ሃዋሳ የከተማ አውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ልትጀምር ነው
ሀዋሳ ፣ ሀምሌ 20፣ 2004 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃዋሳ የከተማ አውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ልትጀምር ነው።
በቅርቡም አራት አውቶብሶች ገብተው ስራ እንደሚጀምሩ ነው የከተማዋ አስተዳደር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለፀው ።
አውቶብሶቹ ከከተማዋ ውጭ ለሚገኙ አዋሳኝ ከተሞችም የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ ።
የከተማዋ አስተዳደር እንደሚለው ለነዋሪዎች የትራንስፖርት አማራጭ ከመስጠትም ባለፈ በከተማዋ ቀስ በቀስ ደረጃቸውን በጠበቁ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ ያስችላል ።
አውቶብሶቹን ስራ ለማስጀመር 24 የማቆሚያ ፌርማታዎች ተለይተዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ከ3 ሺህ በላይ የሚበልጡ ተሽከርካሪዎች ሲኖሩ ፥ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ባጃጆች ናቸው።
የአስተዳደሩ የትራንስፖርት ፅህፈት ቤት እንደሚለው የአውቶብሶቹ ወደ ከተማዋ መግባት ነዋሪው አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ፤ ዘገባው የታደሰ ብዙዓለም ነው።
Comments
Post a Comment