በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ ይለማል

New

አዋሳ, የካቲት 23 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በሲዳማ ዞን የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆነችው ቦርቻ ወረዳ በተያዘው የበልግ ወቅት ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው፡፡ ከልማቱም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በበኩላቸው የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለማሻሻል በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አዴላ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በወረዳው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሁሉም አርሶ አደር ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡
በወረዳው ከሚሰበሰበው ምርት 70 በመቶ ያህሉ በበልግ ወቅት ከሚለማ መሬት የሚገኝ በመሆኑ ለበልግ እርሻ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የእርሻ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታዲዮስ ነዲ በበኩላቸው ዘንድሮ 16 ሺህ 614 ሄክታር መሬት በቦሎቄ፣ በበቆሎ እና በተለያዩ ስራስሮችና ዓመታዊ በሆኑ የተክል ዓይነቶች እንደሚሸፈን ገልፀዋል፡፡
በዘንድሮው በልግ በልዩ ልዩ ዘር ከሚሸፈነው መሬት ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የተያዘውን ዕቅድ ለመሳካት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ከሚገኙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ ከደቡብ ክልል ምርጥ ዘር አቅርቦት ድርጅት ጋር በመቀናጀት ከ1ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 850 ኩንታል ምርጥ ዘር ተገዝቶ ለአርሶ አደሩ መቅረቡንም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም 37 ሺህ 700 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ገልፀው ግብአትን በአግባቡ በመጠቀም ከዘንድሮ የበልግ እርሻ በአንድ ሄክታር በአማካይ ከ70 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡
በወረዳው ዘንድሮ የተያዘው የምርታማነት ዕቅድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በሄክታር 40 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ይህንኑ እቅድ ለማሳካትም ምርታማነቱ በምርምር የተረጋገጠ ምርጥ ዘር መጠቀም፣ ማሳውን ከ3 ጊዜ በላይ በሚገባ ማረስ፣ አርሶ አደሮች ማሳቸውን በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ እንዲሸፍኑ የማድረግና የአረም ቁጥጥርና ሌሎች ተዛማጅ ስራዎችን በተሟላ መንገድ የማከናወን ስራዎች ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በወረዳው የአላ ዋርኬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ብርሃነሽ ኤርሚያስና አቶ ጫንጌ ኡሜሶ የተባሉ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት በሄክታር የሚያገኙት ምርት ዝቅተኛ በመሆኑ የእለት ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ይቸገሩ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከዞን ጀምሮ በተደረገላቸው ድጋፍ በሄታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት በማግኘት ከእጅ ወደ አፍ ከነበረ ኑሮ በመላቀቅ ገቢያቸው እጅግ መሻሻሉን ገልፀው ከጎጆ ወደ ቆርቆሮ ቤት መሸጋገራቸውንና ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በወር ከሚያገኙት ገቢ መቆጠብ መጀመራቸውን አስርድተዋል፡፡
አርሶ አደሮች ለምርቱ መሻሻል እንደምክንያት የገለፁት በቀበሌው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎች አስፈፃሚ አካላት በሚሰጡዋቸው ምክርና ድጋፍ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት በመጀመራቸው ነው፡፡
በተጨማሪም መሬትን ደጋግሞ በማረስ ፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ መጠቀማቸውና ለምርት እድገት በሚያግዙ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው ለለውጥ እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በዘንድሮ የበልግ እርሻም በሄክታር ከ70 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አንድ ለአምስት በመቀናጅ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው ለዚህም ይረዳቸውን ዘንድ መሬትን ከአራት ጊዜ በላይ ደጋግመው በማረስ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤትም ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በመረከብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በበልግ አምራችነቷ የምትታወቀው ቦርቻ ወረዳ በ39 የገጠር እና በ3 የከተማ ቀበሌዎች የተዋቀረች ሲሆን ከ280 ሺህ በላይ ህዝብ ይኖርባታል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የተያዘውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግም በክልልና በወረዳው የአስተዳደር አካላት እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ41 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር ቀበሌዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የመንገድ ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብና ግብአት ወደ ቀበሌያቸው ለማስገባት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማቀላጠፍ እንደሚያስችላቸው ተገልጿል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር