቁ  ‹‹የአቢሲኒያ›› ሀይሎች ምንም አቅም በሌለው ህዝብና ነፃ መሬት ላይ ያደረጉት ወረራ ከቀኝ ግዛት አይነት አስተዳደር ጋር የሚስተካከል ነው ይሉታል። ገበሬዎቹ በራሳቸው መሬት ላይ ጭሰኛ ሲሆኑ ወራሪዎቹ በበኩላቸው በሰው ሀገር መሬት ከበርቴ ሆነው ከመቶ አመታት በላይ ቆይተዋል ባይ ናቸው።
እነዚህ ኃይሎች በፈፀሙት ወረራ ምክንያት የብሔሩ ቋንቋ፣ ባህልና መንፈሳዊ እሴቶች በእጅጉ
ተፅዕኖ እንደ ደረሰባቸው ይከሳሉ። ይህንንም የባህል ጭፍጨፋ (Cultural genocide) በማለት ከሰው ልጆች አካላዊ ጭፍጨፋ ጋር አመሳጥረው ያቀርቡታል።
ሐውልት 3- የሲዳማ የባሕል አዳራሽ
ከሐውልቱ ስር፡- በሰፊው በተንጣለለው  የሲዳማ የባህል አዳራሽ ላይ ኢህአዴግ የሲዳማን ዝብ ይደርስበት ከነበረው ጭቆና ገላግሎ ቋንቋውን፣ባህሉን እና እምነቱን ነፃነት የሚያራምድበትን ነፃነት እንዳጐናፀፈው ምስክር ሆኖ ቀርቧል። የባሕል አዳራሹ የሲዳማን ህዝብ መወከያ ቋሚ ቅርስ
ከሆኑት መካከል አንዱ ነው።
የመንግስት አቋም፡- ከላይ የቀረበው አስረጂ ተምሳሌት የመንግስትን አቋም በደንብ ይገልፀዋል። የአሁኑ አገዛዝን በሚመለከት በብሔሩ ወካይ ቡድኖች መካከል ልዩነት እንመለከታለን ።
የምሁራኑ አቋም፡- ወላሳ ኩሞ “Why do Sidama reject SNNPR” በሚለው ፅሁፋቸው 
ላይ ሲዳማ ከሌሎች 45 ከሚሆኑ ብሔሮች ጋር በአንድነት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በሚባለው ጥቅል ማዕቀፍ ውስጥ መጠቃለሉን ይተቻሉ። እርሳቸው ይህንን አካሄድ ጭቆናን በሌላአይነት መንገድ ጠምዝዞ ከማምጣት ውጭ የህዝባዊ ትግሉ ጥያቄ መልስ እንዳላገኘ ይተነትናሉ።
ፀሐፊው ሲዳማ ብቻውን ክልል መሆን ሲገባው አለመሆኑ ኢህአዴግ ብሔሩን ለማዳከም ያደረገው እርምጃ ነው እስከማለት ሄደዋል። ለዚህም ሶስት ምክንያቶችን ያቀርባሉ። የመጀመሪያው ብሔሩ ለረጅም አመታት ሲጠይቅ የነበረውን የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ለማፈንና ከሌሎቹ ጋር በአንድነት ጨፍልቆ ለማስቀረት ያደረገው ነው የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት ክልሉ
በውስጡ ያመቀውን የተፈጥሮ ሀብት ለመበዝበዝ እንዲመቻቸው የቀየሱት ስትራቴጂ ነው ባይ
ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የሲዳማ ህዝብ ከ5 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ህዝብ ቁጥር በታች ያላቸው ህዝቦች የክልል መብት ሲሰጣቸው ሲዳማ ግን አላገኘም። አቶ ወላሳ በ1994 ይህንን ጥያቄ ያነሱ የሲዳማ ተወላጆች በመንግስት የተወሰደባቸውን እርምጃ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
ሶስተኛው ምክንያት ሲዳማ ጠንካራ ብሔር ሆኖ ከሌሎቹ በተለይ ከኦሮሞአቻው ጋር ህብረት ፈጥሮ
ለስርዓቱ አደጋ ይሆናል ከሚል ስጋት የመነጨ ነው ይላሉ እኚህ ፀሐፊ።
መውጫ
በሁለቱ ጎራ የተሰለፈ የብሔሩ መብት ተሟጋቾች የብሔሩ ታሪክን በሚመለከት የጋራ መረዳት ቢኖራቸውም ልዩነቶቻቸው በይበልጥ ጎልቶ የሚወጣው ካለፉት 20 አመታት ወዲህ በተከሰተው የታሪክ አተናተን እና የፖለቲካ ሁነት ትርጓሜ ላይ ነው። ለዚህ ልዩነት ያለውን ነባራዊ ሙግት በግርድፉ እንኳን ካየነው የሚከተሉት መደምደሚያዎች ላይ መድረስ እንችላለን።
የመንግስት ልሂቃን፡- ብሔሩን ወክለው በስልጣን ላይ ያሉት ግለሰቦች አሁን ያለውን ፖለቲካዊ ድል የሚያነፃፅሩት ቀድሞ ከነበረው  የአገዛዝ ስርዓት ጋር ስለሆነ የብሔሩ ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ተመልሷል የሚል እምነት አላቸው። በሌላ ጫፍ ከስልጣን ጋር ተያይዞ የሚገኙ መደላድሎች ከባለስልጣኖቹ በኩል በቀጣይ የሚነሱ ብሔር ተኮር
ጥያቄዎችን ለማፈኛ ይጠቀሙበታል።
የብሔሩ ልሂቃን፡- ብሔሩን የሚወክሉ ሌሎች ምሁራን እስከአሁን የብሔሩ ጥያቄ መልስ አላገኘም ባይ ናቸው። ለዚህም ለስርዓቱ ታማኝ በሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ። ለዚህ በመነሻነት የሚያቀርቡት መከራከሪያ የሲዳማ ህዝብ የራሱን ክልል የማዋቀር እውቅና የተከለከለበትን ሂደት በመጥቀስ ነው።
ሁለቱም (የብሔሩና የመንግስት ልሂቃን) በጋራ በቀደመው ታሪካችን ላይ ባላቸው ግንዛቤ ላይ ክፍተት ያለ ይመስለኛል። ሚኒልክ ያደረጉትን ወረራ የቅኝ ግዛት አባዜ ነው በሚለው ማመናቸው አደጋ አዝሎ እንደሚመጣ እረዳለሁ። የመጀመሪያው  ስር የሚወጡት ታዳጊዎች በአብሮነታችን ላይ ወደፊት ጥያቄ መጫራቸው አይቀርም። ማንም ቢሆን ቅኝ እንደተገዛ እየተነገረው፣ ግዛቱ ያለአግባብ እንደተቀማ እያሰበ፣በቀጣይ ነፃ መሆንን እንጂ ያለውን ስርዓት ተቀብሎ ይቀጥላል ለማለት አዳጋች ነው።
ሁለተኛው ከዚህ ታሪክ ጋር የሚጋጨው የአሁኗን ኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀበላቸው ሁነት ነው። ከላይ በ‹‹ቅኝ ግዛት ተይዘን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠቃለልነው›› የሚለው ትርክት
እንዳለ ሆኖ፤መልሶ ‹‹መብታችን ተከብሮ ነው›› ያለነው ከሚለው የአሁኑ የፖለቲካ አቅጣጫ ጋር
ይጋጫል።
ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ፖለቲካዊ ጭብጥ የማንኛውም ብሔር ጥያቄ መሰረቱ የመብት ጥያቄ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ሲዳማዎች አሁንም
ቢሆን የክልል ይገባኛል ጥያቄያቸውን እያነሱ ያሉት ያልተሟሉላቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ነው። ስለዚህም ተገቢ እና አሳማኝ መልስ ሊሰጣቸው ይገባል። ኢትዮጵያዊ መሆን የውዴታ እንጂ የግዴታ ጥያቄ መሆን የለበትም። ውዴታን የሚያመጣው ነገር ደግሞ የመልካም አስተዳደር
ጥያቄ ነው።ከኃውልቱ ስር ያለው ታሪክ የነባሩ ሳይሆን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲሱ የታሪክ ድሪቶ መገለጫ ነው፡፡
ሲዳማን እንደ ተሞክሮ
ከላይ የሲዳማን አጠቃላይ ተሞክሮ ለመዘርዘር ሞክሬያለሁ። ኢህአዴግ ከዚህ የፖለቲካ
ቁመራ ምን ሊያተርፍ ፈልጐ ነው? የሚለውንም በተጨማሪነት ማቅረብ ተገቢ ነው።
ሲዳማ የህዝብ ቁጥሩ ከሐረሪ፣ አፋር፣ሶማሊያ፣ ትግራይ……..የሚበልጥ ከሆነና ክልል የመሆንን መስፈርት ማሟላት ከቻለ ለምን ክልል የመሆን እድል ተነፈገው? የሚለውን ጥያቄ መንግስት ሊመልሰው ከቻለ መልካም ነው፤ ካልሆነ ግን ይህንን ጥያቄ በሌላ በኩል መመለስ ያስፈለገባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ማንሳት ይቻላል።
በአሁኑ ጊዜ ‹‹በብሔር›› ደረጃ አብዛኛውን የህዝብ ቁጥር የያዙት ኦሮሞ እና አማራ ናቸው።
እነዚህ ብሔሮች ካላቸው የቁጥር ብልጫ አንፃር የስልጣን ይገባናል ጥያቄን ማንሳታቸው አይቀርም።
ህጉም ቢሆን ይደግፋቸዋል። የፌዴራል ስርዓቱ ለዚህ ዋስትና እንደሆነ ህገ-መንግስቱ በግልፅ አስቀምጧል።
በኢህአዴግ ፖለቲካ ሽረባ የእነዚህ ሁለቱ የብሔር ልሂቃን ወደ መንበረ ስልጣኑ መጠጋታቸው
‹‹ታግለናል፣ ስልጣኑ ይገባናል›› ከሚሉት ገዢዎች ጋር ፊት ለፊትያላትማቸዋል። ስለዚህ የነዚህን ህዝብ ቁጥር ሊገዳደር የሚችል ሌላ ክልል መፈለግ
አስፈላጊ ነው።አሁን ባለው ደረጃ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በጋራ በመሆን፣ የተሰበጣጠረውን ውክልና ወደ አንድ በመጠቅለል እኩል እንኳን መሆን ባይቻል በተመጣጣኝ የህዝብ ቁጥር ተፎካካሪ
እንዲሆን ያስችለዋል። ስለዚህ ከዚህ ህብረት ውስጥ ሲዳማን ነጥሎ አውጥቶ የክልል መብት መስጠት ለኢህአዴግ ፖለቲካ ከሁለት ነገሮች አንፃር አደጋ
ይኖረዋል። የመጀመሪያው ሲዳማ ከደቡብ ጥቅል ህብረት ወጥቶ ክልል መሆኑ ከላይ የአማራን እናየኦሮሞን በፖለቲካው የሚገዳደራቸውን የህዝብ ቁጥር መቀነስ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ ለህወሓት ተወካዮች አደጋ መሆኑ አይቀርም።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሲዳማ እራሱን ችሎ እንደ ክልል መዋቅሩ ሌላ ተወዳዳሪ ኃይል ወደ ፖለቲካው ፉክክር ማምጣት ነው የሚሆነው። ሁለተኛው ምክንያት
የሲዳማን ፈለግ እየተከተሉ ሌሎች ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው በደቡብ ህብረት ውስጥ የተጠቃለሉ  ብሔሮችን የክልል ይገባኛል መብት ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ የሚለው ስጋት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ
ጥያቄውን እንደ ጥያቄ ከማየት ውጭ ለጊዜው መልስ ሊሰጥ የሚችል  ይመስለኝም።
የክልል ይገባኛል ጥያቄ በደቡብ አካባቢ መነሳቱ ለኢህአዴግ መንግስት እንደታዛቢ አግባብ መሆኑ ቢታመንበትም መንግስት ጥያቄውን አቻችሎ ሊያልፍበት የሚችልባቸው ሌሎች ዘዴዎችንም ቀይሷል። ከደቡብ ክልል የተገኙ ልሂቃንን በከፍተኛ የመንግስት ማዕረግ ሹመት የመስጠትን ጉዳይ።
ሹመቱ በግርድፉ ስናየው በሁለት አቅጣጫ ጠቀሜታዎች አሉት። እነዚህን  ቀሜታዎች ከወደ ጐን (Horizontal) እና ከወደ ላይ (Vertical) በኩል ልናያቸው እንችላለን።
ወደ ጐን (Horizontal)- የደቡብ ተወካይ በመንግስት የስልጣን ደረጃ ከፍ ብሎ መቀመጡ በትይዩ ከማንም ብሔር በተሻለ ቅድሚያ እየተሰጣቸው እንደሆነ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።
ይህ ደግሞ ልሂቃኑ የተቀረውን ተከታያቸው ለሌላ የመብት ጥያቄ እንዲነሳሱ አይገፋፏቸውም።
ተነሳሱትንም ለማፈን መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል። ወደ ላይ (Vertical)- በክልሉ ውስጥ
የሚገኙ የማህበረሰብ ተወካዮች ከሌሎቹ አንፃር የበታችነት እንዳይሰማቸው ያደርጋቸዋል። በከፍተኛ የመንግስት መዋዕቅር ውስጥ ከእነርሱ የተገኘ ግለሰብ ቦታውን በኃላፊነት መምራት መቻሉ ለብሔረሰቦቹ ትልቅ ደስታን ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ይታመናል።
ወደ ጐንም ወደ ላይም ኢህአዴግ ከብሔሮቹ ልሂቃን ጋር በመሆን ክልሉን በደንብ ተቆጣጥሮታል ለማለት ይቻላል። ጥያቄው ይሄ አካሄድ እስከመቼ 
ሊቀጥል ይችላል? የሚለው ነው። ምንአልባት ኢህአዴግ በመንበረ ስልጣኑ እስካለ ድረስ? ትክክለኛ
ማረጋገጫ ባይሆንም ሊቀጥል ይችላል የሚለውን እንቀበል ቢባል እንኳን የኢህአዴግ መንግስት የመላዕክት ስብስብ አይደለምና መውደቁ አይቀርም።
በዚህ ጥልፍልፍ ፖለቲካ ከኢህአዴግ በኋላስ መብታቸው የታፈነባቸው ብሔሮች በኢትዮጵያ
ወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ምን ጥያቄ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ? የሚለውንም አብሮ ማየት ያስፈልጋል። 
 http://www.fetehe.com/themes/bartik/images/185.pdf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር