የአዋሳው እሳት የወያኔ መጥፊያ ይሆናል!!!


ከአስር ዓመታት በፊት “ሲዳማ ክልል ሁና ትደራጅ” የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው በአንድ ቀን ውስጥ ከ60 በላይ የሆኑ የአዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በአጋዚ ጦር በግፍ ተጨፈጨፉ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ለአካል ጉዳቶች ተዳረጉ፤ በርካቶች ታሰሩ። ከሰባት ዓመታት በፊት ደግሞ  - በምርጫ 97 ማግሥት – “ድምፃችን ይከበር” በማለታቸው እስካሁን ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ የአዋሳ ወጣቶች ተገደሉ፤ በርካታ ወጣቶችና አዛውንት ታሰሩ፣ ተደበደቡ፣ ተጋዙ።

ዛሬም አዋሳ በውጥረት ውስጥ ነች።

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ሠራዊት እንደለመደው የአዋሳን እና የአካባቢው ነዋሪዎች ሊገድል፣ ሊያቆስል፣ ሊያስር ዘምቷል። ከአዋሳ ወጣ ብላ በምትገኘው አለታ ጭኮ የመለስ ዜናዊ ፓሊሶች ነዋሪዎችን ገድለዋል፤ በርካቶችን አቁስለዋል። ነዋሪዎችም በፓሊሶች ለደረሰባቸው ጥቃት በወሰዱት የመከላከል እርምጃ አንድ ፓሊስ ሕይወቱን አጥቷል። የሚሰማቸው ጆሮ አላገኙም እንጂ ሕዝብን ከሕዝብ በማጣላት ሙያ የተካኑት  የመለስ ካድሬዎች “አዋሳ ከተማ ወደ ፌደራል ትጠቃለል  ያሉት ወላይታዎች ናቸው” እያሉ በማስወራት ላይ ናቸው።

መለስ ዜናዊ የፈጠረው ዘርን ብቻ መሠረት ያደረገው “ፌደራሊዝም” በማር የተለወሰ መርዝ መሆኑ ባለፉት ሃያ ዓመታት በተግባር ያየነው ጉዳይ ነው። የመለስ ዜናዊ የውሸት ፌደራሊዝም ከሁሉም የአገራችን ክፍሎች በባሰ የተሳለቀበት “የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት” በሚባለው የአገራችን ክፍል ነው። አዋሳ ደግሞ የዚህ የአቅጣጫ ስያሜ የተሰጠው “መንግሥት” መቀመጫ ናት። አዋሳ እና እሷ የምትወክለው “የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት” የመለስ ዜናዊ ፌደራሊዝም አስከፊ ገጽታ ማሳያዎች ናቸው። በመለስ ዜናዊ ፌደራሊዝም ምክንያት ውቧ አዋሳ የግጭቶች ማዕከል ሆናለች።

ይሁን እንጂ የአዋሳም ሆነ ሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች የመለስ ዜናዊን ዘረኛ አደረጃጀት እና ዘረኛ አገዛዝ ተቀብለው አያውቁም።  መምህር የኔሰው ገብሬ ኅዳር 4 ቀን 2004 ዓ.ም

“በደል በዛ!!! ፍትህ በሌለበት አገር መኖር አልችም!!! በዚህ ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም!!! ግፍና መከራ እያየሁ መኖር አልችልም!!!”

ብሎ  በራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ  የተሰዋባት ዋካ የምትገኘው በዚሁ ክልል በዳውሮ ዞን መሆኑ ማስታወሱ ብቻውን የክልሉ ሕዝብ ለመለስ ዜናዊ አገዛዝ ያለው የተቃዉሞ  መጠን ገላጭ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአዋሳና የአርባ ምንጭ ተደጋጋሚ ሕዝባዊ አመፆች እና የቤንች ማጂ ዞን ነዋሪዎች የከርሰ ምድር ሃብታቸውን ለወያኔ ባለሃብቶች ላለመስጠት በማድረግ ላይ ያሉት ትንንቅ በአብነት ማንሳት ይቻላል። ደቡብ፣ በ1997 ምርጫ ወቅት የወያኔ ካድሬዎች እግራቸውን ማሳረፊያ ያጡበት ክልል እንደነበር ማስታወሱም ይጠቅማል።

በምርጫ 97 ወዲህ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ “በደቡብ” እግሩን ለመትከል በብርቱ ጥሯል፤ በተወሰነ መጠንም ጥረቱ ፍሬ አፍርቷል። ጥቅም እስካገኙ ድረስ ስለ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ ደንታ የሌላቸው፤ የራሳቸውን የቤተሰብ አባላት ሳይቀር ለእርድ ለማቅረብ የማይሰቀጥጣቸው  አድርባዮችን ‘ከደቡብ” መመልመል ችሏል።  እነዚህ ወራዳ የመለስ ምልምሎች ናቸው የአዋሳን እና የአካባቢውን ሕዝብ እርስ በርስ በማጣላት የሕዝቡን ፀረ-ወያኔ የትግል ትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ተግተው ውሸቶችን እያሰራጩ ያሉት።

ይሁን እንጂ ከቀድሞው በባሰ  ዛሬ ሲዳማው በወያኔ መሠሪ ተንኮል ተቆጥቷል። ወላይታውም የዚያኑ ያህል በወያኔ መሠሪ ተንኮል ተቆጥቷል። ሃድያው፣ ጉራጌው፣ ጋሞው፣ ከምባታው፣ ስልጢው፣ ሃመሩ፣ ሙርሲው ….  “ደቡብ” በተባለ ቋት ውስጥ የገቡት የውዲቷና የዉቧ አገራች ልጆች በሙሉ በወያኔ ላይ ተንኮል ተቆጥተዋል። እናም የመለስ ዜናዊ ሎሌዎችሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጣላት የሚደርጉት መሯሯጥ እነሱ የሚፈልጉትን ውጤት አያመጣም። ወያኔ በደቡብ የቆሰቆሰው እሳት መጥፊያው እንደሚሆን ምልክቶች እየታዩ  ነው።

ግንቦት7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ወያኔ “የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት” እያለ በሚጠራው የአገራችን ክልል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በትግራዩ ገዢ ጉጅሌ መሠሪ ተንኮል ሳቢያ ዓይናቸውን ከዋነኛ ጠላታቸው ወያኔ ላይ እንዳይነቅሉ በጥብቅ ያሳስባል።

የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ ጠላት የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ነው። ይህ ዘረኛ አገዛዝ ከተወገደ  ችግሮቻችንን ሁሉ በምክክር መፍታት እንችላለን። ስለሆነም ዛሬ ትኩረታችን ሁሉ ወያኔ የጫነብንን ዘረኛ አገዛዝ አስወግደን ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑባት ኢትዮጵያን መፍጠር ነው።

መምህር የኔሰው ገብሬን ጨምሮ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የተሰውት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፤ ከዚያም አልፎ ስለ ሰው ልጅ ነፃነት መሆኑ ለአፍታም አንዘነጋም።

ወያኔ በአዋሳና አካባቢዋ ነዋሪዎች ላይ የቆሰቆሰው እሳት የራሱ የወያኔ መጥፊያው እንዲሆን ለማድረግ ተግተን እንድንሠራ ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።

በዚህ አጋጣሚም በእነዚህና መሰል ግጭቶት ሳቢያ ለሚጠፋው እያንዳንዱ የሰው ሕይወት በመለስ ዜናዊ የሚመራው የትግራይ ገዥ ጉጅሌ በኃላፊት የሚጠየቅ መሆኑን ግንቦት 7 በጥብቅ ያስገነዝባል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
http://www.ginbot7.org

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር