የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ከ190 በላይ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል



አዋሳ ሃምሌ 10/2004 የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ከ190 በላይ የተለያዩ የምርምር ሰራዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስታወቁ ።
ከነዚህም ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ በዩኒቨርስቲው አካባቢ በሚገኙ የቴክኖሎጂ ማመንጫና ማስፋፊያ ወረዳዎች ላይ መሆኑም ተገልጧል ።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው በነደፈዉ የአምስት ዓመት የምርምርና የልማት ስትራቴጂ ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ በሚያስገኙና ችግር ፈቺ ለሆኑ ምርምሮች ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቷል ።
ዩኒቨርሲቲዉ በተለይ በምግብና በቢራ ገብስ ቴክኖሎጂ፣ በጤፍ አመራረት፣ በድንች ፣ በደጋና በወይና ደጋ የቅባት እህሎች፣ በምርጥ የቡና ዝርያ ብዜት፣ እንዲሁም በእንሰት አዘገጃጀት ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን አስታዉቀዋል ።
በእንስሳት እርባታና በተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር ምርታማ የሆኑ የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን በምርምር ጣቢያዎች በማባዛት የማስተዋወቅ፣ የተሻሻሉ የበግና የፍየል ዝርያዎችን የማዳቀል፣ ዘመናዊ የንብ ማነብ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ስራ እያካሄደ መሆኑን ገልጠዋል ።
ዉጤታማነታቸዉ በምርምር የተረጋገጡ የሳርና የዛፍ ዝርያዎችን የተፋሰስ ስራዎች በተካሄዱባቸዉ አካባቢዎች እንዲተከሉ ለአርሶ አደሮች በማከፋፈል አበረታች ተግባር እያከናወነ መሆኑን ዶክተር ዮሴፍ አስታዉቀዋል ።
በተጨማሪ ዩኒቨርሰቲው የአምስት ዓመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ስድስት የቴክኖሎጂ መንደሮችን በመለየት ከክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮና ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት፣ በማስተዋወቅና በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው የተጀመሩ የምርምርና የልማት ስራዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተያዘው ዓመት የኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርስቲ፣ ዩኒቨርስቲኦፍ ካልፎሪኒያ፣ ኦስሎ ዩኒቨርስቲ፣ ኬፒታን ዩኒቨርስቲ ኢንቻይናን ጨምሮ አስራ ሰባት ከሚሆኑ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ዮሴፍ አመልክተዋል ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር