የጭኮ እና የይርጋለም ህንጻዎች መፈክሮች ተውበው ታዩ፣ መፈክሮችን ለማጥፋት ህንጻዎች እንዲፈርሱ ተደርጓል


ሰኔ ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጭኮና በይርጋለም ከተሞች ዛሬ ጠዋት የታየው ነገር በከተማዋ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ይላል ዘጋቢያችን።  ሰላም የራቀውና በሀዘን ድባብ ላይ የሚገኘው የከተማው ህዝብ ከቤቱ በጧት ሲወጣ የጠበቀው  እንደ ሰሞኑ ፍርሀትና ጭንቀት ሳይሆን ደስታና ተስፋ ነበር።  በከተማዋ የሚገኙ ህንጻዎች  ሁሉም በሚባል ደረጃ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ሌሊቱን በሙሉ  በደማቅ ቀለማት ሲሸለሙ አድረዋል። ህዝቡም በግድግዳዎቹ ላይ የተጻፉትን መፈክሮች ለማየት እየተደዋዋለ ወደ አደባባዩ ጎረፈ። የሚይዙት የጠፋቸው የመንግስት ባለስልጣናት እና ፖሊሶች መፈክሮችን በውሀ ለማጥፋት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ተስፋ በቆረጠ ስሜትም ጽሁፎችን ለማጥፋት የፊት ግድግዳዎች መፍረስ እንደገና መልሰውም በስሚንቶ መለሰን ነበረባቸው። ፖሊሶች የህንጻ መቦርቦሪያ ማሽኖች እየያዙ በየህንጻዎች ላይ በመውጣት ሲቦረቡሩ ፣ ሲለስኑ የከተማው ህዝብም በፖሊሶች ድርጊት ይዝናና ነበር።

ከ 10 በላይ መፈክሮች በከተማዋ አስፓልት ላይም ተጽፈው ነበር። ፖሊሶችም መኪኖችን አስቁመው አስፓልቱን በጋዝ ሲወለውሉ ውለዋል።

ዘጋቢያችን በጭኮ ወረዳ በግድግዳዎች ላይ ከተጻፉት መፈክሮች መካከል የተወሰኑት እንደሚገኙበት ገልጧል።፡” በጭኮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ” ሽፈራው ሽጉጤ የሲዳማን ህዝብ አይወክልም፣ የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ይመለስ፣ ጥያቄያችን ሳይመለስ ትግላችን አይቋረጥም” ይላል። ከተማ መሀከል ከተጻፉ መፈክሮች መካከል ” የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ይመለስ ” የሚል ተጽፎአል። በከተማዋ መናሀሪያ ላይ ደግሞ ” አዋሳና ሲዳማ አይነጣጠሉም “፣   የኢህአዴግ ካድሬዎች የሲዳማን ህዝብ ደም ማፍሰስ ያቁሙ፣ የሲዳማ ተወላጆች የወገኖቻቸውን ደም ማፍሰስ ያቁሙ፣ ሲዳማ ክልል መሆንም ማስተዳደርም ይችላል።” ይላል። በውሀ መውረጃ ቱቦዎች ላይ ደግሞ ” ኢህአዴግ በቃን፣ አታበታብጡን” የሚሉ መፈክሮች ተጽፈዋል።

በመናሀሪያ አካባቢ ፖሊሶች ህዝቡ ወደ መናሀሪያው እንዳይገባ በመከልከል መፈክሮችን ሲያጠፉ ውለዋል። መናሀሪያው አካባቢ የነበረው ሰውም ድርጊቱን እያየ ይስቅ ነበር።፡ ፖሊሶቹ በይርጋለም የተጻፉትን መፈክሮች ቶሎ ለማጥፋት ችለዋል። አብዛኞቹ መፈክሮች በቀይ ቀለማት ነበር የተጻፉት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሶስት ቀናት በፊት በጭኮ የተነሳውን ተቃውሞ አነሳስተዋል የተባሉ 15 የከተማዋ ታዋቂ ባለሀብቶች፣ የፖሊስ አዛዥና የመንግስት ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀርበዋል። አቃቢ ህግ ለፍርድ ቤቱ ግለሰቦቹ ግንቦት7 ከተባለው አሸባሪ ድርጅት ጋር  በማበር ድልድይ ለማፍረስ፣ መኪናዎችን ለማቃጠል እንዲሁም ከግንቦት7 የተጻፈ ወረቀት ሊበትኑ ሲሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የሚል ክስ በንባብ አሰምቷል። ፍርድ ቤቱም ድልድይ ማፍረስና መኪና ማቃጠል በግላጭ የሚታይ ድርጊት በመሆኑ መረጃውን እስከ ነገ ስምንት ሰአት ድረስ እንዲያቀርብ አዘዋል። አቃቢ ህግ የአንድ ሳምንት የጊዜ ቀጠሮ ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ግን ሳይቀበለው ቀርቷል።

በተያያዘ ዜናም በሲዳማ ዞን የተለያዩ ባለስልጣናትን ስም ዝርዝር የያዘ ወረቀት እየተበተነ ነው። ወረቀቱ ባለስልጣናቱ የሲዳማን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያቆሙ  የሚያሳስብ ነው። በስም ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት መካከል አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ ቃሬ ካውቻ፣ አቶ ደሴ ዳልኬ፣ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፣ ወ/ሮ ብዙነኝ፣ አቶ አስፋው ጎነብሶ፣ አቶ አብረሀም ማርሼሎ፣ አቶ ባጢሶ ወዲሳ፣ አቶ ማቲዎስ ዳንኤል፣ አቶ ወርቅነህ ፍላቴ፣ አቶ አማኑኤል መንግስቴ፣ አቶ ጸጋየ ላሊጎ ይገኙበታል። ይህ ባለ 3 ገጽ ወረቀት በመጨረሻ ላይ ” ስማችሁ ከዚህ በላይ ለተዘረዘረ ሌቦችና አስመሳዮች አንድ ጥያቄ አለን፣ የሲዳማ ህዝብ ለሌላው ቅድሚያ ከመስጠት፣ ያለምንም ችግር ለሌላው እራሱን አሳልፎ ከመስጠት፣ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ብቻ የእኛ ናቸው ብሎ ሹመት ከመስጠት፣ ሌላውን ከራሱ በላይ ከመውደድና ከማክበር በላይ ምን በደለ። የማንን ከተማ እና ህዝብ ተመኘ። አስቡበት ለህሊናችሁ ብትኖሩ ይሻላል።” ይላል።

በዛሬው እለትም በጩኮ ከተማ መሀከል ላይ ልሳኑ የሚባል ሳይክስ ሰራተኛን ፖሊሶች አናቱን በቆመጥ መትተውት ደሙን እያዘራ ሲንከባለል ፣ ቤተሰብ እንዳይጠይቀው ፣ ህክምና እንዳያገኘው ተደርጓል። ወጣቱ ተቃውሞውን አስተባብሯል ተብሎ በመጠርጠሩ መደብደቡን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር