የሀዋሳ ከተማን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ የቱሪዝም ማዕከል ለማደረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎች ገለጹ


 የሀዋሳ ከተማን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ነዋሪዎች ከከተማው አስተዳደሩ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡
የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ የመንግስት ሰራተኞችና የንግዱ ማህበረሰብ ጨምሮ በከተማው ስምንቱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የጽዳትና የተተከሉ የዛፍ ችግኞችን የመንከባከብ የስራ ዘመቻ ትናንት ተካሄዷል፡፡ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ በየክፍለ ከተማው ተዘዋውረው በስራው የተሳተፉትን ነዋሪዎች አበረታትዋል፡፡
"እያንዳንዱ አካባቢውን ካጸዳ ከተማዋ የጸዳች ትሆናለች" በሚል መርህ ትናንት ለግማሽ ቀን በተካሄደው የስራ ዘመቻ ከተሳተፉት መካከል በባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ የሀረር ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ሙሉቀን አለማየሁ በሰጠው አስተያየት አካባቢቸውን ከቆሻሻና ከብክለት ለመከለካል ከሰፈር ጓደኞቹና ነዋሪው ጋር በራሳቸው ተነሳሽነት የጽዳት ዘመቻውን በዓሉን ምክንያት በማድረግ ብቻ ሳይሆን በቋሚነት በየሳምንቱ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
አካባቢያቸውን ከፍሳሽና ከደረቅ ቆሻሻ ማዕዳት ለጤናቸው ብሎም ለሀዋሳ ውበትና አረንጓዴ ልማት የላቀ አስተዋጾኦ እንዳለው በመገንዘብ በቀጣይም ከከተማው አስተዳደርና ማዘጋጃ ቤት ጋር በመተባበር የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዚሁ ክፍለ ከተማና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች በቀለ በበኩላቸው ሀዋሳ ያላትን ጽዳትና ውበት ለማስጠበቅ ጽዳትን ከቤታቸውና ከመንደራቸው በመጀመር እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የመሃል ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 ነዋሪ ወይዘሮ እናኑ መዘምር በሰጡት አስተያየት ጽዳት ለጤንነትና ለከተማ ውበት ወሣኝ መሆኑን በመረዳት ቆሻሻን ከአካባቢው በማስወገድ ከተማዋን ውብና አረንጓዴ ለማድረግ ከከተማው አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ከመንግስት ሰራተኞች መካከል አቶ አበበ ዶንጋና አቶ አብረሃም አላሮ በየበኩላቸው በዓሉን ምክንያት በማደረግ ለነዋሪው አርአያ ለመሆን ትናንት ከጥዋቱ 12 ሰዓት እስከ እኩለ ቀን ድረስ የቆሸሹ አካባቢዎችን ከማጽዳትና የተተከሉ የዛፍ ችግኞችን ከመንከባከብ ባሻገር የጽዳት አስፈላጊነት ለነዋሪው በማሰተማር መሳተፋቸውን አመልከተው ወደፊትም በትርፍ ጊዜያቸው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የሀዋሳ ከተማ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት አቶ ወሌ አበጋዝ በሰጡት አስተያየት ሀዋሳ ባላት ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ሀብት ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ማዕከልነት ተመራጭ መሆኗን ገልፀው ይህንን ምቹ ሁኔታ ይበልጥ ለማጠናከር የንግድ ማህበረሰብ ገንዘቡን፣ ዕውቀቱንና ጉልበቱን አስተባብሮ ከተማዋን ጽዱ ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ በበኩላቸው ነዋሪው ህብረተሰብ የከተማውን ውበትና ጽዳት ለማስጠበቅ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው የከተማ አስተደደሩም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ቆሻሻ ከየቦታው አሰባስቦ በአንድ አካባቢ በማከማቸት ተመልሶም ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ ማመቻቸቱን አብራርተዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር