ባላፉት ሁለት እና ሶስት ሳምንታት በከፍተኛ የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ የነበረችው ሲዳማ ዞን እየተረጋጋች ነው፤እሁድ ማታ ወልደ ኣማኑኤል ዱባሌ ሃውልት ኣካባቢ ኣንድ ሰው በፈዴራል ፖሊስ ተገደለ ተብሎ የተወራው ወሬ ከእውነት የራቀ ኣሉባልታ ነው



የሜትሮፖሊታን ከተማችንን እንዴት እንምራው? በሚል የደኢህዴን ስራ ኣስፈጻም ኮሚቴ በሃዋሳ ከተማ የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ በየደረጃው ካሉት ከሚመለከታቸው ኣመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ኣዘጋጅቶት የነበረው የማወያያ ጽሁፍ ባልታወቁ ሰዎች ተባዝቶ ከህዝብ እጅ መግባቱን ተከትሎ የጽሁፉን ይዘት ሚቃዎሙ ሰዎች ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተቃውሞቸውን በተለያየ መልኩ ሲገልጹ ቆይተዋል።

የክልሉም መንግስት በማወያያ ጽሁፍ ላይ የተነሱ ጉዳዮች በሃሳብ ደረጃ ያሉና ገና ውሳኔ ያልተሰጣቸው እንዳውም ላልተወሰነ ጊዜ መተዋቸውን በመግለጽ ህዝብ እንድረጋጋ ጥሪ ከማቅረቡ ባሻገር በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው ኣካላት ጋር ውይይት ማድረጉ ይታወሳል።

ሆኖም ከሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር ጋር በተያያዘ እንደ መስቀል ወፍ እየጠፉ ብቅ የሚሉ ጉዳዮች ለኣንደና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ እንዲያገኙ በማለት የዞኑ ምክር ቤት የክልል ጥያቄ እንዲያነሳ የሚፈልጉ ግለሰቦች በዞኑ ውስጥ ህዝባዊ ንቅናቄ ኣድርገዋል።

የተፈጠረው ህዝባዊ ንቅናቄ ከግጭቶች ያላመለጠ ሲሆን፤ ክልል ይገባናል በሚሉ እና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሰዎች መጎዳታቸው ብሎም ዞኑ በከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ መግባቱን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል።

ምንም እንኳን በህዝባዊ ንቅናቄ የክልል ጥያቄ እንዲያነሱ ግፊት የተደረገባቸው የዞኑ ምክር ቤት ኣባላት ውሳኔ ምን እንደሆነ በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም ፤ በኣሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ውጥረቱ እየረገበ እና ህዝቡም እየተረጋጋ በመምጣት ላይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው እሁድ ማታ በሃዋሳ ከተማ ወልደ ኣማኑኤል ኣደባባይ ላይ በፈዴራል ፖሊስ ኣንድ ሰው ተገድሏል ተብሎ የተወራው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን የሲዳማ ወራንቻ ዘጋቢዎች ከቦታው ኣረጋግጠዋል።

እንደ ዘጋቢዎቹ ከሆነ በወቅቱ በፈዴራል ፖሊስ እና በኣከባቢው ነዋሪዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ ሰው ግን ኣልመሞተም።


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር