ኢሳት “ሰበር ዜና” የሲዳማ ወጣቶች “ሲወን” የሚል አዲስ የህቡዕ ድርጅት ዛሬ በአዋሳ መሰረቱ


ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሶስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣  የግብርና ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የክልሉ ፖሊስ ተወካዮች፣ የምክር ቤት አባላትና  እና ሌሎችም ከ 300 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ዛሬ በአዋሳ ከተማ በህቡእ ተሰባስበው የሲዳማ ወጣቶች ንቅናቄ የሚል ድርጅት መስረተዋል። በጉባኤው ላይ ከ22 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የተወከሉ ወጣቶች የተገኙ ሲሆን፣ የትግል ስትራቴጂያቸውን እና አላማቸውን ለተሰብሳቢው ይፋ አድርገዋል።

በከፍተኛ ሚስጢር በተካሄደው ጉባኤ ላይ የወጣቱ አመራሮች የሲዳማ ህዝብ ማንነቱን ለማረጋገጥ የሚያደረገውን ትግል ወጣቶቹ ወደ ፊት ለመግፋት መወሰናቸውን የገለጡ ሲሆን ፣ የመጨረሻ ግባቸው ኢትዮጵያን አሁን ከገባችበት ፈተና ለማላቀቅ ትግል ማድረግ መሆኑን ገልጠዋል።

የወጣቶቹ አመራሮች የተለያዩ ብሄረሰብ ተወካዮችን ለመጥራት የተገደዱትም አላማቸው አካባቢያዊ ሳይሆን ብሄራዊ አጀንዳ ያለው መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል።

በጉባኤው ላይ የወላይታ ተወካይ ” እኛ ወንድማማች ህዝብ ነን፤ ኢትዮጵያዊነታችን ይበልጣል፣ ሀይለማርያም ደሳለኝ በሰራው ስህተት ወላይታ በሙሉ በሲዳማ የሚጠላበት እና የምንለያይበት ምክንያት የለም ፣ ሀይለማርያም በምንም አይነት መልኩ ወላይታን አይወክልም፤ ስለዚህ በእርሱ አይን ባታዩን፣ አብረን ብንሰራ ይህችን አገር እናሳድጋለን፣ ከገባችብት ችግር እናወጣለን” ብሎአል።

የንቅናቄው አመራሮች “የእኛ ትግል የብሄር ጥያቄ አይደለም ፤ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ እና የሌሎች ብሄርና ብሄረሰቦችን ተወካዮችን የጋበዝነውም አላማችን ብሄራዊ መሆኑን ለማሳየት ነው፣ አሁን የሲዳማን ጥያቄ አንስተናል ትግላችን ግን በዚህ አያቆምም፣ አብረን ለኢትዮጵያ ነጻነት እንታገላለን” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

አንድ ሌላ ተወካይ ደግሞ ” መንግስት የዚህን እንቅስቃሴ ዱካ ቢደርስበት ሃላፊነቱን ማን ይወስዳል” በማለት የጠየቀ ሲሆን፣ የንቅናቄው ተወካዮች  የንቅናቄው ደህንነት በእያንዳንዱ አባል ላይ መውደቁን ተናግረዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሲዳማን ተወላጆች ከሌላው ህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚናገሩት ንግግር ፣ የሲዳማን ህዝብ እንደማይወክል የንቅናቄው አመራሮች ተናግረዋል።

ከእንግዲህ ወደ ሁዋላ እንደማይመለሱ የገለጡት ወጣቶች፣ የሌሎች አካባቢ ወጣቶችም እንዲቀላቀሉዋቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶቹ የገዢውን ፓርቲ የደህንነት መረብ አልፈው ይህን ያክል ወጣቶችን ለመሰብሰብ መቻላቸው ታዳሚውን አስገርሟል። በተለይ የፖሊስ አባላትና የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለወጣቶች እንቅስቃሴ ድጋፍ መስጠታቸውና ወጣቶቹ ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር ና ለለውጥ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆን ንቅናቄው በአጭር ጊዜ ውስጥ አስፈሪ ሀይል ሆኖ እንዲወጣ እንደሚያስቸለው በጉባኤው የተሳተፈው የኢሳት ዘጋቢ ገልጧል።

ጉባኤው በስነምግባራቸውና በችሎታቸው በወጣቱ ዘንድ ከበሬታ ያላቸውን ሰዎች በአመራርነት መርጧል። ለንቅናቄው ደህንነትና ዘላቂ ህልውና ሲባል የጉባኤውን መሪዎች ስም እና ጉባኤው የተካሄደበትን ቦታ ከመግለጥ እንቆጠባለን።

በመጨረሻም በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎች ሁሉ የሚበተን ፍላየር ለጉባኤተኛው ታድሎ ጉባኤው ተጠናቋል።

በሌላ ዜና ደግሞ በሲዳማ ዞን በጭኮ ወረዳ የተነሳውን ብጥብጥ ተከትሎ የታሰሩት 15 ሰዎች ተፈቱ። አቃቢ ህግ ግለሰቦችን ከግንቦት7 ጋር በተያያዘ የከሰሳቸው ቢሆንም፣ ለፍርድ ቤቱ ማስረጃ ማቅረብ ሳይችል ቀርቷል። ዘጋቢያችን እንዳለው አቃቢ ህግ ማስረጃ የለኝም በሚል ሰበብ እስረኞቹ እንዲፈቱ ያደረገው መንግስት ከጎሳ መሪዎች ጋር ከተነገጋረ በሁዋላ ነው ። ኢሳት ባላፈው ሳምንት እንደዘገበው የጭኮ ከተማ ህዝብ በፌደራል ፖሊስ አባላት ጉዳት ከደረሰበት በሁዋላ የከተማው ነዋሪ አፊኒ እየተባለ በሚጠራው ባህላዊ ስነስርአት አማካኝነት፣ ወደ ፊት ስለሚወስደው እርምጃ ከጎሳ መሪዎች ጋር ለማነጋገር ወደገጠር አምርቶ ነበር።  የመንግስት ባለስልጣናትም በተመሳሳይ መንገድ ወደ ገጠር በመውረድ የጎሳ መሪዎች ተቃዋሚዎችን እንዲመክሩዋቸው ጠይቀዋል። የጎሳ መሪዎች ና የሁሉም ቀበሌዎች አርሶአደሮች “ከእኛ ጋር ከመነጋገራችሁ በፊት ሁሉም እስረኞችን ፍቱ” የሚል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣቸው፣ እሰረኞቹ ተፈትተዋል።
http://www.ethsat.com/

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር