በሐዋሳ በተነሳው የእሳት አደጋ ንብረት አወደመ: በሐዋሳ ከተማ የንግድ ተቋማት ባለንብረቶች: ከኢንሹራንስ ይልቅ ማኅበራዊ ተራድኦን የሚመርጡ መሆናቸው ተነገረ


 በአደጋው የከተማው አስተዳደር እሳት አደጋ መከላከል አቅም ተፈትሿል
መጋቢት 9 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ገደማ በሐዋሳ ከተማ ፒያሳ አካባቢ በሁለት መደብሮች የተነሳው እሳት ንብረት አወደመ:: ወደ ክብሩ ሆስፒታል መሄጃ ላይ እየሩሳሌም የጨርቃ ጨርቅ መደብርንና አጠገቡ ያለው ጥሩወርቅ የኮምፒውተር ጽሕፈት አገልግሎት በእሳቱ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ ባለንብረቶቹ እንደሚሉት 1.3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት በተነሳው እሳት የእሳት አደጋ መከላከያ በወቅቱ ባለመድረሱና ዘግይቶ ከደረሰም በኋላ አቅሙ ውስን በመሆኑ፣ በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ማዳን እንዳልተቻለ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ እማኞቹ አስተያየት ያለምንም መከላከያ ለ20 ደቂቃዎች ያህል ሲቀጣጠል የነበረው እሳት፣ በመደብሮች ውስጥ የነበሩትን ጨርቃ ጨርቆችና ኮምፒውተሮች በፍጥነት ጋይተዋል፡፡

የእየሩሳሌም ጨርቃ ጨርቅ መደብር ባለቤት አቶ ጌቱ ደምቦባ ስለደረሰው ጉዳት ተጠይቀው፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጣቃዎችና የተዘጋጁ ልብሶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጸው፣ የእሳቱን መንስዔ በተመለከተ ለተጠየቁት ሲመልሱ፣ ማናቸውንም የኤሌክትሪክ ዕቃዎችንና ካውያዎችን በአግባቡ ካጠፉ በኋላ መደብራቸውን መዝጋታቸውንና እሳቱ ከየት እንደተነሳ እንደማያውቁ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ የጥሩወርቅ ኮምፒውተር ጽሕፈት አገልግሎት ባለቤት በበኩላቸው፣ ከ300 ሺሕ ብር በላይ የሚገመቱ ኮምፒውተሮችና የፎቶ ኮፒ ማሽኖች እንዲሁም የስቴሽነሪ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጸዋል፡፡

በምሽቱ የተፈጠረውን እሳት ለመከላከል የሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የእሳት አደጋ መከላከያና የከተማው የእሳት አደጋ መከላከያ በአጠቃላይ ሦስት ተሽከርካሪዎችን በማሳተፍ ባደረጉት ርብርብ፣ ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት አካባቢ እሳቱ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ ችሏል፡፡ 28 ቀበሌዎች ያሉት የሐዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሁለት የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች ውኃ ስላልነበራቸው እሳቱ በተነሳ ጊዜ ከሐዋሳ ሐይቅ እየተመላለሱ ሲቀዱ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በከተማዋ ከዚህ ቀደም በአቶቴ ካፌና ሬስቶራንት ተመሳሳይ የእሳት አደጋ ተከስቶ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ በሐዋሳ ከተማ የንግድ ተቋማት ባለንብረቶች ከኢንሹራንስ ይልቅ ማኅበራዊ ተራድኦን የሚመርጡ መሆናቸውን የሚገልጹ አንድ የኢንሹራንስ ባለሙያ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ አቅም ውስን በሆነበት በአሁኑ ጊዜ፣ የመድን ዋስትና ጠቀሜታ ቦታ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

በሌላ ዜና በሐዋሳ ከተማ የተከሰተው የስኳር እጥረት ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ባሉት የችርቻሮ መደብሮች ስኳር በኪሎ ማግኘት እንደማይቻል፣ ከተገኘ ደግሞ በድብቅ እስከ 30 ብር የሚሸጥ መሆኑንና አብዛኛውን ጊዜ በችርቻሮ ብቻ እንደሚሸጥ ነዋሪዎች በምሬት እየተናገሩ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር