ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የማኀበረሰብ ተኮር ሬዲዮ ጣቢያ ለመክፈት የሚያስችል ፈቃድ አገኘ



አዲስ አበባ, የካቲት 3 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) - ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የማኀበረሰብ ተኮር ሬዲዮ ጣቢያ ለመክፈት የሚያስችለውን ፈቃድ ወሰደ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ማርኬቲንግ ዳይሬክተር የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳዊት በዳሳ ለኢ ዜ አ እንዳስታወቁት ዩኒቨርሲቲው ፈቃዱን ያገኘው ባቀረባቸው ምክረ ሃሳብ /ፕሮፖዛል/ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፉ ነው፡፡
በፈቃዱ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስፈላጊ መስፈርት መሟላታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ዩኒቨርሲቲው በኤፍ ኤም 90 ነ ጥብ 9 የአየር ሞገድ ፕሮግራሞችን ማቅረብ ይጀምራል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባሉት አራት ካምፓሶች በአሁኑ ወቅት ከ24 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ፕሮግራሞች እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ባሉት ደረጃዎች እያስተማረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በይርጋለም ከተማ ላይ ግንባታው በመፋጠን ላይ በሚገኘው ካምፓስ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም 120 የሚሆኑ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺና አሳታፊ የምርምር ሥራዎች በዩኒቨርስቲው ሥር በመካሄድ ላይ የሚገኙ ሲሆን የሬዲዮ ጣቢያው መከፈት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው የማኀበረሰብ አገልግሎት ከማጠናከር በተጨማሪ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ሬዲዮውን በዋናነት ለመጠቀም መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ሬዲዮ ጣቢያውን ለመክፈት የሚያስችለውን ወጪ በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኤምባሲ የተሸፈነ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በኋላ ለሐዋሳ ከተማና አካባቢው ማኀበረሰብ ሥርጭት እንደሚጀምር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር