የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ያቋቋመዉ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ስርጭቱን ጀመረ



ሃዋሳ ሰኔ 21/2004 የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ከ2 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በዋናው ግቢ ያቋቋመው የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ትናንት ተመርቆ ስርጭቱን በይፋ ጀመረ፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ የሬዲዮ ጣቢያውን ለአገልግሎት ሲከፍቱ እንደተናገሩት የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዉን ለማቋቋም የተቻለዉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ባደረገዉ ድጋፍና በዩኒቨርሲቲዉ ጥረት ነዉ ። በአሁኑ ጊዜ የጣቢያዉ የስርጭት አቅም 50 ኪሎ ሜትር ሬዲዬስ የሚሸፍን ሲሆን ወደፊትም ይህንን አድማሱን በማስፋት የተጠቃሚዉን ህብረተሰብ ቁጥር ለማሳደግ እቅድ ተይዟል ብለዋል ።
የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ በተለይ የመማር ማስተማሩ ስራ ከምርምር፣ ከዕውቀትና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር አያይዞ ለእድገትና ልማት የሚበጁ መረጃዎችን በማስተላለፍ ጠቃሚ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታዉቀዋል ።
ህብረተሰቡ በሬዲዮ ጣቢያው ተጠቅሞ ጥያቄ የሚያቀርብበት፣ መረጃ የሚሰጥበት፣ ስራዉን የሚገመግምበት፣ ያሉትን ክፍተቶች የሚጠቁምበት እንደሚሆንም ያላቸዉን እምነት አሳስበዋል ።
ዩኒቨርሰቲው በቅርቡ በጋዜጠኝነትና ማስ ኮሙኒኬሽን ለከፈተው አዲስ ፕሮግራም የተግባር መለማመጃ በመሆን ጭምር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ዶክተር ዮሴፍ አስታዉቀዋል ።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ተወካይ ሚስተር ሮበርት ፖስት/m.r robert post /በበኩላቸው መንግስታቸው የሀገሪቱን ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ በተለይ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና የእናቶች ጤንነትን ለማጎልበት የሚረዱ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አስታዉቀዋል።
ከዚህም ባሻገር የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ለማሰፋፋት በሚደረገዉ ጥረት ከአሁን ቀደም ለሀሮማያ ዩኒቨርስቲ አሁን ደግሞ ለሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መንግስታቸዉ ድጋፍ ማድረጉን ገልጠዋል።
ለወደፊትም የቁሳቁስና የባለሙያ ስልጠናን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
የሬዲዮ ጣቢያው ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ባለው የስርጭት ፕሮግራም የትምህርት፣ የምርምር ውጤቶችን፣ የግብርና ልማት ፣ ጤና ፣ ጠቅላላ እውቀት፣ መዝናኛና ሌሎችንም ፕሮግራሞችን እንደሚያቀርብ የጣቢያው ኃላፊ አቶ አንተነህ ደግፌ አስታዉቀዋል ።
በዚሁ ጊዜ ለማህበረሰቡ ሬዲዮ ጣቢያ መቋቋም የላቀ አስተዋጾኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የማበረታቻ የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሲዳማ ባህላዊ አልባሳት ተበርክቶላቸዋል ።

http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=362&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር