በደቡብ ክልል አዲሱ የሊዝ አዋጅ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል -የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር



በደቡብ ክልል አዲሱ የሊዝ አዋጅ ከዛሬ ጀምሮ በየደረጃው ተግባራዊ እንደሚሆን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የንግድ ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊ አስታወቁ ።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ህብረተሰቡም ለአዋጁ ተግባራዊነት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የቢሮው ሃላፊ አቶ ታገሰ ጫፎ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በሀገር ደረጃ ህዳር 18/2004 የጸደቀው አዲሱ የሊዝ አዋጅ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
መሬት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዘቦች የጋራ ሀብት እንደመሆኑ የከተማ ቦታ በሊዝ ጨረታ ወስዶ ያለማ ሰው እሴት እንደሚፈጥርለትና ተጠቃሚ እንደሚሆን አስታዉቀዋል ።
በአዋጁ መሰረት የተከለከለው ባዶ መሬት በሊዝ ከወሰደ በኋላ ሳይሰራበት መሬቱን አሲዞ አለአግባብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከባንክ መበደርና መሸጥ ነው ብለዋል፡፡
መሬት ልማታዊ ባልሆነ መንገድ ወስዶ በአቋራጭ መበልጸግና ሀብት ማግበስበስ እንደማይቻል በአዋጁ ላይ በግልጽ መደንገጉን ያስረዱት አቶ ታገሰ በዚህ ዐይነት ህገ ወጥ አካሄድ የመሬት ዋጋ ጣሪያ ከመድረሱም በላይ ለልማት የሚውለው ገንዘብ በመሬት ግዥና ሽያጭ እየባከነ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የመሬት አስተዳደር ስርዓትና የመሬት አቅርቦትን ከከራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ለማድረግ አዋጁ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመልከተው በፕላን መሰረት ቤት የሰራና በዙሪያው ያለማውን ሀብት መሸጥ እንደሚችል ፣ ነገር ግን መሰረት በመጣልና ከ50 በመቶ በታች ግንባታ በማካሄድ በከፍተኛ ገንዘብ መሸጥ የማይቻል መሆኑን ህዝቡ በግልጽ መገንዘብ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ነባር ይዞታዎች በውርስ ማስተላላፍ እንጂ ወደ ሊዝ የሚገባን መሬት ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንደማይቻል ጭምር በክልሉ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት መዋቅሮችና ለህብረተሰቡ ባለፉት ሶስት ወራት በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡
ለኢንቨስትመንት ተብለው ከተወሰዱ በኋላ ሳይለሙ ለሁለት አመትና ከዚያ በላይ ጊዜ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች በህዝብ ሀብትነት ወደ መሬት ባንክ ይገባሉ ያሉት አቶ ታገሰ ለጨረታ ሲቀርብ የሃሰት ማስረጃ የሚያቀርቡና ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ግንባታ የሚያካሄዱ በህግ እንደሚጠየቁም ገልጸዋል፡፡
አዋጁ በርካታ ጉዳዮችን መያዙን ጠቁመው በተለይ የከተማ ቦታዎች ግልጽነት በተላበሰና በበቂ ማስረጃ ለተገቢው ልማት ማዋል የሚያስችል በመሆኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ውጪ ጉዳት እንደማይኖረዉ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከተሞች ከንጉሱ ጊዜ አንሰቶ እስከአሁን ያሉ ሰነድ አልባ ይዞታዎች ለዘመናት ግብር ሲከፈልባቸው የቆዩ በመሆናቸው በተደራጀ አሰራር ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ ኤጀንሲም ተቋቁሟል ብለዋል፡፡
በክልል ደረጃ የተቋቋመው ኤጀንሲ በየደረጃው ባለው መዋቅር መሬትና መሬት ላይ ያለውን ሀብት በመመዝገብ ወደ ህጋዊነት የሚዞሩበት የህግ አግባብ መመቻቸቱንና ይህም ስራ በሚቀጥሉት አራት አመታት እንደሚጠናቀቅና በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ስጋት ሊኖር እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡
መሬት ከሊዝ ጨረታ ውጪ በምደባ የሚሰጠው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻና መሸጫ፣ ለልማታዊ ባለሀብት፣ለማንፋክቸሪ ኢንዱስትሪዎች፣ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ የመሳሰሉት እንደሆነ በህጉ ላይ መቀመጡን አመልክተው አሰጣጡም በርዕሰ መስተዳድሩ አቅራቢነት በካቢኒ ከተወሰነ በኋላ በግልጽ አሰራርና ከኪራይ ሰብሳቢነት በጸዳ መልኩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በራስ አገዝ የቤት ግንባታ ፕሮግራም የመንግስት ሰራተኞች 40 በመቶ በቁጠባ 60 በመቶ በሚሰጣቸዉ ብድር፣ መረት በምደባ መንግስት እንደሚያቀርብና ወጪን በሚቀንስ የቴክኖሎጂ ግንባታና ግብአት በመጠቀም የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ሁኔታ መመቻቸቱን ገልጠዋል ።
አዋጁን በክልሉ በየደረጃው ተግባራዊ ለማድረግ ግንዛቤ ከመፍጠርና አስፈጻሚዎችን ከማደራጀት ጀምሮ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንና ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኘው አመራር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በብቃት እንዲወጡና ህዝቡም የድርሻው እንዲያበረክት አሳስበዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር