በሲዳማ ዞን አሮሬሳ ወረዳ በመጠጥ ውኃ እጥረት መቸገራቸውን የመጆ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡


በሲዳማ ዞን አሮሬሳ ወረዳ በመጠጥ ውኃ እጥረት መቸገራቸውን የመጆ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡በተከሰተው የውሀ እጥረት የተነሳ ለህብረተሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት ለመስጠት መቸገሩን የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡
የወረዳው ውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ችግሩ እስከ ሚያዚያ 3ዐ ባለው ጊዜ ይፈታል ብሏል፡፡የመጆ ከተማ የአሮሬሳ ወረዳ ዋና ከተማ ስትሆን ዙሪያዋ 8 በሚበልጡ የተፈጥሮ ምንጮች የተከበበች ናት፡፡
ይሁንና ምንጮቹ በበጋ ወራት መድረቅ በመጀመራቸው በተለይም ካለፈው አመት ጀምሮ ለከፍተኛ የመጠጥ ውኃ ችግር መጋለጣቸውን ነው ነዋሪዎች የተናገሩት፡፡አንዳንዶቹ እንደሚሉት በውኃ ማድያ ወረፋ ለመያዝ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ጀምሮ ከቤት ስለሚወጡ ዘረፋና ድብደባ እንደሚደርስባቸውና ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚጋለጡ ተናግረዋል፡፡
የወረፋውን ሰልፍ ይዘው እስከ እኩለ ቀን ድረስ እንደሚቆዩ የገለፁት ነዋሪዎቹ በዚህም የተነሳ በረሃብ እንደሚጐዱና ወረፋው ሳይደርሳቸው ሲቀር ደግሞ በዐ.5ዐ ሣንቲም የሚገዛውን ባለ 2ዐ ሊትር አንድ ጀሪካን ውኃ ከአትራፊዎች ከ5 እስከ 6 ብር ለመግዛት እንደገደዳለን ብለዋል፡፡
እነዚህ አትራፊዎች ከከተማው በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘውና ጪጩ ከተባለ ወንዝ ንጽህናው ያልተጠበቀ ውኃ ቀድተው ስለሚሸጡላቸው ለተለያዩ ውኃ ወለድ በሽታዎች እየተጋለጡ እንደሚገኙ አስድተዋል፡፡የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት በበኩሉ በከተማው በተፈጠረው የውኃ ችግር የተነሳ ለህብረተሰቡ ንፅህናውን የተጠበቀ የጤና አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን አመልከቷል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙንጣሽ ብርሃኑ እንዳሉት በከተማውና በአካባቢው የሚገኙ 4 ጤና ጣቢያዎች ከመኝታና ከመፀዳጃ አገልግሎቶች አንስቶ ለህሙማኑ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት መሰጠት አልቻሉም፡፡ለህክምና ወደ ጤና ተቋማቱ ከሚመጡ ህሙማንም አብዛኛዎቹ ንፅህናው ያልተጠበቀ ውኃ በመጠቀም በተለያዩ ውኃ ወለድ በሽታዎች የተጐዱ መሆናቸውን ነው አቶ ሙንጣሽ ያስረዱት፡፡
በወረዳው ውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የመጠጥ ውኃ አቀርቦትና የተቋት አስተዳደር ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አሰጋኸኝ ቱኑና በሰጡት ምላሽ ችግሩ መከሰቱን አምነው ምክንያቱ ደግሞ ከ13 አመታት በፊት ከ3 እስከ 4 ሺህ ለማይበልጥ ለከተማው ነዋሪ ታስቦ የተገነባው የውኃ ኘሮጀክት ዛሬ ከ1ዐሺህ ከሚበልጠው የከተማ ነዋሪ ፍላጐት ጋር መጣጣም ስላልቻለ ነው ብለዋል፡፡
በከተማው ዙሪያ የሚገኙና በክረምት ወራት ለነዋሪው በቂ የመጠጥ ውኃ የሚሰጡ ምንጮች በበጋ ወራት እንደሚደርቁ በመጠቆም፡፡ይሁንና ችግሩን እስከፊታችን ሚያዚያ 3ዐ በመጠናቀቅ በሴኮንድ 5 ነጥብ 2 ሊትር ውኃ የሚያመረተው ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ እየተካሄደ ነው ማለታቸውን የዘገበው የዞኑ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር