የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት “እኔ ከተከሰስኩ ወ/ሮ አዜብ መስፍንም መከሰስ አለባቸው” አሉ (በመምህሩ መልካሙ)

New


የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ የክልሉ ፓርቲ ባደረገው ድርጅታዊ ግምገማ ውሳኔ አስተላለፈ።
ፕሬዚዳንቱ “እኔ ብቻዬን መከሰስ የለብኝም። ከተከሰስኩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር መሆን አለበት” በማለት ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ምንጮች አስታወቁ። አቶ መለስ ድርጅቱ የወሰነውን ውሳኔ ቀለበሱ። በዚህም ሳቢያ በደቡብ ክልል የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻና የፖለቲካው ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
ይህ የሆነው ከየካቲት 5 ቀን እስከ የካቲት 11 ቀን 2004 ዓም ድረስ የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን የሚመራው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ደኢህዴን) የከፍተኛ አመራር ግምገማ ባካሄደበት ወቅት ነው። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት በክልሉ በተካሄደው ከባድ የተባለ ግምገማ ቅድሚያውን የያዙት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ነበሩ። የሲዳማ ቡና ላኪዎች ማህበር አባልና በማህበሩ ከፍተኛ ባለአክሲዮን እንደሆኑ በግምገማ የቀረበባቸው ፕሬዚዳንቱ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መዝብረዋል በሚል ጠንካራ አውጫጪኝ ተካሄዶባቸዋል። በኢህአዴግ የፖለቲካ ቋንቋ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን በ”ኪራይ ሰብሳቢነትና በሙሰኝነት” ተፈርጀዋል። እንደ መረጃ ምንጮቹ ገለጻ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ወርደው በህግ እንዲጠየቁ ድርጅታዊ ውሳኔ ሲበየንባቸው፣ ”እኔ ብቻዬን አይደለሁም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር በጋራ ገንዘቡን ወስደናል፡፡ የምንጠየቅም ከሆነ ሁለታችንም በህግ ፊት መቅረብ አለብን፡፡ ብሩን መመለስም ካለብን ሁለታችንም እንመልስ” በማለት የግምገማ መድረኩን ረግጠው ወጥተዋል።
ይህ ሁኔታ ከፍተኛ መደናገጥን የፈጠረባቸው አቶ መለስ ዜናዊ በድርጅቱ የተወሰነውን ፖለቲካዊ ውሳኔ ሳያጸድቁ ቀልብሰውታል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የክልሉ አመራር “የፓርቲው ውሳኔ የተገለበጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት በጉዳዩ ስላሉበት ነው። ውሳኔው በፓርቲው ውስጥ አለመተማመን ፈጥሯል” ብለዋል። አያይዘውም “ፕሬዚዳንቱን በግልጽ ገምግመው ውሳኔ የወሰኑ ክፍሎች እንዴት በቀጣይ አብረው ሊሰሩ ይችላሉ” ሲሉ ጠይቀዋል።
አቶ መለስ ውሳኔውን ለመገልበጣቸው እንደ ምክንያት የተነገረው የሲዳማ ብሔር ተወላጅ የሆኑትን አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከሥልጣን ከተባረሩና ህግ ፊት ከቀረቡ፣ በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሲዳማ ህዝብ ያምጻል የሚለው ስጋት እንደሆነ ታውቋል። የሃዋሳ ምንጮቻችን ያነጋገሩዋቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ክፍሎች ግን ይህንን አይቀበሉትም። ይልቁንም የሲዳማ ብሄረሰብ አባላት ህግና ስርዓት እንዲከበር የሚወዱ ህዝቦች እንደሆኑ አስረድተዋል። ስርዓቱን በመሞዳሞድ ሃብት ካፈሩት በስተቀር የታችኛው የሲዳማ ብሄር አባላት እንደማንኛውም የአገሪቱ የህብረተሰብ ክፍሎች ያተረፉት ነገር የለም።
“በክልሉ ዋና ከተማ ሃዋሳ ከአርባ አምስት በላይ ተለያዩ ብሄረሰቦች ይተዳደራሉ። ክልሉን እየመራ ያለው ፓርቲ ያካሄደውን ግምገማና የግምገማ ውሳኔ ተከትሎ የደቡብ ክልል ህዝቦች መዲና መሆኗ ቀርቶ የብጥብጥና የጦርነት ከተማ ትሆናለች” በማለት ከዚህ ቀደም የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ከነበሩትና የሲዳማ ብሔር ተወላጅ ከሆኑት አቶ አባተ ኪሾ ጋር ያገናኙትም አሉ። በጊዜው የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ ቢተው ትዕዛዝ እየተቀበሉ ክልሉን ሲመሩ የነበሩት አቶ አባተ ከአለቃቸው ጋር “ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” በሚል በአቶ መለስ ቀጥተኛ ትእዛዝ መታሰራቸውን ያስታወሱት ምንጮቻችን፣ አቶ መለስ መከላከል ሲፈልጉና ማሰር ሲያምራቸው ውሳኔ መቀያየር እንደሚችሉበት አስረድተዋል።
አቶ አባተ በታሰሩበት ወቅት የእስራቸውን ሁኔታና ሚስጥር የሚያውቁ በፈጠሩት ግፊት መፈታታቸውን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎች፣ ያሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከደቡብ ክልል ፕሬዚዳንትነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት በሲዳማ ህዝብ አመጽ ሳቢያ እንደሆነ ተደርጎ መነገሩ እንደሚምታታባቸው ያስታውሳሉ።
አቶ ሽፈራው ከ1997 ዓም ጀምሮ ክልሉን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ሲቀናቀኑዋቸው የነበሩትን ሰዎች “ሊገሉኝ አሲረዋል” በሚል ያለ በቂ ማስረጃ እንዲታሰሩ ማድረጋቸው ከፍተኛ ቅሬታ ቀስቅሶባቸው እንደ ነበር ያስታወሱት የደኢህዴን አባላት ባለፈው ሳምንት በክልሉ መሪ ድርጅት በተካሄደ ግምገማ የተወሰነው ውሳኔ በቀጣዩ የኢህአዴግ ግምገማ ወ/ሮ አዜብ በሚገኙበት፣ አቶ መለስና አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እየመሩት ይካሄዳል ብለዋል።
“መገጣጠም” በሚል የተነገረው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት የተናገሩት ነው። አቶ ኦሞት ኦባንግ “እኔ የምታሰር ከሆነ መሳሪያ የሰጡኝ አቶ መለስም መታሰር አለባቸው” በማለት እንደተናገሩት ሁሉ አቶ ሽፈራው ሽጉጤም “እኔ የምከሰስ ከሆነ ወይዘሮ አዜብ መስፍንም መከሰስ አለባቸው” ማለታቸው ነው።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር