የሀዋሳ ሀይቅን ከብክለትና ከደለል የመከላከል ሥራ በማህበር በተደራጁ ወጣቶች እየተከናወነ ነው



ሀዋሳ ፤የካቲት 03 2004 /ዋኢማ/ - በሀዋሳ ከተማ በማህበራት የተደራጁ ወጣቶች የሀዋሳ ሀይቅን ከብክለትና ከደለል የመከላከል ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ፡፡
በማዘጋጃ ቤቱ የአካባቢ ጥበቃ መምሪያ ሃላፊ አቶ ተፈራ ባንቶ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት የሀዋሳ ሀይቅን ከብክለትና ከደለል የመከላከል ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኙት በ20 የአካባቢ ጥበቃና ጽዳት ማህበራት የተደራጁ 378 ወጣቶች ናቸው ፡፡
ወጣቶቹ በሀይቁ ዙሪያ የሚገኙ ደላሎችን ለመከላከል በሐይቁ የተፋሰስ መሬቶች ዙሪያ 16 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን እና የዝናብ ውሃን ወደ መሬት ለማስረግ የሚያስችሉ 57 የጨረቃ እርከኖችን መገንባታቸውን ሃላፊው አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከመጠበቅ በተጨማሪ ለውበት ለጥላና ለመናፈሻ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ከ92 ሺህ በላይ የአገር በቀል እና የባህር ማዶ ችግኞችን መትከላቸውን አመልክተዋል፡፡
በማህበር ተደራጅተው በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ወጣቶች ቀደም ሲል ሥራ አጥ እና በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ እንደነበሩ ያስታወሱት ሃላፊው በአሁኑ ወቅት ግን ለራሳቸው ከፈጠሩት የሥራ ዕድል በተጨማሪ ለሀዋሳ ሐይቅ እና ለከተማው አካባቢ ጥበቃ ሥራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የከተማው ማዘጋጃ ቤትም ወጣቶቹ እያከናወኑ የሚገኙት ሥራ አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ከገመገመ በኋላ በየወሩ ለማህበራቱ አባላት የደሞዝ ክፍያ የሚውል የ150 ሺህ ብር ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ከሃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር